
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ፍርድ ቤቶችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ። በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ክፍተቶችን መሠረታዊ በሆነ መልኩ የሚቀይር የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል ፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የክልሉ መንግሥት ካለው ውስን በጀት ላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ፍርድ ቤቶችን ዲጂታላይዝድ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ነው። በቀጣይ ሁለት እና ሦስት ወራት ውስጥም ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፕሮጀክቱ ከኢትዮ -ቴሌኮም ጋር በመተባበር እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ፣ፕሮጀክቱ ተገልጋዮች ወጪያቸውን እና ጊዜያቸውን በሚቆጥብ መልኩ ባሉበት አካባቢ ሆነው ፤ መዝገብ ከፍተው ክርክር እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
“የለሙት የዲጅታል መተግበሪያዎች የክልሉ ዳታ ቤዝ ላይ መጫናቸውን ጠቁመው፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ተጠናቋል፡፡ አዳዲስ ህንጻዎችም ተገንብተዋል፤ ህንጻዎች ለዲጅታላይዜሽን በሚመች መልኩ ታድሰዋል” ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ የሕዝቡን እንግልትና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ አመልክተው ፤ የሥራ ከባቢ ሁኔታን ምቹ ማድረግ ለፍርድ ቤት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል። ቢሮዎችን ምቹ ማድረግና ማስዋብ ብቻ በራሱ በቂ እንዳልሆነ ፤ ዜጎች በግልጽ ችሎት የመዳኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት አብዛኞቹ ክርክሮች የሚመሩት በቢሮ ውስጥ ነበር፡፡ ይህን ችግር በሚቀርፍ መልኩ ማንኛውም ሰው ገብቶ መታዘብ በሚችልበት በግልጽ ችሎት ክርክሮች እንዲመሩ ለማድረግ በዞን ደረጃ የአዳዲስ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንጻዎች ግንባታ ተካሂዷል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤትም የእድሳትና የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፤ የግንባታ ሥራዎቹም በአብዛኛው እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ የአማራ ክልል በፍርድ ቤት ከሚታዩት የመዛግብት የጉዳዮች ፍሰት ብዛት አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ሰፊ ጉዳዮች የሚታዩበት ክልል ከመሆኑ አኳያ አገልግሎት አሰጣጡን በአግባቡ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡
እንደ ሀገር የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በክልላችንም በተመሳሳይ የሦስት ዓመት የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን እቅድን እየተገበርን እንገኛለን። አሁን ትግበራው ከተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖታል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በሀገር ደረጃና በአማራ ክልል በተሠሩ የፍትህ ማሻሻያ ሥራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን አስታውሰው፤ ነገር ግን አሁንም በተደረጉ ጥናቶች በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሰፊ ክፍተቶች በመኖራቸው ማህበረሰቡ እርካታ የለውም፡፡ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ክፍተቶቹን መሠረታዊ በሆነ መልኩ ይቀይራል ተብሎ እንደሚታመን ጠቁመዋል፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም