
“ረጅም እድሜና ጤና ስጠኝ” ብለው ፈጣሪያቸውን ሲለምኑ ኖረዋል:: አሁን ላይ እሳቸው እድሜያቸውን አስታውሰው መናገር ባይችሉም ፈጣሪ የለመኑትን እድሜ ችሯቸው በግምት ሰማንያዎቹን ስለማገባደዳቸው ብዙዎች ይናገሩላቸዋል::
እኚህ ሴት አማከለች አየለ ገብሬ ይሰኛሉ:: የዛሬን አያድርገውና ውሃ የመሰለች መኪና ለ50 ዓመታት ሲያሽከረክሩ ኖረዋል:: ያኔ እንዲህ በሰው እጅ ገብቶ፤ መመገብን፤ መፀዳዳትን፤ ይቅርና መሬትን ለመርገጥ እንኳን በበርቱ የሚጠየፉም ነበሩ::
ታላቁ መጽሐፉ ቅዱስ “በእርጅናህ ወቅት ሱሪህን ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማታውቀው እና ወደማትፈልገው ቦታም ይወስድሃል” እንዳለው እናት አማከለችም ወደ “የወደቁትን አንሱ” በጎ አድራጎት ማህበር የመጡት እንዲሁ ሳይፈልጉ ነው:: ማህበሩም ሆነ ማንኛውም ሰብዓዊነት የሚሰማው ዜጋ እና በተለይ አረጋዊያንን ለመጦር የተቋቋሙ ማዕከላት ደግሞ እንዲህ ያሉትን ዜጎች ሰብስበው የመጦር ኃላፊነት አለባቸው:: በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ቢሆን አረጋዊያንንም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ በሕይወት ዘመናቸው ራሳቸውን የመሸከፍ አቅም ያጡ ዜጎችን የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው በሕግ ተደንግጓል::
የወደቁትን አንሱ ማህበር መሥራችና አመራር አቶ ስንታየሁ አበጀ ወይዘሮ አማከለችን በሰው ጥቆማ የልጃቸው ጓደኛ በስድስት ሺህ ብር ተከራይታ አስቀምጣቸው ከነበሩበት የግለሰብ ቤት ሲያመጧቸው አልሄድም ብለው ለያዥ ለገናዥ አቅተው ነበር::
በብዙ ትግል ወደ ማዕከሉ ሲደርሱም ቢሆን እንዳዩት “እኔ እንዴት እንዲህ ባለቤት” እኖራለሁ በሚል ማዕከሉን እርሳቸው ይኖሩበት ከነበረ ቅንጡ ቪላ ቤት ጋር በማነፃፀር ላለመግባት በብርቱ አስቸግረዋል:: በርግጥ እናት አማከለች እውነት አላቸው:: እንዴት ቢባል ከአንድም ሁለት ሦስት የሚያዝዙና የሚናዘዙበት የተንጣለለ ቤት ነበራቸው:: በተለይ ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘው ቪላ ቤታቸው ውብና ለመርገጥ የሚያሳሳ እጅግ ዘመናዊ የነበረ ስለመሆኑ አሁንም ብዙዎች ወደ ማዕከሉ ሊጠይቋቸው የሚመጡ ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል:: በዚህም ሆነ በሌሎቹ ቤታቸው ጎንበስ ቀና ብለው የሚታዘዟቸው ሠራተኞቻቸውም አያሌ ነበሩ:: በየጊዜው ሊጠይቋቸው ወደ ቤታቸው የሚመጡ እንግዶች ብዛትም ለቁጥር ያዳግት ነበር::
እናት አማከለች የዘር ሀረጋቸውም ቢሆን ከመኳንንቱና ከነገሥታቱ የሚመዘዝ ነው:: አባታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሐረር ክፍለ ሀገር ገዢ የነበሩት ብላታ አየለ ገብሬ ናቸው:: ብላታ አየለ ገብሬ በዘመኑ ከንጉሡ ከአፄ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ የነበሩ ትልቅ ሥልጣን የያዙ እንዲሁም በመኳንንቱና መሳፍንቱ የተከበሩ ታላቅ ሰው የነበሩ ስለመሆናቸው የታሪክ መዛግብት ሳይቀር ይመሰክሩላቸዋል:: ብላታ አየለ ገብሬ የሀረር ክፍለ ሀገር ገዢ ብቻ ሳይሆኑ በዘመኑ የዳኞች ሚኒስቴር መሪም በመሆን ኢትዮጵያን አገልግለዋል:: የዳኞች ልዑካንን በመወከል እንግሊዝ፤ ጣሊያን፤ ፈረንሳይና ሌሎች የአውሮፓና የዓለም ሀገራት ሲጓዙ፤ ሀገራዊ ጉዳዮችን ሲያስፈፅሙ የነበሩ ባለውለታ ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪም ብላታ አየለ ገብሬን ከሌሎች ከአፄው ዘመን ሚኒስትሮችና መኳንንቶች በብርቱ የሚለያቸው በርካታ የሰብዓዊነት ተግባራት አከናውነዋል:: አንዱ ወላጅ አልባ ሕፃናትን እየሰበሰቡ ማሳደግና ማስተማር ሲሆን፤ በዚህ መልኩ ካሳደጉና ካስተማሯቸው ሕፃናት 50ዎቹ ዛሬም በዓለም ዙሪያ ተበትነው በትላልቅ ሥራ ላይ በመቀመጥ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት የበቁ መሆናቸው ይጠቀሳል::
ታዲያ ክቡር ብላታ አየለ በሥጋ ከወለዷቸው አምስት ልጆች መካከል አንዷ የሆኑት እናት አማከለች በዘመኑ የባለባት ልጆች ገብቶ ይማሩበታል ተብሎ በተገነባ ስመጥር ትምህርት ቤት ገብተው የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል:: የባለባት ልጅ እንደመሆናቸው በ12ኛ ሳይገደቡና ለሴት ልጅ
ከዚህ በላይ ትምህርት ምን ያደርግላታል ሳይባሉ ከዚህ ያለፈ እውቀት ለመቅሰም በቅተዋል:: ይሄን ትምህርት አጠናቅቀው ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ በጋብቻ የተጣመሩትም ቢሆን እንዲህ ተራ ከሚባለው ሰው አልነበረም:: በዘመኑ ሥራውም ሆነ ዘሩ ጨዋነው ተብሎ ከሚታመነው እንዲሁም ታላቅ ከበሬታ ከሚሰጠው ከክቡር ብርጋዴር ጄኔራል ዳንኤል መንግሥቱ ጋር ነው::
እናት አማከለች ከክቡር ብርጋዴር ጄኔራል ዳንኤል መንግሥቱ ጋር በትዳር ያሳለፉትን ጊዜ ዛሬ ላይ መለስ ብለው ሲያስታውሱ “አንድም ቀን ተጣልተን አናውቅም:: ልጆቻችንን በፍቅር ነው ያስተማርነው እና ያሳደግነው” ይላሉ:: በትዳር አንድ ላይ የቆዩበት ጊዜ እርጅና የተጫነው አእምሯቸው ቢዘነጋውም በቆይታቸው ሁለት ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ በድምሩ ሦስት ልጆች ስለማፍራታቸውም ይናገራሉ:: አሁን ላይ አንዱ ልጃቸው ካናዳ፤ ሁለተኛው ሴት ልጃቸው ደግሞ አሜሪካ፤ በሙያዋ የአየር መንገድ መስተንግዶ ባለሙያ (ሆስተስ) ስትሆን ኑሮዋን በባሕር ማዶ አድርጋ ስለመገኘቷ ያወሳሉ::
ሆኖም “ሲያልቅ አይምር” ሆነና እናት አማከለች የበስተ እርጅና ዘመን የወላድ መካን አደረጋቸው:: ልብ ድካም፤ ስኳር ደም ግፊት እና ሌሎች ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው ከመጡ በሽታዎች ጋር ተያይዞ የመጣው የእድሜ ጫና ልጅ እያላቸው ቀና አድርጎ ውሃ እንኳን የሚሰጣቸው አጡ:: ዘመደ ብዙዋ እናት አማከለች እንዲያ ቤታቸው በመንጋጋት በመስተንግዶ ያስቸግራቸው የነበረ እንግዳ ሳይቀር ስለራቃቸው ቀና አድርጎ ውሃ እንኳን የሚግታቸው አጥተው በባዶ ቤት ወደቁ::
ከአንባቢዎቻችን ‹‹ሀረር፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢ የነበረውን ጨምሮ ከአንድም ሦስት የተንጣለለ ቅንጡ ቤታቸው፤ ልጆቻቸውስ የት ገቡ እና ነው የሚጎበኛቸው ያጡትና መጦሪያ ማዕከል የሚገቡት›› በሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: ልጆቻቸውም ውጭ ሀገር በሕይወት አሉ፤ ቤት ንብረታቸውም ቢሆን ባለበት ነው ምላሻችን:: ግን ደግሞ በተለይ ቤት ንብረት፤ የሀብትና ገንዘብ ብዛት እድሜ እንደ መርግ ተጭኖ እጅ እግር በተያዘ ጊዜ ቀና አድርጎ ውሃ የሚያጠጣ ሰውን ያህል እንኳን ዋጋ እንደሌለው መገንዘብ ያስፈልጋል:: በሀብት ንብረቱ እና በገንዘቡም ሠራተኛ ቢቀጠር፤ ዘመድ አዝማድም እንዲያስተዳድር ቢደረግ እንደ ልጅ እናትን መንከባከብ አይችልም::
ሆኖም ልጆቻቸው ባሕር ማዶ የራሳቸው ሕይወት አላቸው:: የኔ የሚሉት የየራሳቸው ቤተሰብም መስርተዋል:: እነዚህ በየራሳቸው የመሰረቷቸው ቤተሰቦች ደግሞ ለወላጅ እናታቸው አማከለች የሚሰጡትን ጊዜ ይሻማሉ:: በዚህ ላይ የውጭ ሀገር ያው የውጭ ሀገር ነው:: እንደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሳይሠሩ መብላት ብሎም ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አይችሉም:: ወደ ሀገር ቤት ለመምጣትም ሁሌ ፈቃድ እንደ ልብ አይገኝም::
እንደዚህ ሆኖም እናት አማከለችን ልጆቻቸው ለብዙ ዓመታት እየተጨናነቁ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ሲጎበኟቸው እና ሲንከባከቧቸው ቆይተዋል:: ጥሩ ሆስፒታል አስተኝተው አሳክመዋቸውም ያውቃሉ:: ሌሎች ዘመድ አዝማዶችም ቢሆኑ በአባታቸውም ሆነ በእሳቸው ከተደረገላቸው ውለታ ብዛት ወደ ሀገር ቤት በመጡ ቁጥር ሲጎበኟቸው ኖረዋል:: የፈለጉትንም ያደርጉላቸው ነበር:: ልጆቻቸው ይሄን ማድረግ እየተሳናቸው ሲመጣ በዘመድ አዝማድ፤ ብሎም በሠራተኛ ሊከባከቧቸው ሞክረዋል:: ሆኖም የሰው ልጅ ሰው ነውና ቃሉን ለመጠበቅ ፍፁም ባለመሆኑ ይሄም አላዋጣም::
እናት አማከለች እንደሚሉት ከዓመታት በፊት የልጃቸው ጓደኛ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሰሚት አካባቢ በስድስት ሺህ ብር የግለሰብ ቤት ትከራይላቸዋለች:: ልጅቱ ባሕር ማዶም ሀገር ውስጥም በማለት ነው የምትኖረው:: እንዲሁም ሆኖ በተቻላት መጠን እየመጣች ትጎበኛቸው፤ እንዴት ኖት፤ አይዞት እያለችም ስታጽናናቸው ቆይታለች:: የሚያስፈልጋቸውንም ቢሆን ከማቅረብ ተቆጥባ አታውቅም:: በዚህ ሁኔታ ለዓመታት አብራቸው ዘልቃለች:: ሌላዋ አባታቸው ያሳደጓቸው እና ለጊዜውም ቢሆን ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ የሆነው ወይዘሮ ኢትዮጵያ የተባሉ እናት ልጅቱ ከምታደርግላቸው እንክብካቤ ጎን ለጎን እናት አማከለችን ሲንከባከቡ ቆይተዋል:: ሰርክም ሲጎበኟቸው ነው የኖሩት::
ቤት ንብረት ይዘው አዘው ናዝዘው ሲኖሩ ከነበሩበት ሁኔታ በግለሰብ ቤት፤ ያውም በዚህ ሁኔታ በሰው እየተጎበኙ መኖሩ ለእናት አማከለችም ብዙም አልጣማቸውም፤ ደስተኛም አላደረጋቸውም:: በመሆኑም ስሜታቸው መነካቱ በእጣ ፈንታቸውም ማዘናቸው አልቀረም:: በተለይ ሰርክ ይጎበኟቸውና ያጽናኗቸው የነበሩት ወይዘሮ ኢትዮጵያ አቅማቸው እየደከመ፤ ሁኔታዎችም ሳይመቻቹላቸው ሲቀር ጉብኝታቸውን ያቆማሉ:: እናት አማከለችን ብቸኝነቱ ከእርጅናው ጋር ተዳምሮ ይጫጫናቸዋል:: ፈጣሪያቸውን ረጅም እድሜ ስጠኝ ብለው ሲለምኑት እንዳልኖሩ ሁሉ የሰው እጅ አታግባኝ፤ ብለው ቢለምኑም መታመማቸው እና ዳይፐር ከሚቀይርላቸው ጀምሮ ሰው መናፈቅ አልቀረላቸውም:: ይሄኔ እናት አማከለች የእለት ሞቴን ስጠኝ፤ በፍጥነት ውሰደኝ እስኪሉ በሕይወታቸው በብርቱ ይማርራሉ::
በዚህ ማዕከል ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የመጣችው የልጃቸው ጓደኛ እሳቸውን ለመጎብኘት ተከራይታ ወደ አስቀመጠቻቸው ቤት ትመጣለች:: በሁኔታቸው አዝና እንባ ማፍሰስ ፀጉር መንጨት አልበቃትም:: በተለይ ከውጭ ዓመታት ቆይታ በመመለሷ የሚናገሩት ንግግር፤ ባልተለመደ ሁኔታ መነጫነጫቸው ከእርጅና ሳይሆን ከአእምሮ ሕመም ጋር የተያያዘም ስለመሰላት ብርቱ ስጋት ይገባታል:: በፍጥነት ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ፤ ሕክምናም እንዲያገኙ ታደርጋለች:: ልጅቷ ከሐኪሙ በተለይ በታዳጊ ሀገር የሚኖሩ አረጋዊያን እርጅና የሚጫናቸው ከአኗኗራቸው እና ሊደረግላቸው ከሚገባ እንክብካቤ ጋር በተገናኘ ከሚገጥማቸው ሕመም ጋር በመዳመር እንደሆነ ትረዳለች:: ሐኪማቸው የልብ ሕመም፣ የመስማት ችግር፣ እንዲሁም መነጫነጭ በእናት አማከለች ላይ የመጣው ከእርጅና ጋር ተያይዞ ነው:: እንዲህ ያሉ የእርጅና ምልክቶች አንድ ሰው በአማካይ 65 ዓመት ሲሞላው የሚታዩ በመሆናቸው እንደማያሳስብም ያብራራላታል::
ይሄኔ ልጅቷ እንደሷ ዓይነት ባተሌ፤ ወይም ቀድሞ እንደነበሯቸው ሠራተኞች ዝንጉ እና በአግባቡ የማይታዘዝ ሳይሆን ሌት ከቀን ከአጠገባቸው የማይለይ ተንከባካቢ እንደሚያስፈልጋቸው ትገምታለች:: በውጭው ዓለም እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ መኖሩንም ታስታውሳለች:: ወደ እዛ ባዶ ቤት መመለስ እናት አማከለችን ለስቃይ መዳረግ እንደሆነ ይገባታል:: በመሆኑም ልጅቱ ጊዜ አላጠፋችም:: በፍጥነት እስከ እድሜ ልካቸው ሊጦራቸው የሚችል መጦሪያ ማዕከል ታፈላልግላቸዋለች:: “የወደቁትን አንሱ” የበጎ አድራጎት መጦሪያ ማዕከልም ታገኝና ታስገባቸዋለች::
“ቢያንስ እዚህ ምግብና መጠጥ የሚያቀርቡሎትና የሚንከባከቦት፣ በቀን ሁለቴ ዳይፐር የሚቀይርሎት ሰው ያገኛሉ በማለትና በማባበል አስገባናቸው” ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱት::
ሆኖም በወቅቱ ከእርጅና ጋር በሽታ ተደማምሮ ያዳከማቸው እናት አማከለች እዚህ መጦሪያ ማዕከል ለመግባት በፍፁም ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም ነበር:: በብዙ ቢለመኑም በብርቱ ረብሸዋል:: ፍፁም እምቢተኝነታቸውን የተረዱት እና በእድሜም በበሽታ ጫናም ወደ ማዕከሉ ከሚመጡ እናት አረጋዊያኖች የተካበተ ልምድ የቀሰሙት ብልሁ “የወደቁትን አንሱ” የበጎ አድራጎት መስራች እና ባለቤት አቶ ስንታየሁ ወደ መጡበት ቤት እንዲመልሷቸውና በቤታቸው የማዕከሉ ሠራተኞች እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው አደረጉ:: ከትንሽ ቀን ቆይታም በኋላ ሆስፒታል ልንወስዶት ነው በማለት የሚኖሩበት ቤት ድረስ ሄደው ወደ መጦሪያ ማዕከሉ አመጧቸው:: እናት አማከለች አሁንም “ድኛለሁና ከዚህ ሆስፒታል ልውጣ” ማለታቸው አልቀረም::
የማህበሩ መሥራች በበኩላቸው የእናት አማከለችን ሕይወት በእንክብካቤና ድጋፍ ጡረታ እስከ ወዲያኛው ለመታደግ መላ ዘየዱ:: ይሄም ማዕከሉን አባቶት ብላታ አየለ ገብሬ ናቸው የሠሩት ማለት ነበር:: እናት አማከለች ይሄን አመኑ:: አሁን ላይ ሊጠይቃቸው ለመጣ ሰው ሁሉ ማዕከሉን አባታቸው ብላታ ገብሬ ያሠሩት እንደሆነ በመናገር ተረጋግተው በሰላም ለመጦር በቅተዋል:: ክብር ለእናት አባቶቻችን ይሁን!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም