
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሶስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሊትር ወተት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቶሌራ ደበላ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የወተት ምርታማነት ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ለመሥራት ታቅዶ፤ በዘጠኝ ወራት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ማሳካት ተችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሊትር ወተት ለማምረት መታቀዱን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ በዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር መሰብሰብ ተችሏል። አፈጻጸሙም ከእቅድ በላይ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ በዚህ ዓመት 738 ሺህ ጥጆች እንዲወለዱ ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ በዘጠኝ ወራት አምስት መቶ ሺህ ጥጆች ተወልደዋል፡፡ ለተገኘው ውጤት እንደ ክልል በሌማት ትሩፋት የሚሳተፉ አካላት ፣ አመራሩ እና አርሶ አደሩ ያሳዩት ቁርጠኝነት ተጠቃሽ እንደሆነ አመልክተዋል።
አቶ ቶሌራ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ እንደ ክልል መቶ ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ለማሰራጨት ታቅዷል። እስከ ሶስተኛው እሩብ ዓመት ወጣቶችን፤ ሴቶችን፤ አርሶ አደሮችን በማደራጀት እና በዶሮ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችን በማሳተፍ 63 ሚሊዮን የእንቁላል እና የሥጋ ጫጩቶች ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡
ከእንቁላል ምርት አንጻር በበጀት ዓመቱ አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ለማምረት ታቅዶ፤ በዘጠኝ ወራት ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ተመርቷል፡፡ ከቀይ ስጋ ምርት አንጻርም አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ስጋ መመረቱን ጠቁመዋል ፡፡
የመኖ ግብዓት መወደዱ እና በመኖ ሽያጭ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጨመሩን ተከትሎ የዶሮ መኖ ዋጋ በመወደዱ የዶሮ ልማት ሥራ ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን አመልክተው፣ ችግሩን ለግብርና ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። ዶሮ አርቢዎች በአካባቢያቸው ባለ ግብዓት መኖ እንዲያዘጋጁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ምክትል ኃላፊው እንደገለጹት፤ እንደ ኦሮሚያ ክልል የማር ምርት በስፋት ለማምረት በንቅናቄ መልክ እየተሠራ ነው፡፡ ከንቅናቄው በፊት በክልሉ ያለው የማር ምርት ቀፎ ከ47 ሺህ የማይበልጥ ነበር፤ የዘንድሮን ሳይጨምር አሁን ላይ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዘመናዊ ቀፎ በክልሉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በሚሠራበት አካባቢ ሴቶችን እና ወጣቶችን አደራጅቶ የማር ቀፎዎችን በማስቀመጥ በዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ 161 የማር መንደሮችን ለማደራጀት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሚሊዮን ዘመናዊ የማር ቀፎ ተሠራጭቷል፤ 103 ሺህ ቶን የማር ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ፤ አዳማ፤ ጅማ አካባቢ ላይ በስፋት የአሳ መንደሮችን የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። እንደ ክልል በዘጠኝ ወራት 84 የአሳ መንደሮች ማደራጀት መቻሉን አመልክተው፤ ከኦሮሚያ አሳ ምርምር ማእክል ጋር በመሆንም አንድ ሚሊዮን የአሳ ጫጩት መሰራጨቱንም አስታውቀዋል፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም