እ.ኤ.አ ከ1884-1885 በጀርመኑ ቻንስለር ኦቶ ቮን ቢስማርክ መሪ ተዋናይነት በበርሊን ከተማ አንድ ጉባዔ ተካሄደ። “ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች በአንድ ላይ ይበራሉ” እንዲሉ ጉባኤውን ያካሄዱት የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች ነበሩ። በጉባኤውም ቅኝ ገዥ አውሮፓውያን “በመካከላችን ምንም አይነት ሽኩቻ እና ጥላቻ ሳይኖር እንዴት አድርገን አፍሪካን እንቀራመት” ሲሉ መከሩ። የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ነጻነቷን አርቀው ለመቅበር ተማማሉ።
ማሕላቸውን እውን ለማድረግ ኢምፔሪያሊስቶቹ መላ አፍሪካን በወረራ ያዙ። መጋዘኖቻቸው ሞልተው እስኪያፈሱ ድረስ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ያለማንም ከልካይ ዘረፉ። አፍሪካ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቿ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቻው በጽንፈኛ ነጮች ተደፈጠጡ። ይህንንም ጭቆና ለማስወገድ የነጻነት ታጋይ አፍሪካውያን የሚያደርጉት ትግል ውጤት እንዲያፈራ ንቅናቄዎችን መሰረቱ። በድርጅቶቻቸው ጥላ ስር ሆነው ለነጻነታቸው መታገል ጀመሩ።
ከንቅናቄዎች መካከል “ኢትዮጵያኒዝም” (ETHIOPIANISM) አንዱ እና የመጀመሪያው ነው። ኢትዮጵያኒዝም በዘመናዊው የቅኝ ግዛት ዘመን ለኃይማኖት እና ለፖለቲካዊ ነፃነት የተነሱትን ቅስቀሳዎች ያቀፈ፤ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የተደረገ የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ ሲሆን የጀመሩትም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ “የሚሽነሪ” ሰራተኞች ናቸው።
ዋና ዓላማውም ከአውሮፓውያን ተጽዕኖ ነፃ የሆኑ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቋቋም የታለመ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያኒዝም “በኃይማኖት ብቻ ሊገለጽ የማይችል መሆኑን ፖለቲከኞች እና የታሪክ ጸሐፊዎች ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያኒዝም (Ethiopianism) የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው በደቡብ አፍሪካ የቀድሞው «የዌስሊያ» ቤተክርስቲያን አገልጋይ ማንጌና ሞኮን እኤአ በ1892 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን (Ethiopian Church) ሲመሰርት ነው።
በንቅናቄ “Africa for the Africans” “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” የሚለው መፈክር በሰፊው የተቀነቀነ ሲሆን የአፍሪካውያን የዕምነት ነጻነት እንዲረጋገጥ እና በፖለቲካው ዘርፍም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል።
የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ መሪዎች እና ተከታዮቻቸው የአፍሪካውያን ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያ “አፍሪካዊት ጽዮን” “African Zion” እያሉ ይጠሯት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ንቅናቄያቸውን ኢትዮጵያኒዝም ብለው እንዲሰይሙ ያደረጋቸው አንደኛው ምክንያት ይኸው ስለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በአጼ ምኒሊክ እየተመሩ ወራሪውን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ጣልያን በዓድዋ ድል መንሳታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ በከፍተኛ ደረጃ ጎመራ። የኢትዮጵያኒዝም የተሰኘውን ቃል የሚጠቀሙ አፍሪካውያን ቁጥር በእጅጉ ጨመረ።
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ
ፓን አፍሪካኒዝም (Pan Africanism) ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው። ፓን (Pan) የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን ሁሉም (All) የሚል ትርጉም አለው። ስለሆነም ፓን አፍሪካኒዝም (Pan Africanism) ማለት ደግሞ ሁሉም አፍሪካ (All Africa) የሚል ትርጉም ይሰጣል።
ፓን አፍሪካኒዝም (Pan Africanism) የተሰኘው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው ሁለት ዐብይ ጉዳዮችን ለማሳካት ነው። የመጀመሪያው የአፍሪካውያንን አንድነት (African Unity) ለማምጣት ያለመ ነው። ይህ ሲባል ከአፍሪካ ውስጥ የሚኖሩትን አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዙትን በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦችን አንድ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው። ሌላኛው የፓን አፍሪካኒዝም ዓላማ ደግሞ ሁሉም በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያንን በተለይም በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና በትሪንዳድ (West indies) የሚኖሩ ጥቁሮችን የጋራ ወንድማማችነት (Common Brotherhood ) ለመፍጠር ትኩረት ያደረገ ነው።
ፓን አፍሪካኒዝም የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የተወለደው ወይም የተፈጠረው ከአፍሪካ ውጭ ሲሆን የፈጠሩትም የዘር ግንዳቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ በአሜሪካ እና በካሪቢያን የሚገኙ ጥቁሮች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች ከእናት አኅጉራቸው አፍሪካ በግፍ የተወሰዱ ስለነበሩ በሚኖሩባቸው ሀገራት ራሳቸውን እንደባይተዋር የሚቆጥሩ ነበሩ። እንደዚህ እንዲያስቡ ያበቃቸው ደግሞ በጽንፈኛ ነጮች የሚደረስባቸው መገለል እና መድሎ ነበር።
ይህን ተከትሎ እነዚህ ዜጎች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እኩል እንዲሆኑ አጥብቀው ይፈልጉ ነበር። በምዕራባውያን የተነጠቁትን ፍትህ ለማግኘት አጥብቀው ታገሉ። በፓን አፍሪካኒዝም የመጀመሪያዎቹ እንቅስቃሴዎች በጥቁርነት የሚደርስን ዘረኝነት የሚቃወሙ ነበር።
የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ መሬት የረገጠ ለማድረግ መሪዎቹ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በርካታ ኮንፈረንሶችን አካሂደዋል። የመጀመሪያው ፓን አፍሪካኒዝም ስብሰባ የተካሄደው በእንግሊዝ ለንደን እ.ኤ.አ በ1900 ነው። ስብሰባውም የተደራጀው በትሪኒዳዱ (West indies) የሕግ ባለሙያው ሲልቬስተር ዊሊያምስ ነበር። ይህ ኮንፈረስ ከኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ከተጀመረ ማግስት በመሆኑ ከጥቁር ሕዝቦች ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት ተደርጎበታል።
ፓን አፍሪካኒዝም ሁለት ታዋቂ መሪዎች የነበሩት ሲሆን አንደኛው በሀገረ አሜሪካ ነዋሪ የነበረው ተመራማሪ እና ጸሐፊ ዶክተር ዱ ቦይስ ነው። ዶክተር ቦይስ የፓን አፍሪካኒዚም አባት በመባል ይታወቃል። ሌላኛው የፓን አፍሪካኒዝም መሪ ደግሞ ጃማይካዊው ማርከስ ጋርቬይ ሲሆን አሜሪካ ይኖር የነበረ የነጻነት ታጋይ ነው። ሕይወቱ ያለፈውም በጽንፈኛ ነጮች በተፈጸመበት የጭካኔ ግድያ ነበር።
ጋርቬይ የዓለም አቀፍ ኔግሮ አሶሴሽን (Universal Negro Association) መስራች እና መሪ ነበር። ሁለቱም የፓን አፍሪካኒዝም መሪዎች ቢሆኑም ሁለቱም ግን በአፍሪካውያን የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ መሰረታዊ ልዩነቶች ነበሯቸው። ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን በአፍሪካ ውስጥ ለሚኖሩ አፍሪካውያን በመታገል የመላ የጥቁር ሕዝቦችን መብት ማስጠበቅ ይቻላል የሚል ነበር። ጋርቬይ በበኩሉ የአፍሪካውያንን መብት ለማስከበር ከአፍሪካ ውጭ የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችን በሙሉ ወደ አፍሪካ መመለስ አለባቸው የሚል ነው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እኤአ ግንቦት 25 ቀን 1963 በአዲስ አበባ ሲመሰረት ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ለነበሩት የፓን አፍሪካኒዝም የጥቁር ሕዝቦች ትግል ተቋማዊ ቅርጽ በመስጠት ነበር። ከዚህም ባሻገር ከዚህ በፊት ለብዙ ግዚያት ከአፍሪካ አኅጉር ውጭ የነበረውን የጥቁሮች እንቅስቃሴ ወደ አፍሪካ ምድር በአስተማማኝ መልኩ ያመጣ የድርጅት ምስረታ ነበር።
በተለይም የጋና ነጻ መውጣት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ወደ አፍሪካ አኅጉር መጥቶ በአፍሪካውያን የሚዘወር ሆነ። የመሪዋ የክዋሜ ንክሩማ ‹‹የጋና ነጻነት ሌሎች አፍሪካውያን ነጻ እስካልውጡ ድረስ ትርጉም የለሽ ነው›› በማለት ዋናው የፓን አፍሪካኒዝም ትኩረት የአፍሪካ ሀገሮችን ከቅኝ አገዛዝ ለማላቀቅ የሚደረገውን ትግል ማገዝ ነው አለ። በንኩሩማ አስተሳሰብ የአፍሪካ ሀገሮች የፖለቲካ ነጻነት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ወደ አንድ አገርነት ተለውጠው የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።
የኢትዮጵያ ውለታ
ይህ ሃሳብ ግን በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። የእንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች ልዩነት ነበራቸው። የሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ልዩነት እንዳለ ሆኖ በዋነኝነት ሁለት ቡድኖች ነጥረው ወጥተዋል። የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖች የሚል መጠሪያ ነበራቸው። ኢትዮጵያ ከሁለቱም ወገን ሳትወግን በገለልተኝነት አቋም ሁለቱን በማስማማት አዲስ ታሪክ ጽፋለች። አጼ ኃይለሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ‹‹እኛ ሞኖሮቪያም፤ ካዛብላንካም አይደለንም። እኛ ከአፍሪካ ጎን ነን›› የሚል ንግግር በማሰማት ሁለቱን ወገኖች ወደ አንድ ለማምጣት ችለዋል።
ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች ካስማማች በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት እንቅስቃሴ ጀመረች። ነጻ ወጡ የ32 ሀገር መሪዎችን ወደ አዲስ አበባ በመጥራት በአፍሪካ አንድነት ምስረታ ላይ ውይይት አደረጉ። በወቅቱ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ፤ የመሪዋ አጼ ኃይለሥላሴ በሳል ዲፕሎማሲ አካሄድ እና በተለይም ለበርካታ አፍሪካውን የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷ ኢትዮጵያ የምታነሳቸው ሀሳቦች በመሉ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሏታል።
አፍሪካውያን ገና ነጻ ባልወጡባቸው ዓመታት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባልነቷ ለነጻነታቸው ተከራክራላቸዋለች። እኤአ በ1958 ኢትዮጵያ ለ200 አፍሪካውያን ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥታለች። በዚህ የትምህርት ዕድል ኬንያ፣ ታንጋኒካ፣ ዛንዚባር፣ ዩጋንዳ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን ፣ግብጽ፣ ላይቤሪያ ተጠቃሚ ሆነዋል። በደቡብ አፍሪካ ሻርፕ ቪል ሰልፍ ላይ በመጋቢት 21 ቀን 1960 በግፍ የተገደሉ ሰዎች ልጆችን ሙሉ ወጪያቸውን ችላ የአፍሪካውያንን ልጆች አስተምራለች።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የምታደርጋቸው ጥሪዎች በሙሉ ያለምንም ልዩነት ተቀባይነት ነበራቸው በግንቦት 23 ቀን 1963 የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎችና ርዕሳነ ብሔሮች በአዲስ አበባ ተገኙ። ስብሰባውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት አፄ ኃይለሥላሴ በመክፈቻ ንግግራቸው አፍሪካውያን ድምጻቸውን አንድ ማድረግ እንደሚገባቸው እና ችግሮቻቸውንም በራሳቸው የሚፈቱበት አንድ አሰባሳቢ ድርጅት መመስረት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናገሩ። ይህንኑ ንግግር መሰረት በማድረግም ግንቦት 25 ቀን 1963 እስከ ሌሊት ድረስ ስብሰባ በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር ጸደቀ። በዕለቱ አጼ ኃይለሥላሴ በጣም በመደሰታቸው 3000 ለሚሆኑ እንግዶች በታላቁ ቤተመንግስት የእራት ግብዣ አድርገው ነበር።
የአፍሪካ አንድነት መመስረትም የኢትዮጵያን ተሰሚነት የጨመረ ሲሆን በአዲስ አበባ የተከፈቱ ኤምባሲዎች ቁጥርም እንዲጨምር አድርጓል። ሆኖም የአፍሪካ አንድነት ቻርተር ቢጸድቅም ቀሪ የቤት ሥራዎች ነበሩ። የድርጅቱን መቀመጫ መወሰን እና ዋና ፀሃፊውንም የመምረጥ ሥራዎች አልተከናወኑም ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመስረቻ ቻርተር ከተፈረመ ከአራት ወራት በኋላ በነሐሴ 1963 ድርጅቱ ስብሰባውን በዳካር ሴኔጋል አደረገ። በዚህም ስብሰባ ላይ በሚስጥራዊ ድምጽ አሰጣጥ የአፍሪካ አንድት ድርጅት መቀመጫ ተወሰነ።
በውጤቱም ኢትዮጵያ 15፤ ሴኔጋል 12፤ ዛየር 1፤ናይጄሪያ ምንም ድምጽ በማግኘት አዲስ አበባ የድርጅቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ተመረጠች። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለማጠናከር የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች። ከእነዚህም መካከል በወቅቱ ለፖሊስ ኮሌጅ ተብሎ የተሰራውን ባለብዙ ክፍል ሕንጻ በግምት 250ሺ ካሬ ሜትር ከሚሆን ቦታ ጋር ለድርጅቱ እንዲሆን በነጻ አበርክታለች። በተጨማሪም የአፍሪካ አንድነት እስኪጠናከር ድረስ የድርጅቱን የሶስት ዓመት ሥራ ማስኬጂያ ወጪ በራሷ ስትሸፍን ቆይታለች።
ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ በኋላም ዋነኛ ዓላማዋ የነበረውን አፍሪካን ከቅኝ ግዛት የማላቀቅ ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ አስተባባሪ ከሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። የኮሚቴው ዋነኛ ዓላማም የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ የሚያካሂዱትን ትግል በገንዘብ መርዳት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ ጨርሶ ለማላቀቅ በሚደረጉ ትግሎች አንደኛው ዘርፍ የሆነውን የዲፕሎማሲ ሥራ መስራትንም ያካትታል። ለነጻነት የሚዋጉ አፍሪካውያን ኃይላቸውን ወደ አንድ አሰባስበው እና ልዩነታቸውን ትተው ግንባር እንዲፈጥሩ ማደራደርም ሌላኛው ተልኮ ነበር።
ኢትዮጵያ በግሏ ለነጻነት ታጋዮች የገንዘብ፣ የሚሊቴሪ እና የሎጀስቲክስ አቅርቦት ታከናውን ነበር። ኋላ ላይ ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ውስጥ የውትድርና ስልጠና እንደተሰጣቸው ይታወቃል። እሳቸውም ‹‹A Long Walk to Freedom›› በተባለው መጽሃፋቸው ውስጥ ‹‹አሜሪካንን፣ እንግሊዝንና ፈረንሳይን በአንድ ላይ ከምጎበኝ ኢትዮጵያን ማየት እመርጣለሁ›› ብለዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተልኮውን ጨርሶ ወደ አፍሪካ ሕብረት ሲሸጋገርም ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና ተጫውታለች። የአፍሪካ ሕብረት እንዲጠናከርም በመዲናዋ ዘመናዊ መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲገነባ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ በማስተባበር ተሳትፋለች።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ደረጃዋን የጠበቀችና ለሕብረቱ መቀመጫነት የምትመጥን እንድትሆን በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በኮሪደር ልማትም ውበት እና ዘመናዊነትን በማጣመር ለእንግዶች ተስማሚ እና ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም