ከሁለት ሳምንታት በፊት (ታኅሳስ 2 ቀን) ‹‹ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ለምን እንፈራለን?›› በሚል ርዕስ በሕክምና ተቋሞቻችን ውስጥ ያለውን አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ፣ ይባስ ብሎም ለሌላ ህመም የሚዳርግ ወከባ መኖሩን በትዝብት ዓምዳችን አይተናል::በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለውን የሐኪሞች ውለታ ራሱን በቻለ ክፍል እንደምናየው በገለጽነው መሠረት እነሆ ዛሬ ደግሞ የሐኪሞችን ውለታ እናያለን::
የሰው ልጅ ከፈጣሪ ቀጥሎ የሚተማመነው በሐኪም ይመስለኛል፤ ከፈጣሪ ቀጥሎ ሕይወቱን አደራ የሚሰጠው ለሐኪም ነው::ፈጣሪ የፈጠረው ፍጡር መላ ገመናውን የሚያሳየው ለሐኪም ነው::ከሐኪም የሚደበቅ ነገር የለም::
የሐኪሞችን የሕይወት ውለታ እንዳስታውስ የሚያደርጉኝ ወደ ሆስፒታል ጎራ የምልባቸው አጋጣሚዎች ናቸው::ከወር በፊት ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ በመዋል እና በማደር ሰፋ ባለ ሁኔታ ለማስተዋል ችያለሁ::ምንም እንኳን የሙያቸው ባህሪ ግልጽ እና ተገማች ቢሆንም፤ ማየት ደግሞ የበለጠ በሁኔታዎች ለመገረም ያስገድዳል፡፡
የሕክምና ሥራ እንጀራ ነው ከማለት ይልቅ በጎ አድራጎት ወይም ለሰዎች ውለታ የመዋል የህሊና ሥራ ነው ማለት ይሻላል::ምክንያቱም እንደኔ አይነቱ ሰነፍ ‹‹እንዲህ ሆኜ ከፍተኛ ደሞዝ ከማገኝ ለምን የቀን ሥራ እየሠራሁ አልኖርም!›› ሊል ይችላል::ሥራው የሙያ ሥራ ብቻ ሳይሆን የህሊና፣ የትዕግስት፣ የአስተዋይነትና የምሉዕነት ሥራ ነው::ከሕክምና ሙያ የተረዳሁት ነገር፤ የተዋጣለት ስፔሻሊስት ሐኪም የሚያደርገውን ቴክኒካል ሙያ መቻል ብቻውን በቂ አለመሆኑን ነው::ሐኪሞች የሞት አፋፍ የደረሰን ሰው ከማዳናቸው በላይ የሚገርመኝ የሚጠቀሙት አዕምሯዊ ጥበብ ነው::አዕምሯዊ ጥበብ ደግሞ የሰውነት ከፍታ መለያ ነው፡፡
የህክምና ሙያን ከሌላው ሙያ ጋር አነፃፀሩት::የሚያስተናግዱት ታማሚ ሰው ነው::የታመመ ሰው ደግሞ የሚኖሩትን ባህሪያት መገመት ቀላል ነው::በራሳችንም፣ በዙሪያችን ባሉ ሰዎችም የምናየው ነገር ነው::እንደ ህመሙ ሁኔታ ቢለያይም የታመመ ሰው ነጭናጫ እና ቁጡ መሆኑ የሚጠበቅ ነው::በትንሽ ትልቁ ሆድ የሚብሰው እና ተስፋ ቆራጭ የሚሆን ያጋጥማል::እንደ ሌላው አገልግሎት በመደበኛ ኮምኒኬሽን ሳይሆን በልዩ ጥንቃቄ እና ታጋሽነት የሚያዝ ነው::ሐኪሞች ይሄን ነው በጥበብ የሚወጡት፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሲሆን ደግሞ አስቡት! ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም የሚሄዱት ህመሙ አደገኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው::ለሕይወት አስጊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው::በዚያ ላይ ደግሞ የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ሳይቀር ባህላዊ መድኃኒቶችን እና ሌሎች ልማዳዊ ነገሮችን ይጠቀማል::ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች አልፎ ህመሙ አደገኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው ወደ ሕክምና ተቋም የሚሄደው::በዚህን ጊዜ ለሐኪሞች ሌላ ፈተና ይሆናል ማለት ነው::
አንደኛው ችግር፤ ህመሙ ገና ሳይጠነክር አለመሄዱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ችግር ደግሞ በልማዳዊ መንገድ የተሞከረው መድኃኒት ሌላ ጣጣ ይዞ ሊመጣ ይችላል::ሁለቱም ችግሮች ሕክምናውን አስቸጋሪ ሊያደርጉት ይችላሉ::በልማዳዊ መንገድ የተሞከረው መድኃኒት ምናልባትም የጀመሪያውን ህመም ወደ ሌላ ደረጃ ሊወስደው ይችላል::
እርግጥ ነው የባህል መድኃኒቶች የዘመናዊው መድኃኒት መቀመሚያ ግብዓቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ፈውሰው የሚያውቁም ይኖራሉ::ችግሩ ግን አስተማማኝ አይደለም፤ የሚዘጋጀው በልማዳዊ መንገድ ነው::ብዙ ቤተ ሙከራ አልፎ የተረጋገጠ አይደለም::
በነገራችን ላይ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ አንድ መድኃኒት ሙሉ ሂደቱን ጨርሶ፣ በዓለም ጤና ድርጅት ተረጋግጦ፣ በመድኃኒት መልክ መሰጠት እስከሚጀምር ቢያንስ እስከ 7 ዓመት ሊወስድ ይችላል::ለእኛ ሩቅ በሆነ በብዙ አይነት መንገድ ሲጠና እና ሲረጋገጥ ነው የሚቆየው::ዋናው መድኃኒት በዚህ ሁኔታ የሚዘጋጅ ከሆነ፤ ከጓሮ በተቀጠፈ ቅጠላቅጠልና ሥራሥር እርግጠኛ መሆን አደገኛ ሊሆን ይችላል::
ህመሙ እንደጀመረ ወደ ሕክምና ተቋም ባለመሄድ፣ ወይም በልማዳዊ መንገድ በተሞከረ መድኃኒት ህመሙ አደገኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ የመጨረሻው አማራጭ ሐኪም ቤት መሄድ ነውና ታማሚው በሰዎች እገዛ ይሄዳል::ይህኔ ሕመሙ ብዙ ሒደት የሚጠይቅ ይሆናል::በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ የሐኪሞች ሥራ አስቸጋሪና ውስብስብ የሚሆንባቸው ማለት ነው::ታማሚው ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ ስለሚሆን የቤተሰብ ጭንቀት፣ ባስ ሲልም ለቅሶ እና ጩኸት ይኖራል::ይህኔ ሐኪሞች ሥራቸውን ለመሥራት ይቸገራሉ::እርግጥ ነው ህመሙ ሲብስ አስታማሚ እንዳይገባ ይደረጋል::ሆኖም ግን ቤተሰብ ናቸውና ጋዎን የለበሰ ሐኪም ባዩ ቁጥር እግሩ ላይ እየወደቁ ማልቀስና መጮህ የተለመደ ነው::
አንዲት እናት ልጇ ሊሞት ፃር ላይ እያለ ‹‹ዝም በይ!›› ብትባል የማይሆን ነገር ነው::አንድ ሰው እናቱ ወይም አባቱ ሊሞቱ እያጣጣሩ ‹‹ዝም በል!›› ቢባል የማይሆን ነገር ነው::ታማሚው ያለበት ክፍል አካባቢው ለቅሶ በለቅሶ ይሆናል::አንዳንዶቹ ሐኪሞችን እንደ ፈጣሪ በማየት የተማጽኖ ድምጽ ያሰማሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሐኪሞችን በመሳደብ እና በመራገም ‹‹ትገሉብኛላችሁ!›› ወይም ደግሞ ‹‹እናንተ ናችሁ እንደዚህ ያደረጋችሁት!›› በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ ይላሉ::ያው እንግዲህ ጭንቅ ነውና ምንም ሊሉ ይችላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሐኪሞች ሁሉንም ነገር ለምደውታልና ቀጥ ብለው ሥራቸውን ነው የሚሠሩት::በተሳዳቢዎች ግንዛቤ ልክ ወርደው አይሰዳደቡም፤ ደረጃቸውንና የሙያቸውን ክብርነት ያውቃሉ::ጥድፊያቸው የማዳን ሥራው ላይ እንጂ ተሳዳቢዎች ላይ አይደለም::
ሌላው ከሐኪሞች ጥበብ ቀልቤን ገዝቶት የነበረው ታማሚን የሚጠይቁበት እና የሚንከባከቡበት መንገድ ነው::እዚህ ላይ መደበኛው የሐኪምነት ሥራቸው ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ሥብዕናቸውም ይታያል::ማታ ፈረቃ ሲቀያየሩ ቀን በሙያ ልብሱ (ጋዎን) ያየነው ሐኪም ማታ ሌላ ልብስ ለብሶ (ሊወጣ ሲል ማለት ነው) በየአልጋ ክፍሉ እየዞረ ይጠይቃል::እዚህ ላይ የሚጠይቀው በሁለት ነገር ይመስለኛል::አንደኛ፤ እንደ ሰው ‹‹ፈጣሪ ይማራችሁ›› ለማለት፤ ሁለተኛ፤ እንደ ሙያ ሲሠራው የዋለውን ሁኔታ አይቶ መሄድ ስላለበት፣ ደህና ሆነው ሲያይ የሚሰማው የህሊና እርካታ ስለሚኖረው ነው::ምናልባትም ማታ ስትወጡ መጠየቅ አለባችሁ ከተባሉም፤ የሙያ ታማኝነትንና የህሊና ተገዥነትን ያሳያል::
በሥራ ላይ እያሉ የሚሰጣቸው አልጋ (ታማሚ) ይኖራል::የሚጠይቁት ግን ክፍሉ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ታማሚ ነው (ምናልባት የሙያው ባህሪ ሊሆን ይችላል)::ሲጠይቁ ታዲያ በማሳሳቅ እና በመቀለድ ጭምር ነው::ሥነ ልቦናዊ ጥበብ ያልኩት ይህንን ነው::እንኳን የታማሚውን የአስታማሚውን እንኳን ቀልብ ያረጋጋሉ::ታሞ የተኛ ቤተሰቡን ወይም ጓደኛ የሚያስታምም ሰው የሚኖረውን ጭንቀት ማንም መገመት የሚችለው ነው::ሐኪሞች እየዞሩ ሲጠይቁ፤ ታማሚውን እየቀለዱ፣ አንዳንድ ቀለል ቀለል ያሉ ሰዋዊ የሆኑ ነገሮችን እየጠየቁ… ታማሚውንም አስታማሚውንም ያረጋጋሉ::
ያም ሆኖ ግን ቁጡ እና ነጭናጫ የሚሆኑ ፈፅሞ የሉም ማለት አይደለም::ማየት ያለብን ግን ጥቂቶችን ሳይሆን ብዙዎችን ነውና የሐኪሞችን ውለታ እናስብ! የሐኪሞችን ውለታ የምናስበው ደግሞ ሕመም ሳይጠነክር እና ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን በመሄድ መሆን አለበት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም