መረጃ ቅንጦት አይደለም፤ ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን፤ ለምንወስናቸው ውሳኔዎች ጉልህ አሻራ የሚያኖር ጠቃሚ ሀብት ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ ከመወሰናችን አስቀድመን ጥቅሙንና ጉዳቱን ለመመዘን መረጃ ምን ያህል አስፈላጊ ግብዓት እንደሆነ በርካታ ማሳያዎችን ልናነሳ እንችላለን። አንድ አርሶ አደር የአየር ሁኔታን የሚገልጽ ወይም አንድ ነጋዴ የምርት ዋጋን የሚያሳይ መረጃ በፍጥነትና በቀላሉ ማግኘት አለባቸው። ይህም በተሠማሩበት መስክ ስኬታማ ያደርጋቸዋል።
የመረጃን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም በሕገ መንግሥቱና በመረጃ ነፃነት ሕጉ የዜጎችን የመረጃ የማግኘት መብት በግልጽ ይደነግጋል። በሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ሰው ኃላፊነት በተሞላበት አግባብ መረጃን የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማሰራጨት መብት እንዳለው ያመለክታል። ይህንን መብት በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የመረጃ ነፃነት አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማሕቀፎች ወጥተው በሥራ ላይ ይገኛሉ።
የመረጃ ነፃነት አዋጅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል። ከጠቀሜታዎቹም መካከል ከመረጃ ስርጭት ጋር በተያያዘ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈን አንዱ ነው። የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ተጨባጭ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ ሀገራዊ ቁርጠኝነት ስለመኖሩ ማሳያ ጭምር ነው።
ካላቸው ሙያዊ ኃላፊነት አኳያ የመረጃ ጉዳይ ከሁሉም በላይ ለመገናኛ ብዙኃን ወሳኝ ነው። ከተቋማቱ የሥራ ባሕሪይ አኳያ የሕልውናቸው መሠረት ተደርጎም ይወሰዳል። እንደ ሕግ አውጪ፣ ተርጓሚ እና አስፈፃሚ አካላት እንደ አራተኛ የመንግሥት አካል የሚያስቆጥራቸውን ወሳኝ ሚና መጫወት የሚችሉት መረጃን መሠረት አድርገው ነው።
መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት፤ ከዛም ባለፈ መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊ እና የግል ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውን የመከታተል ችግር ተፈጥሮ ሲገኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማስቻል ሂደት ውስጥ ሙያዊ ኃላፊነት አለባቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በለውጥ ሂደት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት ከዚህም ባለፈ እንደሆነ ይታመናል። የለውጥ አስተሳሰቦችን ወደ ማኅበረሰቡ ማስረጽን፤ ለውጡ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ እንዲገኝላቸው መሥራት፤ የሕዝብ ተሳትፎን ማሳደግ..ወዘተ ተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነቶች ናቸው።
በዚህ ትልቅ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ተልዕኮ ውስጥ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ፍላጎት ማሟላት የየትኛውም ተቋም ኃላፊነት ነው። ሕዝብ ካለው መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አንጻር ለተቋማቱ ፍላጎት መረጃ ለመስጠት አለመተባበር የሕግ ተጠያቂነትን ሊያስከትል የሚችል የሕግ ጥሰት ነው።
የመረጃ ነፃነትን በሕግ በደነገገችና በለውጥ ውስጥ በምትገኝ ሀገር ውስጥ የአንዳንድ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) ሲጠየቁ ላለመስጠት “ስብሰባ ላይ ነኝ”፣ “ከቢሮ ውጪ ነኝ” “እኔ ራሴ እደውላለሁ” ወዘተ ..በሚል በዛው የሚጠፉበት ሁኔታ እየጨመረ ነው። ይህ ያልተገባ አካሄድ (ሽሽት) መገናኛ ብዙኃን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጡ ፈተና እየሆነ ነው።
አሁን አሁን ፍጹም ለመገናኛ ብዙኃን በራቸውን የዘጉ፤ ከዛም አልፈው ካልፈለግናችሁ አትምጡብን የሚሉ የመንግሥት ተቋማት እየበዙ ነው። የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለማግኘት ደጅ የሚያስጠኑ ተቋማት መኖራቸው ደግሞ ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል። ያለ ተጨባጭ እና በቂ ምክንያት ‹‹በደብዳቤ ጠይቁን›› የሚሉና ጊዜ በመግዛት ሂደቱን የሚያጓትቱም እንዲሁ ጥቂት አይደሉም።
ሲሆን ሲሆን አብዛኛው መገናኛ ብዙኃን የሚጠይቋቸው መረጃዎች ወደ ተቋሙ በአካል መገኘት ሳይስፈልግ ድረ ገጽ ላይ ይፋ መሆን ያለባቸው ናቸው። በወራት ቀርቶ በዓመታት እንኳን ወቅታዊ የማይደረግ ድረ ገጽ ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ ቢሮዎቻቸው ለጋዜጠኞች ክፍት አይደሉም።
ችግሩን ይበልጥ የሚያከፋው የመረጃ ተደራሽነትን እንዲያቀላጥፉ የተመደቡ አንዳንድ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጭምር መረጃ ለመስጠት ዳተኝነት ማሳየታቸው ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ሚዲያ ቢሯቸው ከማንኳኳቱ አስቀድመው መረጃ ተደራሽ ማድረግ የሚጠበቅባቸው አካላት ናቸው።
ለሁነት ዝግጅት ብቻ ሚዲያን መጥራት ብቸኛ ኃላፊነታቸው እስከሚመስል ድረስ ዋናውን ኃላፊነታቸው የዘነጉ ናቸው። እንዲህ ባለ ሁኔታ በተቋማት እና በሚዲያ መካከል ተባብሮ የመሥራት መንፈስን መፍጠር አይቻልም። ሚዲያን ከመሸሽ ለሥራቸው አጋዥ መሣሪያ አድርገው ቢወስዱት ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ማሳያ የሚሆኑ ጥቂት ተቋማት አሉ።
አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ‹‹ሰጠን ለማለት ብቻ›› መረጃ የሚሰጡ ንፉግነታቸውን የሚያሳብቅ ድርጊት ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ። ለትንታኔ የማይሆን ለንጽጽር የማይበቃ፤ ተቋሙ የተሻለ አፈፃፀም ይኑረው፤ ደካማ አፈፃፀም ምኑንም የማያሳዩ የሰዎች አስተያየት መረጃ ብለው ይሰጣሉ።
በተለይ አኃዛዊ መረጃዎች ወይም ቁጥሮች ለትንታኔ ወሳኝ ግብዓት ስለሆኑ ከተለያየ ምንጭ በተወሰዱ መረጃዎች ተዛብተው እንዳይቀርቡ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ በትክክለኛ ጊዜ ማቅረብ አለባቸው።
ከላይ የጠቀስናቸው በተቋማት የሚታይ መረጃ የመስጠት ዳተኝነት የሚዲያ ሥራ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ያለ፤ ኃላፊነትን የመሸሽ አንዱ መገለጫ ነው። ምክንያቱ የአፈፃፀም ክፍተትን ለመደበቅ ወይስ ስለሚሠሩት ሥራ ስለማያውቁ ነው? መልሱን ለተቋማቱ በመተው መረጃ መስጠት ግዴታ መሆኑን ለዘነጋ አካል ኃላፊነትን አለመወጣት ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ደግሞ ደጋግሞ ማስገንዘብ ይገባል።
የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዜጋ መረጃ ጠይቆ ሊከለከል እንደማይገባ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው እና የመረጃ ባለቤቶች ጭምር እንደሆኑ በሕገ መንግሥት የሰፈረ ጉዳይ ነው። ተቋማት በእጃቸው የሚገኘው መረጃ የግል ንብረታቸው ሳይሆን የሕዝብ ሀብት ነው።
ሲፈልጉ የሚሰጡት ካልፈለጉ ደግሞ የሚከለክሉት አይደለም። ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ለሕዝብ የሚቀርቡ መረጃዎች በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በአሠራር ሊመራ ይገባል። ለዚህም ነው ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥት እና በአዋጅ መደንገግ ያስፈለገው።
የሚመለከታቸው አካላት ሆነ የተቋም አመራሮች አሁን ካለንበት ሀገራዊ የለውጥ ጎዞ ስኬት የመገናኛ ብዙኃንን ሁለንተናዊ ጠቀሜታን ግምት ውስጥ በማስገባት መረጃዎችን በጥራት እና በስፋት በማደራጀት ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ መረጃ ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን መረጃ የሚያመነጩ ተቋማት፣ መረጃ የሚያደራጁና የሚያሰራጩ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ተቆጣጣሪ አካላት የየድርሻቸውን ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል እንላለን። ሰላም!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም