አሜሪካዊውን ባለሥልጣን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ክስ ቀረበበት

አሜሪካዊውን የጤና መድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሪያን ቶምፕሰንን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ሉዊጂ ማንጂዮን የግድያ ክስ እንደተመሠረተበት የኒውዮርክ ግዛት አስተዳዳሪ ገለጹ። ማንጃዮኒ የአንደኛ ደረጃ ግድያ እና ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ግድያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች ቀርበውበታል። ከእነዚህ መካከል አንዱ “የሽብር” ተግባር የተላበሰ ግድያ የሚል መሆኑን ብራግ ተናግረዋል።

የኒውዮርክ አውራጃ ዓቃቤ ሕግ አልቪን ብራግ እንደተናገሩት “ዓላማው ሽብርን ማስፋፋት ነበር” ከማለት ባለፈ ተኩሱን “አስፈሪ፣ በሚገባ የታቀደበት እና ዒላማውን የጠበቀ ግድያ” በማለት አስረድተዋል። ማንጃዮኒ በተከሰሰበት ክስ ወደ ኒውዮርክ ተላልፎ ይሰጥ እንደሆነ ለመወሰን ታኅሣሥ 19 ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀጠሮ ተይዟል። ተጠርጣሪው ተላልፎ መሰጠቱን ላይቃወም እንደሚችል ብራግ ጠቁመዋል።

“ተከሳሹ ችሎቱን ሊተው እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉን” ብለዋል ብራግ። በፔንስልቬንያ ውስጥ ከሽጉጥ ጋር የተያያዙ ክሶች ማንጃዮኒ ላይ በሚቀርብበት በተመሳሳይ ቀን የክስ ሂደቱ መርሐ ግብር እንደሚጀምር ቀጠሮ ተይዞለታል። ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ብራግ እና የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት ኮሚሽነር ጄሲካ ቲሽ በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ ብዙዎች ማንጃዮኒን ማሞገሳቸውን ተቃውመዋል።

“ቶምፕሰን ከተገደለ በኋላ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ፣ በደም የተጨማለቀውን ግድያ የሚያሞግሱ መኖራቸውን አይተናል። ግድያ አናከብርም እናም የማንንም መገደል ከፍ ከፍ አናደርግም” ሲሉ ጄሲካ ተናግረዋል። ተጠርጣሪው ከግድያ በተጨማሪ የጦር መሣሪያ በመያዝ እና በሐሰተኛ ማስረጃ ክስ ቀርቦበታል። በቀረበቡት የአንደኛ ደረጃ ግድያ እና ሁለተኛ ደረጃ የሽብር ግድያ ተግባር ከተፈረደበት ማንጃዮኒ ያለ ይቅርታ ዕድሜ ልክ እሥራት ሊተላለፍበት ይችላል።

ስለ ልዩ የሽብርተኝነት ክሱ የተጠየቁት ብራግ “ይህ ሽብር ለመቀስቀስ ታስቦ የተደረገ ግድያ ነው” ሲሉ መልሰዋል። የዩናይትድ ሄልዝኬር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቶምፕሰን በጥይት ተመትተው ከተገደሉ ከአምስት ቀናት በኋላ ማንጃዮኒ በአልቶና ፔንሲልቬንያ በሚገኘው ማክዶናልድ ውስጥ በሐሰተኛ መታወቂያ እና “ሽጉጥ” ይዞ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ተናግሯል።

ጠበቃው ቶማስ ዲኪ በበኩላቸው የማንጃዮኒን ሽጉጥ ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኘውን ማስረጃ አላየሁም ብለዋል። የኒውዮርክ ዓቃብያነ ሕግ ባለፈው ሳምንት በማንጃዮኒ ላይ የክስ ማስረጃቸውን ለዳኞች ማካፈል ጀምረዋል። የ26 ዓመቱ ማንጃዮኒ ተላልፎ ከተሰጠ በሪከር ደሴት ወይም በሌላ የኒውዮርክ እስር ቤት ሊታሰር ይችላል። በማንጃዮኒ ላይ የቀረበው ማስረጃ በወንጀል ቦታ ከተገኙት ጋር የጣት አሻራ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ያካትታል ሲሉ ኮሚሽነር ጄሲካ ተናግረዋል።

ብራግ በበኩላቸው ተጠርጣሪው ኒውዮርክ ደርሶ በማንሃተን ሆስቴል ውስጥ የውሸት መታወቂያ በመጠቀም ለ10 ቀናት ከቆየ በኋላ ቶምፕሰን ላይ ጥቃቱን ፈጽሟል። ማንጃዮኒ በቁጥጥር ስር ሲውል ሽጉጥ፣ ሐሰተኛ መታወቂያ፣ ፓስፖርት እና “ተነሳሽነት እና አስተሳሰብን” የሚያመለክት በእጅ የተጻፈ ሰነድ መገኘቱን ፖሊስ ተናግሯል።

በኒውዮርክን የተከፈቱ ክሶችን በተመለከተ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኒውዮርክ ፖሊስ የመርማሪዎች ዋና አዛዥ ጆሴፍ ኬኒ በኅዳር ወር ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ለልጇ መጥፋቱን ሪፖርት ካደረገችው ከተጠርጣሪው እናት ጋር ግንኙነት መፈጠሩን ጠቁመዋል። እንደ ኬኒ ገለጻ እናቱ ልጇን ተጠርጣሪው ስለመሆኑ ባታውቅም ግን “እሱ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ሊሆን ይችላል” ስትል ተናግራለች።

ማንጃዮኒ በሐሰተኛ ማስረጃ፣ መሣሪያን ያለፍቃድ በመያዝ፣ መዝገቦችን ወይም መታወቂያዎችን በማበላሸት፣ የወንጀል መሣሪያዎችን በመያዝ እና ለፖሊስ የሐሰት መታወቂያ በመስጠት ወንጀል በፔንስልቬንያ ውስጥ ክስ ተመስርቶበታል። ማንጃዮኒ የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ውሳኔን በሃንቲንግዶን ግዛት፣ ፔንስልቬንያ ውስጥ ባለው የሃንቲንግዶን ስቴት ማረሚያ ተቋም ሆኖ ይጠብቃል። ተከሳሹ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You