ወይዘሮ አየሁ ደመቀ ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጉዳይ መከታተያና ማስተባበሪያ ስርጸት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ጠንካራና ብርቱ ሴት መሆናቸውን ንግግራቸው ይናገራል፡፡ በአይነ ስውርነታቸው በኑሮና ሕይወታቸው በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል፡፡ በየአጋጣሚው ለሚደርሱባቸው ችግሮች ግን በዋዛ እጅ ሰጥተው አያውቁም፡፡ ሁሌም ቢሆን ‹‹ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ማንነቱን መቀበልና ለቀጣይ ሕይወቱ መሥራት አለበት›› ብለው ያምናሉ፡፡
ወ/ሮ አየሁ በእችላለሁ መንፈስ ነገሮችን ወደፊት መመልከት የተሻለ እድልን እንደሚያጎናጽፍ እርግጠኛ ናቸው፡፡ በእሳቸው ሕይወት ከትናንትና ይልቅ ዛሬ የተሻለ የመሆኑ እውነት ይህ አይነቱ ምስጢር ነው፡፡ ጠንክረው በመማራቸው፤ የተለያዩ ልምዶችን በመቅሰማቸው የአመራርነት ቦታን እንዲቆናጠጡ አስችሏቸዋልና፡፡ እሳቸው ባሉበት ዘርፍ ጥሩ መሪ ሆነው ለዚህ ክብር የበቁት ከምንም ተነስተው አይደለም፡፡ ለፈተና እጅ አለመስጠታቸውና አለመሸነፋቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጥሩ ተሞክሯቸው ለሌሎች እንዲተርፉ አድርጓቸዋል፡፡ ልምዶቻቸውን እንዲያጋሩ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል፡፡
የወይዘሮዋ መርህ ሁሌም በአንድ እውነታ የታሰረ ነው፡፡ ‹‹እችላለሁና ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ እንጂ አልወድቅም›› የሚል ፡፡ ሌሎችም በዚህ መንገድ ቢጓዙ አትራፊ እንደሚሆኑ ምክራቸው ነው፡፡ በተለይ አካል ጉዳተኞች ካለባቸው የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ጫና አንጻር ራሳቸውን ወይም ማንነታቸውን ለመቀበል አዳጋች ነውና ማንም እንዲረዳቸው ከመጠበቅ ይልቅ ብዙ መልፋት እንደሚጠበቅባቸው ያምናሉ፡፡ ራሳቸውን በእውቀት ማጎልበት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነም ያስባሉ፡፡
በእሳቸው ዕምነት አካል ጉዳተኝነት ተቆጥረው በተቀመጡ ሰዎች ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከር አይደለም፡፡ በየጊዜው አዲስ ቁጥርን የሚያክል እንጂ፡፡ ዛሬን አካል ጉዳት የሌለበት ሰው ነገ ላይ ምን እንደሚገጥመው አያውቅም፡፡ ስለአካል ጉዳተኝነት ሁሉም ሰው ቀድሞ ማሰብ ያለበት ራሱን በእነርሱ ጫማ ውስጥ አስገብቶ ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነትን ልንከላከለው እንጂ ልናስቀረው እንደማንችልም አምኖ ለመፍትሄው መሥራት ግድ ይላል፡፡ ወይዘሮ አየሁ ይህ አይነቱ ጥረት ዛሬ ላይ ያለውን አካል ጉዳተኛ ብቻ ሳይሆን ነገ የሚፈጠረውንም ለመቀነስ እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡ ሰዎችም በዚህ ልክ ቢሠሩ ምኞታቸው ነው፡፡
አካል ጉዳተኞችን ወደ አመራርነት ማምጣት ዜጎችን በእውቀት ማበልጸግ ነው፡፡ ለሀገራቸው በጎነትን የሚፈጥሩ ዜጎችን ማበራከት፣ ከተሞክሯቸው የሚያስተምሩና ለአካል ጉዳቶች የሚሟገቱ ዜጎችን ጭምር መፍጠር ነው። ከምንም በላይ አካል ጉዳተኛ መሆን ከማንኛውም ሥራ የማያግድ መሆኑን አምኖ እድሉን መስጠት ያስፈልጋል። ይህ እውነት በወይዘሮ አየሁ፤ ማንነት ውስጥ በጉል የሰረጸ ነው፡፡ በርካታ የሥራ ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን ሊያካትቱ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ቢሳተፉባቸው ውጤታማ የሚሆኑባቸው ተግባራት ብዙ መሆናቸውን ያውቃሉና ፡፡ በዚህ ዘመኑ በዘመነበት ወቅት አይነስውር ስለሆነ፤ በዊልቸር ስለሚሄድና መስማት ስለማይችል አመራር ለመሆን ብቁ አይደለም የሚል አስተሳሰብ መቀየር እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡ “ አመራርነት እውቀትና ጥበብ እንጂ ዓይን አልያም እግርና ጆሮን አይጠይቅም፡፡ እውቀት ካለውና ለቦታው በሚመጥን መልኩ ከሠለጠነ ቦታው ለሚመለከተው አካል ሁሉ ይገባዋል ባይ ናቸው፡፡
ወይዘሮ አየሁ የአካል ጉዳተኞች የሠራተኝነትና የአመራርነት ምደባ ጉዳይ ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ከአመራርነት ውጪ ስለሆነው የሠራተኛ ቅጥር ጉዳይም ማንሳት እንደሚያስፈልግ ይረዳሉ፡፡ ከአካል ጉዳተኝነት ውስጥ የሚመደበው የአዕምሮ እድገት ውስንነት በምንም መልኩ እየተነሳ አለመሆኑ ደግሞ ሥጋታቸውን አይሸሸጉም፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደ አንድ ዜጋ የመቀጠር መብታቸውን ተነፍገዋልና ወደፊት አሠራሩ ቢሻሻል ይወዳሉ፡፡
እነዚህ ዜጎች እንደ ሀገር ምንም የሚሠሩ አይደሉም ተብለው የተፈረጁ ናቸው፡፡ ይህ እውነታም በሥራ ቅጥር ላይ እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል፡፡ ለእነርሱ ሲባል የተለዩ የሥራ ዘርፎችም አልተፈጠሩም፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎቹ ችግራቸውን ለይተው በእውቀታቸው እንዳይሠሩ ገድቧቸዋል፤ ከችግራቸውም እንዳይወጡና ከማህበረሰቡ እንዲገለሉም ሆነዋል፡፡ በውጪው ዓለም እንዲህ አይነቱ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች በተለየ ትኩረት እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ክፍት የሥራ ቦታ ጭምር ተቀምጦላቸዋል። ማናቸውም በዚህ ዘርፍ መሠማራት እንዲችሉ፣ በሕግ ተደግፎም እድሉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ለአብነት የመላላክ ሥራና የመለጣጠፍ ሙያዎች የእነርሱ የሥራ ድርሻዎች ናቸው፡፡ ለእኛ ሀገርም እንዲህ አይነት እድሎች መመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዜጎችን ለተሻለ አማራጭ እዲነሳሱ እድሉን የመፍጠር አስፈላጊነቱን አመላክተዋል፡፡
ወይዘሮዋ እንደሚሉት በአካል ጉዳት ውስጥ ያሉ ወገኖች ዝም ብለው ይቀመጡ ማለት አይደለም፡፡ በአመራርም ሆነ በሠራተኝነት ተቀጥሮ ለመሥራት ራሳቸውን በእውቀት፤ በሥራ ትጋትና በተለያዩ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ማብቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአመራርነት ቦታ በዕድል የሚታደሉት አይደለምና ለውድድር የሚያበቃቸው አቅም ላይ መቀመጥ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ለእነርሱ ፈተናው ቀላል እንዳልሆነ በማመን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ወደ ፊት መራመድን ከምንም በላይ መልመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ቦታው አይገባችሁም የሚል አካል ሲመጣ አካሄዱን ተከትለው መከራከር ይችላሉ፡፡ አሸናፊነታቸውም በማሳያዎች ይረጋገጣል ይላሉ፡፡
የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና ማጎልበት በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የጠቆሙት በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ ተሐድሶ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሐሙድ ከድር በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስና የሰው ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ያነሳሉ፡፡ በእውቀት የተመራ ሁሉን አካታች የሆነ ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ያግዛል፡፡ በተለይም በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ወሳኝ የሆኑ አካል ጉዳተኛ አመራሮችን ለመፍጠር ይረዳልም ይላሉ፡፡
እንደ መንግሥት ፖሊሲ የመቅረጽ፣ የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይሁን እንጂ ሥራው በአንድ አካል የሚከናወን አይደለምና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ከቻለ አካል ጉዳተኞችን ለመሪነት ለማብቃት የሚያግደን ነገር አይኖርም ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
አዎ! ዛሬ ጤነኛና ሙሉ አካል ሊኖረን ይችላል። ነገር ግን ማንም ሰው የወደፊቱን ሊያውቅ አይችልም፡፡ ነገ አካል ጉዳተኛ እንደማይሆን ምንም ዋስትና የለውም። ምክንያቱም አካል ጉዳተኛነት በማንኛውም ሁኔታ፣ ጊዜና ሥፍራ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ከጽንሰት እስከ ሕልፈት ሊከሰት ይችላልና፡፡ በአንድ የሕይወት አጋጣሚ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ተገቢውን ቦታና ክብር ሳያገኙ የበይ ተመልካች ሊሆኑ አይገባውምና ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል፡፡ የተዛባውን አመለካከት በማረቅ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋልና ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም