የፖለቲካ ባሕላችንን መለወጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው!

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ከጦርነቶች ጋር የተያያዘ ሰፊ ትርክት ያለን ሕዝቦች ነን። ስለ ፍትሕ እና ነፃነት ተገድደን የገባንባቸው ጦርነቶች የብሔራዊ ክብራችን አካል በመሆን በየዘመኑ መጥቶ ለሚሄድ ትውልድ የሀገር ፍቅር ምን እንደሆነ እንዲማር፤ ለሀገር መሞት ክብር እንደሆነ በተጨባጭ እንዲማር አስችለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም እንደ ሀገር የገነነ ልብ የሚያሞቅ፤ አንገት የሚያቀና ታሪክ ባለቤት አድርገውናል ።

ይህም ሆኖ ግን ችግሮቻችንን በውይይት እና በሠላማዊ መንገድ በድርድር መፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባሕል መፍጠር ባለመቻላችን፤ ለብዙ ግጭቶች እና የለየላቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች ተዳርገናል። በዚህም እንደሀገር ከነበርንባቸው የሥልጣኔ ማማዎች ወርደን በድህነት እና በኋላቀርነት ዋጋ ከሚከፍሉ ሀገራት መካከል አንዱ ሆነናል። ይህም በብዙ መስዋዕትነት ያስጠበቅነውን ነፃነትን እና ነፃነቱ የሰጠንን ሞገስ አደብዝዞታል።

በአንድ ዘመን አያቶቻችን ባሕር ተሻግሮ በንግድ እና በጦር ኃይል ገናና ያደረጓትን ሀገር፤ እንደ አክሱም እና ላሊበላን ያሉ ዓለምን ያስደመሙ፤ ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑ፤ የአባቶቻችን የአዕምሮና የእጅ ጥበብ ውጤቶች፤ ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘን መሻገር አቅቶን፤ ለሥልጣኔ እና ሥልጣኔ ለሚወልደው መደመም አዲስ ሆነን በቁልቁለት የጉዞ ትርክት ከራሳችን ዕጣ ፈንታ ጋር ተጣልተን እና በተቃርኖ ቆመን ዓመታትን አስቆጥረናል።

እንደ ሀገር ጥላ ሆኖ የሚከተለን ይህ እውነታ ዛሬም በቁጭት ለጀመርነው እና ተስፋ ላደረግነው በልማት ድኅነትን የማሸነፍ አዲስ የታሪክ ጉዞ ትልቅ መሰናክል፤ እንደ ሕዝብ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለፈጠርነው ሀገራዊ መነቃቃት ተግዳሮት ሆኖብናል። ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ለጀመርነው የመለወጥ ጉዞ ፈተና፤ ለመጪው ትውልድ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር አስበን ለጀመርነው ትውልድ ተሻጋሪ ተስፋችን ጋሬጣ ሆኖብናል።

ይህ የሀገራችን ፖለቲካ የተገዛበት፤ ከመነጋገር እና ከመወያየት ይልቅ ኃይል እና መጠላለፍን መሠረት ያደረገ የተዛባ አስተሳሰብ፤ እና የፖለቲካ ባሕል ትናንቶቻችን እንዳበላሽ፤ ዛሬ ላይ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል እንዳስገደደን ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም። በሰከነ መንፈስ ቆም ብሎ ማሰብ ከተቻለ እውነታው የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ያልተፈታተነው ዜጋም አይኖርም።

ዛሬም ቢሆን ስለትናንት ችግሮቻችን ብዙ እየተወራ፤ ስላስከፈሉን ዋጋ በብዙ እየተተረከ፤ ችግሮችን/አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የተከፈተ ልብ እና የተገራ ህሳቤ መፍጠር ያልቻሉ፤ ዛሬም በፉከራ እና ፉከራ በሚወልደው መደንደን የሠላም ትርጉም የማይገባቸው፤ የኃይል፣ መጠላለፍ እና የሴራ መንገድ አዋጭ ሆኖ የሚታያቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች አሉ።

የእነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች መንገድ በየትኛውም ሁኔታ የሕዝባችንን የሠላም እና መልማት ጥያቄ መመለስ እና የቀደሙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስብራቶቻችንን መጠገን አይችልም። ከግጭት አዙሪት ወጥተን ሠላማዊ እና ለዜጎቿ የተሻለች ሀገር መፍጠር፤ ትውልዶችን ቀጣይነት ላለው ለውጥ እና ለለውጥ ፍሬዎች የሚያነቃቃ ሀገራዊ ትርክት መፍጠርም አያስችለንም።

ይህንን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ለበለጠ ድል እና ውጤት እንዳንራመድ ያደረገንን የፖለቲካ ባሕል የመለወጥ ሥራ ለፖለቲከኞቻችን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። የኃላፊነት ደረጃውም ከመጪ ትውልድ ዕጣ ፈንታ እና ከሀገር ሕልውና ጋር በጥብቅ የሚተሳሰር፤ ከትናንት በአግባቡ ተምሮ ራስን በሁለንተናዊ መልኩ ከመለወጥ የሚነሳ፤ ነገን ብሩህ አድርጎ ማየት እና መሥራትን ተስፋ አድርጎ መራመድን የሚጠይቅ ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You