በማውገዝ ስም ማስተዋወቅ

ባለፈው ሳምንት በአንዱ ዕለት ጠዋት ወደ ሥራ በሚወስደኝ የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ የተከፈተው የኤፍ ኤም ሬዲዮ በሀገራችን ባህልና ወግ ነውር ስለሆነ አንድ ድርጊት እያወራ ነው፡፡ በእርግጥ የዜናው ዓላማ ነገርየውን ማውገዝ ነው፡፡ በዕቅድ ተይዞ የተሠራ ዜና ነው፡፡ ከባህልና ወጋችን ጋር የማይሄድ፣ በሞራል እና በየትኛውም ሃይማኖት የተወገዘ መሆኑን መግለጽ ነው። ዜና አንባቢዋ ይህን የምትናገረው ግን ለኢትዮጵያ እናቶችና አባቶች ሰቅጣጭ የሆነውን እንግዳ ቃል እንደወረደ በመጥራት ነው፡፡

ገና ቃሉን ስሰማው ምቾት ስላልሰጠኝ ምናለ በዚህ ቃል ባይናገሩት እያልኩ ነበር፡፡ ሆኖም እኔ በጣም ወግ አጥባቂ ስለሆንኩ ይሆናል እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት ከኋላዬና ከፊቴ ያሉ ሰዎችም (ለዚያውም ወጣት ሊባሉ የሚችሉ) ‹‹ኤጭ!›› እያሉ አገላለጿን ሲወቅሱ ሰማሁ፡ ፡ ቀጥለውም ጉዳዩን በዚህ ልክ ጉዳይ ማድረግ ልክ አለመሆኑን አብረው የተቀመጡ ሰዎች ሲያወሩበት ሰማሁ፡፡ ፍርሃታቸው እንዲህ እንዲህ እያለ ቃሉ እየተለመደ ይሄድና አስፈሪነቱ ሊቀር ይችላል የሚል ነው፡፡

በእርግጥ ጋዜጠኛዋ ስሙን ሳትናገር ዜናውን መሥራት ላይመች ይችላል፡፡ ‹‹ታዲያ በምን ቃል ይገለጽ?›› የሚል ክርክር ያስነሳል፤ በዜና ቋንቋ ደግሞ በግልጽ እንጂ በቅኔ አይነገርም፡፡ ትዝብቴ፤ ምንም በሌለበት ጉዳዩን አጀንዳ ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሚለው ነው፡፡ ምንም በሌለበት ማለቴ፤ ድርጊቱ በፍጹም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር አይችልም በሚል እርግጥኝነት ሳይሆን፤ አጀንዳ ሊያደርገው የሚችል ወቅታዊ ክስተት በሌለበት ለማለት ነው፡፡

ሰመረ ባሪያው የሚባለው የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅ በአንድ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሰጥ የሰማሁት አስተያየት ጥሩ ሆኖ አግኝቸው ነበር፡፡ ደጋግሞ በማውራት አጀንዳ ባናደርገው የሚል ነበር! አጀንዳ መሆን ያለበት ነገርየው አፍጦና አግጦ ከወጣ በኋላ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን እና የሚወሰዱ ርምጃዎችን ለማሳወቅ ቢሆን፡፡ አለበለዚያ ግን ነውር መሆን ለመናገር ብቻ ብሎ አጀንዳ ማድረግ ነገርየውን ማስተዋወቅ ነው፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ባህልና ወግ፣ በሃይማኖት ነውር መሆኑን አድራጊዎችም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

የብዙዎቻችን ስህተት የትርክትን ኃይል ልብ አለማለት ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለማስተማር ተብሎ የሚደረጉ ነገሮች ድንበራቸውን ያልፉና ማስተዋወቅ ወይም ያላሰቡትን ማስተሳሰብ ይሆናል፡፡ ሁለት ገጠመኞችን ላንሳ፡፡

ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለን (1990ዎቹ) የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎችን ሳይቀር እየሰበሰቡ ስለኮንዶም አጠቃቀም ማስተማር ፋሽን ሆኖ ነበር፡፡ አብዛኞቻችን እኮ በወቅቱ ኮንዶም የሚበላ ይሁን የሚጠጣ አናውቅም፡፡ ወሲብም ጉዳያችን አልነበረም፡፡ አምናለሁ ሥነ ተዋልዶን ከልጅነት ጀምሮ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዳሩ ግን ዕድሜና ሁኔታዎች (ዓውድ) ሊወስነው ይገባ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ግን ያስተማሩን መስሏቸው የማናውቀውንና ያላሰብነውን ነገር እያስተዋወቁን ነበር፡፡

ከትምህርት ቤት መልስ፤ ከእኛ በዕድሜ ከፍ የሚሉ ልጆች ወሬያቸው ሁሉ ወሲባዊ ነገሮች መሆን ጀመረ፡፡ በተለይም 7ኛና 8ኛ ክፍል አካባቢ ላሉት ደግሞ ጭራሽ ማነሳሳት ሆነ፡፡ ምንም እንኳን ተፈጥሮ በራሱ የሚያነሳሳ መሆኑ ቢታወቅም፤ በማስተማር ስም የሚደረጉ ማነሳሳቶች ግን ከሚያስተምሩት ይልቅ የሚያበላሹት በልጦ ነበር፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከዓመታት በፊት በአንድ ሆቴል ውስጥ ተማሪዎችን ለማስተማር ተብሎ በታየ የመድረክ ድራማ ላይ ተማሪዎች የሰጡትን የቁጣ ግብረ መልስ ያስተዋልኩበት ነው፡፡ በድራማው ላይ ለማስተማር ተብሎ ጫት ይቃማል፣ ሲጋራ ይጨሳል፡፡ ዓላማው ጫትና ሲጋራ መጥፎ ነው ለማለት መሆኑ ነው፡፡ ልጆቹ ግን ከፊታቸው (ለመድረኩ ቅርብ ስለነበሩ) ‹‹ሲጋራ አጨሳችሁብን!›› ብለው ተቆጡ፡፡ እነዚህ ልጆች ከድራማ ሰሪዎቹ በላይ የሲጋራን ጉዳት ያውቃሉ ማለት ነው፡፡ ደግሞስ ባዶ ወረቀት (ትንባሆ የሌለው) ጠቅልለው በመለኮስ ለማሳየት ያህል ብቻ አይበቃም ነበር ወይ?

ትርክት ኃይል አለው፡፡ አንድን ነውር ነገር ደጋግሞ አጀንዳ ማድረግ ለማያውቁት ሰዎች ጭምር ማስተዋወቅ ነው፡፡ እናቶቻችንና አባቶቻችን ከቅርብ ዘመን ወዲህ እየተደረጉ ነው የሚባሉ ነውር ነገሮችን አያውቁም፤ ሲሰሙ ‹‹እንዲህም ይደረጋል እንዴ?›› እያሉ ቤት ውስጥ ልጆች ባሉበት የመገረም አጀንዳ ያደርጉታል ማለት ነው፡፡

አንድ ነገር የሚጀመረው ከድርጊቱ በፊት አዕምሮ ውስጥ በማሰብ ነው፡፡ እንደዚያ አይነት ነገር መኖሩን ለማያውቁ ሰዎች በማስተዋወቅ ነው፡፡ ሰዎች በተፈጥሮ ሊሆን አይችልም ብለው ያመኑትን ነገር፤ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋወቅ መገፋፋትም ጭምር ነው፡፡

የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በባህሪያቸው ለሁሉም ተደራሽ ናቸው፡፡ ልጁም አዋቂውም፣ የተማረውም፣ ያልተማረውም የሚከታተላቸው ናቸው፡፡ ጋዜጣ፣ መጽሔትና መጽሐፍ በዕድሜም ሆነ በትምህርት ደረጃ ከፍ ያለ ሰው ስለሆነ የሚያነባቸው ቢያንስ ክፉ ደጉን መለየት ይችላል፡፡ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ግን ከምሁር እስከ ሕጻናት የሚከታተሏቸው ናቸው፡ ፡ ቃሉ ሲጠራ የሰሙ ሕጻናትና ልጆች ‹‹ምን ማለት ነው?›› ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ምን ማለት እንደሆነ ሲነገራቸው ሊደረግ እንደሚችል አወቁ ማለት ነው፡፡ በሂደት መደበኛ (ኖርማል) ሊያደርጉት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

በአውሮፓና አሜሪካ ነጮች ይደረጋሉ የሚባሉ ኢ-ተፈጥሯዊ የሆኑ ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ የማይደረጉት በሕግ ክልከላ ብቻ ሳይሆን በሞራልና ባህል ነውርነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነዚያ ቃላት ጋር ስላልተለማመደ ነው፡፡ ቃሉ ራሱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ድርጊቱን በተደጋጋሚ መግለጽ ነገርዬውን ማስተዋወቅ እየሆነ ነው፡፡

እርግጥ ነው እኔ በጣም ወግ አጥባቂ ሆኜ ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን በኢትዮጵያ ሕግ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ሞራል የተከለከለ ነው እስከተባለ ድረስ ቃሉም ነውር መሆን አለበት፡፡ ከምንም በላይ ግን ልብ መባል ያለበት ነገር፤ ነገርዬውን እንዳይኖር የሚያደርገው ከክልከላ በላይ በየሬዲዮ ጣቢያው አጀንዳ አለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ከነ ስሙ እንኳን የማያውቁት ሁሉ እንዲያውቁት እየሆነ ነው፡፡

ዝም ማለት ነገሩን አያስቀረውም፤ እንዲያውም ማስፈራራትና ደጋግሞ ማውገዝ ይሻላል፤ አለበለዚያ እንደ ቀላል እየታየ ይሄዳል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ፍርሃታቸው ልክ ነው፤ ጥያቄው ግን መቼ ተፈቀደና ነው መከልከሉን የምንናገር? የሚለው ነው፡፡ እንኳን በእንደ ኢትዮጵያ አይነት ሃይማኖታዊ ሀገር፣ በብዙ የዓለም ሀገራት እኮ እንደ ነውር የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ የተከለከለ መሆኑን ማሳወቅ አለብን የሚለው በተዘዋዋሪ ማስተዋወቅ ይሆናል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የተከለከለ መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡

ከዚያ ይልቅ ለእንዲህ አይነት ነገር አጠራጣሪ የሆኑ ቤቶችንና የወንጀል ድርጊቶችን ማጋለጥና የተወሰደውን ርምጃ ማሳወቅ ሳይሻል አይቀርም፡፡ በተቻለ መጠን ግን እንዲህ አይነት ነገሮች የሚነገሩበት ሚዲየምና ሰዓት ጥንቃቄ ቢደረግበት ይሻላል፡፡ የቃላት አጠቃቀም ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል!

 

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You