
ከሦስት ፊደላት የተዋቀረች አንዲት ቃል፤ ከሰዎች አንደበት የማትጠፋ፤ ለየትኛውም ፍጡር በተለይም ለሰው ልጆች እጅጉን ወሳኝ የሆነች ጉዳይ፤ ሁሉም አብዝቶ የሚሻት፣ ነገር ግን ኅልው ለመሆኗ ጥቂቶች ለሚለፉና ዋጋ የሚከፍሉላት፤ በዋጋ የማትተመን፤ በሰው ልጆች ስሪት ልኬት የማትሰላ ናት፤ ሰላም::
ይህች መልካም፣ መከሰቻዋም ብዙ የሆነችው ሰላም ታዲያ፤ ከሙላቷ እየጎደለች፤ ከልኬቷ እየወረደች፤ በብዙዎች ብትፈለግም፣ በጥቂቶች እየተገፋች፤ ከነቢብ ያለፈ ለተግባር የሚተጉላት እያነሱ፤ የሚናገሩላትም ቢሆኑ ከልባቸው ባልደረስ የማስመሰል ብሂል ላይ የተመሰረቱ የሆኑባት፤ አጠቃላይ የሰላም ጉዳይ የመንግሥትና መንግሥት ሥራ ብቻ ተደርጎ እየተወሰደ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል::
ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ዓለም በየፈርጁ ሰላም ርቋት በጦርነት የምትታመሰው:: ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ሰላሟ እየደበዘዘ፤ ሰላሟም በሙላት የመገለጽ ትርጉሙ በአንጻራዊ ተቀጽላ እየተደገፈ የሚነገርበት አግባብም ተፈጥሯል:: የተሟላ ሰላም የሚባለው ጉዳይ በአንጻራዊ ሰላም ተተክቶ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረም አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል::
ለዚህ ደግሞ ምክንያት እንቁጠር ከተባለ ለቁጥር የሚታክት ምክንያት መደርደር ይቻላል:: ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰላም ዋጋ እያነሰ፤ የሰላም ሚዛን እያጋደለ መምጣቱን መገንዘብ ግን የሚከብድ አይደለም:: የሰው ልጆች ወጥቶ የመግባታቸው፤ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሠርቶ የመኖራቸው፤ ሃብት አፍርቶ የመጠቀማቸው፤… ጉዳዮች ጥያቄ ውስጥ ከገቡና በአንጻራዊ ልኬት ከተመዘኑ ውለው አድረዋል::
ለዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ፣ የኃይል ፖለቲካችን ነው። መሻቴን፣ ፍላጎቴን፣ እሳቤዬን፣ በኃይል ማስፈጸም እችላለሁ። ክላሽ ካነገትኩ የኔ መሻት ይሳካል ብለው የሚያምኑ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል እና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያስቡ፤ ኃይል በብቸኝነት የመጠቀም ሥልጣን የመንግሥት መሆኑን የማይቀበሉ፤ በመግደል መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ እንደሌለ የማያምኑ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው::
የከሰሩ ፖለቲከኞች፤ ከግጭትና ከጦርነት የሚያተርፉ፤ ኑሮና ሕይወታቸውም በዚሁ ላይ የተመሰረቱ ግለሰቦችና ቡድኖች ደግሞ የዚህ ቀዳሚ ባለ አጀንዳዎች ናቸው:: እነርሱ በተመቻቸው ቦታ ሆነው ድሃውን ሕዝብ ወደ ግጭትና ጦርነት እየነዱ በመማገድ እሳቱን መሞቅና እንጀራቸውን መጋገር ተቀዳሚ ተልዕኳቸውም፤ የኑሮ መሰረታቸውም ነው:: በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ከፍ ባለ ግጭትና ጦርነት ውስጥ አልፋለች::
በሰሜኑ ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት፤ በአማራ እና ትግራይ ክልል የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት እንደ ሀገር ያስከፈሉት ዋጋ ቢኖርም፤ ለእነዚህ ኃይሎች ግን ሕልውናቸውን ለማቆየት፤ የተሻለ ትርፍም ለማግኘት አግዟቸዋል:: ዛሬም ሀገርና ሕዝብ ከዚህ ችግር ተላቅቀው አንጻራዊ ሰላምን ባገኙበት ወቅት ለዳግም ግጭትና ጦርነት ዙሪያውን የሚጭሩትም ለዚሁ ነው:: ይሄም ሆኖ ዛሬ ኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም ላይ ትገኛለች::
ዋናው ጉዳይ አንጻራዊ ቦታ ሲይዝ፤ ሁሉም ነገር አንጻራዊነትን ይላበሳል:: የሰላምም አንጻራዊ ሆኖ መገለጽ በሌላውም መስክ እንዲሁ አንጻራዊነትን ይፈጥራል:: አንጻራዊ ሰላም ባለበት፣ ልማቱም አንጻራዊ ነው፤ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሁነቱም አንጻራዊ ነው፤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተግባራቱም አንጻራዊ ናቸው:: ሌላው ቀርቶ የትውልድ ግንባታና ቀረጻ ሂደቱም አንጻራዊ ግዴታ ውስጥ ይወድቃል::
በዚህ መልኩ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ አንጻራዊነት ውስጥ መገለጥ ሲጀምሩም፤ ልማቱም ሆነ ሌሎች ጉዳዮቻቸው ሁሉ እንዲሁ በአንጻራዊነት ማሕቀፍ ውስጥ ይፈረጃሉ:: ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች አንጻራዊ ልማት፤ አንጻራዊ መሠረተ ልማት፤ አንጻራዊ ትምህርት፤ አንጻራዊ የጤና አገልግሎት፤ አንጻራዊ የትውልድ ግንባታ፤ አንጻራዊ…፤ እያልን ለመግለጽ የምንገደደው::
በዚህ በአንጻራዊነት ልኬት ውስጥ ሆነንም ነው፤ እንደ ሀገር ልማትን የምናራምደው:: ዴሞክራሲን እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የምንተጋው:: የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና ሌሎችም መሠረተ ልማቶችን የምንገነባው:: ኢንቨስትመንትን የምናሳድገው፤ የወጪ ንግዱን ሚዛን ለማመጣጠን የምንታትረው:: የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለመትከልም፤ የፖለቲካውን አውድ አካታችነት ከፍ ለማድረግ ልምምዱን የጀመርነው::
ለአብነት፣ ሰላም በኢኮኖሚ ሚዛን ላይ በአንጻራዊነት በተቀመጠባቸው ዓመታት አያሌ ሥራዎች ተሰርተዋል:: በዚህም በግብርና፤ በቱሪዝም፤ በማዕድን፤ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፎች የተጀመሩ ኢንሼቲቮች ውጤት እያመጡ ይገኛሉ::
ለምሳሌ፣ ሰላምን አብዝተው ከሚሹ ጉዳዮች መካከል አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው:: አርሶአደሩ በማሳው ላይ ውሎ የሚያርሰው፣ የሚዘራውና ሰብሉን የሚሰበስበው ሰላም ሲኖር ነው:: በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ ሆኖ የሚፈጽመው ግን እንዲሁ በአንጻራዊነት የሚገለጽ ነው::
በዚህ በኩል፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንዳስረዱት፤ በዘንድሮው ዓመት 31 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል:: ይሄ እንዲሆን ደግሞ በርካታ ግድቦች ተሰርተዋል፤ የመስኖ ልማት ሥራውም ከፍ ብሎ ተገልጿል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሌማት ቱሩፋት ኢኒሼቲቭ ሥራም ቢሆን፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ”ፓረንት እና ግራንድ ፓረንት” በመታገዝ የጀመረችው የዶሮ እርባታ የእንቁላል ምርትን በብዙ አሳድጓል:: በአርቴፊሻል ኢንተርሚኒሽን እየተስፋፋ ያለው ላሞችን የማራባት መንገድም የወተት ምርትን በማሳደግ፣ በሰው 66 ሊትር የነበረውን የወተት ፍጆታ ወደ 88 ከፍ አድርጎታል:: በማር እና በዓሣ ምርት በኩልም ከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል::
በተመሳሳይ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማምጣት ተችሏል:: ኢንዱስትሪ ዘንድሮ 12 ነጥብ ስምንት በመቶ እንዲያድግ ታስቦ ነው የተሠራው:: ኢትዮጵያ ታምርት ደግሞ የዚህ አንዱ መንገድ ሲሆን፤ በዚህም ዘንድሮ እድገቱን 65 በመቶ ማድረስ ተችሏል:: ይሄ ደግሞ ፋብሪካው እያለ በተለያየ ችግር ምክንያት ማምረት ከሚችለው ያነሰ ያመርት የነበረው ፋብሪካ በማሻሻል ላይ ተመስርቶ የመጣ ነው::
ለምሳሌ፣ ሲሚንቶ 16 በመቶ በማደጉ የሲሚንቶ ምርት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል:: የለሚ የሲሚንቶ ፋብሪካም የዚህ ቀዳሚ አቅም ነው:: የብረት ውጤቶችም በ18 በመቶ አድገዋል:: መስታወት ምርት በኩልም ዛሬ ላይ በዓመት 600 ሺህ ቶን ገደማ የሚያመርት የመስታወት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል::
ማዕድን ሌላው አንጻራዊነት የወለደው የኢኮኖሚ ዘርፍ ሲሆን፤ በዘርፉ በርካታ ውጤትም እየታየም ነው:: ለምሳሌ ወርቅ፣ በዓመቱ 37 ቶን ኤክስፖርት በማድረግ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል:: በሌላ መልኩ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዝን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል:: በዚህም ጋዝን ለማውጣት በንጉሡ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢሕአዴግ ዘመን ሙከራዎችን ወደ ተጨባጭ እውነት ለመቀየር ጫፍ ላይ ተደርሷል::
ምክንያቱም፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ/ፌዝ ሥራ አልቋል:: ይሄ በቅርቡም ይመረቅና ሁለተኛው ምዕራፍ ይጀመራል:: ይሄ ደግሞ ለግብርናውም እድገት ያራሱ ተጽዕኖ አለው:: ምክንያቱም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሥራ በቅርቡ ይጀመራል:: ስለዚህ በማዕድን ዘርፉ አጠቃላይ በጋዝ፣ በወርቅ፣ በማዳበሪያ መልኩ የሚገለጽ ከፍ ያለ ሥራ ተሰርቶ፤ አመርቂ ውጤትም እየተገኘበት ይገኛል::
ሌላኛው በአንጻራዊነት ልኬት ውስጥ የሚገለጠው የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና አገልግሎት ናቸው:: በዚህም የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አራት ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል:: ከአገልግሎት/ከሰርቪስ የተገኘው ኤክስፖርትም ስምንት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። በዚህና መሰል መልኩ አጠቃላይ 32 ዶላር ማግኘት ተችሏል::
ከመሠረተ ልማት አኳያም ቢሆን መንገድና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች በእጅጉ ለአንጻራዊነት የተጋለጡ፤ ከሰላም ጋርም የተቆራኙ ናቸው:: በዚህ ውስጥም ቢሆን የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማነታቸው አጠያያቂ አይደለም:: ለአብነት፣ መንገድን በተመለከተ ዛሬ የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን 175 ሺህ ኪሎ ሜትር ደርሷል::
የአፈጻጸም ደረጃቸው ቢለያይም፣ በቀጣይ አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ብር የሚጠይቁ 300 ፕሮጀክቶች ፀድቀውና ኮንትራት ተፈርሞላቸው ሥራ ተጀምሯል:: ከእነዚህ ውስጥ ከ11 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሆኑ 169 የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ:: አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላዩም ዘንድሮ ይመረቃሉ:: በአዲስ አበባ ብቻ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ይመረቃል::
ከግንባታ ጋር በተያያዘ ከመንገድ ግንባታ ባሻገር በግድቦች፣ በህንጻዎችና አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኮሪዶር እድገት ጨምሮ የተነቃቃ የኮንስትራክሽን መስክ ተፈጥሯል:: የኢነርጂውን መስክ ብንመለከት፤ ህዳሴ፣ ኮይሻ፣ አይሻ፣ አሰላ እና አሉቶ ቢያንስ እያለቁ ያሉ ሥራዎች ናቸው:: የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ (ዓባይ) ግድብም በመጪው መስከረም ይመረቃል::
ከማኅበራዊ መሠረተ ልማት አኳያም፣ ለአብነት ከጤና ጋር በተያያዘ፣ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ለምሳሌ፣ እንደ ሀገር ካሉት 22 ሺህ ተቋማት መካከል ስድስት ሺህ የሚሆኑት በቅርብ ጊዜያት የተገነቡ ናቸው:: የጤና መድህንን ተደራሽነትንም ማስፋት ተችሏል:: የጤና ባለሙያዎችንም እንዲሁ በቁጥርም፤ በሙያ ብዝሃነትን ከፍ ማድረግ ተችሏል::
በትምህርት በኩልም፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና በማስፋፋት በዚህ ዓመት አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕጻናት ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል:: 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናትም ቅድመ መደበኛ ላይ መግባት ችለዋል:: ለእነዚህ ሁሉ መምህራን ተቀጥረዋል:: ይሄ ደግሞ ትውልድን ከመሠረቱ ጀምሮ ለማነጽና ለመገንባት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት የተከናወነ ተግባር ነው::
ከሰላም ጋር አብሮ የሚነሳውና ተጽዕኖውም የሚያርፍበት ሌላው ዘርፍ፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ነው:: በዚህ በኩልም ቢሆን፣ በምርጫ ያሸነፈ መንግሥት ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ባሉ የሥልጣን ቦታዎች፤ አልፎም በውሳኔ ሰጪ የካቢኔ ቦታዎች ሳይቀር ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን፤ ስለ ኢትዮጵያ አበርክቶ ይኖራቸዋል የተባሉ ከፖለቲካ ውጪ ያሉ ግለሰቦችን ሳይቀር አሳትፎ መሥራት ተችሏል::
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የመነጋገር፤ የመወያየትና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ የመሥራት ልምምዱም አድጓል:: ሰዎች በአመለካከታቸው፣ በማንነትና በሌላም ምክንያት እንዳይገፉ፤ እንዳይታሰሩና ሌላም ሰብኣዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው የሚያደርጉ ርምጃዎች ተወስደዋል:: በተግባርም ተገልጠዋል::
ይሄ ሁሉ በአንጻራዊ ሰላም ሚዛን ውስጥ ሆኖ የተገኘው ውጤት ዘላቂ እንዲሁን፤ እንደ ሀገርና ሕዝብም ወደታሰበው ብልፅግና መድረስ እንዲቻል ታዲያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም፣ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ሰላም ነው:: የሚያስፈልገው ብልፅግና ነው:: ይሄ እንዲሆን ደግሞ ተደምሮ መሥራት ያስፈልጋል:: ለመደመር ደግሞ መነጋገር፤ መወያየት፤ መደራደርና መግባባት ይጠይቃል::
ይሄ አውድና ሁኔታ እንዲፈጠር ደግሞ ሰላም እጅጉን ወሳኝ ነው:: ሰላም ደግሞ ከራስ በራስ ሰላም ይጀምራል:: አንድ ሰው ውስጡ ሰላም ሲሆንና ሰላማዊነት ሲሰማው በዙሪያው ላሉ ሰዎች ሰላምን ያጋባል:: ተነጋግሮ መግባባትን ይፈጥራል:: የግለሰቦች ሰላም ድምር የማኅበረሰብን ሰላም ይፈጥራል:: የማኅበረሰብ ሰላም ሲደመር ደግሞ የሀገርና ሕዝብን ሰላም ይፈጥራል::
ይሄ ሰላም ሲኖር ተነጋግሮ መግባባት፤ ተወያይቶ የጋራ ሕልም መያዝ፤ ለጋራ ሕልም መሳካትም በጋራ ተደምሮ መቆም ይወለዳል:: በመነጋገር የተፈጠረ የጋራ ሕልም፤ በመደመር(አብሮ በመቆም) የተጀመረ የሕልም ጉዞ ደግሞ፤ መዳረሻው ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ነው:: በመሆኑም ሰላም ከአንጻራዊነት ልኬት ወጥታ ወደ ተሟላ ልዕልናዋ እንድትመለስ የሰላምን ዋጋ እንረዳ::
ስለ ሰላም ያለንን ምልከታ እንግራ:: ሰላምን ከምላሳችን ወደ ልባችን እናውርዳት:: ከመንግሥታዊ ኃላፊነት ከሚል ፍረጃ አውጥተን፤ ወደ ሁላችን ኃላፊነትና ሥራ እንውሰደው:: ለዚህ ደግሞ አንዱና ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያን ስትባላና ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች መኖራቸውን መረዳት፤ ተረድቶም መከላከል ነው:: ይሄ ሲሆን ሰላም ልኳን ታገኛለች፤ ለእኛም ወረታውን ትከፍላለች::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዐምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም