ድሮ ቃሉን ማንሳት እንደነውር መታየቱ ሲያስከፋኝ ኖሯል። ዘንድሮ ደግሞ ስለባሕር በር ጉዳይ መነጋገር እንደክብር መታየቱ ልዩ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኛል። ለእዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛው ኢትዮጵያን ያለባሕር በር ማሰብ እጅግ ከባድ ስለሚሆንብኝ ነው።
ሌላው ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ተራ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይዋ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው። ይህንን ዓለም እየተቀበለው እንደሆነ ሳስብ ደግሞ ደስታን ፈጥሮልኛል። ቢቻል በቅርቡ ባይቻል ደግሞ ቀጣይ ትውልድ የባሕር በር ባለቤት እንዲሆን መታሰቡ ትክክለኛ እና ይበል የሚያሰኝ ተግባር በመሆኑ የደስታ ስሜት ውስጥ ገብቻለሁ።
ታላቂቷ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ከ120 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ብዛት ያላት፤ ከፍተኛ ኢኮኖሚን የምታንቀሳቅስ መሆኗ እንዲሁም ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነቷ ሲታወስ፤ በእርግጥም ኢትዮጵያን ያለባሕር በር ማሰብ ይከብዳል።
ሀገሪቱ አሰብን ከ1950ዎቹ ጀምሮ በስፋት አልምታ ስትጠቀምባት ቆይታለች። አሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ብዙም የማትርቀዋ ምፅዋ ከሦስት አስርተ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ እንደነበሩ ሲታወስ፤ አሁን ላይ የባሕር በር የሌላት አገር መሆኗ ያስከፋል።
በርበራም ሆነች ቦሳሶ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ አካል እንደነበሩ ታሪክ አገላብጦ መጥቀስ ከባድ አይደለም። ዙሪያዋን የቀይ ባሕር መዳረሻ እንዳይከባት ታስቦ የተሠመረላት በሚመስል ካርታ ላይ የተቀመጠችዋ ኢትዮጵያ፤ በዓለም ካርታ ላይ ስትታይ አንጀት ትበላለች። በተለይ ከባሕር በር ጋር ኢትዮጵያን የሚያውቃት ሕዝብ ያለባሕር በር ሲያስባት ይሳቀቃል። ለባሕር በር እየተከፈለ ያለውን ዋጋ ሲሰማ ደግሞ ይሸማቀቃል።
ሌላኛው ዓለም በፈጣን ፉክክር ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ሕልውና ከባሕር በር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑ ነው። ዓለም በውሃ ሽሚያ በፉክክር እየተናጠች ባለችበት በዚህ ጊዜ፤ ያለባሕር በር መቀመጥ የወጪ ንግድን እና ከውጭ የሚፈለጉትን ግብዓቶች በኪራይ ወደብ ማስገባት እና ማስወጣት ኪሳራው ብዙ ነው።
በሌላ በኩል ለደኅንነትም ሆነ ለዋስትና አንድ ትልቅ ሀገር በምንም መልኩ የሌላ ሀገር ሙሉ ጥገኛ መሆን ከባድ እና ማንም የማይቀበለው ነው። ይህ ሲባል በጅቡቲ መስመር ላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር፤ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን የፍጆታ ዕቃ እና ማንኛውም ከውጭ መግባት ያለበትን ምርት ማስገባት አዳጋች መሆኑን ማስተዋል ይገባል። በሌላ በኩል የፀጥታ መሣሪያዎችን ማስገባት ያስፈልጋል። በእርግጥ በአየር የተወሰነ ነገር ማስገባት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የሚፈለገውን ሁሉ በአየር ማስገባት አዳጋች ነው።
በቀጣይ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴን ልታስተናግድ ዓለም ሊከፋፈላት እስከማኮብኮብ የደረሰባትን ቀይ ባሕር በብዙ ኪሎ ሜትር ትዋሰን የነበረችዋ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ባዶዋን መቅረቷ ሳያንስ፤ በአንድ በሌላ ሀገር ተፅዕኖ ውስጥ ሊወድቅ በሚችል ሀገር ላይ ጥገኛ ሆና፤ እንደተፈለገ በየቀኑ የሚጨምር የባሕር ወደብ ኪራይ እየከፈለች ዘመንን መግፋት ለዚህ ዘመን ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ዘመን ትውልድም ከባዱ እርግማን ነው።
በእርግጥ ሆን ተብሎ በውጪ ተፅዕኖም ሆነ ባለማወቅ በእኛው ኢትዮጵያውያን ስህተት የነበረው የባሕር በር የሚታጣበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ስለዚህ በቀላሉ ከባሕር በር ጉዳይ ችግሮች ነፃ መሆን ከባድ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የባሕር በር ስለሌላት ለተደጋጋሚ ወጪ እየተዳረገች ነው። አሁን ያለው ወጪ እንዳይቀጥል ለቀጣዩ ትውልድም መርገምት ሆኖ እንዳይተላለፍ ከወዲሁ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ከመነጋገር ጀምሮ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የሚያስመሰግን ነው።
ቀደም ሲል ሃሳቡ ሲነሳ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የባሕር በር ጥያቄ መቅረቡ እንደችግር ታይቶ ነበር። አሁን ግን ዓለም ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የሚያምንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለእዚህ የቅርቡን የአንካራን ስምምነት ማንሳት ይቻላል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ሃሳብን ለምን አነሳች? የሚለውን ጉዳይ አንስተው ተቃውሞ ሲያስነሱ ከነበሩት መካከል ጎረቤቶቻችን ተጠቃሾች ናቸው።
ነገር ግን አሁን የባሕር በር ለኢትዮጵያ የግድ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ከማወቅ አልፈው አምነዋል። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እና የሕዝብ ብዛቷም ከፍተኛ በመሆኑ በአነስተኛ ወደብ፤ በደካማ መሠረተ ልማት ላይ ተወስና መኖር ያዳግታታል የሚለውን ሃሳብ ተቀብለዋል። ለሕዝቧ የሚያስፈልገውን ሰፊ ግብዓት ለማግኘትም ሆነ ሰፊው ሕዝብ ያመረተውን ወደ ውጭ ለመላክ ሰፊ የባሕር በር መዳረሻ እና ምርጥ መሠረተ ልማትን እንደምትሻ ተማምነዋል።
በዚህ ዘመን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን መክፈል ብቻ ሳይሆን፤ በአንድ መስመር ላይ ለዛውም የተጋነነ የወደብ ኪራይ ዋጋ እየከፈለች፤ ምስጢሯን ለመሸፈን አዳግቷት በትንሿ ጅቡቲ ላይ የተንጠለጠለች ሀገር አማራጭ የባሕር በር በጣም ያስፈልጋታል። ቀጣዩ ትውልድም ያለአማራጭ የባሕር በር እንዲኖር መፍረድ በቀጣይ ዓለም ላይ ሊኖር ከሚችለው ፉክክር አንፃር ሀገር ላይ ታሪካዊ በደል መፈፀም ነው።
ዛሬ ካልሆነም ነገ ኢትዮጵያ አማራጭ የባሕር በር ማግኘት የግድ ያስፈልጋታል። ወደ ፊት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ወይም በአፍሪካ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ትችላለች የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያ ጥንት እንደነበረው በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የመቻል ዕድል እና አቅሙ አላት። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አትችልም። አንድ ነገር ይጎድላታል። እርሱም የባሕር በር ነው። አማራጭ የባሕር በር ያስፈልጋታል።
ቀጣዩ ነገር ኢትዮጵያ እንዴት የባሕር በር ታገኛለች የሚለው ነው። ለእዚህ ደግሞ ብዙ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ አቅጣጫዎች እየታዩ ስለመሆናቸው እየሠማን እንገኛለን። በእርግጥ ቃሉ መነገሩ እንደነውር የሚታይበት ዘመን አብቅቶ በድፍረት ስለባሕር በር እንነጋገር ከሚለው አልፎ፤ ከውስጥ የተነሳው ሃሳብ ወደ ውጭ ተላልፎ የባሕር በር ኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት ዓለም ማመን መጀመሩ ያስደስታል።
ቢቻል በቅርቡ ባይቻል ዘግየት ብሎም ቢሆን አሁን እየተሄደበት ካለው አቅጣጫ አንፃር ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ። ለእዚህ ሁላችንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን በየተሠማራንበት ቦታ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት ማድረግ አለብን እላለሁ። ሠላም!
ፌኔት ኤሊያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም