በባከነች ክፍለ ጊዜ

በዩኒቨርሲቲው የስነ ጥበባት ክፍል መምህር የሆነው ዶክተር ጢሞቲዎስ፣ ከሰማይ ጠቀስ ቁመቱ የተነሳ ተማሪዎቹ ሁሉ “ጢሞ ሰንደቁ” እያሉ ነው የሚጠሩት። በግቢው ውስጥ ሁለት ለየት ያሉ ነገሮች አሉት፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው ነገር የዓመቱ የመጀመሪያው የትምህርት ቀን፣ የመጀመሪያዋ ክፍለጊዜ ነው፡፡

ወደ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች በገባ የመጀመሪያው ቀንና ክፍለጊዜ፣ የመጀመሪያ ሥራውና ንግግሩ “ተማሪዎች! ከአሁን ሰዓት ጀምሮ የሕይወትም፣ የጥበብም ጉዞ ልንጀምር ስለሆነ፤ እባካችሁን! ጥበብ ሳትጠራችሁ፣ ድንኳን ሰበራ የመጣችሁ ተማሪዎች ካላችሁ ሳይረፍድ መክሊታችሁን ፈልጉ፡፡ አሊያ ግን እናንተን ወደሚመስለው የትምህርት ክፍል አቅኑ፡፡

ስለተማራችሁ ብቻ ጥበብን በእጄ አስገባታለሁ ብላችሁ እንዳታስቡ!…” ሲል ያልጠበቁትን ድንገተኛ መአት ያወርድባቸዋል፡፡ ታዲያ ተማሪው ሁሉ እርስ በርሱ እየተፋጠጠ “እኔን ግን ጠርታኝ ይሆን? ሰምተሃል? ሰምተሻል?” እየተባባለ ከማይተዋወቀው ጋር በዓይን የሚጠያየቅ ይመስላል፡፡ በዚህ አድራጎቱ ደንግጠው የሚወጡለትም፣ ደርቀው የሙጢኝ የሚሉም በየዓመቱ ያጋጥሙታል፡፡

ሁለተኛው መለያው የሆነችው ደግሞ “የባከነችው ክፍለጊዜ” ናት፡፡ ራሱ ጢሞቲዎስም እንዲያ ሲሉ ከቁብ ባይቆጥረውም፣ እርሱ ግን “መንገድ ጥርጊያ” ይላታል። መቀጸል የሕይወት መክሊቱ ለሆነው ተማሪ ግን ይህ በቂ አይደለምና “የተሀድሶ ገዳም” ሲል ይጠራታል፡፡ በሁለገብነት የተገነባው ጢሞቲዎስ በትምህርት ክፍሉ ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አሉ ከሚባሉ ጎበዝ መምህራንም መካከል ነው፡፡

በዋናነትም በስነ ጽሁፍ እና ሙዚቃ፣ በሁለቱ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ያስተምራል፡፡ ጉብዝናውን ማናቸውም ባይጠራጠሩም በተለይ የቋንቋና ስነ ጽሁፍ ክፍል ኃላፊው ስለምትባክነው ክፍለጊዜ ይወቅሱታል። ስውር ሽርካቸው በሆነው በአንደኛው የተማሪ ወኪል በተጠነሰሰ ድፍድፍና የወሬ ጠላ ተሳክረው፣ ተማሪ አሳምጸሃል በሚል ውስጥ ውስጡን ብዙ ተዳርሰዋል፡፡

ይሁንና ጢሞቲዎስ እንደሆን ለምንም ግድ ብሎት አያውቅም፡፡ ማንም፣ ምንም ቢል ድንገት ነሸጥ ያደረገው ዕለት ሕገወጧን፣ የባከነች ክፍለ ጊዜን መቀስቀሱ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ጊዜማ የቀበሌ ስብሰባ እየመራ አጀንዳው ላይ ግጥም እንደሚጽፈው የጥበብ ዛር የሰፈነበት ሊቀመንበር ያደርገዋል፡፡ ለማካካሻ ትምህርት (ሜካፕ) ጠርቶ እንኳን ድንገት የጥበብ ውቃቢው ይነሳል፡፡ ለማስተማር የተዘጋጀውን ርዕስ ትቶ፣ ሌላ ነገር ሲቀበጣጥር ሰዓቱን ጨርሶ ይወጣል፡፡ “ምን ላርግ… በጥበብ የመሥራት ብቻ ሳይሆን ስለ ጥበብ የማውራትም ልክፍት አላት” ይላል፤ ከጨርሰ በኋላ ማባከኑን ሲያውቅ። ለምን እንደሚያባክናት የሚረዱት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ በተማሪዎቹ የፈተና ወረቀት፣ በየገጾቹ አናት ላይ ሁሌም “ጥበብ ወርቅ ናት ሙዳይዋን ትሻለች” የሚል ጥቅስ ያሰፍርበታል፡፡ ቢገባቸውም ባይገባቸውም ሁሉም ያነቡታል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን፣ ለአንደኛው የሚባክን ክፍለጊዜ እንደልማዱ ሰከም! ሰከም! እያለ ወደ ሁለተኛ ዓመት የስነ ጽሁፍ ተማሪዎች ገባ፡፡ በያዘው ሠሌዳ ማጥፊያ፣ ነጩን ሠሌዳ ካሟሸው በኋላ መጻፊያውን ከኪሱ አውጥቶ ከሠሌዳው አናት ላይ “Chapter 5, The History of Ethiopian literature” ብሎ ጻፈና ድንገት ምን ትዝ ብሎት እንደሆን አቀርቅሮ፣ በለሆሳስ የምጸት ሳቅ እየሳቀ “ተአምር ነው!…የኢትዮጵያን የስነ ጽሁፍ ታሪክ እኮ በእንግሊዝኛ? እንዴት ያለነው ባዱላ ወጥቶናል…” እያለ ሲልጎመጎም መልሶ አጠፋውና የሆነ ማለት የፈለገው ነገር እንዳለ ወደ ተማሪዎቹ ዞሮ ቆመ፡፡

ዝም ብሎ እንደቆመ ጥቂት ቆየና አሁንም ሌላ ነገር ትዝ እንዳለው “እስቲ እናባክናት” እያለ “መንገድ ጥርጊያ. ምዕራፍ ሁለት ክፍል 7” ሲል ጻፈ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ በዓመቱ የባከነች ሰባተኛዋ ክፍለጊዜ፣ ሰባተኛዋ ሕገወጥ አርዕስት መሆኗ ነው፡፡ ቀጥሎም ከስር “የጥበባት ማጠንጠኛ” ብሎ ደገመ፡፡

ፊቱን ወደተማሪዎቹ መልሶ “ሁላችሁም ብዕርና ወረቀት አዘጋጁ፡፡ በመርጣችሁት ርዕስም ባለአራት ስንኞች ግጥም ጻፉ፡፡ አሥር ደቂቃ አላችሁ” ብሎ እየተንጎራደደ በበሩ ወጣ፡፡ ከአሥር ደቂቃዎች በኋላ ሲንጎራደድ ተመልሶ ገባ፡፡ “እሺ…አሁን ደግሞ ሁላችንም በረድፍ እየተነሳን የጻፍነውን እናነባለን” በማለት ከፊት ወንበር ለተቀመጠው ተማሪ በእጁ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የመጀመሪያው ተማሪ ብድግ ብሎ በፈገግታ “ርዕሴ ከፍቅር ጋር ፍቅር ይሰኛል፡፡ ይህን ያልኩበትና የጻፍኩበት…” ከማለቱ “በቃህ! በቃህ! ማቲያስ ደጀኑ ርዕሱ በቂ ነው ግጥም ማብራሪያ አያስፈልገውም፡፡ ያውም ለአራት ስንኝ…” አለው መምህር ጢሞቲዎስ፡፡ ሁለተኛው ተማሪም “አጃኢቡ ፍቅርሽ” ሲል የቋጠራቸውን አራቱን ስንኞቹን አከታትሎና አስጨብጭቦ ተቀመጠ፡፡ “ስማኝማ” ያለችው ሦስተኛዋ ተማሪም ሰልሳው አበቃች። “ልተንፍስሽ፣ ትዝታዋ፣ የመውደድ አባዜ…” አራት…አምስት እያለ አርባውም ተማሪ አነበነበ፡፡ “የእውነትም አባዜ…እንጂማ ምን…” አለ ጢሞቲዎስ ለራሱ፡፡ ተማሪው ሁሉ ግጥሙን እንጂ መምህራቸው ምን ፈልጎ ስለምን እንዳጻፋቸው አልገባቸውም ነበር፡፡

“ዳዊታችሁን ደገማችሁና የሁላችሁንም ሰማን” ብሎ በረዥሙ ተነፈሰና “ምርጫ አሊያም ዳሽ ሙላ ቢሆን ኖሮ ተኮራርጃችኋል እል ነበር፡፡ ግን ይሄ ራሷ ጥበብም የተለከፈችበት ዛር ነውና የአዕምሮ ንቅለ ተከላ ያሻዋል፡፡ ይገርማችኋል! ትናንት እንደናንተው ሙዚቃ ክፍል ገብቼ ከምታውቁት ብል ከምትወዱት ሙዚቃ፣ ከሙከራችሁ ብል…ወይ ፍንክች! ከአንዲት የፍቅር ዛር በስተቀር ጠብ የምትል ጠፋች…” ብሎ ለአፍታ ዝም አለ፡፡ ከወትሮው በተለየ ተማሪው ሁሉ ግር ብሎት ዓይን ላይን ተቧዘዘ፡፡

የተማሪዎቹን ብዥታ ያጤነው መምህር ጢሞቲዎስ ይባስ በግራ መጋባት ሊያጦዛቸው ፈለገ፡፡ “ከዕለት በአንዱ ቀን ከአንድ ፈላስፋ ቢጤ ወዳጄ ጋር ቁጭ ብለን ስንጨዋወት… በጥበብ መቅደስ ውስጥ የምናስቀድስም፣ የምንቀድስም የሁላችንም ልብ በአምልኮተ ፍቅር ተጋርዷል” አለኝ፡፡ እኔም እንዴት? ስል ጠየቅኩት፡፡ “ጥበብ ያለ ፍቅር ጣኦት፣ ያለ ፍቅር አድባርና ውቃቤ ሕልውና የሌላት እስክትመስለን” አለ፡፡ እንደገና መልሼ ጠየቅኩት፡፡ “ምክንያቱም ሁላችንም ጋር ያለችው ጥበብ ያለ ጾታዊ ፍቅር ውጪ ሌላ መልክ ያላት አይመስለንም፡፡ ተሰጥኦ አለኝ የሚለው ሁሉ የሚያንዶቀዱቀው ስለ ፍቅር ነው፡፡ አድማጭ፣ ሰሚና ተመልካቹም ሲያንቃርር ደስ የሚለው ስለፍቅር ነው፡፡

የብዕረኛው ብዕር፣ የድምጻዊውም ድምጽ ካለፍቅር አይከፈትም፡፡ የወደዳትን እያሞገሰና እያለቃቀሰ አፉን ፈቶ፣ እንዲያው በዚያው ተቋጥሮ አፈር ይለብሳል፡፡ …ብቻ ባናውቀውም አብዛኛዎቻችን በጥበብ አምልኮተ ፍቅር ውስጥ ነን” ነበር ያለኝ፤ እያለ ጥቂት ተንጎራደደ፡፡

“ግጥሙን ጽፋችሁ አንብቡልኝ ያልኩት ሁላችንም እውነታውን እንድንገነዘብ እንጂ የናንተን የግጥም ችሎታ ለመለካት አልነበረም፡፡ ፍቅር ለሰው ልጆች መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች አንደኛው እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ ልብ በሉ እያልኩ ያለሁት ስለጾታዊውና አሁን እናንተ ስለጻፋችሁት ፍቅር ነው፡፡ መልካም ነውና ነገም ዛሬም ደግማችሁ ጻፉት… ነገር ግን እዚሁ አንድ ክፍል ውስጥ ካላችሁ 40 ተማሪዎች መካከል የሠላሳ ሦስታችሁ ያው ስለ አንድ ዓይነት ፍቅር ነበር፡፡

ይህን ቁጥር ይዛችሁ ሽቅብ ወደ ጥበብ ሥራዎች ተራራ ብትወጡ ቁልቁል የምትመለከቱት ይህንኑ ነው፡፡ ፍቅር የደስታ ምንጭ ናትና ጻፏት…ግን የሁላችንም ጥበብ በአንዲት ፍቅር ላይ ብቻ ተቃጥላ ትለቅ ወይ?” ተማሪው ሁሉ ውዝግብግብ ብሎ፤ አንዳንዱ ስለምን እንደጻፈ ደግሞ ደጋግሞ ወረቀቱን መመልከት ጀመረ፡፡

“ጢሞ ሰንደቁ ልቧ ተሰብሯል ማለት ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ነው” አለ፤ አንደኛው ተማሪ ጎኑ ለነበረው እያንሾካሾከ፡፡ “ገና አላገባም እኮ” ሁለተኛው በሽኩሹክታ፡፡ “በቃ ፍቅረኛው ናታ…እኔስ ከፍቅር ጋር ፍቅር እንጂ ስለሴት አልጻፍኩም” ብሎ በኩራት ለጠጥ ሲል “ጉልቻ ቢለዋወጥ….አሉ፤ ደግሞ ያለው ነገር ሳይገባህ አትዘባርቅ!” ብሎት ዞረ፡፡

ጢሞቲዎስ ግን አሁንም ቀጠለና “እዚህ ክፍል ውስጥ ያላችሁ ነገ ላይ ገጣሚ፣ የሙዚቃና ዜማ ደራሲ፣ ሙዚቀኛ…ሁላችሁም ወደ ጥበብ ናችሁ፡፡ ግን በብዛት አሁን በምንመለከተው ዓይነት ሙቀት ውስጥ ገብታችሁ ጥበብ ማለት ፍቅር ነው በማለት ብቻ በፍቅር አጥማቂነት ተወስናችሁ እንዳትኖሩ ነው፡፡ ሙዚቀኛ ብትሆኑ ለአንዲት ሴት፣ ለአንዲት ፍቅር ርዕስ እያገለባበጣችሁ፣ ከ12 የአልበም ሙዚቃዎች አሥሩን ሁሉ መደርደር አያሻችሁም፡፡ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ሌላም ነገር፤ በአንድ ነገር ብቻ አትከበቡ፡፡ የምላችሁም ከሁለት ነገሮች አንጻር ነው…አንደኛው ጥበብ ማለት በአዳዲስ እይታና ፈጠራ እንጂ እንደ ዳዊት ሲደጋግሟት ታላዝናለች፡፡ ብዙዎች የኢትዮጵያ ፊልም ሲሉ የሚሳለቁት ለምን ይመስላችኋል? አንድም በሀ-ፐ ባለው የፍቅር እንቅልፍ ነው፡፡

ምናባችሁን በአንድ ነገር ላይ ከጠነቆላችሁት ስለሌላ ነገር የመፍጠርና የማሰብ አቅማችሁ ይከስማል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ጥበብ ሀገር፣ ባህል፣ በአጠቃላይ ማሕበረሰብ ማለት ናት፡፡ ታዲያ የናንተ ማሕበረሰብ ያለውና ሆድ ያስባሰ የቸገረው ነገር ፍቅር ብቻ ነው? አይደለም!” ሲል ጮኸ ራሱ መለሰውና “የናንተ ማሕበረሰብ በናንተ ጥበብ ሊጠነጠን ይፈልጋል፡፡ አጠንጥኑት፤ ልክ እንደ ካሴት ክር!” እያለ አንድ በአንድ ተመለከታቸው፡፡

ጢሞቲዎስ የእጅ ሰዓቱን መልከት አደረገና እንደገና ሌላ መባከን ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፡፡ ፈገግ አለና “ፈላስፋው ወዳጄ ልክ እንደስሙ ሁሉ አያልቅበት ነው፡፡ እንዲህ አለኝ፤ “ያኔ አራትና አምስተኛ ክፍል ሳለን የምናነበው ግጥም “ሀገሬ” የሚል ርዕስ ያለው ነበር፡፡ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ስንሆን “የሀገር ፍቅር” የሚል ሆነ፡፡ ቀጥሎም “ሀገር ማለት ፍቅር ነው” ብለን ማሰብ ጀመርን፡፡ በኋላም “አይ ፍቅር ማለት ነው ሀገር” አልን፡፡ በስተመጨረሻችን ተቀጣጥለው ለሁለት ሲሄዱ እንደነበሩ የባቡር ክፍሎች፣ የኋላኛው ከፊተኛው ተቆርጦ የተገላቢጦሽ “ፍቅር” የሚለው ባቡር ብቻውን መክነፍ…ወዳጄ እያለኝ የነበረው ስለትናንትናውና ስለዛሬው ትውልድ አካሄድና አመለካከት ነበር፡፡ አሁን ግን በባከነው ደቂቃችን እስቲ ለአምስት ደቂቃ ተወያዩና የምትሉትን ወዲህ በሉኝ ” ብሎ ለራሱ በጀመረላቸው የወዳጁ ወግ በምናብ ሰመጠ፡፡

ይሄም ከዕለታት በአንዱ ቀን የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ ከፕሮፌሰሩ ወዳጁ ጋር ቁጭ ብለው የሆድ ያንጀታቸውን ሲጨዋወቱ ቆይተው፣ ተጋግለው ነበር፡፡ በመሃል በነበረችው የዝምታ ቅጽበት ነበር ከወዳጁ ኪስ የተሸጎጠችውን መጽሐፍ የተመለከታት፡፡ ጢሞቲዎስ እጁን ሰዶ ቢያወጣው “የልጆች ተረት…” የሚል ነበር። አጋጣሚውን በመጠቀም ከዚህ ቀደም ሊያወራው ሲፈልግ የነበረውን ትዝታ አስታውሶ ይመስል የመጽሐፉን ገጾች ገለጥ አድርጎ ማንበብ ያዘ፡፡ “ጎልተኸኝ ጭራሽ ከሕጻናት ተረት ጋር?” አለው ፕሮፌሰሩ፡፡

ጢሞቲዎስ ግን የፍቅር ደብዳቤ ያህል ተመስጦበት ሲያበቃ ግርምትና ቁጭት የተቀላቀለበትን ሳቅ ሳቀና “ይሄ የሕጻናት ተረት ሳይሆን ላንተ ነው” አለው፡፡ “እንዴት?” ሲል ፕሮፌሰሩ በአግራሞት ተመለከተው፡፡ ጢሞቲዎስም “ተረት ተረት!” ሳይል ፕሮፌሰሩም “የመሠረት!” ብሎ ሳይመልስ፣ ከመሃል ገልጦ አንዱን ተረት ጀመረለት፡፡ “…በንግስቲቱ ፍቅር ያበደው ንጉሥ…” ብሎ በመጀመር ጢሞቲዎስ ሙሉ ተረቱን ለወዳጁ አነበበለት፡፡

“ሶ ዋት ኢዝ ሮንግ?” ሲል ፕሮፌሰሩ ይባስ የጢሞቲዎስ ነገር ቂልነት መስሎ ታየው፡፡ “እኔ ያንተን የልጅ አስተዳደግ አውቀዋለሁ ፕሮፌሰር፡፡ ቤት ቁጭ ብለን ቲቪው ላይ የሆነ ነገር ሲመጣ ወደ ክፍልህ ግባ ስትለው ተመልክቻለሁ፡፡ ትዝ ይልህ እንደሆን ያኔ “ቀሽ ገብሩ” የሚለውን ዶክመንተሪ ፊልም ስንመለከት እንኳን ይሄን የጦርነት ትዕይንት ለዕድሜህ አይመጥንም ብለህ እንዳያይ አድርገኸዋል፡፡ ትልቁ ችግር ልጆቻችን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ፍቅርን ማወቃቸው ሳይሆን፤ ያወቁት ፍቅር መልሶ ይተዋወቃቸውና በኃያል ክንዱ ይኮረኩማቸዋል ስትልም ሰምቼሃለሁ፡፡ ግን ዞር አሉ እንጂ አልሸሹም ነው፡፡ እንዲያውም ልንገርህ ያንተ ነው ብለህ ከምትሰጠው ከዚህ የተረት ፍቅር ሊረዳው የማይችለው፣ ቀውጢው የፊልም ውስጥ ፍቅር የተሻለ ነው” አለው፡፡ ፕሮፌሰሩ አሁን ገና የገባው ያህል ሀሳብ ያዘው፡፡

ጢሞቲዎስ ልክ ነበር አብዛኛው የተረት የምንለው መጽሐፍና የሕጻናት ፊልሞች ይዘው የሚገኙት ያለ እድሜ እንዲያውቁት የማንፈልገውንና የምንፈራውን ነገር ነው፡፡ ያለምንም መፍራት ገብቷቸው በትንሹ ከሚለማመዱት ነገር፤ ሳይገባቸው በትልቁ የተመለከቱት ይሻላል። ሀሁ፣ ኤቢሲዲ የምንቆጥረው እኮ ነገ ላይ በእነዚያ ፊደላት የተጻፈውን ዕውቀትና ጥበብ እንድንቀስም ነው፡፡ ፊደላቱን ሳንቆጥር መጽሐፉን ለማንበብ አይቻለንም። እውነቱን ለመናገር ድሮ ድሮ የምናውቃቸው እነ “አያ ጅቦ፣ አፍንጮ…” መሰል ተረቶች የሞኝነት ቢመስሉም፤ የልጆችን ማንነት ከመቅረጽ አንጻር እንዲያ ዓይነቶቹ የተሻሉ ናቸው፡፡ ለሕጻናት የሚሆኑ መጽሐፍትን ለሚጽፉና ፊልሞችን ለሚያዘጋጁ ትልቅ የቤት ሥራ ነው። ከዚህ በተለየ ደግሞ ጥቁር ደም ላላቸው የሐበሻ ሕጻናት በነጭ አምሳል የተሠሩ አሻንጉሊቶችን ስናስታቅፋቸው፣ ለማንነታቸው እየሰጡ የሚያድጉት ምን ዓይነቱን ስሜትና አመለካከት እንደሆነም ማሰብ ነው፡፡

ነገሩን ጢሞቲዎስ በዚያ መልክ ቢያሳልፈውም፤ ከላይ ሆኖ ከታች የሚፈሰውም የሚያሳስበውና የሚያበሰብሰው ነውና፡፡ ከምንም፣ ከማንም በላይ የልጅነት አዕምሮን የሚስበውና የሚቀርጸው ነገር ጥበብ ናት ብሎ ያስባል፡፡ ግን ጥበብን ካወላገድናት እነርሱም መወላገዳቸው እንደማይቀር ያውቀዋል፡፡ በዚህ ሀሳብ በመባከን ላይ ሳለ ነበር የጦፈው የአንደኛው ቡድን ክርክር ወዲህ ያነቃው፡፡ ከብዙ ንትርክ ውስጥ የሚቃወም፣ የሚደግፍ፣ የራሱን እየጨመረ የሚተርክ፣ የሚነታረክ ብዙ ነው፡፡ “መምህር! …” አለ ክፍሉ ውስጥ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል ከመጨረሻው ወንበር የተቀመጠውና ጥያቄ ባቃጨለበት ቁጥር ሁሉ ሽንት የወጠረው ያህል የሚያጣድፈው በተወዛግቦ አወዛጋቢነቱ “ወዝጊ አወዝጊ” ሲሉ የሚጠሩት ተማሪ። “ቆይ ግን መምህር ስለፍቅር መዝፈን፣ የፍቅር ሙዚቃ ማድመጥ፣ ራሱ ፍቅርስ አያስፈለግም ነው የምትለው?”

“እንዴት ልል እችላለሁ? ያለፍቅር መኖርስ ይቻላል እንዴ? ጥበብ ራሷ በተነደፈችበት ፍቅር ውስጥ፣ ጥበብን እስከወደድናት ድረስ አብረን ልንነደፍላት ግድ ነው፡፡ ፍቅር መልካም ነውና መልካሙን ያዙ፡፡ ሥሩ፣ ስሙ፣ ተመልከቱ፣ አሁንም ነገም ደጋግማችሁ፡፡ ግን በፍቅር አጥማቂነት ብቻ የጥበብን ጽድቅ አትሹ፡፡ ማጠንጠኛው እልፍ ነው” እንዳለም በባከነችው ክፍለ ጊዜ ይባስ ላለመባከን ከክፍሉ ወጥቶ ሄደ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You