ቻው የፕላስቲክ ከረጢት

የዓለም መንግሥታት ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ የማይሆኑ ከሆነ 1ነጥብ3 ቢሊዮን ቶን የሚመዝን ፕላስቲክ እአአ በ2040 በምድር እና በውሃ አካላት ላይ ሊገኝ ይችላል ሲል አንድ ጥናት አመላክቷል::

ጥናቱ ፕላስቲክ ጥቅም ላይ የሚውልበት መጠን እና አወጋገዱ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተለያየ መሆኑ መረጃዎች በቀላሉ እንዳይገኙ አድርጓል ይላል። የፕላስቲክ ምርቶች በውሃ አካላትና እንስሳት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

እስከ 700 አይነት የባሕር እንስሳት እና ንጹሕ ውሃ ላይ የሚኖሩ ከ50 በላይ የዓሣ ዝርያዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፕላስቲክ ተመግበዋል ወይም በሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል።

በተጨማሪም የፕላስቲክ ብክለት የሰዎችን ሕይወት እጅጉን ከባድ እያደረገው መጥቷል። በቀላሉ ማስተዋል የሚቻሉ ብዙ ጉዳቶችም አሉት። ለምሳሌ የውሃ መውረጃዎች መድፈን፣ ለተለያዩ ባክቴሪያዎችና ጎጂ ተህዋሲያን ምቹ የመራቢያ ቦታ መሆን፣ መሬት ውስጥ ውሃ እንዳይገባ መከልከል፤ ተክሎች እንዳያድጉ ማድረግ፤ ለረጅም ዘመን አለመበስበስና ወደ አፈርነት አለመለወጥ እና መሰል ተዘርዝረው የማያልቁ ጉዳቶች አሉት::

ይህ ደግሞ በሚያደርሰው ጫና ዓለማችን በየዓመቱ እስከ 13 ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ አድርጓታል:: ስለሆነም ፕላስቲኮችን መልሶ ከመጠቀም ይልቅ የሚመረተውን ፕላስቲክ መቀነሱ አዋጭነት አለው ሲሉም ተመራማሪዎቹ ያሳስባሉ::

ከዚህ አንጻርም መላ ማበጀት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም:: ኢትዮጵያም ብትዘገይም በቅርቡ ረቂቅ አዋጅ አውጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ አቅርባለች::

የፕላስቲክ ጉዳይ እንደ ሀገር የተለያዩ መመሪያዎች ቀድመው የወጡበትና ሲሠራበት የቆየ ቢሆነው በሚፈለገው ልክ ለውጥ አልመጣም። እንዲያውም ይባስ ብሎ የሚመረቱ ፕላስቲክ ከረጢቶች ለአንድ ጊዜ እንኳን እቃ መያዣነት የማይሆኑ ጥንካሬ የሌላቸው። በማንኛውም ቦታ ላይ ምንም አይነት ሸቀጥ ለሚገዛ ሰው በገፍ የሚሰጡም ናቸው ይሄ መሆኑ ደግሞ አካባቢን በመበከል ለዓይን እይታም ጭምር አፀያፊ ሆኖ ቆይቷል።

በመሆኑም የፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀምና አወጋገድ ብዙ ችግር ያለበት በመሆኑና በጥብቅ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው በአዲስ መልክ ረቂቅ አዋጁ እንዲዘጋጅ ተደርጓል:: ረቂቅ አዋጅም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበትም ጊዜ አስፈላጊነቱ በስፋት ተብራርቷል::

ረቂቅ አዋጁ በርከት ያሉ ሀሳቦችን የያዘ ነው። በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀምን፣ ማምረት እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት በገንዘብ እና በእስራት የሚያስቀጣ ድንጋጌ የተካተተበት ነው::

ረቂቅ አዋጁ የተለያዩ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፤ አንዱን የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር ገንዘብ ይቀጣል የሚለው ነው። በተመሳሳይ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ መሸጥ ወይም ለንግድ ዓላማ ማከማቸት ከሃምሳ እስከ መቶ ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ያብራራል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣም በረቂቁ ላይ ሰፍሯል:: ይህ ድርጊት ከግለሰቦች አልፎ ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው ድርጅቶች የሚፈጸም ከሆነ ቅጣቱ ይጠነክራል:: ምን ያህል ነው ከተባለም እንደ ረቂቅ አዋጁ ከሆነ ሦስት እጥፍ ይጨምራል ተብሏል::

ይህ ረቂቅ አዋጅ “የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ” ሲሆን፤ ስድስት ክፍሎች እና 28 አንቀጾች ያሉት ነው:: የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ እና አወጋገድን የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም ይዟል። ከረቂቅ አዋጁ ሦስት መርሆዎች መካከል አንደኛው “የበከለን ማስከፈል” የሚለው ነው።

ይህ ደግሞ ቆሻሻን ከምንጩ እንዲቀንስ ያደርጋል:: መልሶ ለመጠቀምም ያስችላል:: ከዚያም ባሻገር መልሶ ዑደት ማድረግን ያስለምዳል:: ለዚህ ግን የኅብረተሰብ ተሳትፎ የግድ ይላልና በረቂቅ አዋጁ አንዱ መርሕ ተደርጎ ተካቷል::

አዋጁ ከ18 ዓመታት በፊት የወጣውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ የሚሽር እንደሆነም በማሳያነት የሚጠቀሱ ሀሳቦችን ይዟል:: አንዱ በአዲሱ ረቂቅ የተሻረው አዋጅ “በቀላሉ በስብሶ ወደ አፈር የሚደባለቅ መሆን አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያልተደረገበትን የፕላስቲክ ከረጢት ለገበያ ማቅረብ” ክልክል ነው የሚለው ነው::

በሌላ በኩል አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀምን ይከለክላል:: ነገር ግን ይህ ድንጋጌ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በተመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ በገባ፣ ለመግባት በሂደት ላይ ባለ ፕላስቲክ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን በአዋጁ ተካቷል:: ይሁን እንጂ ይህ ልዩ ሁኔታ ተፈጻሚ የሚሆነው ይህ አዋጅ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወር ብቻ እንደሆነም ተቀምጧል::

ማንኛውም ችግር ከተፈጠረ፤ ከአዋጁ ውጪ የሚወጣ ሰው አለያም ድርጅት ከተገኘ ቅጣቱን ወይም እርምጃውን የሚወስደው አካል ማን እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠ ሲሆን፤ ይህም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነው:: በዚህም አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክን የተመለከቱ በአዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት አፈጻጸሙን ይቆጣጠራል::

ጥሰት ሲያጋጥምም ተገቢውን የእርምት እርምጃ የሚወስድ ይሆናል:: ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች እንዲመረቱ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመመሪያ ሊወስን እንደሚችልም በረቂቅ አዋጁ ሥልጣን ተሰጥቶታል::

ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ይህን ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችለው በዘፈቀደ አይደለም:: ፕላስቲክ ማሸጊያው በቀላሉ በሌላ ምርት የማይተካ መሆኑ እና ፕላስቲኩ ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው::

ይህ ጉዳይ ብዙዎች ያልተመለከቱት ነው:: አደጋው ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ሄዷል:: እናም መጀመሪያ ስለ እራሳችን በማሰብ ልንጠነቀቅ ይገባል:: በተለይ ለልጆቻችን የሚተርፈው ችግር በቀላሉ የምናልፈው አይሆንም:: በተለያየ መልኩ ጤናቸው ላይ ጉዳት ያደርሳል:: እኛም ቢሆን ከዚህ ችግር የምናመልጥበት ሁኔታ እንብዛም ነው:: እናም ነገ በሳንባ በሽታ፤ በደም ካንሰርና በሌሎች አሰቃቂ በሽታዎች ተይዘን ከመጮኻችን በፊት ዛሬ ላይ ጥንቃቄ ማድረጉ፤ የተባሉትን መፈጸሙ አዋጭነት አለው::

ክብረ መንግሥት

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You