ኢትዮጵያ የብዙ ስመጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙአቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል።
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም:: በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው::
ከላይ ለተነሳው ሃሳብ ትክክለኛው መስፈርት የሚያሟሉት መሆናቸውን ደግሞ ክቡር አቶ ተሾመ ገብረማርያም መሆናቸውን ታላላቅ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ የቅርብም የሩቅም የሥራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ፤ እንዲሁም ታሪካቸውን ያነበበ ሁሉ የሚረዳው ነው። የክቡር አቶ ተሾመ ገብረማርያም ታሪክ እጅግ ሰፊ እና ትልቅ በመሆኑ በዚህ ተርከን የምንጨርሰው አይደለም። ነገር ግን ታላላቆች የሄዱበት፣ የሠሩት ሥራ፣ ትዕግሥት፣ ሙያ፣ ሀገርን መውደድ እና ለሕግ (እውነት) መቆምን ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት እና አርአያ በመሆኑ ዛሬ ልናነሳቸው ወደድን።
ክቡር አቶ ተሾመ ገብረማርያም ከአባታቸው ከባላምባራስ ገብረ ማርያም ቦካን እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ላቀች አብቹ በአዳማ ከተማ ልዩ ስሙ ሰቀቀሎ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ::
ህፃኑ ተሾመ ከተወለደ ከአምስት ዓመት በኋላ ሀገራችን የኢጣልያ ወረራ ስለገባ የፋሺስቶችን ግፍና ጭቆና ለማምለጥ ወላጆቹ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ አብረው በመንከራተት የህፃንነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል:: የፋሽስት ጦር ድል ተመትቶ በኢትዮጵያ ነፃነት ሲመለስ አባታቸው የሲዳሞ ገዢ ሆነው በተሾሙበት በራስ አደፍርሰው ሥር በመመደባቸው ህፃን ተሾመም ከ1935ዓ.ም ጀምሮ ሲዳማ ይርጋ ዓለም በምትባለው ቦታ መኖር ጀመረ::
በ1937ዓ.ም ቀ.ኃ.ሥ የሲዳሞን ጠቅላይ ግዛት በሚጎበኙበት ወቅት በአቶ ቦጋለ ዋለሉ አቅራቢነት 12 ታዳጊዎች በግርማዊ ጃንሆይ ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ሲወሰን አቶ ተሾመም ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ነበረ:: በዚሁ መሠረት ዕድለኞቹ ተመራጮች በቀጥታ ቤተ መንግሥት ተወስደው ለተወሰኑ ቀናት እዚያው ከተቀመጡ በኋላ ለሁሉም አልጋ፣ ፍራሽ እና አልባሳት ተሟልቶላቸው በአዳሪነት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ወደ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተልከዋል::
ወጣቱ ተሾመ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ትምህርቱን በትጋት ከመከታተሉም በተጨማሪ በስፖርት ጭምር ታዋቂነት ካተረፉት ከነአቶ ንጉሤ ፍትህ አወቅ እና ፕሮፌሰር መስፍን ከመሳሰሉት ግንባር ቀደም ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበረ:: ወጣቱ ተሾመ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን በተከፈተው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከገቡት የመጀመሪያ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን የባችለር ዲግሪውን በአስተዳደር ዘርፍ በማዕረግ ተቀብሏል::
ጠላት ሀገራችንን ወሮ ኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ላይ ታችትል ነበር:: ያኔም ተፈሪ መኮንን ፤ ከጄኔራል ዊንጌት፤ ከዳግማዊ ምኒልክ ከሌሎችም የተውጣጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዲገቡ ተደርጎ ነበር:: አብዛኛዎቹ ከተፈሪ መኮንን ነበሩ::
ከተፈሪ መኮንን በጊዜው ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ቁጥር 72 ይጠጋ ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አቶ ተሾመ በተመረቁበት ጊዜ 13 ተማሪዎችን አስመርቆ ነበር:: አቶ ተሾመን ጨምሮ እነዚህ 13 ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመመረቅ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ተማሪዎቹ የተመረቁት በ1946 ነበር::
ከመጀመሪያዎቹ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ፤ ዶክተር መንገሻ ገብረህይወት፤ ዶክተር ሀብተማሪያም ማርቆስ፤ ጌታቸው መድሃኔ፤ መሐመድ አብዱራህማን ፤ መሐመድ ሃሚድ ፤ ጌታቸው ክብረት፤ በላቸው አስራት እና ራሳቸው አቶ ተሾመ ገብረማሪያም ነበሩ::
በመቀጠል ለሁለተኛ ዲግሪ ወደ ካናዳ በመሄድ በታዋቂው የመጊል ዩኒቨርሲቲ ኤም ሲ ኤል ማለትም ማስተርስ በኮምፓራቲቭ ሎው ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው ወደ እናት ሀገራቸው ከተመለሱት የመጀመሪያዎቹ ወጣት ኢትዮጵያውያን መካከል አቶ ተሾመ አንዱ ነበር::
አቶ ተሾመ ትምህርታቸውን በ1950 አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ፦
- ከ1950-1952 በመገናኛ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የሕግ አማካሪነት፤
- በ1953 በሥራ ሚኒስቴር በዋና ዳይሬክቶሬትነት፤
- 1954 በልማት ባንክ ዋና የሕግ አማካሪነት፤
- በ1955 የአፍሪካ አንድነት ማኅበር ቻርተር አርቃቂ ኮሚቴ አባልነት፤
- በ1957-1959 የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግነት፤
- በ1959- 1966 በማዕድን ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታነት::
በእነዚህ ዘመናት ክቡር አቶ ተሾመ በበርካታ የሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ሀገራችንን በመወከል የጥናት ጽሑፎችን አቅርበዋል፤ በሳል ንግግሮችን አድርገዋል፤ ሀገራቸውን ወክለው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በገላጋይ ሽማግሌዎች ፊት በቀረበ ዓለም አቀፍ ክርክር ላይ ገጥመው የረቱበት አጋጣሚ አለ::
በተጨማሪም ታዋቂው የፍትሐ ብሔር ሕጋችን አርቃቂ የነበረው ፕሮፌሰር ሬኔ ዳቪድ በተሳተፈበት ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ሀገራቸውን ወክለው ተሳትፈዋል::
በተለይ የሥራ ሚኒስቴር በነበረበት ወቅት የአየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የወቅቱ የሥራ ሚኒስቴር ክቡር ደጃዝማች መንገሻ ስዩም (ልዑል ራስ) አየር መንገዱን ለማሳደግ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ተገቢውን የሕግ ምክር በመስጠት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል::
በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ ከባለ ሞተር አውሮፕላን ወደ ጀት እንዲሸጋገር በቦርዱ ሰብሳቢ የተጀመረው ውጥን እውን በማድረግ የመጀመሪያውን 707 ቦይንግ ከክቡር ሚንስትሩ ጋር አሜሪካን ሀገር በመሄድ ተረክበዋል:: ክቡር አቶ ተሾመ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጠቅላይ አቃቤ ሕግም ሆነው ለ3 ዓመታት ያህል አገልግለዋል::
የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመሥረቻ ቻርተርን ካረቀቁት አንዱ ነበሩ። የአፍሪካ አንድነት ድርጀት ሲመሠረት አቶ ተሾመ ከፍተኛ የሕግ ድጋፍ አድርገዋል። በማዕድን ሚኒስቴር በነበሩ ጊዜም ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ትልቁ የተፈጥሮ ጋዝ የተገኘውም እርሳቸው በግንባር ቀደምትነት ባደረጉት ድርድር ነው። በዚህ ዓይነት ሥራቸውን ሲሠሩ እያሉ በ1966 አብዮት ሲከሰት እሳቸውም የቀድሞው ሥርዓት ባለሥልጣን በመባል ከ1967-1976ዓ.ም ድረስ ለ9 ዓመት በእሥራት ቆይተዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዚዳንት አቶ ወንድማገኘሁ ገ/ሥላሴ የሀገሪቱን የማዕድን አዋጅ የተሟላ ለማድረግ አቶ ተሾመ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ ይናገራሉ። «ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ የፕላቲኒየም፤ ወርቅ እና ማዕድናት ፍለጋን የተመለከቱ የተለያዩ የተቆራረጡ ሕግጋት ነበሩ።» የሚሉት አቶ ወንድምአገኘሁ አቶ ተሾመ የማዕድን ሚኒስቴርን ከተቀላቀሉ በኋላ የተሟላ አዋጅ ገቢራዊ እንዲሆን አድርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል በዕደማርያም መኮንን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመሥረቻ ቻርተር ዝግጅት ላይ አቶ ተሾመ በጊዜው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ እና አቶ ክፍሌ ወዳጆን ከመሳሰሉ ባለሙያዎች ጋር ላቅ ያለ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
ልዑል በዕደማርያም በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ የአስተዳደር ሥርዓት ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩት አቶ ተሾመ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት ጋር ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በእስር ላይ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ። በንጉሳዊው ሥርዓተ-መንግሥት ውስጥ በባለሥልጣንነት በማገልገላቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት አቶ ተሾመ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው በነፃ እንዲለቀቁ ቢወሰንላቸውም ሳይፈቱ መቅረታቸውን ልዑል በዕደማርያም መኮንን ተናግረዋል።
አቶ ተሾመ ገብረማርያም በስማቸው ባቋቋሙት የጥብቅና ተቋም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ከእስር በተፈቱ ማግሥት በፖለቲካ እና ሕግ አማካሪነት የተሰጣቸውን ሥራ ጥለው በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት አቶ ተሾመ የአፍሪካ ሀገራት የማዕድን ዘርፍን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያማክሩ ነበር። ልዑል በዕደማርያም፤ አቶ ተሾመን «ስኬታማ» ሲሉ ይገልጿቸዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዚዳንት አቶ ወንድምአገኘሁ ገ/ስላሴ አቶ ተሾመ በተደጋጋሚ ለተሻሻለው የኢትዮጵያ የማዕድን አዋጅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል ሲሉ ይናገራሉ። የውጭ የማዕድን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ይጋብዙ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ወንድማአገኘሁ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር መጠናከር ድጋፍ ያደርጋሉ ይሏቸዋል።
አቶ ተሾመ ገብረማርያም የራሳቸውን የጥብቅና ፈቃድ በማውጣት የራሳቸውን የጥብቅና ቢሮ ከፍተው ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ደንበኞች የሕግ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። አቶ ተሾመ ገብረማርያም ዓለም አቀፍ የጠበቆች ማህበር(IBA)፣ ALN የተባለ የ11 ሀገሮችን ጠበቆች የሚያስተባብር ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር እና ከሌሎች በርካታ የውጭ የሙያ ማህበራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቢሮአቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነ ማድረግ ችለዋል።
በሥራ ዓለም ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቁት አቶ ተሾመ ገብረማሪያም ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አምሳለ መኮንን ፤ ወሰንየለሽ ተሾመን ወልደዋል:: አቶ ተሾመ በታኅሣሥ 2009 በናሚቢያ ለሥራ ባቀኑበት ሰዓት ድንገት በመታመማቸው ሐሙስ ሌሊት ታኅሣሥ 6 ፤ 2009 ዓ.ም ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል:: የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2009 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንበረ ጸባኦት ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የሕግ ምሁርና የኢትዮጵያ ባለውለታ አቶ ተሾመ ገብረማርያምን ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም