ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የሕዝቧን ቁጥር ከግምት ያስገባና አሁን የደረሰችበትን የኢኮኖሚ ደረጃ የሚመጥን የባሕር በር ያስፈልጋታል። ይህንን ፍላጎቷን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ አቅርባለች። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ኃይሎች ከውስጥም ከውጪም ጥያቄዋን በጸብ አጫሪነት ለመተርጎም ብዙ ተንቀሳቅሰዋል። የአድመኝነት ህብረትም ፈጥረዋል። ሆኖም ሁሉም የሄዱበት መንገድ አዋጪ ባለመሆኑ አንዳንዶች ወደ ቀልባቸው መለስ ማለትን መርጠዋል።
ጥያቄውን ተከትሎ የተሄደበት የዲፕሎማሲ አካሄድ የጥፋት ኃይሎችን ምሽግ ያፈረሰ፤ የባሕር በር ጥያቄዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ያደረገ ነው። በተለይ የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውቅና የሰጠ የዲፕሎማሲያዊ ድል መገለጫ ነው። ይህም ሆኖ አሁንም የሴራ እንቅስቃሴያቸውን የቀጠሉ ሀገሮች አልጠፉም።
“የሰጠናትን የወደብ አገልግሎት ተረክባ አላስተዳደረችም” እያሉ የሚከሱም አልጠፉም። የኢትዮጵያ ጥያቄ ዛሬም ነገር አንድን ወደብ እንጠቀም የሚል አይደለም። የባሕር በር ያስፈልገናል ነው ።እንጀራ ለጠየቀ ሊጥ እንካ አይባልም። 120 ሚሊዮን ዜጋ ያላት ሀገር ኢኮኖሚያዋ በፍጥነት እያደገ የመጣ ሀገር አንድና ሁለት ወደብ ይዛ እድገቷን ማረጋገጥ ከቶ እንዴት ይቻላታል።
በበቂ ሁኔታ የወጪ እና የገቢ ምርቷን ለማስወጣትና ለማስገባት በአቅራቢያዋ ያሉ የባሕር በር ተጠቃሚነት ሊረጋገጥላት ይገባል። ጥያቄዋ ይሄ ነው። ይሄ ጥያቄዋ መልስ ባገኘ መልኩ በቱርክ አሸማጋይነት “የአንካራ ስምምነት” በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ተካሂዷል።
በስምምነት ሰነዱ ላይ የሰፈረው የተስማሙባቸው ጉዳዮችም የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት ፣ አንድነት ፣ነፃነት እና የግዛት አንድነት ለማክበር ቁርጠኛነታቸውን የገለጹበት ነው።
በወዳጅነት እና በመከባበር መንፈስ ልዩነቶችን እና አከራካሪ ጉዳዮችን በመተው፤ በመተጋገዝ ለጋራ ብልፅግና ለመስራትም የተስማሙበት ነው። መንግሥት አልባ ሆና የአልሸባብ መፈንጫ የነበረችውን ሀገር በማገዝ የኢትዮጵያ ወታደሮች ህይወታቸውን ገብረዋል። አካላቸውን አቁስለዋል። ይሄ ሶማሊያ ሀገር ሆና እንድትቀጥል የተሠራ ሥራ ነው።
በችግሯ ወቅት ዞር ብለው ያላይዋት እነ ግብፅ ዛሬም የቀጣናውን ሰላም ለማደፍረስ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በወዳጅነት እንዳትቀጥል ሴራ ከመጠንሰስ አላለፉም። ሆኖም ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥታለች። ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ የባሕር በር ተጠቃሚ መሆኗ / ወደ ባሕር እና ከባሕር / ሊያስገኝ የሚችለው ልዩ ልዩ ጥቅም ላይ መተማመን የተደረሰበት መሆኑ በስምምነት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
እንዲሁም ሁለቱንም ተጠቃሚ ባደረገ ሁኔታ የንግድ ውል ይታሰራል። ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ቀጣይነት ያለው / ዘላቂ የባሕር በር መዳረሻ / አክሰስ እንዲኖራትም የሚል ሃሳብ በስምምነት ላይ ሰፍሯል፤ ይህም በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስልጣን ስር የሚተገበር ይሆናል።
የኢትዮጵያ አንድና አንድ ጥያቄ የባሕር በር ይገባኛል የሚል ነው። ይሄንን ጥያቄዋን ደግሞ በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው ስታቀርብ የቆየችው ፤አሁን የተደረሰበት ስምምነትም ቴክኒካል ጉዳዩ ከአራት ወራት በኋላ የሚፈጸም ቢሆንም ለጥያቄዋ ያገኘችው ምላሽ ጠላትን ያሳፈረና አንገት ያስደፋ የወዳጆችን አንገት ቀና ያደረገ ነበር።
ኢትዮጵያ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የባሕር በር ከሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ተሰልፋ ቆይታለች። ይሄ መሆኑ ደግሞ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንድታስተናግድ አስገድዷታል። አንዱ ተግዳሮት በቂ የሆነ የገቢና ወጪ ምርቶችን በወቅቱ ማድረስ አለመቻል ነው። እንደ ማዳበሪያ ያሉ ምርቶች የሚዘገይበት ሁኔታ ነበር። ሌሎች በርካታ የሚነሱ ተያያዥ ችግሮችም አሉ።
ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ እንደማንኛውም የዓለም ሀገራት በአቅራቢያዋ የሚገኝ የባሕር በር መጠቀም አለባት የሚለው ጉዳይ አሁን ላይ መነሳቱ ወሳኝ ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዎችን አንስታ አታውቅም። የባሕር በር ጥያቄ የነውር ያህል የሚቆጠርበት ዘመን ነበር። ይሄ ግን የትም አላደረሰንም፤ ሀገሪቱንም ከእድገት ወደ ኋላ ከመጎተት ይልቅ ወደፊት እንድትራመድ አላደረጋትም።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት አሁን የተፈረመው የአንካራው ስምምነት በራሱ ምስክር ሆኖ መጥቷል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ላነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ሶማሊያ የሰጠችው ምላሽ ተገቢነት ያለው አልነበረም። ከአዎንታዊነት ይልቅ አሉታዊ፤ ጦርነትን የጎሰመ ነበር። ውሎ ሲያድር እውነታን ሲረዱ መካሪ ሲገባቸው ወደ ይሁንታ መጥቷል። አዎ! ኢትዮጵያ የ120 ሚሊዮን ዜጎች ሀገር ናት የባሕር በር ያስፈልጋታል። የባሕር በር የማግኘት መብቷ ሊከበርላት ይገባል።
የአንካራው ስምምነት ለኢትዮጵያ መልካም ነገርን ይዞ የመጣ ነው። ሆኖም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ፖለቲካዊ ለማድረግና ለማደነቃቀፍ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብፅ ተኝታ አላደረችም። የኢትዮጵያና የሶማሊያ መስማማት ራስ ምታት ሆኖባታል። በምን መልኩ ይሄን ስምምነት ላደናቅፍ የሚለው የቤት ስራዋ ሆኗል። አሁንም የቤት ስራዋን በተለያየ ሴራ ቀጥላለች። ኢትዮጵያም ሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገዷን ተከትላለች።
ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጋር የተደረሰው የአንካራው ስምምነት ቢያንስ አንድን ነገር ያሳያል። ከዚህ ቀደም ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማያውቀውን ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ቢያንስ በጉዳዩ አስፈላጊነት ዙሪያ አለመግባባት ላይ ተደርሷል። የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ባሕር በር ማውራት ላለፉት ረጅም ዓመታት ነውር ነበር። መሪዎቻችንም የሚሽኮረመሙበት ጉዳይ ነበር። ይሆናል ብሎ ጉዳዩን እንደጉዳይ ያነሳም አልነበረም። የባሕር በር ለኢትዮጵያ ወሳኝ እና የመብት ጉዳይ ቢሆንም በመሽኮርመም ብቻ ያልተነሳ ነበር። አሁን ጉዳዩ ሊነሳ ወቅቱ የግድ ሆኗል፤ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
አሁን ኢትዮጵያውያን ልክ ናቸው። ወደብ ሳይሆን የባሕር በር ያስፈልጋቸዋል ወደ ሚለው ሃሳብ ተደርሷል። ይሄ ጉዳይ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ወዳጆችም ሆነ ከጠላቶቿ ጭምር አጀንዳ ሆኗል። እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ማንሳት ጦርነት የሚያስነሳ ጉዳይ ተደርጎ ነበር የሚታሰበው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሲነሳ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና ላይ ፍላጎቷ ምንድነው? ሁለት ብሔራዊ ጥቅሞች አሉ ለድርድር የማይቀርቡ ። አንደኛው የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ ነው። በቀይ ባሕርም ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላምና ደህንነትን አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል እንቅስቃሴ በመንግሥት በኩል አልተደረገም።
ያሉ የተደቀኑ አደጋዎችን የመቀነስ ቀጣናውን ሰላማዊ የማድረግ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው የምትሠራው። የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ከቀይ ባሕር ጥያቄ በላይ ነው። በቀይ ባሕር የሚኖረው የገቢና ወጪ ምርት እንቅስቃሴ የተሳለጠ ካልሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶና ጠጥቶ የማደር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።
ብሔራዊ ደህንነት ሰላምና ደህንነት፣ ኢኮኖሚ የባሕር በር ጥያቄ ያስነሳል። በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ሰፍኖ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥያቄ መመለስ አለበት። ያንን ጥያቄ ለማስመለስ አንዱ ጉዳይ የባሕር በር ማግኘት ነው።
ሀገሪቱ ብዙ አማራጮችን ትጠቀማለች፤ የጁቡቲን የኬንያን ወደብ ትጠቀማለች። እንዲሁም ከሶማሌ ላንድ ለመጠቀም የሚያስችል የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። አሁን ከሶማሊያ ጋር የተገባው የአንካራ ስምምነት ኢትዮጵያ አማራጮቿን ባሰፋች ቁጥር ወደብ ያላቸው ጎረቤት ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው።
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የኢትዮጵያን ገበያ አግኝተው ካልተጠቀሙበት ወደብ መኖራቸው ምንም ማለት አይደለም። ወደብ መኖሩ ብቻ እነሱ ኢኮኖሚ ላይ ጠብ የሚያደርገው ነገር አይኖርም። እነ ጅቡቲም ማደግ የጀመሩት በኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ምርት ወደብ አጠቃቀም ላይ ተንጠልጥለው መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ስለዚህ የመደራደሪያ አቅም ከሶማሊያም ወደ ሌሎችም ሀገሮች ሊሄድ የሚችል ይሆናል።
በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ናት፤ ሆኖም ለቀይ ባሕር ባላት ቅርበት ወደቡን መጠቀም የህልውና ጉዳይ ይሆናል። ወደቡ በሊዝ ወይም በኪራይ ወይም በሽያጭ ሊሆን ይችላል መጠቀም የምትችለው። የአንካራው ስምምነትም አንዱ የሂደቱ አካል ነው። በቃ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል የሚለውን ጥያቄ ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አዕምሮ ገብቷል። በመሆኑም በዓለም ላይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ላላት ከፍተኛ መጠን ያለው የገቢና የወጪ ምርት የተለያዩ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም አለባት የሚለውን ሃሳብ ነው መንግሥት ያነሳው። ይሄ ደግሞ ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው። ይሄን እንደ ሀገርም እንደዜጋም መነሳት ያለበት ነው። ኢትዮጵያ ካላት የወጪና ገቢ ምርቶች ብዛት አንጻር ሶማሌ ላንድን ፣ ሶማሊያና ጅቡቲን በአማራጭነት ብትጠቀም ይሄ አማራጭ ወደብን የማግኘት ጉዳይ ይሆናል። በዘላቂነት ደግሞ የራሷን የባሕር በር ማግኘት ይገባታል።
አፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሕዝብ ቁጥራቸው በአጠቃላይ ቢደመር የኢትዮጵያን ግማሽ ያህል እንኳን አይሆንም። ስለዚህ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያለው ሀገር የባሕር በር ጥያቄ ማቅረቡ አማራጭ የባሕር በሮችን ማማተሩ ተገቢነት ያለው እንጂ የሚወገዝ ወይም የሚያስወቅስ ሊሆን አይገባም። ወቀሳውም ውገዛውም የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ እንጂ ኢትዮጵያ ሁሌም እንደምትለው ከጎረቤቶቻችን ጋር አብሮ ማደግ፣ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ ከጠብ አጫሪ ድርጊቶች መታቀብ ሲሆን፤ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ደግሞ ተግታ የምትሠራ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ አለባት፤ መብቷን ለማስከበር የትኛውን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መጠቀምና መከተል ይገባል። ከማን ጋር ምን አይነት ስምምነት ማድረግ አለባት፤ መቼ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ይሄንን አዋጪና ሀገርን ይጠቅማል የተባለውን መንገድ መከተል ያስፈልጋል። ይሄ ፖለቲካል ጥበብን የሚጠይቅ እንጂ አንድን ጉዳይ ብቻ ይዞ የሙጥኝ ማለት አይቻልም፤ አያስፈልግም። ኢትዮጵያም እያደረገች ያለችው ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም የቱን መቼ በምን ጉዳይ ላይ ምን ማድረግ አለብን ብሎ አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል። አሁን እየሆነ ያለውም ይሄ ነው።
የአንካራው ስምምነት የሁለቱን ሀገር ብሄራዊ ጥቅም የሚያረጋግጥ እንጂ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ አይደለም። የማንንም ሀገር ለመጉዳት የሚሠራ መንግሥት የለም። የተሠራው ሥራ ጥበብ የታከለበት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ነው። ውጤቱም ድልን ያጎናጸፈ ነው። ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ እንዲሉ አበው አሁን የሚንጫጫ ሁሉ የዲፕሎማሲው የበላይነት ሳይገባቸው ሳይሆን ሁሌም ተቃዋሚ ሁሌም ቅንቅን ከመሆን የመነጨ ፍላጎት ነው። ማንም ቢንጫጫ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ የበላይነት መቀጠሏን ሊገታው አይችልም።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም