በተጠናቀቀው ሳምንት በበርካታ የዓለም ሃገራት በተለያዩ ርቀቶች የጎዳና ላይ ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በአሸናፊነት ሊያጠናቅቁ ችለዋል፡፡ ከማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የአቡዳቢ ማራቶን ሲሆን፤ አሸናፊው አትሌት ጫላ ከተማ ለመጀመሪያ ውድድሩን ያሸነፈ ኢትዮጵያዊ አትሌት መሆን ችሏል፡፡
አትሌት ጫላ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ውድድር አብዛኛውን ኪሎ ሜትር ሲመራ ከቆየ በኋላ መጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ በወሰደው የበላይነት አሸናፊ አድርጎታል፡፡ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓትም 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ ይህ ሰዓት በግሉ ካስመዘገበው ፈጣን ሰዓት በጥቂት ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ቢሆንም በአቡዳቢ ማራቶን ከተመዘገቡት ስድስት ፈጣን ሰዓቶች መካከል አራተኛው ነው፡፡ ውድድሩን በድል መወጣቱን ተከትሎ በስፍራው ለነበሩ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየትም ‹‹የአየር ሁኔታውም ሆነ ውድድሩ ምርጥ ስለነበር አሸናፊ ልሆን ችያለሁ፡፡ በአቡዳቢ ማራቶን አሸናፊ የሆንኩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በመሆኔም ኮርቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ጥቂት የማገገሚያ ጊዜ የሚኖረኝ ሲሆን፤ ወደ ልምምድ በመመለስ ሃገሬን የሚያስከብር ውጤት ለማስመዝገብ እሠራለሁ›› ብሏል፡፡
እጅግ ጠንካራ ፉክክር የታየበትና የጎዳና ውድድር እስከማይመስል ድረስ አሸናፊውን አትሌት እስከመጨረሻው ለመለየት አስቸጋሪ በነበረው ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች የተለያዩት በሦስት ሰከንዶች ብቻ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች የበላይነት በታየበት ሩጫ አሸናፊውን ጫላ ተከትሎ የገባው ጅቡቲያዊው አትሌት ኢብራሂም ቦኸ 17 ሰከንዶችን ብቻ ነው የዘገየው፡፡። ከ14 ሰከንዶች በኋላ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የገባው አትሌት ደግሞ ኬንያዊው አትሌት ዌልፍሬድ ኪገን ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የሕንዱ ካልካታ የ25 ኪሎ ሜትር ውድድር ከትናንት በስቲያ የተካሄደ ሲሆን፤ በሴቶች በኩል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸናፊ ሆናለች፡፡ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ የተካሄደው ይህ ውድድር በርቀቱ በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ያገኘ ቀዳሚው ውድድር ነው፡፡ በቀዝቃዛማው የአየር ሁኔታ ከ20 በላይ ሯጮችን በማሳተፍ ውድድሩ ሲካሄድ የምዕራባዊቷን የሕንድ ከተማ ጎዳናዎች ደምቀው ውለዋል፡፡ ጠንካራውን ፉክክር በድል ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ ከበደ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ፈጅቶባታል፡፡
በጎዳና ላይ ሩጫዎች ስኬታማ የሆነችው አትሌት ሱቱሜ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የውድድር ዓመት በሂውስተን ግማሽ ማራቶን 1 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመግባት የግሏን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዋና ዋናዎቹ ማራቶኖች መካከል በሚጠቀሰው የቶኪዮ ማራቶን ደግሞ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በመሮጥ በርቀቱ ታሪክ ስምንተኛዋ ፈጣን አትሌት መሆን ችላለች፡፡ ጠንካራዋ አትሌት በ25 ኪሎ ሜትር ባለፈው ዓመት የገባችበት ሰዓት ዘንድሮ ርቀቱን ካጠናቀቀችበት በአንድ ደቂቃ የፈጠነም ነበር፡፡ በሕመም ላይ የቆየችው አትሌት ሱቱሜ ውድድሩ ሊካሄድ ቀናት ሲቀሩት ተሳትፎዋን አሳውቃ ለአሸናፊነት መብቃቷ በስፖርት ቤተሰቡ አድናቆት አስገኝቶላታል፡፡
አትሌቷ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየትም ‹‹በድጋሚ አሸናፊ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ የውድድሩን ክብረወሰን ለማሻሻል ፍላጎት ነበረኝ ነገር ግን በጉዞ ምክንያት ተዳክሜ ስለነበር አልተሳካልኝም፡፡ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ለምሳተፍበት ማራቶን ዝግጅት በማድረግ ላይ እገኛለሁ›› ብላለች፡፡ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ውድድር ሰከንዶችን ብቻ በመዘግየት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ አትሌት ቪዮላ ቼፕጌኖ ናት። ባለፈው ዓመት እዛው ሕንድ ላይ በሚካሄደው የዴልሂ ግማሽ ማራቶን ሦስተኛ መሆን የቻለችው አትሌቷ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም አትሌቷ ‹‹ሁለተኛ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፤ ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት ሩጫ ይህንን ደረጃ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ ጥሩ ብቃት በማሳየቴ በራሴ ተደስቻለሁ›› ስትልም ተናግራለች፡፡ እአአ በ2022 የዚህ ውድድር አሸናፊዋ ባሕሬናዊት አትሌት ደሲ ጂሳ ደግሞ 1 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም