የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የከተማዋን የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ለመዘርጋት ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር ሰሞኑን ስምምነት ተፈራርሟል። ከተሞች ስማርትና ዲጂታል እየሆኑ ባለበት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ሥርዓቱን የመዘርጋቱ ሒደት ቢዘገይም ዛሬም አረፈደምና ይበል የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በነገራችን ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ባለፈው ዓመት ይሄን ሥርዓት በመዘርጋት መዲናችንን ቀድማታለች።
ተቋማት፣ ቦታዎች እንዲሁም ቤቶችና የመሳሰሉት የት እንደሚገኙ በዲጂታል መልኩ በየፈርጁ ያልተመዘገቡባት ኢትዮጵያ የአድራሻ ሥርዓቷን ባለማዘመንዋ የተነሳ የይዞታ መረጃዎችን በአግባቡ ለማስተዳደር ስትቸገር መቆየቷ ይነገራል፡፡ይህ መረጃ በአግባቡ ባለመሰነዱ የተነሳም ሀገሪቱ የኢ ኮሜርስና የኢ ሰርቪስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የምታደርገው ጥረት ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ቤቶችና የትላልቅ ተቋማት እንዲሁም የትራፊክ እንቅስቃሴ መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡
በሀገራችን በየከተሞች ያለውን እድገትና መስፋፋት ተከትሎ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ በቂ አድራሻ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሌላው ቀርቶ ችግር ተፈጥሮ ለእርዳታ የሚንቀሳቀሱ የእሳት አደጋ መኪናና ተጎጂዎችን የሚያነሱ አምቡላንሶች ከተጠሩበት ቦታ የሚደርሱት ከብዙ ምሬት በኋላ ነው። ያደጉት ሀገራት ከተሞች የተጠናከረ የአድራሻ ሥርዓት ስላላቸው ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ እየተጠቀሙባቸው ይገኛል። በተጨማሪም የየከተማ አስተዳደሮች በከተሞቻቸው ያሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አድራሻ በመስጠት በቀላሉ ለማስተዳደር እና የማህበረሰባቸውንም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ምቹ እና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ አስችሏቸዋል።
የአካባቢውን፣ የመኖሪያ ቤቱን፣ የሥራ ቦታውን በቀላሉ ለተገልጋዮች ለመግለጽ፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለሌሎች አካላት በቀላሉ ያለበትን አድራሻ ለማመላከት ወይም ለመጠቆም የሚያስችል ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት ባደረገ መልኩ የብሔራዊ ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ሥርአት ደንብ እና መመሪያ ተዘጋጅቷል።
የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት መዘርጋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ግለሰቦች የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ቀላል ከማድረግ ጀምሮ የተቀላጠፈ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ጥገና አገልግሎት ለማግኘት፣ ፈጣን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የዲጂታል ኢኮኖሚን ሥርዓት ለመዘርጋትና እውን ለማድረግ፤ የኤሌክትሮኒክ ግብይቶችን (e-commerce) እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥና ለመደገፍ ዋነኛ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ነው።
የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ማለት መሬት ላይ የሚገኙ ማናቸውንም ነገሮች ህንጻዎች/ቤቶች፣ መንገዶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ ክፍት ቦታዎች፣ ፓርኮች፣ መዝናኛና መናፈሻ ቦታዎች እና ሌሎች ነገሮችን መገኛ (location) በካርታ ላይ የማስፈር እና ዜጎች በቀላሉ አድራሻውን እንዲያገኙ በማድረግ የትራንስፖርት ወጪያቸውን እንዲቀንሱና ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ሥርዓት ነው።
ይህ ሲተገበርም እያንዳንዱ መሬት ላይ ያለው ነገር ከጀርባው የጂ.ኤን.ኤስ.ኤስ (GNSS በተለምዶ GPS) መረጃ የያዘ የራሱ ልዩ መለያ ቁጥር እንዲኖረው ይደረጋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አድራሻ ለእያንዳንዱ ቤት፣ መንገድና ሌሎች በመሬት ላይ ያሉ ንብረቶች የሚሰጥበት ሥርዓት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲሁም አሁንም አብዛኛው ማህበረሰብ የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎት ለማግኘት፣ የተለያዩ ግብይቶችን ለመፈጸም፣ ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅ፣ በየመንገዱ እየቆመ እና ሰዎችን እየጠየቀ የሚሄድበት ሁኔታ ያስቀራል፡፡ይህን እውን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ራሱን የቻለ መመሪያ ጸድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት የመንግሥትና የሕዝብ መሆኑን በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከዚህ በመነሳት የከተማ መሬት ምዝገባን ለማሳለጥ የእያንዳንዷን ቁራሽ መሬት አድራሻ እና ቁራሽ መሬቱም ለምን አገልግሎት እየዋለ መሆኑን በአድራሻው ለማረጋገጥ የሚረዳ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ በመንግሥት ተወስኗል፡፡
ከዚህ አኳያ ከተሞች መሬትን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር በተለይም የአድራሻ ሥርዓት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ዘመናዊ የአድራሻ ሥርዓት በከተሞች ያሉ መንገዶችን እና የአድራሻ ታፔላዎችን ዝርጋታ እና ሌሎች በመሬት ላይ ያሉ ቋሚ ንብረቶችን ለማመላከት የሚያስችል ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ የአድራሻ ሥርዓት በማደግ ላይ ላሉ የከተማ ነዋሪዎች ዘመናዊ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠር እገዛ የሚያደርግ እና መልካም አስተዳደርን ለመገንባት የሚያግዝ አስተዳደራዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ለከተማዋ አጠቃላይ የአድራሻ ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል፡፡ የአድራሻ ሥርዓቱ በዋነኛነት የመንገድ ስያሜ ወይም የመንገድ መለያ ቁጥርና የቤት ቁጥርን በማገናኘት የሚከናወን ሲሆን፤ ከሥርዓቱ ጋር የሚጣጣም የቤት ቁጥር መስጠት ተገቢ ሆነዋል፡፡ ያለፈው መንግሥት በጊዜው ለነበሩ ቤቶች የቤት ቁጥር ከሰጠ በኋላ የተገነቡ በርካታ ቤቶች ስላሉና የቤት ቁጥር ሊሰጣቸው ስለሚገባ፤ በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች የተቀላጠፈ ለማድረግ በተደጋጋሚ በተደረገው አስተዳደራዊ የመዋቅር ለውጥ ምክንያት የቀበሌዎች መቀላቀልና መከፈል ስለተፈጠረ የቤት ቁጥር ድግግሞሽንና ምስቅልቅልነትን የፈጠረ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ይህ ደግሞ ከተማዋን ከማዘመን አንፃር ቀድሞ የነበረው የቤት ቁጥር አሰጣጥ ምቹ ሆኖ ስላልተገኘ፤ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የቤት ቁጥር በምን ሕግ መሠረት ሲሰጥ እንደነበረ ወጥነት ያለው መረጃ ባለመኖሩና እሱን ተከትሎ መስጠት ስላልተቻለ እንደገና ከአድራሻ ሥርዓቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ የቤት ቁጥር መስጠት አስፈልጓል፡፡ ስለዚህ የተቀናጀ የመሬት መረጃ ማዕከልና የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 64/2011 ዓ.ም ከእነ ሙሉ መብትና ግዴታ የተዋሐዱ በመሆናቸውና የአድራሻ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ለማስተዳደር የቤት ቁጥር ለመስጠት ስልጣን የተሰጠው በመሆኑ፤ በፌዴራል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ከተሞች የአድራሻ ሥርዓት ስታንዳርድን መሰረት በማድረግ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡
መመሪያውን የማውጣት አስፈላጊነት
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ የአድራሻ ሥርዓት ትግበራ በመዘርጋት ሂደት ላይ
ይገኛል፡፡ የአድራሻ ሥርዓቱ በዋነኛነት ዋና ዋና አደባባዮችንና የመንገድ ዓይነቶችን
መሰረት በማድረግ በጂኦ-ኮዲንግ ፅንሰ ሃሳብ መሰረት አድርጎ የመንገድ ስያሜ ወይም
የመንገድ መለያ ቁጥርና የቤት ቁጥርን በማቀናጀት የሚከናወን ሲሆን ከሥርዓቱ ጋር
የሚጣጣም አዲስ የቤት ቁጥር በከተማ ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ ለመስጠት ያስችላል፡፡
መመሪያው ለከተማው የሚከተሉት ጥቅሞች ይኖሩታል::
- የቋሚ ንብረት ምዝገባ በማካሄድ ለዜጎች የንብረት ዋስትና ለመስጠት መንግሥት የሚያደርገውን የንብረት ምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ግብዓት በመሆን ሂደቱንም ይበልጥ ለማፋጠን ይረዳል፣
- የመንገድ ቁጥርና የቤት ቁጥርን በማስተሳሰር ለዘመናዊ የአድራሻ ሥርዓት ወይንም ጂኦ-ኮዲንግ ሲስተም በመፍጠር ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላች ከተማ ለማድረግ፡፡
- የከተማዋን ዕድገት መሰረት ያደረገና ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለመፍጠር እንዲቻል ከዘመናዊ የአድራሻ ሥራ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የቤት ቁጥር በስታንዳርዱ መሰረት ለመስጠት፣
- የከተማው ነዋሪ የመብራት፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የፖስታ፣ የእሳት አደጋ፣ የፖሊስ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቅልጥፍና እንዲያገኝና የግል ሴክተሩም በልማት ሥራው ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣
- ዘመናዊ የአድራሻ ሥርዓት እንዲኖራት በማድረግ ቋሚና የማይደጋገም የቤት ቁጥር በመስጠት ወደ አገልግሎት በማስገባት ከመታወቂያ ወረቀት ዕደላ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ሕገ-ወጥ አሠራሮች ለመከላከል ያግዛል። በነገራችን ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓትን ወደ ሥራ በማስገባት ፋና ወጊ ናት ማለት ይቻላል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ባለፈው የቢሾፍቱ ከተማን ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት መርቀው በከፈቱበት ወቅት፤ “የአድራሻ ሥርዓት ሳይኖር የዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት አይታሰብም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በማያያዝም መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ፤በዚህም የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች እንዲሁም የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ዝርጋታ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በ73 የኢትዮጵያ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ያለው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት “(eDAS)”አስተዳደራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የከተሞችን ምቾትና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓቱን ያለማው የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ነው፡፡ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው፤ በቢሾፍቱ ከተማ የተገኘውን ልምምድ በመጠቀም ፕሮጀክቱን በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ በወቅቱ አሳስበዋል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የአሊባባ እህት ኩባንያ አሊኤክስፕረስ ይህ የዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ከመዘርጋቱ በፊት ኢትዮጵያ ገብቶ ሥራ ጀምሯል። የኤሌክትሮኒክ ግብይት(e-commerce)ያለ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ማሰብ ከባድ ነውና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሊገባ ይገባል። ስለ አሊባባ ካነሳሁ አይቀር ትንሽ ልበል።
በዓለማችን በአንድ ቀን በቻይና የላጤዎች ቀን singles day በኤሌክትሮኒክ ግብይት አሊባባ ያስመዘገበውን ሽያጭ አማዞንና ኢቤይ ተደምረው በቫላንታይስ ፣ በአዲስ ዓመት ፣ በጥቁሩ ሰኞ እና በሌሎች በዓላት ካስመዘገቡት ሽያጭ በላይ ነው። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከአሊባባ ጋር መሥራት በዓለም ገበያ ያለከልካይ የመቅዘፍ ያህል ነው። ለመሆኑ ጃክ ማ ማን ነው? ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በebs ቴሌቪዥን የTeckTalk አዘጋጅ “ግርምተ ሳይቴክ” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ “ዓለምን የቀየሩ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን 20 ምርጦች” በሚል ንዑስ ርዕስ እንዲህ ያስነብበናል።
“ … ‘ አሊ ባባ ’ የተሰኘው ግዙፍ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከድሀ ቤተሰብ በመስከረም 1964 ዓ.ም ተወለደ። በትውልድ ስሙ ማን ዩን በፕሮፌሽናል የስም አጠራሩ ጃክ ማ በመባል ይታወቃል። በበርካታ የህይወት ፈተና ያለፈው ጃክ ማ እንኳን ግዙፍ የሆነ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤት እንደሚሆን ሊያስብ ቀርቶ በሂሳብ ትምህርት ደካማ እንዲሁም እስከጉልምስናው ኮምፒውተር ባለበት ድርሽ ብሎ አያውቅም። በወጣትነቱ በቱሪስት አስጎብኚነት ተሰማርቶ የነበረው ጃክ ማ በህይወቱ በርካታ ውድቀቶችን አስተናግዷል።
የኮሌጅ መግቢያ ፈተናን ሶስት ጊዜ ወድቆ በአራተኛው ነበር የተሳካለት። ኮሌጅ ገብቶ የተማረውም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር። ከጨረሰ በኋላ ለ30 የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አመልክቶ ሳይሳካለት ቀረ። በአንድ “KFC” በሚባል ምግብን በርካሽ የሚሸጥ ምግብ ቤት በአነስተኛ ደመወዝ ለመቀጠር ከ24 ሥራ ፈላጊዎች ጋር አመልክቶ ሁሉም ሲቀጠሩ እሱ ብቻ ሳይሳካለት ቀረ። ለፖሊስነት ለመቀጠር ተወዳድሮም ወድቋል። “ተስፋ መቁረጥ ትልቅ ውድቀት ነው።” የሚለው ጃክ ማ በዚህ ሁሉ ፈተና እና ውድቀት ቢያልፍም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ በኋላ ተሳክቶለት በወር 12 ዶላር እየተከፈለው በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመምህርነት ተቀጠረ።
በዚህ ከባድ ፈተና በማለፍ ላይ ሳለ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1994 ዓ.ም ስለኢንተርኔት የሰማው። ከአንድ ዓመት በኋላ በተፈጠረለት መልካም አጋጣሚ ወደ አሜሪካ አቀና። በዚያም ስለኢንተርኔት አጠቃቀም መሰረታዊ ግንዛቤ እንዳገኘ ስለሀገሩ ቻይን ለማወቅ ጉጉት አድሮበት መረጃ ሲያስስ እንደሌሎች ሀገራት የደለበ መረጃ ማግኘት አለመቻሉ ቁጭት ፈጠረበት። በዚህ በመነሳሳት ከጓደኛው ጋር ስለ እናት ሀገሩ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ድረ ገጽ ፈጠረ። በጥቂት ሰዓታት የአብረን እንስራ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ጎረፉለት።
በዚህ ጊዜ ነበር ጃክ የኢንተርኔትን ኃይል የተረዳው። ከባለቤቱ እና ከጓደኛው ጋር 20ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወረት በማሰባሰብ በሚያዚያ 1995 ዓ.ም “ቻይና የሎ ፔጅን / chaina yellow page ” አቋቋመ። በሶስት ዓመቱ 800ሺህ ዶላር አተረፈ ። 1999 ዓ.ም ከ18 የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የዛሬውን “አሊ ባባ” መሰረተ። በጥቂት ወራት ውስጥም ከባለሀብቶች 25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አሰባሰበ። በ2005 ዓ.ም ያሁ / yahoo / አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ከአሊባባ የ40 በመቶ ድርሻን ገዛ። ነጮች የተቀረው ታሪክ ነው ቢሉም የጃክ ማ ጉዳይ ከታሪክ በላይ ስለሆነ እንቀጥል።
በ2006 ዓ.ም አሊ ባባ በታዋቂው የኒዮርክ የአክሲዎን ሽያጭ / New York Stock Exchange / ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ሲቀርብ ነጮች Initial Public Offering / IPO / ይሉታል ። 25 ቢሊዮን ዶላር የተተመነለትን ሽርክና በመሰብሰብ ከአንጋፋ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተርታ ተሰለፈ። በ2008 ዓ.ም የ463 ቢሊዮን ዶላር ግብይት አከናወነ። የቅርብ ጊዜ ተመኑም ከትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል። ዛሬ ተአምረኛው ጃክ ማ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ባለፀጋ ነው። በዓለማችን በቁጥር አንድነት በሚታወቀው የአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመከታተል 10 ጊዜ አመልክቶ ውድቅ እንዳልተደረገበት በኋላ ላይ ግን በክብር ጥሪ ተደርጎለት የክብር ተናጋሪ ለመሆን በቅቷል። ታዋቂውና ተነባቢው የTIME መጽሔት በ2009 ዓ.ም ከዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ አድርጎ መርጦታል። …”
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም