
አቶ አሰፋ ሹንባጋ ይባላሉ፡፡ አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ ነዋሪነታቸው አዲስአበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነው። አካል ጉዳተኛነት ሳይበግራቸው የራሳቸውን ሥራ ፈጥሮ ከመሥራት ባሻገር ለሌሎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ከጫማ ማስዋብ (ሊስትሮ) ሥራ ተነስተው የራሳቸውን የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት በመክፈት የቆዳ ምርቶች እያመረቱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ትምህርታቸውን እስከአስራ ሁለተኛ ክፍል የዘለቁት አቶ አሰፋ፤ የመጀመሪያው ፍላጎታቸው በትንሹ ጀምረው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነበር፤ የጫማ ማስዋብ ሥራ እየሠሩ የራሳቸው የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ከፍተው የመሥራት ህልም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡
ባደረጉት ጥረትና ትግል ህልማቸው ተሳክቶ በ2009 ዓ.ም የማምረቻ ሥፍራ ከቂርቆስ ክፍለከተማ አግኝተው ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡‹‹ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ የሚጎድለኝ ነገር ስለሌለ ቁጭ ብሎ መሥራት የምችለው ሥራ በመምረጥ ሥራ ጀመርኩ፡፡
ለዚህም ሥራ ቀደም ሲል የሠራሁት የጫማ ማስዋብ (ሊስትሮ) ሥራ በእጅጉ ጠቅሞኛል ፤ ይህንኑ ሥራ እያሳደግኩ የቆዳ ውጤቶችን ወደ ማምረት ሥራ ገባሁ ›› ይላሉ ፡፡
ጫማ ከማስዋብ ባለፈ ጫማዎችንም መስፋት፣ ሶል የመቀየርና የማደስ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፤ ሥራን አጠናክሮ በማስቀጠልና በማሳደግ ጫማዎችና ቦርሳዎች በመሥራት ጀምረዋል ፤ ጎን ለጎን፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ዋሌት እና የመሳሰሉ የቆዳ ምርቶች በማምረት ሥራውን ለማስፋፋት ችለዋል።
ቀስበቀስ ሥራዎችን በማሳደግ የተማሪ ቦርሳዎችን ሳይቀር ወደ ማምረት ሥራ መግባታቸውን፤ ብድር በመውሰድ ሥራውን በማስፋፋት ምርቶች አዲስ አበባን ጨምሮ ለተለያዩ ክልሎች የሚልኩ መሆኑን ፤ ምርቶችን በብዛት በማምረት ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠሩ እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡
የአቶ አሰፋን የሥራ ትጋትና ውጤታማነት የተመለከተው የቂርቆስ ክፍለ ከተማም መጀመሪያ ለማምረቻ ከሰጣቸው 12 ካሬ የመሥሪያ ቦታ ተጨማሪ 20 ካሬ የመሥሪያ ቦታ እንደሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ አሁንም ተጨማሪ ማሽኖችን በማስገባት ሥራዎችን በማስፋፋት መሥራት መቀዳቸውን ጠቅሰው፤ ተጨማሪ ማስፋፊያ ቦታ እየጠየቁ ነው ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን ላይ ድርጅታቸው ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ የተማሪ ቦርሳዎች፣ ነጠላ ጫማዎች፣ ዋሌቶች፣ ቀበቶዎች እና ሌሎች የቆዳ ምርቶች ያመርታል፡፡ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ከዘመኑ ጋር አብሮ እንዲሄዱ ተደርገው ለገበያ ይቀርባሉ፡፡
ድርጅታቸው ለስድስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በቀጣይ ምርቶች ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ይናገራሉ፡፡
ለምርቶች የሚውሉ አክሰሰሪዎች ከውጭ በማስመጣት እንደሚሠሩ አሁን ላይ የየአክሰሰሪ እጥረትና የቆዳ ዋጋ መናር ለሥራቸው ፈተና ሆኖባቸዋል ፡፡ ኬሚካል ፣ አክስስሪዎችና ቆዳ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ የሚመረተውን ምርት አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ ባነሰ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለም ያመላክታሉ፡፡
ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን፤ ተመሳሳይ የሆኑ ምርቶችን ሌላ ቦታ ዋጋቸው ከእጥፍ በላይ ነው፤ ይሄ አግባብነት እንደሌለው ያስገነዝባሉ፡፡
መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ ለዚህ ደረጃ እንደበቁም የሚናገሩት አቶ አሰፋ፤ ‹‹ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ አካላት የተለያዩ ድጋፎችና እገዛ አድርገውልኛ፤ የከተማ አስተዳደሩም በተለያዩ ቦታዎች በሚዘጋጁ አውደርዕዮች እንዲሳተፉ ዕድሉንም እያመቻቸልን ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።
‹‹እንደእኔ ያሉ አካል ጉዳተኞች በብዙ የሥራ መስክ ላይ አላይም፤ መሥራት እየቻሉ ለምን ወጥተው አይታዩም የሚል ቁጭት በውስጤ ይመላለሳል›› የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ማንኛውም ሰው ሥራ ሲጀምር ብዙ ፈተናዎችና ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፤ ችግሮቹ አካል ጉዳተኞች ላይ ተደራራቢ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ የተለየ ችግር አይሆንም ብለዋል፡፡
ዋናው የሚያጋጥሙ ችግሮችን አልፋለሁ፤ እወጣዋለሁ፤ እሻገራለሁ ብሎ ራስን በማሳመን ወደፊት ለመጓዝ ጥረት ማድረግ ነው የሚሉት አቶ አሰፋ፤ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ ማመን ይኖርባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ አቶ አሰፋ በሦስት ሺህ ብር መነሻ ሥራውን ‹ሀ› ብለው ጀምረው ዛሬ ላይ ስድስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ማስመዘገብ ችለዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም