181 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን በማረፊያው ላይ ባጋጠመው ችግር አደጋው ስለመፈጠሩ እየተነገረ ነው
ደቡብ ኮሪያ በትናንትናው ዕለት ካጋጠማት አስቸጋሪ የአውሮፕላን አደጋ በኋላ በቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ ፍተሻ እንዲደረግ አዛለች፡፡
የሀገሪቱ የመሰረተ ልማት እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአነስተኛ አየር መንገዶች በስፋት ጥቅም ላይ በሚውለው የቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖች ላይ ልዩ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ይህ የተባለው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ከባንኮክ 181 ሰዎችን አሳፍሮ ከሴኡል በስተደቡብ ምዕራብ 290 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሙአን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር ከግድግዳ ጋር ተጋጭቶ አደጋ መፈጠሩን ተከትሎ ነው፡፡
ቀደም ሲል የደቡብ ኮሪያ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ቾይ ሳንግ-ሞክ የአውሮፕላን አደጋ ተደጋጋሚነትን ለመከላከል በሀገሪቱ አጠቃላይ የአየር መንገድ ሥርዓት ላይ የአደጋ ጊዜ ደህንነት ፍተሻ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡
የ179 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ መንስኤ በአሁኑ ወቅት በምርመራ ላይ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ግኝቶች በማረፊያ ቁሶች ብልሽት አደጋው ስለመፈጠሩ አመላክተዋል፡፡
በዛሬው እለት በጄጁ ኤር የሚተዳደረው ሌላ ቦይንግ 737-800 በተመሳሳይ በማረፊያ መሣሪያው ላይ ባጋጠመው ችግር በደቡብ ኮሪያ ወደሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ መመለሱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል ።
ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖች በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በአነስተኛ በጀት በሚሰሩ የሀገር ውስጥ አየር መንገዶች ነው።
የትናንቱን አደጋ ያስተናገደው ጄጁ ኤር በአሁኑ ጊዜ 39 አውሮፕላኖች ሲኖሩት፤ 62ቱ ደግሞ በቲዌይ ኤር፣ ጂን ኤር፣ ኢስተር ጄት፣ ኤር ኢንቼዮን እና ኮሪያ ኤር በተባሉ አየር መንገዶች ውስጥ ይገኛሉ።
ከአደጋው በኋላም በጄጁ አየር መንገድ ለመጓዝ ትኬት ቆርጠው የነበሩ ደንበኞች በብዛት ጉዟቸውን እየሰረዙ ሲሆን፤ እስካሁን 33 ሺህ የሀገር ውስጥ 34 ሺህ ዓለም አቀፍ በረራዎች በተጓዦች ተሰርዘዋል፡፡
ዮንሀፕ የተባለው የሀገሪቱ ሚዲያ በአሁኑ ወቅት በመላው ደቡብ ኮሪያ ጉዟቸውን ከሚሰርዙ ተጓዦች ባለፈ የአውሮፕላን ትኬት የሚገዙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም