የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል። በጠቅላላ ጉባዔው ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመራ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ፕሬዚዳንት ይመረጣል። በምርጫው ለመወዳደር የቀረቡ የመጨረሻ ዕጩዎችንም ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ አሳውቋል።
ከዚህ ቀደም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በምርጫው የሚወዳደሩ ተወካዮቻቸውን ያሳወቁ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ከተገቢነት አኳያ አጣርቶ ተገቢ ናቸው ያላቸውን የመጨረሻዎቹን ተፎካካሪዎች አሳውቋል። በዚህም በፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚዎች ዕጩዎች ላይ ቀደም ሲል የተገለፁት ለውጥ ተደርጓል።
ፌዴሬሽኑ ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የቀረቡትን ዕጩዎች ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ በአንዳንድ ክልሎች የቀረቡ ዕጩዎች ከተገቢነት አኳያ የስፖርት ቤተሰቡን ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ባለፉት ቀናትም ፌዴሬሽኑ ከሕግና ደንብ አንጻር ተገቢነት ላይ አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች አሳውቋል። በዚህም የተወሰኑ ለውጦች መኖራቸው ግልጽ ሆኗል። ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ተከትሎ ቀድሞ ከነበሩት ሰባት ዕጩዎች መካከል አንድ ክልል ያቀረበው ተወካይ ተቀንሶ ለሥራ አስፈጻሚነት እንደሚወዳደር ለማወቅ ተችሏል። ለሥራ አስፈጻሚነት በሚደረገው ውድድርም የተወሰኑ ክልሎች ዕጩዎች ላይ ለውጥ ተደርጓል።
ቀድሞ ሃገራቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሃገራቸውን ማስጠራት የቻሉ አትሌቶችና የስፖርት ባለሙያዎች በተሰባጠሩበት የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ላይ በዕጩነት ከቀረቡት መካከል አንዱ አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ነው። በትግራይ ክልል የተወከለው አትሌት ገብረእግዚአብሄር ከዚህ ቀደም በአትሌቶች ተወካይነት እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ማገልገሉ የሚታወስ ነው። ከቀናት በኋላ በሚደረገው ምርጫም በድጋሚ ፌዴሬሽኑን ለመምራት በተወዳዳሪነት ቀርቧል።
በኦሮሚያ ክልል በእጩነት የቀረበው አትሌት ስለሺ ስህንም በተመሳሳይ ከስኬታማ የሩጫ ልምዱ ባለፈ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ፌዴሬሸኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ይፎካከራል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው አቶ ዱቤ ጅሎ ረጅም ዓመትን ካስቆጠረው የአትሌቲክስ ባለሙያነታቸው በአመራርነት ለመቀጠል በውድድሩ ውስጥ ተካተዋል። የቀድሞ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ያየህ አዲስም ስፖርቱን ለመምራት በክልላቸው ተወክለዋል። ብቸኛዋ ሴት ፕሬዚዳንታዊ እጩ ሪሳል ኡፒየው ደግሞ በጋምቤላ ክልል የተወከለች ሲሆን፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ኮማንደር ግርማ ዳባን አቅርቧል።
ቀደም ሲል ለፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ኢንጂነር ጌቱ ገረመው አሁን በሥራ አስፈጻሚነት እንዲወዳደሩ መደረጉ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ የጫረ ሆናል። የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብ ቦርድ አመራር የሆኑትና ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው ከዚህ ቀደም በተግባር ያሳዩት እኚህ ዕጩ ፌዴሬሽኑ ባልገለጸው ምክንያት በሥራ አስፈጻሚነት እንደሚወዳደሩ አሳውቋል። ድሬዳዋ በምትኩ በፕሬዚዳንትነት ሌላ ዕጩ አለማቅረቡም ታውቋል።
እአአ በ2022 የዩጂን ዓለም ሻምፒዮና 3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው በአስፈጻሚነት እንደምትወዳደር ታውቋል። በርቀቱ የአፍሪካ ሻምፒዮና እና ዳመንድ ሊግ አሸናፊ በመሆንም ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት ርቀት መድመቅ የቻለች ወጣት አትሌት መሆኗ የሚታወቅ ነው።
በተመሳሳይ የሥራ አስፈጻሚ ዕጩዎች ላይ የተወሰኑ ለውጦች የታዩ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ያገለገሉትና ጡረታ የወጡት እንዲሁም በተለያዩ የስፖርት ማኅበራት ሥራ አስፈጻሚነትና ኃላፊነት ላይ የሠሩት የአማራ ክልል ተወካዩ አቶ ቢልልኝ መቆያ ከዕጩነት ተሰርዘዋል። በምትካቸውም ዘላለም መልካሙ (ዶክተር) ቀርበዋል። ምንም ዕጩ ያላሳወቀው የሶማሌ ክልል ደግሞ አቶ አብዲ መሐመድ እና ኢፍረህ መሐመድ (ዶክተር)ን ወክሏል። የሲዳማ ክልል በበኩሉ አቶ ፍሬው አራራን በአቶ አሥራት አሰፋ ቀይሯል። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ወይዘሮ አልማዝ ጋሜን የሥራ አስፈጻሚ ዕጩዎቹ ላይ አካቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም