“መቄዶንያ ብዙዎችን ተስፋ ከመቁረጥ አውጥቶ ሕይወት የዘራ ማዕከል ነው” – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፡- መቄዶንያ ብዙዎችን ተስፋ ከመቁረጥ አውጥቶ ሕይወት የዘራ ማዕከል ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።ፕሬዚዳንቱ የመቄዶንያ የበላይ ጠባቂነትን ጥያቄ ተቀብለዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ትናንት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ መቄዶንያ ብዙዎችን ተስፋ ከመቁረጥ አውጥቶ ሕይወት የዘራ ማዕከል ነው።የልመናና የጉስቁልና ማርከሻው ለሀገር በርትቶ መሥራት በመሆኑ በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የሕይወትና የመኖር ትርጉም የሚገለጸው ለሌሎች ሰዎች በጎ በማድረግ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አርዓያ የሚሆን እንደሆነ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የሰውን ልጅ ብርታት ተመልክቻለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ተስፋ መቁረጥም እንደሚሸነፍ ተረድቻለሁ። ከተባበርንና ከተጋገዘን ተስፋ መቁረጥም ያልፋል፤ ሞትም ይሸነፋል።እዚህ ያየሁት ይህንን ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያዊነት ብርታት ከሚለኩባቸው ተግባራት አንዱ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ወገንን መታደግ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ብርታት አንዱ መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ቅርንጫፎቹን ወደ 240 ለማድረስ ማቀዱን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በ60 ሰዎች ጀምሮ ስምንት ሺህ መድረሱና ከአዲስ አበባ አንስቶ ወደ 44 ከተሞች መድረሱ ወደፊት ይህን ዕቅዱን ለማሳካቱ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።

ማዕከሉ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሚጀምረው የሕንፃ ግንባታ ማጠናቀቂያ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይም የማዕከሉን በጎ ሥራ የተመለከተ ሁሉ በወገን ተቆርቋሪነት መንፈስ ድጋፉን እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።

መስጠት የተቀባዩን ልብ የሚሞላውን ያህል የሰጪውንም መንፈስ ይሞላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህን ተቋም መርዳት ለወገኖቻችን፣ ለእናት ለአባቶቻችንና ለተጎሳቆሉ ሁሉ የሚውል በመሆኑ እገዛ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በጎነትን መንገድ ያደረገና ቅንነትን የተላበሰ ሁሉ በመቄዶንያ ለተጀመሩ የወገን አድን ሥራዎች እንዲተባበሩ ጠይቀው፤ ይህ ተቋም ትናንት ያልነበረ፣ ዛሬ ያለ ለወደፊቱ የሚተጋ ነው። በረከቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኑ በዚሁ በርትታችሁ እንድትቀጥሉ አደራ እላለሁ ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎችም ይህን ሃሳብ በማገዝና ወደ ሕዝብ የማድረስ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የማዕከሉን ሃሳብ እውን ለማድረግ እንዲተባበር ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ለመንግሥት ሠራተኞችና ለኩባንያ ኃላፊዎች በፊትም ታደርጉት እንደነበረው ልግስናችሁ እንዳይለይ አደራ እላለሁ የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አረጋውያን ያቀረቡላቸውን የበላይ ጠባቂነት ጥያቄ ተቀብለዋል።

እንደ ርዕሰ ብሔር የሁሉም ተቋም የበላይ ጠባቂ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከአረጋውያኑ እንደማይለዩና ሁሉም ሰው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

የአረጋውያኑ ሁለተኛ ጥያቄ የሆነውና በየዓመቱ ታኅሣሥ 18 ቀን እየመጡ እንዲጎበኟቸው የቀረበውን ጥሪም በተመለከተም ፕሬዚዳንቱ በየዓመቱ በዚሁ ቀን ወደ ማዕከሉ እየመጡ እንደሚጎበኟቸው ቃል ገብተዋል።

ነጻነት አለሙ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You