ጥቅም ላይ ያልዋለ የቤቶችና መሬት ልማት ማፋጠኛው አዲስ መንገድ

ጥቅም ላይ ባልዋሉ ቦታዎችና አገልግሎት በማይሰጡ ህንጻዎች ላይ ከፍተኛ የንብረት ታክስ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው። ይህን አስመልክቶ በቅርቡ በተካሄደ ውይይት ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊ የሰጡትን ማብራሪያ ዋቢ ያደረገ አንድ ዘገባ እንዳመለከተው፤ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ጥቅም ላይ ያልዋለ ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻል ነው።

ይህ ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ሰፊ ቦታ ይዘው እንዲሁም ህንጻ ገንብተው ሳያከራዩ ያስቀመጡ ሁሉ ከፍተኛውን የንብረት ታክስ ክፍያ እንዲከፍሉ ይደረጋል። ይህ አዋጅ እንደተባለው ሰፋፊ ቦታዎችን ያለ ምንም ሥራ አጥረው የያዙ አካላት ያሉባት አዲስ አበባ፣ ህንጻዎችን ገንብተው ወደ ሥራ ያላስገቡ ወገኖች በርካታ እንደሆኑ የሚነገርባት አዲስ አበባ ከተማ ቦታዎቹም ህንጻዎቹም በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።

የቦታዎቹም ሆነ የቤቶቹ ወይም ህንጻዎቹ ወደ ሥራ መግባት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ይታወቃል፤ ከተማዋ ከኪራይና ከመሳሰለው ግብር እንዲሁም ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋል። በከተማ የሚታየውን የመኖሪያ እንዲሁም የንግድና የመሳሰሉት ቤቶች እጥረትን በተወሰነ መልኩ በመፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የከተማ አስተዳደሩ ቦታዎችን ምንም ዓይነት ጥቅም በማይሰጡበት ሁኔታ አጥረው ያስቀመጡ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ህንጻ ገንብተው ለአገልግሎት ያላበቁ ዘግተው ያስቀመጡ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች ምን ያህል ስለመሆናቸው የተካሄደ ጥናት ቢኖር በጉዳዩ ላይ በደንብ መነጋገር የሚቻል ቢሆንም፣ ስለችግሩ አሳሳቢነት ለመናገር ግን የግድ ይህ መረጃ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። እውነታው የአደባባይ እውነታ ነውና።

በከተማዋ ይህን ዓይነት ቦታዎችና ህንጻዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ይታወቃል፤ በከተማዋ ለብዙ ዓመታት የኖረ ሰው በከተማዋ በጣም በርካታ ሥራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች እንዲሁም ህንጻዎች ስለመኖራቸው መመስከር አይቸገርም።

የአዋጁ መዘጋጀትም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ቦታና ህንጻ ብዙ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነው ብሎ መናገር ግን ይቻላል። ረቂቅ አዋጁ ቦታ የሚወርስ ወይም የሚነቅል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ባለይዞታዎቹ ታክሱን ፈርተው መሬቱን እንዲሁም ባለህንጻዎቹ ህንጻውን ወደ ሥራ እንዲያስገቡ ግፊት የሚፈጥር ነው።

በግል መኖሪያ ቤት ይዞታዎች፣ አንዳንድ የግልና መንግሥታዊ ተቋማት ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጥ ሰፊ ቦታ ዳዋ በልቶት ይገኛል። ይሄን ጉድ ሲያልፉ ሲያገድሙ ማየት ይቻላል፤ ከዚህ በተረፈ ደግሞ በአካባቢው ካለ ባለወለል ህንጻ ላይ ሆኖ መመልከት ይቻላል።

በግቢያቸው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ እና ሊወገዱ የሚገባቸው አገልግሎት ካቆሙ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽኖች፣ ወዘተ ዳዋ ለብሰው የሚታዩባቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኢንዱሰትሪዎች ወዘተ. ተቋማት ጥቂት አይደሉም።

በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥም እንዲሁ ምንም አገልግሎት የማይሰጥ ሰፊ ቦታ ማግኘት ቀላል ነው። በዚህ ሰፊ ትርፍ ቦታ ላይ ቤት ተገንብቶ ለተለያዩ አገልግሎቶች አልዋለ ወይም አረንጓዴ ሥፍራ ሆኖ ለግቢውም ለከተማም ውበት አላገለገለ የከተማ ጢሻ የሆነ ቦታ በነባርምም በማስፋፊያም የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ ባለይዞታዎች ግቢ ውስጥ በብዛት ይታያል።

በከተማዋ ትላልቅ ቪላ ቤቶች ብቻ የሚታይባቸው ከዚያ በተረፈ የረባ ግንባታ የማይታይባቸው ግቢዎች በብዛት ይገኛሉ፤ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ግቢዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፤ ይህን ሁሉ በመመልከት እነዚህ የሀገር ሀብቶች እንዴት ወደ ልማት ይግቡ በሚል ወደዚህ ርምጃ ለመግባት መታሰቡ በጣም ጥሩ እይታ ነው፤ ትልቅ ሀብት እየባከነ መሆኑ በሚገባ ታይቷልና።

አንዳንድ ግቢዎች ውስጥ የረባ ቤት በሌለበት ሁኔታ ቦታው ለነዋሪውም ለሰፈሬውም ለከተማዋም በማይጠቅምበት ሁኔታ ባክኖ የሚታይበት ሁኔታ ከዚህም በላይ ርምጃ ቢወሰድ ተገቢ አይደለም የሚያስኝ ሁኔታ አለ ብዬ አላስብም።

እነዚህ በመንግሥት እይታ ውስጥ የገቡት ቦታዎችና ህንጻዎች ባለቤቶችን ወደ ልማት ማስገባት የሚያስገድዳቸው ጠንካራ የሕግ ማሕቀፍ አልነበረም ብሎ ማለት አይቻልም። በየግቢው ያለውን ትርፍ መሬት ለሌላ ልማት ማዋል የሚያስችል ሥራ በቀደመው መንግሥት ተግባራዊ ሊደረግ ታስቦ ነበር ይመስለኛል። ያ አሠራር ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፤ እሱም ቢሆን ከዚያ ወዲህ አልታየም።

መንግሥት እነዚህ ይዞታዎች ላይ ሊከተል የፈለገው አሠራር ልማቱን ያፋጥነዋል፤ የንብረት ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ባለይዞታዎቹ መሬቱን እንዲያለሙት ግፊት ያሳድራል። የሚጣልባቸው ከፍተኛ ታክስ ይህን ወደ ማድረግ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው። ይህን ከፍተኛ ታክስ እየከፈሉ መቆየት ይችላሉ ታብሎ አይታስብም፤ ፈጥነው ወደ ማልማቱ ይገባሉ ተብሎ ይታሰባል፤ የመንግሥትም ርምጃ ይህን ማድረግ ነው። ይህ ሁኔታ ለባለይዞታዎቹም ከተማዋን በማልማት ላይ ትልቁን ኃላፊነት ይዞ ለሚሠራው መንግሥት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህ አንድ አዲስ ነገር ነው።

አሁን ደግሞ መንግሥት ለአካባቢው ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ነው እንዲያለሙ የሚደረጉት። የእነሱ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የከተማዋ ፍላጎትም ታሳቢ ይደረጋል። እስከ አሁን ከተማዋ ያለ ፕላን የተመሠረተች ይመስል ብዙ የፕላን ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በኮሪደር ልማቱ ለዚህ መፍትሔ ተቀምጧል። እነዚህ ቦታዎችም በዚሁ መሠረት እንዲለሙ የሚደረግ በመሆኑ ሳይለሙ መቆየታቸው የተሻለ ከተማ ለመገንባት ተጨማሪ እድል ይፈጥራል።

ወደ ትግበራው ከመገባቱ በፊት ግን ጥቅም ላይ ያልዋለ ቦታ ማለት ምን ማለት ስለመሆኑ በሚገባ ግልጽ መደረግ አለበት። ጥቅም ላይ ማዋል ማለት ህንጻ መገንባት ብቻ ነው? ወይስ ሌላ ግንባታን ያካትታል? ይህም መታየት ይኖርበታል።

በከተማዋ ሰፋፊ ግቢ ያላቸው መኖሪያ ቤቶች ወይም ድርጅቶች መኖራቸው የሚጠላ አይመስለኝም። ሰፋፊ ግቢ ውስጥ የተገነቡ፣ የአረንጓዴ ሥፍራ፣ መዋኛ፣ ወዘተ ያላቸው መኖሪያ ቤቶችን በከተማዋ መመልከት እንዳ ውበት ተደርጎ መታየትም ያለበት ይመስለኛል። በዞን ተለይቶ ይለማ ይሆናል እንጂ የውጭ ሀገሮች ተሞክሮም ይህን የሚፈቅድ ይመስለኛል።

በዚህ ዓይነት ግቢ ውስጥ ያለ ቦታም የባከነ ተብሎ የሚታይም አይመስለኝም። በአረንጓዴ ተክሎች ከሸፈኑ፣ ለእነሱም ለከተማዋም ውበት ከጨመሩ ጥሩ ነገር ነው፤ ይህ ግን በተቀመጠ ስታንዳርድ መሠረት የሚመዘን ይሆናል። ይህን ማድረግ ከቻሉ ባለይዞታዎቹ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን ይዘዋል የሚባሉ አይመስለኝም፤ ከዚያ ይልቅ በዚያ ደረጃ ያሉ ይዞታዎች ለመንግሥት መክፈል ያለባቸው ግብር ከፍተኛ መሆን ሊኖርበት ይችላል።

እንደተባለው ጥቅም ላይ ያልዋለ በሚል ብቻ ሰፋፊ ግቢ ያላቸውን ይዞታዎች በሙሉ ወደ ህንጻ መገንቢያነት እንዲቀየሩ ማድረግ አሉታዊ ጎን ይዞ እንዳይመጣም መገንዘብ ይገባል። ይህን ማድረግ ከተማዋ በግል ይዞታዎች ውስጥ ከፍት ቦታዎች እንዳይኖራት ያደርጋል። ዋናው ነገር ግን የግቢው መልማት መሆን አለበት። በግቢው ውስጥ ከከተማዋ ልማት ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ልማት እንዲካሄድ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከዚህ ውጪ ከተማዋ ያንን ዓይነት ግቢዎች ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ድርጅቶች አያስፈልጋትም ወይ፣ የውጭ ሀገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል፣ የሚሉትን መመልከትም ይገባል። ያለውን ቦታ ሁሉ ግንባታ እንዲካሄድበት ማድረግ ትክክል ነው ብዬ አላምንም።

ከዚህ ውጪ መንግሥት ያለሙ ቦታዎች እወስዳለሁ አላለም፤ ፍላጎቱ ቢሆንማ አልሙ፤ ካላለማችሁ ለሌላ አልሚ አስተላልፋለሁ ይል ነበር። አሁን እያለ ያለው ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ወደ ልማቱ እንደሚጡ እሰራለሁ ነው። እነዚህ አካላት እንዲያለሙ ጊዜ ይሰጣቸዋል? ወይስ የተጠላባቸውን ታክስ እየከፈሉ መቀመጥ ይችላሉ? እነዚህም መልስ ይፈልጋሉ።

ታክሱ አስመርሯቸው ቦታውን ያለሙታል ተብሎ ታስቦ ሊሆን ይችላል ወደዚህ ርምጃ የተገባው፤ ይሄ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፤ ከእነዚህ አካላት ገንዘብ መሰብሰብ ትኩረት የሚደረግ ከሆነ ዳዋ የበላው ግቢ ገንዘብ እየተከፈለበት ባለበት ይቀመጥ ማለት እንዳይሆን እሰጋለሁ። የማያለሙት ከሆነ ከፍተኛውን ታክስ እንዲከፍሉ መደረጉ እንዳለ ሆኖ ቀጥሎ ምን ወደ ማድረግ እንደሚገባም ጠቆም ማድረግ ይገባል።

እንደሚታወቀው በከተማዋ ቦታ የለም እየተባለ ልማቱ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ሲገፋ ኖሯል። እነዚህ መሠረተ ልማት በሚገባ የተዘረጋላቸው ቦታዎች ከተማዋ መሀል እያሉ መሠረተ ልማት ወዳልተዘረጋላቸው ቦታዎች አልሚዎችን በመውሰድ ልማቱን ለማስቀጠል ሲሠራ ቆይቷል።

በርካታ ህንጻዎች የውሃ፣ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም የጤና የትምህርት ወዘተ መሠረተ ልማት ባልዞረባቸው አካባቢዎች ህንጻዎች ተሠርተው የሚፈለግባቸውን አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህን አገልግሎት ለመስጠት እነዚህ መሠረተ ልማቶች የግድ ናቸው። በማስፋፊያ አካባቢ በርካታ ወጪ የወጣባቸው መኖሪያ ቤቶችና ግዙፍ ህንጻዎች ተዘግተው እንደሚገኙ ይገለጻል፤ እነዚህ ህንጻዎች ወጪ የተደረገባቸውን ታሳቢ ያደረገ ኪራይ በማያገኙበት ሁኔታ እንዲከራዩ ቢደረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ለማጠናቀቂያ ብዙ የወጣባቸው ህንጻዎች ለጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ።

መንግሥት ወደ አዋጁ ትግበራ ከመግባቱ በፊት እነዚህ ህንጻዎች የገጠማቸውን ችግር በቅድሚያ መፍታት ይኖርበታል፤ በማስፋፊያ ቦታዎች ውሃ ፣ የመጸዳጃ መሠረተ ልማት፣ ኤሌክትሪክ ባልተዘረጋበት እንዲሁም ሊፍት ለሚያስፈልጋቸው ህንጻዎች ሊፍት ባልተገጠመበት ሁኔታ ህንጻዎቹ ያለ ጥቅም ተቀምጠዋል ብሎ መፍረድ ውስጥ መግባት አይገባም፡፤ ሊፍት የሚያስፈልጋቸው የ40 በ60 እና ባለ ሰባት ወለል ቤቶች ካለ ጥቅም ተቀምጠዋል ብሎ መፈረጅም እንዲሁ ትክክል ላይሆን ስለሚችል መንግሥት አስቀድሞ የእነዚህን ቤቶች የመሠረተ ልማት ችግር መፍታት ይኖርበታል።

እነዚህ ህንጻዎች በከተማዋ ያለ ምንም አገልግሎት በግለሰቦችና ድርጅቶች ተይዘው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ተገንብተው ቢሆን እንደተጠናቀቁ አገልግሎት መስጠት ይጀምሩ ነበር። ምንም እንኳ አሠራሩ ትክክል ነው ባይባልም በለሙት አካባቢዎች የተገነቡትን አንዳንድ ህንጻዎች ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ጭምር ምን ያህል ተፈላጊ ስለመሆናቸው ይታወቃል። ይህም የመሠረተ ልማቱን አስፈላጊነት ያመለክታል።

ከዚህ ውጭ ያሉ ሁሉም መሠረተ ልማቶች ባሉባቸው በከተማዋ መሀል ከተገነቡ አንዳንድ ህንጻዎች የተወሰኑትን ወለሎቻቸውን ወደ ሥራ በማስገባት የተቀሩትን ግን ያለቁ እንዲመስሉ ውጪያቸውን ብቻ አሳምሮ ውስጣቸውን ሳያጠናቅቁ ያስቀመጡ ባለህንጻዎች እንዳሉም ይታወቃል።

አዋጁ ወደ ሥራ ሲገባ በቀጥታ ሥራ ሊጀምርባቸው ይገባል ተብለው የሚታሰቡ ያለምንም ሥራ የተቀመጡ፣ ለከተማ ውብትም ደንቃራ የሆኑ የሀገር ሀብት በከንቱ እንዲበሰብስ እየተደረገባቸው የሚገኙ ያለ ጥቅም የተቀመጡ ቦታዎች ጥቂት አይደሉም፤ እነዚህ ቦታዎችና ህንጻዎች ላይ በሚገባ መሠረት ይኖርበታል።

ከዚያ ውጭ በሚገባ ሊታዩ የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል። ያለጥቅም የተቀመጡ ቦታዎችን መንግሥት እወስዳለሁ አላለም፤ ባለይዞታዎች እንዲያለሟቸው ግፊት የሚያሳደር አሠራር ነው ያስቀመጠው። ይሄ ጥሩ ነገር ነው።

ባለይዞታዎች በገዛ ቤቴ በገዛ ህንጻዬ በገዛ ይዞታዬ መንግሥት ምን አገባው ሊሉ አይችሉም፤ ቤቶቹም ይሁኑ ህንጻዎቹ የተገነቡት ለባለቤቶቻቸው ብቻ አይደለም፤ ለሀገርም ለከተማም ለሕዝብም ጭምር ነው። ከተማዋ በመኖሪያ ቤት እንዲሁም በንግድ ቤት እጥረት እየተቸገረች ባለችበት ሁኔታ ግንባታዎችን ቶሎ አጠናቆ፣ የተጠናቀቁትንም ፈጥኖ ለአገልግሎት አለማብቃት ሊያስጠይቅ እንደሚችል ለማስገንዝብ አዋጁ ሁነኛ መሳሪያ ይሆናል።

ለዚህ ማጠንከሪያ የሚሆን አንድ ጉዳይ ላንሳ። ብዙ ዓመታት ሆኖታል፤ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ እየተጓዝን ነበር። ጥቂት እንደተጓዝን ከታሪፍ ጋር በተያያዘ አንድ ተሳፋሪና ረዳቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ይገባሉ። ውዝግቡ እየተሟሟቀ መጣ፤ ሾፌርም ከረዳቱ ወገን ሆኖ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ጀመረ። አውቶብሱን አቁሞ ተሳፋሪው ወዳለበት ወንበር አካባቢ መምጣት ጀመረ፤ አሽከርካሪው የአውቶብሱ ባለቤት ሳይሆን አይቀርም፤ አነጋገሩ ይናገራል። እንዳውም ከመኪናዬ ላይ ውረድ ሲል ተሳፋሪውን በማሳሳብ ጎትቶ ሊያወርደውም ቃጣው።

ተሳፋሪውም ቆፍጠና ነበሩ፤ አልወርድም፤ አውቶብሱ ምንህም አይደለም፤ ሕዝብ ለማገልገል ያሰማራኸው ነው፤ አረፈህ ተቀምጥ ሲሉ መለሱለት። በመሀል ሰው ገባና ችግሩ ተፈታ። እኛ ቤታችን የኛ ቤት ብቻ ይመስለናል፤ የመንግሥትም የሕዝብም መሆኑን እንስታለን፤ ወይም ይህን ማሳወቅ ያለባቸው አካላት አላሳወቁን ይሆናል፤ ስለዚህ ቤታችን ድርጅታችን መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት ነው የሚተዳደረው፤ እኛም የምንተዳደረው።

ብዙ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎች ህንጻዎች በከተማዋ እንደመኖራቸው አዋጁ እነዚህ ቦታዎችና ህንጻዎች የሕዝቡን፣ የመንግሥትን እንዲሁም የተከራዮችንና የመሳሰሉትን ፍላጎቶች ሊያሟሉ ስለሚችሉ ያለሙት እንዲለሙ የለሙት ደግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ባለይዞታዎችና ባለንብረቶች ሊያስቡበት ይገባል። እንዲያለሙ ፣ ያለሙትም ወደ ሥራ እንዲያስገቡ የሚያስችል አዋጅ ነው እየተዘጋጀ ያለው። ይህን መልካም እድል በመጠቀም መሬታቸውን ያላለሙ ወደ ማልማቱ፣ ህንጻ ግንባታ ጨርሰው ወደ አገልግሎት ያላስገቡም እንዲሁ ህንጻዎቹን ወደ አገልግሎት ለማስገባት በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው።

ርምጃው የቤት፣ የመሬት ልማትን የሚያፋጥን አዲስ መንገድ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ሀገሪቱ ከመሬቷ፣ ከህንጻዎችና ቤቶች ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ያለባት እንደመሆኑ፣ ካለማ፣ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ካልገባ ህንጻ፣ ወዘተ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ብቻ አይደለም የሚያስችለው።ሌሎች በቀጣይ ቦታ የሚወስዱ እንዲሁም ህንጻ የሚገነቡ አካላት ፈጥነው ግንባታ እንዲያካሂዱና ህንጻዎቹን ለአገልግሎት እንዲያበቁ፣ በዚህም ለሀገሪቱ አኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላል።

እስመለዓለም

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You