የሕይወትን ክፉ እና ደግ ገጽታዎች በአረቦቹ ምድር ኖራ አይታዋለች፤ ለድፍን አስር ዓመታት። አጋጣሚዎች ምንም ይሁኑ ምን ለእሷ የለውጥ ርምጃዎች ናቸው። ሁሌም ጥንካሬን ከብርታት ደርባ ለመነሳት ምክንያት ይሆኗታል። ምንጊዜም ሃሳብን ወጥኖ፣ በሥራ መተግበርና ለሌሎች ጭምር ሥራ መፍጠር ብርቋ አይደለም ወይዘሮ መቅደስ ውብነህ።
ከዓመታት በፊት እሷና ጥቂት ጓደኞቿ ብዙ የማይባል የመነሻ ካፒታል ይዘው በጋራ ለመሥራት ተደራጁ። ያኔ ‹‹ጉድሼፐርድ›› የተባለ ግብረሠናይ ድርጅት አጋር ሊሆናቸው ከጎናቸው ቆመ። በወቅቱ ሥልጠናን ጨምሮ ለሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና የመቋቋሚያ ገንዘብ ከእጃቸው አላጡም። ውሎ አድሮ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር አቅም አገኙ። መደራጀታቸው ኃይል ሆኖም ትጋታቸው በተግባር ይገለጽ ያዘ።
እነመቅደስ በአዲሱ ገበያና አካባቢው ቦታ አግኝተው ሥራ ሲጀምሩ በቁጥር አስራ አምስት ነበሩ። ብርቱዎቹ ነገን የተሻለ ለማድረግ ጠንከረው መሥራት ጀመሩ። የመጀመሪያው የጥረታቸው ሀሁ የታየው ዳቦ ጋግሮ መሸጥ ላይ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ከሥራው መጀመር ጋር እክል አላጣቸውም። ዳቦውን ለመጋገር የተሰጣቸው የመብራት ኃይል መጠን ዝቅተኛ መሆን አቅማቸውን ያንገዳግደው ያዘ። እንዲያም ሆኖ እጅ አልሰጡም። በቻሉት አቅም ከነሱ ሳያጎድሉ ሌት ተቀን ባተሉ። ያለው የመብራት አቅም የዳቦ ማሽኑንና ማቡኪያውን ማንቀሳቀስ አልቻለም። እንዲህ መሆኑ በግለት የጀመሩትን ሥራ ማቀዛቀዙ አልቀረም። ውሎው አድካሚ ቢሆንም ትግላቸው ያለ እረፍት ቀጠለ። ጥቂት ለማይባል ጊዜ ሁሉም ሥራውን ለማሸነፍ ጣረ፣ ደከመ።
ውሎ አድሮ ግን ‹‹ሰለቸን ፣ደከመን›› ያሉቱ ከቡድኑ ተንጠባጠቡ። አብዛኞቹ በሚሆነው ሁሉ ተስፋ ቆርጠው ነበር። የተቀሩት ጥቂቶች ላባቸውን ጠርገው፣ ትከሻቸውን አጉብጠው ወደሥራው ተመለሱ። አሁንም ትግሉ አልቆመም። መቅደስና ጥቂት ባልንጀሮቿ ከዓላማቸው አልሳቱም። አድካሚውን ውሎ ለማቃናት ደፋ ቀናቸውን ተያያዙት።
መቅደስ ፈጽሞ ክንዷ አልዛለም። እንደሷ የበረቱትን ይዛ ከሥራው ላይ ዋለች። ድካሟ ውሉን አልሳተም። የጠፋውን እያረመች፣ የጎደለውን እየሞላች በጽናት መጓዟን ቀጠለች። ይህ ትግል ካሰበችው ሊያደርሳት አልዘገየም። በበቂ የኤሌክትሪክ ኃይል የዳቦ ማሽኑን ተክላ፣ ማቡኪያውና ማኮፈሻውን አቁማ ሥራውን በአዲስ መልክ ጀመረችው።
የመቅደስ ተጨማሪ ሌላ ሥራም ወጠነች፤ እንጀራ እያስጋገረች ማከፋፈሉን ቀጠለች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለብዙዎቹ መልካም ሆኖ ሥራ የመፍጠር ዕድሉን አሰፋ። አስር ሠራተኞች ቋሚ የደሞዝ ተከፋይ ሆነው መተዳደሪያቸውን አገኙ። በእንጀራው ዝግጅቱ ሌሎችም እንጀራ ወጣላቸው።
ሥራ ባለ ጊዜ እየተገኙ ጎዶሏቸውን አሟሉ። በየቀኑ ትኩስ እንጀራ በተፈለገበት ቦታ በጊዜው መድረስ፣ መከፋፈሉን ቀጠለ። መቅደስና አጋሮቿ ሥራው በዚህ ብቻ ‹‹ይብቃን›› አላሉም። የእጅ ሙያቸውን የሚያስመሰክሩበትን ዕድል አስፋፉ። ሙሉ የባልትና ውጤቶች፣ ቡላና ቆሎ፣ ቅመማ ቅመሞች መታወቂያቸው ሆነ። ባዘርና መሰል ዝግጅቶች በኖሩ ጊዜ ፈላጊ ደንበኞቻቸው በረከቱ።
ምርቶቻቸው ከተለመደው ሽያጭ ተሻግረው በመርካቶ ሱቆች ማከፋፈላቸው ደግሞ እውቅናን ማስደሩ አልቀረም። በአውቶቡስ ተራና አካባቢው አሁንም ድረስ የእነሱ ቆሎ ተመራጭ ሆኗል። መቅደስ መቼም ቢሆን ይህን ጅማሬ ባለበት ማቆም አትሻም። ከተለያዩ ክልሎች የምታስመጣቸውን ምርቶች ወደ ውጭ ሀገራት የመላክ ህልምን ሰንቃለች።
እንደ ወይዘሮዋ አባባል የቡላ ምርትን የምታስመጣው በአብዛኛው ከደቡብ የሀገራችን ክፍል ነው። ምርቱ ተፈላጊና ተመራጭ በመሆኑ ማስተዋወቅና አስፋፍቶ መሸጥ የወደፊት ዕቅዷ ነው። የተለያዩ የማር ዓይነቶችን በአግባቡ በማስገባትም በተለያየ የኪሎ መጠን አሽጋ ትሸጣለች። የምታስመጣቸው የማር ምርቶች መገኛቸው ይለያያል። እንዲህ መሆኑ ሽያጩን በዓይነት፣ በጥራትና በፍላጎት ለይቶ ለማቅረብ አስችሏታል።
መቅደስ አብረዋት ሥራውን የጀመሩ ባልንጀሮቿ በተለያዩ ምክንያቶች ዛሬን ከእሷ ጋር አይደሉም። የእነሱ መለየት ሳይበግራት የቀጠለችው ሥራ ግን አሁን ከራሷ አልፎ ለሌሎች እየተረፈ ነው። አስቀድሞ ስያሜ ያወጡለት የ‹‹ኪነጥበብ፣ መቅደስና ጓደኞቻቸው ህብረት ሥራ በብዙ ፈተናዎች ቢመላለስም ተደናቅፎ አልወደቀም። ዳግም አርማውን ባነሳችው መቅደስ የበረታ ክንድ እስትንፋሱ ቀጥሏል። መገኛዋን አዲሱ ገበያ ዙሪያ ያደረገችው ወይዘሮ የነገው ትጋቷ ሁሌም የሰላ ነው። ትናንትን በዋለችበት መስመር ዛሬን እየበረታች ትጓዛለች።
በየቀኑ እየተጋገረ ለገበያ በሚከፋፈለው እንጀራ ጥራት ጉዳይ አትደራደርም። ከምንም በላይ በንጽህናና በታማኝነት ማዘጋጀት የህሊና እረፍት መሆኑን ትናገራለች። እንጀራው በዋነኛነት ለውጭ ተጠቃሚዎች ተዘጋጅቶ ይቅረብ እንጂ ለራሳቸውም ጭምር የሚመገቡት ነው። በየጊዜው ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢው ክትትልና የጥራት ቁጥጥር ይደረግበታል።
ከመንግሥት በተሰጣቸው ስልሳ ካሬ የማምረቻ ቦታ ላይ ተገቢው ተግባራት መከወን ይችል ዘንድ ጊዜና ጉልበት በወጉ ተቀናጅተዋል። በዚህ ሥፍራ ለሰው ልጆች ምግብ የሚሆነው የዕለት እንጀራ በንጽህና ይጋገራል። ዳቦና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችም በትኩሱ ተዘጋጅተው በየቦታው ይደርሳሉ።
የአካባቢው ሱቆች፣ አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎችና ዳቦ ቤቶች የነመቅደስን የጓዳ ሙያዎች ለመቀበል የሚዘጋጁት ገና ከማለዳው ነው። የዕለቱ ፍላጎት ተጠናቆ የነገውን ለማቅረብ ትዕዛዝ የሚቀበሉት እጆች ፈጣንና እረፍት አልባ ናቸው። ሁሌም በሥራ ውለውና አምሽተው ከነገ ለመድረስ ስንፍና ይሉትን አያውቁም።
ብርቱዋ ወይዘሮ ከዓመታት በፊት ባለቤቷን በሞት አጥታለች። እንዲህ መሆኑ ሀዘኗን ቢያከፋውም ተሰብሮ ለመውደቅ አልተመቸችም። ዛሬም ሁለት ልጆቿን በጥንካሬ እያሳደገች ነው። አንደኛው ልጇ አያቶቹ ዘንድ እየኖረ ቢሆንም ሁለተኛ ዲግሪውን እየተማረ ይገኛል።
ሁለተኛዋ ልጇ ዛሬ የአስራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ነች። ከእሷ ጋር አብራት እየኖረች ትማራለች። የልጇን ጉብዝና ደጋግማ የምታውሳው መቅደስ የእሷ ጥንካሬ እንደተጋባባት የምትናገረው በርግጠኝነት ነው። ልጆቿ ያለ አባት ቢያድጉም በጎዶሎ ስሜት እንዲቀጥሉ አትሻምና ስለትምህርታቸው አብዝታ ታስባለች። በቤትም ይሁን በውጭ የእናት አባትን ኃላፊነት መሸከም የእሷ ድርሻ ቢሆንም ስለእነሱ ዝም አትልም።
ከጠንካራ እጆች በስተጀርባ የበረቱ ሁሌም ሥራቸው በጥንካሬ ይገለጻል። ማንነታቸው በትጋት ጠንክሮም ሕይወታቸው በገሀድ ይመሰክራል። እንዲህ ዓይነት እጆች ያላቸው ብርቱዎች በሻካራው መዳፋቸው ነጋቸውን አሳምረው ይገነባሉ። በጥረታቸው፣ በላባቸው በረከት ብሩህ ተስፋን ያፈካሉ። ሁሌም በዚህ ዓይነት መንገድ የሚራመዱ በጉዞ አይደክሙም። ከራሳቸው አልፈው፣ ለቤተሰቦቻቸው መድህን ሊሆኑ ይቻላቸዋል።
እናት መቅደስ ስለ ልጆቿ ብዙ ታልማለች። ሁሌም የእሷን ፈለግ ተከትለው ከዓላማዋ እንዲደርሱ ምኞቷ ነው። አሁን ያሉበትን ጅማሬ ስትገመግመው ግን ልጆቿ ከእሷ ልቀዋት እንደሚያልፉ ትገምታለች። እሷ ዛሬ ላይ በልማዳዊ አሠራር የጀመረችውን መስመር እነሱ ወደፊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደሚተኩት ስትናገር ያለ አንዳች ጥርጣሬ ነው። ብርቱዋ ወይዘሮ መቅደስ ውብነህ።
ወይዘሮ አሰለፈች አለዶ በተለያዩ የሥራ ፈጠራዎች በሥልጠና ስትሳተፍ ቆይታለች። ለእሷ ውስጠት ቀርቦ ያገኘችው ሙያ ግን የልብስ ስፌትና የሀገር ባሕል ልብሶች ሽያጭን ነው። በዚህ ሙያ የተለያዩ አልባሳትን ሰፍታ በማዘጋጀት ለጠየቋት ደንበኞቿ በመሸጥ ትተዳደራለች።
አሰለፈችን ያገኘኋት በቅርቡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በነበረው ዓለም አቀፉ የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት ላይ ነበር። እሷም ልክ እንደነመቅደስ ሁሉ የራሷን የሥራ ውጤቶች ለእይታ አቅርባ ለሽያጭ አውላለች።
አሰለፈች ሰፍታ የምታዘጋጀቸውን የሀገር ባሕል ልብሶች ከደንበኞቿ ባለፈ በብዛት ለሚፈልጉ ነጋዴዎች ጭምር ታስረክባለች። የእጇን ሙያ የሚያውቁ አንዳንዶች በፍላጎታቸው መጠን እንድትሠራላቸው ይሻሉ። ትዕዛዛቸውን ተቀብላ የልባቸውን ትሞላለች።
አንዳንዴ የሠራቻቸውን የሀገር ባሕል ልብሶች ባዛር ላይ ተገኝታ ትሸጣለች። አሁን እንደተገኘችበት የኢንተርፕሪነርሺፕ ዓይነት ቆይታ ሲኖራት ደግሞ ምርቶቿን በማሳየት ከብዙሃን ጋር መተዋወቅን ልምድ አድርጋለች። አሰለፈች ጥሬ ዕቃዎችን ገዝታ ከባሕላዊው ጋር ማዛመዷ ልብሶቹ ማራኪ እንዲሆኑላት ምክንያት ሆኗል። ይህ እውነታም ተፈላጊነትን አስከትሎ ለገበያው መወደድ አግዟታል።
በአሰለፍ ገበያ ውስጥ የሸማኔ ሥራና የፋብሪካ ውጤቶች የተዛመዱ ናቸው። ጥለትና ጥበቦች በግል ፈጠራዋ ተውበው ከዘመናዊ አልባሳት ተዛምደው ይቀርባሉ። የህጻናትና የአዋቂዎች አልባሳት በተለያየ ዲዛይን መዘጋጀታቸው ለገዢዎች ምርጫና ልዩነትን ለመፍጠር ምክንያቶች ናቸው።
አሰለፈች ይህን መሰል ክህሎት ለማዳበር በሙያው የወሰደችው ሥልጠና አግዟታል። በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅታ በርካታ ዕውቀት አዳብራለች። ከሥልጠናው በኋላ ለአምስት ዓመታት የመሥሪያና መሸጫ ቦታ አግኝታ ምርቶቿን ለገበያ ስታቀርብ ነበር። ከነዚህ ዓመታት በኋላ ወደ ተገቢው ደረጃ በማለፏ ራሷን ችላ እንድትቀጥል አስችሏታል።
መኖሪያዋን ኮዬ ፈጬ ላይ ያደረገችው አሰለፈች ባለችበት ስፍራ ገበያውን ለማላመድ እየጣረች ነው። ከማህበር ሥራ ተነጥሎ ወደግል ሲመለሱ መንገዶች አልጋ በአልጋ አይሆኑም። የመሥሪያ ቦታ፣ የማቴሪያል አቅርቦትና ሌሎችም ግብዓቶች ያስፈልጋሉ። ወይዘሮዋ በቆይታዋ ያዳበረችው ልምድ ለዚህ አጋጣሚ ሲያግዛት ቆይቷል። ያላትን አቅም ላሰበችው ዓላማ ባዋለች ጊዜ አልተቸገረችም።
በአካባቢው አልባሳቶቹን አዘጋጅታ ለመሸጥ የሚያስችላትን ሱቅ ተከራየች። አቅርቦቶቹን አይተው የወደዱላት በርካቶች ደንበኞቿ ሆኑ። ለአዘቦት ቀንና ለዓውደ ዓመት ሱቋን መጎብኘት ልምዳቸው ሆነ።
ወይዘሮዋ የባዛር አጋጣሚዎችን በምታገኝ ጊዜ ዕድሉን ትጠቀማለች። በዓይነትና በብዛት የምታቀርባቸው አልባሳት ገበያ ለመሳብ አይዘገዩም። ባሕላዊ አልባሳቱ አውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ ፈላጊያቸው ብዙ ነው። እሷም እንደየጊዜው ፍላጎት አመቻችታ ማዘጋጀት ይጠበቅባታል።
አሰለፈች ገበያው ቀዝቀዝ ሲልባት ጊዜዋን የምትጠቀመው ምርቶችን በማዘጋጀትና ትዕዛዞችን በመቀበል ነው። ሥራው ላይ በዋለች ጊዜ መሰልቸት ይሉትን አታውቅም። ሙያው በራሱ ያሳደረባት ፍቅር ዕለት በዕለት እንድትገኝበት ምክንያት ሆኗል።
አንዳንዴ አሰለፈች በሥራው ላይ የምትፈተንበት አጋጣሚ አይጠፋም። የመኖሪያ ሰፈሯና የጥሬ ዕቃው መገኛ መራራቁ የምትሻውን ፈጥኖ ለማግኘት ያስቸግራታል። መርካቶ ከምትኖርበት የኮዬ ፈጬ አካባቢ በኪሎ ሜትሮች የራቀ ነው። ለሀገር ባሕል አልባሳቱ ጥልፍ የሚሰሩላት ባለሙያዎችም በአቅራቢያዋ የሉም። ይህ እውነት በተለይ በአውደ ዓመት አካባቢ ቀላል የማይባል የድካም ዋጋ ያስከፍላታል።
ወይዘሮዋ ባለትዳርና የልጆች እናት ነች። ታላቅ ኃላፊነት አለባትና ጊዜዋን ለውጭ ሥራ ብቻ አታውልም። ቤተሰብ ማስተዳደር፣ ቤትን መምራትና ጓዳን መሙላት ይጠበቅባታል። የውጭውን ከቤቱ አቻችላ ለማሳደር እጆቿ ሁሌም ብርቱ ናቸው። በየጊዜው በጥንካሬ ሰልተው ይውላሉ።
አሰለፈች ከጊዜ ወደጊዜ የባሕል አልባሳትን የሚመርጡ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን አስተውላለች። የተጠቃሚው ፍላጎት መጨመርም ለእሷ መሰል ባለሙያዎች ዕድል እንደሚፈጥር አታጣውም። ክንዶቿ ሳይዝሉ የመትጋቷ አንዱ ሚስጥርም ይኸው ነው። በተለይ በዓውደ ዓመት ጊዜ የእጇ አቅርቦት እስኪያንሳት የምትቸገርበት አጋጣሚ ይኖራል።
ወይዘሮዋ የምትኖርበትን አካባቢ የአልባሳት ፍላጎት ለይታለች። እንደ ደንበኞቿ ጥያቄም በተለያዩ ጨርቆች የራሷን ዲዛይን አዘጋጅታ ለገበያ ታውላለች። አሰለፈች በጀመረችው መንገድ ጠንክራ የመግፋት ዕቅድ አላት። ነገን የተሻለ ለማድረግም የዛሬ እርሾዋ በወጉ መዘጋጀት ይኖርበታል።
ይህን ጠንቅቃ የምታውቀው ብርቱ ወደፊት ተጨማሪ ሱቆች የማከል ዓላማን ወጥናለች። ለዚህ ደግሞ በተሻለ አቅርቦትና በዘመናዊ አሠራር ጊዜዋን መጠቀም ግድ እንደሚል ገብቷታል። አሰለፈች ዛሬ ላይ ቆማ ነገን በመልካም እያለመች ነው። ህልሟ ዕውን ይሆን ዘንድ ጠንካራ እጆቿ በአእምሮዋ ታግዘው መትጋታቸውን ቀጥለዋል።
ሁለቱ ብርቱ ሴቶች ከትናንት መነሻቸው ተንደርድረው ዛሬን የተሻለ ለማድረግ እየጣሩ ነው። በግልጽ ከሚታየው ውጤታማ ተግባራቸው ጀርባ ጠንክረው የሚሠሩ እጆቻቸው ድካምን አያውቁም።
እነዚህ እጆች ዛሬ ለተገኙበት ውጤታማ ዓለም መሠረት ሆነው አበርትተዋቸዋል። ነገ ለሚጓዙበት የዕድገት ጎዳናም ምስክር ሆነው ይቀጥላሉ። ከጠንካራ እጆቻቸው በስተጀርባ ታይቶ የሚረጋገጥ፣ ውጤታማ ፍሬ ጎምርቷልና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም