ኦሊምፒክንና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ከመሳሰሉ ታላላቅ የስፖርት መድረኮች በሚካሄዱበት ወቅት አትሌቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃቶች አሳሳቢ መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ አሳውቋል። የዓለም አትሌቲክስ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በሠራው የጥናት ግኝት መሠረት በአትሌቶች ላይ የሚደርሰው የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት መጨመሩን አረጋግጧል። መሰል ጥልቅ ጥናት ሲደረግ በዓለም የስፖርት ማህበራት የመጀመሪያ እንደሆነም ተገልጿል።
አትሌቶች በትልልቅ የውድድር መድረኮች ሲያሸንፉ እንደሚደሰቱት ሁሉ ሽንፈት ሲገጥማቸውም ማዘናቸው አይቀርም:: የተመልካቹ ወይም የስፖርት ቤተሰቡም ስሜት ከዚህ የተለየ አይደለም:: የስፖርት ቤተሰቡ በሁለት መንገድ በማህበራዊ ሚዲያዎች አትሌቶች ላይ ጥቃት ያደርጋል:: ለምን አላሸነፈም ብሎ የገዛ ሀገሩ አትሌት ላይ ጥቃቱን የሚፈፅም አለ:: ‹‹የኔን ሀገር አትሌት ለምን አሸነፈ›› ብሎ ሌላው ላይ ጥቃት የሚሰነዝርም ብዙ ነው:: ጥቃቱ ዘር፣ የቆዳ ቀለምና ፆታን መሠረት ያደረገ ሲሆን ፆታዊ ትንኮሳንም ያካተተ ነው:: ይህም ትልልቅ የውድድር መድረኮችን ተከትሎ የሚመጣ ነው:: በዚህ መልኩ አትሌቶች ላይ የሚደርሰው የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት በፓሪስ ኦሊምፒክ ወቅት ተባብሶ መታየቱን ጥናቱ አረጋግጧል::
ጥናቱ 2021 ላይ ከተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አንስቶ እስከ ፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ ድረስ ባለው ጊዜ በአትሌቶች ላይ የደረሱ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ነው:: በዚህም ከትራክ (መም) እስከ የሜዳ ተግባራትና የጎዳና ላይ ውድድሮች የሚፎካከሩ የተለያዩ ሀገራት አትሌቶች በጥናቱ ተካተዋል:: እነዚህ አትሌቶች በቶኪዮና ፓሪስ ኦሊምፒኮች፣ በ2022 የኦሪገን፣ በ2023 የቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮናዎች የተሳተፉ 2438 መሆናቸው ተጠቁሟል::
በነዚህ ታላላቅ ውድድሮች ወቅት በአርባ ቋንቋዎች አትሌቶችን የተመለከቱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎችና ግብረ መልሶች በጥናቱ ተተንትነዋል::
ጥናቱ በፓሪስ ኦሊምፒክ ወቅት የ1917 አትሌቶችና የስፖርቱ ሃላፊዎች የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደ ናሙና ወስዶ ክትትል አድርጓል:: ይህም በቶኪዮው ኦሊምፒክ ወቅት ከተወሰደው 161 ናሙና አስራ ሁለት እጥፍ የበለጠ ነው:: የቀድሞው ትዊተርና የአሁኑ X፣ ኢንስታግራም፣ ፌስቡክና ቲክቶክ ጥናቱ ትኩረት ያደረገባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ናቸው:: ጥናቱ በአትሌቶቹ የማህበራዊ ሚዲያዎች ገፅ ላይ የተሰጡ ግብረመልሶችን እንጂ በግል የተላኩ መልዕክቶችን አላካተተም::
በዚህም መሠረት ዘር ተኮርና ጾታዊ ትንኮሳን መሠረት በማድረግ አትሌቶች ላይ ያተኮሩ 48 በመቶ ጥቃቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ ብቻ መመዝገባቸውን ጥናቱ ትኩረት ባደረገባቸው የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎችና ግብረመልሶች ታይቷል:: ከነዚህ ልጥፎች ውስጥም 809 ስድብ አዘል እንደሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን 128 ልጥፎችና አስተያያቶች (16 በመቶዎቹ) ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው:: በፓሪሱ ውድድር ወቅት ከ 1 ሺ 917 አትሌቶች ውስጥ ቢያንስ አንድ ንቁ የማበራዊ ድረ-ገጽ መለያ ያላቸው አትሌቶች፣ የስድብና እና ትንኮሳ ሰለባ መሆናቸውም ተጠቁሟል::
የዘረኝነት ጥቃቶች 18 በመቶና ፆታዊ ጥቃቶች 30 በመቶ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል። በዚህም መሠረት አጠቃላይ 20 የተለያዩ ሀገራትን በሚወክሉ አትሌቶች ላይ የተረጋገጠ ጥቃት ተፈጽሟል። 49 በመቶ በአማሪካ አትሌቶች ላይ ነው::
ዘርና የቆዳ ቀለምን የተመለከቱ ጥቃቶች በወንድ አትሌቶች የከፋ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ ይህም በወንድ አትሌቶች ላይ ከሚደርሰው አጠቃላይ ጥቃት 26 በመቶ መሆኑን አስቀምጧል:: ሴት አትሌቶች በፆታዊ ጥቃትና በሌሎች ጉዳዮች ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውም ታውቋል::
የዓለም አትሌቲክስ በአትሌቶች ላይ የሚደርሰውን ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት ለማስቀረት ወደፊት ለሚወስዳቸው ርምጃዎች ጥናቱ ጠቃሚ ነው ተብሏል:: በአትሌቶች ደህንነት እና በአዕምሯዊ ጤና ዘርፍ ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ጨምሮ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተ የበለጠ ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ሥርዓቶችን ለማዘጋጀትም ይረዳል ተብሏል።
የጥናቱን ግኝት ተከትሎ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ ሲናገሩ፣ ‹‹ባለፉት አራት ዓመታት ይህን ጥናት ለማድረግ ብዙ ሀብት አፍስሰናል፣ በዚህም አትሌቶቻችንን ከመሰል የማህበራዊ ሚዲያ ጥቃቶች የምንከላከልበት መላ መዘየድ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራበት ጉዳይ ይሆናል›› ብለዋል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም