የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በየጊዜው የሚገጥመውን አስተዳደራዊ ፈተና በተገቢው መንገድ ባለመመራቱ በስፖርቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ እንቅፋቶች ሲፈጠሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ታላላቅ መድረኮች ዘመን ተሻጋሪ ክዋክብት አትሌቶች መፍለቂያ ብትሆንም ስፖርቱ ወደዘመናዊው የአስተዳደር ደረጃ መሻገር ያልቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ያላትን ትልቅ ስም የሚመጥን ፌዴሬሽንና ተቋሙን ወደፊት የሚያራምዱ የአመራር ብቃቱ ያላቸው ሰዎች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡም የስፖርት ቤተሰቡ ሲጠይቅ ኖሯል። ይሁን እንጂ ስፖርቱን ለመምራት በተለያየ ጊዜ ዕድሉን ያገኙ የአትሌቲክሱን ችግሮች ሳይፈቱ የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው ከመሰናበት የዘለለ ታሪክ ማኖር አልቻሉም።
ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ባለፉት ዓመታት ስፖርቱን ሲመሩ የቆዩ ግለሰቦች ተሰናብተው በአዳዲስ አመራሮች ተተክተው በይፋ ሥራ ጀምረዋል። እነዚህ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ሲመጡ የመጀመሪያ ቢሆንም በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ ወይም ለስፖርቱ ቅርብ መሆናቸውን ተከትሎ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይቀርፋሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ያም ሆኖ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ግልፅ ነው።
በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታዩት የአስተዳደር ግድፈቶች ከምንጊዜውም የበለጠ በጎሉበት ወቅት ኃላፊነቱን መረከባቸው ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ቀላል ላይሆንላቸው ይችላል፡፡ ስፖርቱን ለመምራት ያገኙትን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመውና ተግባብተው መሥራት ከቻሉ ግን ጊዜውና አቅሙ አላቸው። ለዚህም የስፖርቱን ችግሮች ነቅሰው በማውጣት ከወዲሁ በትኩረትና በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
በቀደሙት ዓመታት በፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ደካማ የውሳኔ አሰጣጦች፣ አቅዶ የመተግበር ችግር እና ግልፅ ያለመሆን፣ እንዲሁም አትሌቶቻችን እና አጠቃላይ ስፖርቱን የሚመለከቱ ችግሮችን አግባብ ባለው መንገድ መፍታት ያለመቻል ችግሮች በተደጋጋሚ ታይተዋል። እነዚህ ከአስተዳደር ብቃት እና ቁርጠኝነት ማነስ ጋር የተያያዙ ችግሮች የፈጠሯቸው ክፍተቶችም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እድገት ከማደናቀፍ በዘለለ ከጊዜ ወደጊዜ በፌዴሬሽኑ፣ በአትሌቶች፣ በአሠልጣኞች እና በስፖርቱ እውነተኛ ደጋፊዎች ዘንድ መተማመን እንዲጠፋ እያደረጉ መጥተዋል። አዲሱ አመራር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት እና በውድድሩ ወቅት እንዲሁም ከዚያም በፊት በነበሩት ጊዜያት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ አስተዳደራዊ ድክመቶች በስፋት ተስተውለዋል፡፡ ከድክመቶቹ አብዛኞቹ በቀደሙት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ግዜም የነበሩ እና ባሉበት ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መቀጠል የለባቸውምና አዲሱ አመራር ሊቀርፋቸው ግድ ይላል።
የሀገር ውስጥ ውድድሮች የጥራት ደረጃ፣ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣው የልምምድ እና የውድድር ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት፣ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በተቃረቡ ቁጥር ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚታየው ውዝግብ፣ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለሚያስተዳድር ተቋም የጀርባ አጥንት ከሚባሉ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው የመረጃ ቋት አደረጃጀት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መድፈንም ከአዲሱ አመራር የሚጠበቁ ቁልፍ ተግባራት ናቸው።
አትሌቲክሱን ለመምራት የሚወጡ የመተዳደሪያ ሕግ እና ደንቦችን በመከለስ ለስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ በይፋ ማስተዋወቅ እንዲሁም በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ መከታተል ያስፈልጋል። ለዚህም በስፖርቱ ዙሪያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ለይቶ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ለመተግበር መንቀሳቀስ ይጠይቃል።
ውጤታማ ሥራን ለማከናወን የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ፣ ዕቅዶች ለማዘጋጀት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመፈተሽ ቁልፍ ጥንካሬዎችን፣ ድክመቶችን፣ ዕድሎችን እና ስጋቶችን መለየት አለበት። የአጭር ጊዜ ዕቅዱ ፈጣን ማሻሻያዎችና የቅድሚያ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው በጊዜያዊ የልምምድ እና ውድድር ማዘውተሪያ ችግሮች መፍቻ፣ መቀየር ያለባቸው የአሠራር ሂደቶች፣ የአሠልጣኝነት ሥልጠና መርሐ ግብሮችን ማሳደግ፣ የገቢ ምንጮችን ማጠናከር፣ በቅርቡ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች እና ሌሎችም መካተት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል!
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም