የነርቭ ዘንግ ክፍተት ምንድን ነው?

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1ሺህ በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት ውስጥ አንዱ በነርቭ ዘንግ ክፍተት የጤና ችግር እንደሚጠቃ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ጥቅል ዓለም አቀፍ አህዛዊ መረጃ በእድገት ላቅ ላሉት ሀገራት ሲከፋፈል ደግሞ 0 ነጥብ 8 አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። ይህም የነርቭ ዘንግ ክፍተት በታዳጊ እንጂ በእድገት ግስጋሴ ውስጥ ባሉ ሀገራት ጉልህ የጤና ችግር እንዳልሆነ ያመለክታል። በሌላ በኩል እ.ኤ.አ በ2014 በተሠራ ጥናት በኢትዮጵያ ከ1ሺ በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት መካከል ሰባት ሕፃናት የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው አሃዝ ሰባት እጥፍ ይበልጣል ማለት ነው። ከዚህ አንፃር የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር የጎላ የጤና ጉዳት እያስተከለ ስለመሆኑ መገመት አያዳግትም።

በየካቲት 12 ሆስፒታል የነርቭና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ሕክምና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሳላዲን በድሩ እንደሚናገሩት፤ የወንዱ የዘር ፍሬ ከሴቷ እንቁላል ጋር ተገናኝቶ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ሙሉ የሰውነት ክፍሎች መፈጠር ይጀመራሉ። በዚህ ሂደት ልብ ከተፈጠረ በኋላ ወዲያው መፈጠር የሚጀምረው የነርቭ ሥርዓት ሲሆን፤ የነርቭ ሥርዓት የሚፈጠረው ደግሞ እርግዝና ከተፈጠረ ከሶስተኛው ሳምንት በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ አንጎልን፣ ህብለ ሰረሰርንና ነርቮች የሚሠሩት ክፍሎች በትክክል ሳይፈጠሩ ሲቀሩና ክፍተት ሲፈጠር የነርቭ ዘንግ ክፍተት / spinal bifida/ ይከሰታል። ስለዚህ ይህ የነርቭ ዘንግ ክፍት ከተለመዱ የአፈጣጠር ችግሮች ውስጥ የሚመደብ ነው።

ለነርቭ ዘንግ ክፍተት እንደ ዋና መንስኤ ሆኖ የተቀመጠውና በሳይንስም የተረጋገጠው የፎሊክ አሲድ ንጥረ ነገር እጥረት ሲሆን፤ ፎሊክ አሲድ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጣቸው አስፈላጊ የምግብ ንጥረ ነገሮች ውስጥ አንደኛው ነው። ከቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክስ ውስጥ ፎሊክ አሲድ ‹‹ቢ ናይን›› አንዱ መሆኑም ይታወቃል። ይህ ንጥረ ነገር አስፈላጊ ነው የተባለበትም ዋነኛው ምክንያት በሰውነት ውስጥ ስለማይመረት ነው። ስለዚህ የግዴታ ይህን ንጥረ ነገር ከምግብ ምንጭ ማግኘት ያስፈልጋል።

ፎሊክ አሲድ ሴሎች በሚራቡበት ጊዜ ዘረ-መል/ ዲ ኤን ኤ/ በትክክል እንዲፈጠርና እንዲዳብር ያደርጋል። ፅንስ ሲፈጠር ፈጣን የሆነ የሴሎች እድገት ይኖራል። ከፅንስ በኋላ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ሲፈጠር ከባድ የሆነ የዘረ መል መባዛት ስለሚኖር በዚህ ላይ ፎሊክ አሲድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ስለዚህ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ዋነኛ መንስኤ ነው ተብሎ የጠቀመጠው የፎሎክ አሲድ እጥረት ነው። ከዚህ ውጭ ግን በፅንስ ወቅት ለካንሰርና ለሚጥል በሽታ የሚወሰዱ መድኃኒቶች በተዘዋዋሪ በፎሊክ አሲድ ላይ ጣልቃ ስለሚገቡ ለነርቭ ዘንግ ክፍተት ሊያጋልጡ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ቁጥጥሩ ጥሩ ያልሆነ የስኳር ህመምም ለነርቭ ዘንግ ክፍተት ሊያጋልጥ የሚችልበት እድል አለ። ከእርግዝና በፊት የሚከሰት ቅጥ ያጣ ውፍረት፣ የዘረ መል ችግሮች፣ ከዚህ በፊት በቤተሰብ ውስጥ የነበሩ እርግዝናዎች ላይ ችግሩ ከነበረ የነርቭ ዘንግ ክፍት የመከሰት አደጋን ከፍ ያደርገዋል። ከዚህ ውጭ ወጣት በሆኑና እርግዝና የመጀመሪያቸው በሆኑ ሴቶች ላይም ይህ ችግር ሲያጋጥም ይታያል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሳላዲን ማብራሪያ፤ ፎሊክ አሲድ ንጥረ ነገር በምግቦች ላይ እንደልብ የሚገኝ ነው። ነገር ግን ካለው የሥነ ምግብ ባህሪ ችግር ጋር ተዳምሮ ድህነት፣ ጦርነትና ድርቅ ሲከሰት ፍላጎቱ በጣም ይጨምራል። ስለዚህ የፎሊክ አሲድ እጥረት የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛው እናቶች እርግዝና መከሰቱን እንኳን የሚያውቁት ከሁለትና ሶስት ወር በኋላ ነው። የነርቭ ዘንግ ክፍተት ደግሞ የሚፈጠረው ፅንስ ከተፈጠረ በሁለተኛው ሳምንት ነው። ያ ማለት እርግዝና ከተከሰተ ከሁለትና ሶስት ወር በኋላ እናቶች የፎሊክ አሲድ መውሰድ ቢጀምሩ እንኳን የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግሩን ሊያስቀሩ አይችሉም። ስለዚህ በተቻለ አቅም ከማርገዝ በፊት ከሁለት ወር ቀደም ብሎ፤ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ደግሞ በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ወራት ፎሊክ አሲድ እንዲወስዱ ይመከራል።

ፅንሱ በሆድ ውስጥ እንዳለ በአልትራሳውንድ በሚደረግ ምርመራ የነርቭ ዘንግ ክፍተት አፈጣጠር ችግር እንዳለ መለየት ይቻላል። በተለይ በሁለተኛው የእርግዝና ክፍል ላይ ማለትም ከአስራ ስድስት እስከ ሀያ ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንዳለና እንደሌለ ማረጋገጥ አያዳግትም። ህፃናት ከተወለዱ በኋላ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ሲኖርባቸው በአከርካሪ አጥንታቸው ላይ ክፍተት ወይም እባጭ ነገር ይታይባቸዋል፤ የጭንቅላት መጠናቸውም ይገዝፋል።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት ጤና ችግር ከተከሰተ በኋላ ሊታከም ይችላል። ሕክምናው የሚጀምረውም ልክ እናቲቱ እርጉዝ ሆና በፅንሱ ላይ የነርቭ ዘንግ ክፍት መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ የሚሰጠው የምክርና አማራጭ የሕክምና አገልግሎት ይሆናል። ከቤተሰብ ጋር ውይይቶችም ይደረጋሉ። ይህም የልጁን ቀጣይ የሕይወት እጣ ፈንታ የሚወስን ነው።

በውጭ ሀገር ደግሞ ይህ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ሲፈጠር ፅንሱን የማቋረጥ አማራጭ ይሰጣል። በኢትዮጵያም ይኸው አማራጭ አለ። ይሁንና ከማህበረሰቡ ባሕልና ሃይማኖትና ሥነ ልቦና ሁኔታ አንፃር አብዛኛው ቤተሰብ ፅንስ ማቋረጥን አይደግፍም። የነርቭ ዘንግ ክፈተት ችግር ብዙ የሰውነት ክፍሎችን ሥርዓት ያዛባል። በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ህፃናት በእግራቸው ቆመው መራመድ ሊሳናቸውም ይችላል። ሽንት የመቆጣጠር ችግር ያጋጥማል። በጭንቅላት ውስጥ ውሃ መጠራቀም ይኖራል። የዳሌ መገጣጠሚያ ችግሮችና የእግር መቆልመም ያጋጥማል። ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫናም ያስከትላል። ከዚህ አንፃር በርካታ ሕክምናዎች የሚያስፈልጉት ነው።

ልጁ ከተወለደ በኋላ ደግሞ የመጀመሪያውና ለሁሉም ሕክምናዎች መሠረት የሚሆነው ሕክምና የነርቭ ዘንግ ክፍተቱን መዝጋት ነው። ነርቩ ቀድሞውኑ የአፈጣጠር ችግር ያለበት በመሆኑ ወደነበረበት መመለስ አይቻልም። ቤተሰብና እናት የሚጠብቁት ግን የነርቭ ዘንግ ክፍተቱ በቀዶ ሕክምና ከተስካከለ በኋላ የሽንት መቆጣጠር፣ የእግር መቆልመምና ሌሎችንም ችግሮች እንደሚያቆም ነው። ሆኖም ይህ ቀዶ ሕክምና በዚህ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። ነገር ግን የነርቭ ዘንግ ክፍተቱ በቀዶ ሕክምና ሲሞላ ልጁን ለመንከባከብ፣ በአከርካሪው ላይ የነበረውን እባጭ በማስወገድ በትክክል እንዲተኛ ለማድረግ፣ ኢንፌክሽን ለመቀነስ፣ የሌሎችን ነርቭ ሥራ ለመጠበቅና ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስተናግድ ይረዳዋል።

የነርቭ ዘንግ ክፍተቱን በቀዶ ሕክምና መድፈን የመጀመሪያው ሕክምና ቢሆንም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሌሎች ሕክምናዎች ይኖራል። የዚህ ዓይነቱ አፈጣጠር ችግር ያለባቸው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ህፃናት ጭንቅላታቸው ውሃ ይይዛል። ስለዚህ ቀጣዩ ሂደት የሚሆነው ውሃውን ማከም ነው። በመቀጠል ደግሞ የሽንትና ሰገራ መቆጣጠር ችግርን ለመቅረፍ ቤተሰብን የማስተማርና ልጆቹም ከፍ እያሉ ሲመጡ ተምረው ራሳቸው በራሳቸው እንዲያፀዳዱ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ። የተቆለመመው እግራቸው ደግሞ ሶስትና አራት ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልገው ይችላል። ከፍ እያሉ ሲመጡ ደግሞ አብዛኛዎቹ ህፃናት ለመንቀሳቀስ የተሽከርካሪ ወንበርና ክራንች ድጋፍ ይፈልጋሉ።

ዶክተር ሳላዲን እንደሚሉት፤ የነርቭ ዘንግ ክፍት ዓይነቱና ደረጃው ይለያያል። አንዳንዱ ክፍተቱ አነስተኛ፤ ሌላኛው ደግሞ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ አነስተኛ የሆነው ክፍተት ከተዘጋ በኋላ ሙሉ በሙሉ ጤናማ የሚሆኑበት ዕድል አለ። ሌሎቹ ደግሞ የነርቩ ዘንግ ክፍተቱ በጣም ሰፊ ይሆንና ከአዕምሮ እድገት ውስንነት አንስቶ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ሙሉ በሙሉ በቤተሰብ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በየካቲት 12 ሆስፒታል በአብዛኛው ሕክምና የሚያገኙትም ድጋፍ የሚፈልጉት ናቸው።

በየካቲት 12 ሆስፒታል የነርቭ ዘንግ ክፍተት ቀዶ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል የተሟላ የነርቭ ሐኪሞች፣ የህፃናት ነርቭ ሐኪሞች፣ የሽንት ሐኪሞች፣ የአጥንት ሐኪሞች ቡድን አለ። በሆስፒታሉ በሚገኙ ሁለት የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ በሳምንት አራት በወር 16 ቀዶ ሕክምናዎች ይደረጋሉ። ነገር ግን የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ በጴጥሮስ፣ ዘውዲቱና አለርት ሆስታሎችም ይሰጣል። ይሁንና ከተጠቂዎቹ ቁጥር ከፍተኛነት አንፃር ይህን ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር የሚመጣጠን አይደለም። ያሉትም ቢሆኑ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ አሟልተዋል ማለት አይቻልም። በዚህ ዘርፍ ሕክምና የሚሰጡ ባለሞያዎች ቁጥርም በጣም ትንሽ ነው። በአሁኑ ጊዜ ይህን ሕክምና የሚሰጡ ባለሞያዎች 50 ብቻ ናቸው። ከዚህ አንፃር ገና ብዙ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ይህ የጤና ችግር በመንግሥት በኩል አስፈላጊውን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለ አይመስልም። ከ100 ህፃናት ውስጥ ይህ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ካላቸው ከ70 እስከ 80 ከመቶ ያህሉ የጭንቅላት ውስጥ ውሃ መጠራቀም ያጋጥማቸዋል። ከጭንቅላታቸው ውስጥ የተጠራቀመው ውሃ በትቦ አማካኝነት ነው የሚወጣው። ሆኖም ይህ ትቦ በመንግሥት በኩል በግዢ ቀርቦ አያውቅም። ሁሌም ቢሆን በርዳታ ድርጅቶች ላይ በመንጠልጠል ነው ቱቦው የሚቀርበው። አልፎ አልፎም ቱቦው ያልቃል። ያኔ ደግሞ ሕክምናው ይቋረጣል። ታካሚዎችም እንግልት ይደርስባቸዋል።

ሽንታቸውን መቆጣጠር ለማይችሉ የሚገባ ቱቦ /catheterization/ እንደ ልብ እየቀረበ አይደለም። የቀዶ ሕክምና ክፍሎቹ ለህፃናቱ የተመቹና የእነርሱን ፍላጎቱ ያሟሉ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። በሕክምና ሂደት ለቤተሰብ ወይም አስተማሚ መቆያ ቦታ አለመኖርና ሌሎችም የሕክምናው ተግዳሮቶች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ችግሮች በደንብ ታይተው በመንግሥት በኩል ተገቢውን መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል።

ይህ የነርቭ ዘንግ ክፍተት በህፃኑም ላይ ሆነ በወላጆች ላይ ከባድ ጫና የሚያስከትል ነው። ነገር ግን ችግሩን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። ፎሊክ አሲድ ከ70 ከመቶ በላይ በነርቭ ዘንግ የመጠቃት እድልን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በሕክምና ትልቁ ስኬትና ፎሊክ አሲድን በወሰዱና ባልወሰዱ ሴቶች መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ በቅድሚያ በተቻለ አቅም የታቀደ እርግዝና ባሕል እንዲኖር ይበረታታል። ይህም ከእርግዝና ከሁለት ወር በፊትና እርግዝና ልክ እንደተከሰተ ፎሊክ አሲድንና ሌሎች በፎሊክ አሲድ የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ሊከሰት የሚችለውን የነርቭ ዘንግ ክፍተት አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላልና መጠቀም ያስፈልጋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You