አዲስ አበባ፡– የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን ያማከለ የ5 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ የአዲስ አበባ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት ይፋ አደረገ፡፡ አዲስ አበባ ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖራት ባለድርሻ አካላት ለስትራቴጂው ትግበራ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከከተማ አስተዳደሩ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ማሻሻል፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተደራሽ እና ለሁሉም ነዋሪዎች ተመጣጣኝ የመንቀሳቀሻ ዘዴ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡
በዚህም የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ከ 2010 ዓ.ም ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን አውስተው፤ የተሻሻለው አዲሱ ስተራቴጂም ለቀጣይ አምስት ዓመት ሥራ ላይ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስትራቴጂው በተለይም የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እንዲሁም መሰል የመንገድ ደህንነት ማሻሻያዎችን ያማከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አጠቃላይ በትራፊክ ግጭት የሚሞቱና ከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች ቁጥር እ.አ.አ በ2030 በ25 በመቶ የመቀነስ ግብ ያስቀመጠ ነው ብለዋል።
ስትራቴጂውን ይፋ ማድረግ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት አሁን ላይ በከተማ አቀፍ ደረጃ በልዩ ትኩረት እየተገነባ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ታሳቢ ያደረጉ ትግበራዎችን ለማካተትና ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ድንጋጌዎችን፣ እቅዶችንና ማሻሻያዎችን ማዕከል ማድረግ ተገቢ በመሆኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ክበበው ገለጻ፤ ከዚህ በፊት በጥናት የተለዩ ዋና ዋና የአደጋ መንስኤ የሆነ በተለይም ጠጥቶ በፍጥነት ማሽከርከር ሲሠራ የቆየው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ሌሎች አዳዲስ የአደጋ መንስኤዎች ላይም ልዩ ትኩረት በመስጠት በሰፊው የሚሠራ ይሆናል፡፡
በተሻሻለው ስትራቴጂም በትክክለኛ መረጃ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተደገፉ የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ሥራዎችም ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም አሽከርካሪውም ሆነ እግረኛው የመንገድ አጠቃቀም ላይ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ በግንዛቤ ማስጨበጫ የተደገፈ ሁሉን አቀፍ የደንብ ማስከበር ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን የሚመጥኑ መሰረተ ልማቶችን እየዘረጋ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ይረዳው ዘንድ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ምቹና የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረካ እንዲሆን ዘረፈ ብዙ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። ለዚህ አንዱ ማሳያ የኮሪደር ልማቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት 48 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ መዘርጋቱን ተናግረዋል።
መንገዶቹ ለትራንስፖርት ምቹ፣ ዘመናዊና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አቅርቦቱን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል። የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ የበርካታ ዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ እንዲሁም ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት የሚዳርግ መሆኑን ጠቅሰዋል። አዲስ አበባ ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖራት ባለድርሻ አካላት ለስትራቴጂው ትግበራ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች ዘርፈ-ብዙ በመሆናቸው ግጭቱን ለመከላከልም ሆነ ከአደጋ በኋላ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በተለያየ መስክ ኃላፊነት ያላቸው ተቋማትን ማሳተፍ እና በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል ያሉት አቶ ክበበው፤ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ እርምጃ መውሰድ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም