አዲስ አበባ፡- በ2017 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 172 ሚሊዮን 951 ሺህ 738 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። እቅዶችን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጎን ሆነው አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገለጸ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም አራት ሚሊዮን 277 ሺህ 230 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሠራ ነው። ከዚህም 172 ሚሊዮን 951 ሺህ 738 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
የመስኖ ስንዴ ልማት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፤ ደቡብ-ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ላይ አራት ሚሊዮን 277 ሺህ 230 ሄክታር መሬት ለማረስ መታቀዱን አመልክተዋል።
እስካሁን ድረስ በባህላዊ ሁለት ሚሊዮን 649 ሺህ 184 ሄክታር፣ በትራክተር 365 ሺህ 65 ሄክታር መሬት በድምሩ ሦስት ሚሊዮን 14 ሺህ 249 ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥም ሁለት ሚሊዮን 390 ሺህ 88 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
የክልሎችን ድርሻ ስንመለከት ኦሮሚያ ክልል አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 163 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውሰው፤ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን 819 ሺህ 539 ሄክታር መሬት ታርሷል። ሁለት ሚሊዮን 202ሺህ 674 ሄክታር መሬቱ በዘር መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል 230 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 8 ሚሊዮን 535 ሺህ 800 ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዱን ገልጸው፤ እስካሁን ድረስ 183 ሺህ 981 መሬት ታርሶ፣ 115 ሺህ 40 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አፋር 23 ሺህ 500 ሄክታር፣ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ሺህ 04 ሄክታር፣ ሶማሌ ክልል አምስት ሺህ 100፣ ደቡብ ኢትዮጵያ አምስት ሺህ ሄክታር እንዲሁም ማእከላዊ ኢትዮጵያ ሦስት ሺህ 116 ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ በትግራይ ሁለት ሺህ ሄክታር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንድ ሺህ 60 ሄክታር መሬት፣ ጋምቤላ ክልል አንድ ሺህ እና ሲዳማ ክልል 350 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ አመላክተዋል።
እንደ ሀገር የተቀመጡ እቅዶችን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጎን ሆነው አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉ መሆኑንም መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም