የካበተ ልምድ ውጤቶች

ህልማቸው ግቡን እስኪመታ ልምድ ፍለጋ ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ አልፈዋል። የቀሰሟቸው ልምዶችና ተሞክሮዎች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መሠረት ሆኗቸዋል፤ ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፤ የዛሬ የስኬት አምድ እንግዳችንን የአማሔ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አየለ፡፡

አቶ ዮሐንስ ትውልድና እድገታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ፐርቼዚንግ ኤንድ ሰፕላይ ማኔጅመንት ዲፕሎማ ቀጥሎም በማኔጀመንት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በተመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ተቀጥረው የመሥራት ፍላጎት ብዙም አልነበራቸውም፤ ለዚህም ነው ከሥራው ጎን ለጎን በግል የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰሩ የቆዩት፡፡

በተለይ ከጓደኞቻቸው ጋር የህንጻ መሳሪያ መሸጫ ከፍተው ሰርተዋል፡፡ የህንጻ መሳሪያዎችን በመሸጥ አሃዱ ብለው የጀመሩትን የግል ሥራ፣ በሂደት ወደ ተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመቀየር የኤሌክትሪክ ሥራዎች፣ የገልባጭ መኪና ትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኮንስትራክሽን እና የጤና ሥራዎች ዳይሬክተሪዎች የሥራ ዘርፎች ላይ ሰርተዋል።

‹‹ከያዝኩት ቢዝነስ ውጭ አራት ዓይነት ቢዝነሶች ሰርቻለሁ፡፡ ሁሉም ቢዝነሶች ለትርፍ ሳይሆን ልምድ ለማግኘት ስል የሰራኋቸው ናቸው፡፡ ትንሽ ነገር ስትጀምር ብዙ መሰዋዕትነት ሊያስከፈል ቢችልም አሰቦ ከተገባበት በደንብ መማርና ልምድ ማግኘት የሚቻልበት ነው›› ይላሉ፡፡

ሥራ ሲቀጠሩም ብዙ ውስብስብ ችግሮች ያሉባቸው መሥሪያ ቤቶች ምርጫው እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በዚያ ከሚያጋጠሟቸው ችግሮች ብዙ መማር መፈለግ ነው። በዚህም በብዙ ችግሮቹ የተነሳ ሊዘጋ ጫፍ የተቃረበ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሰርተዋል፡፡ የድርጅቱን ችግሮች በደንብ ነቅሰው በማውጣትና በማስተካከል ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ይገልጻሉ፤ በዚህ ውጤታማነታቸው የድርጅቱ ቦርድ አመራር ሆነው ተመርጠው መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ ድርጅቱ ስገባና ዘርፈ ብዙ ችግሮቹን ስረዳ ዩኒቨርሲቲ የገባሁ ያህል ነው የቆጠርኩት›› ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁን ላለሁበት ደረጃ መሠረተ የሆነኝን ትልቅ ልምድ ያገኘሁትም በዚያ ወቅት ነው ይላሉ፡፡

ተቀጥረው በሚሠሩበት ድርጅት የሥራ መኪና እያላቸው፣ ጥሩ ደመወዝ ተከፋይ ሆነውም እሳቸው ግን ሥራውን መልቀቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ የዚህ ዋና ምክንያታቸው ደግሞ በግላቸው ሠርተው ጥሩ ደረጃ ላይ የመድረስ ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አላማቸው ግብ እስኪደርስ በመጣር የዛሬን ሳይሆን የነገን በማሰብ ደስ ብሎቸው ይሠራሉ፡፡ ቤተሰብ እያለህ እንዴት ያንን የመሰለ ሥራ ትለቃለህ ሲሉ የጠየቋቸው እንደነበሩም አስታውሰው፣ እሳቸው ግን ሥራ የሚለቁት የዛሬ ሳይሆን የነገ እየታያቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም የሚመጣውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል ወስነው ሥራቸውን ለቀው ወደ ራሳቸው ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ ቀደምት ሥራዎቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈልጉት ልክ ለማስኬድ እንዳልቻሉ አስታውሰው፣ ችግር ፈቺ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዲሁም ያካበቱትን ልምድ ይዘው የጀመሯቸውን ሥራዎች ማስቀጠል አሊያም ደግሞ ሙሉ በሙሉ አቁሞ ወደሚቀጥለው መሻገር ይፈልጋሉ፡፡ ይህም የሕይወት መርሃቸው ወደፊት መስፈንጠር እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ፡፡

እናም መፍትሔ ለማምጣት በማሰብ ብዙ ካፒታል፣ ቦታና የሰው ኃይል የማይጠይቅ የጎጆ ኢንዱስትሪ መሥራት አለብኝ ብለው የገቡበት ሥራ ውጤታማ መሆን አስችሏቸዋል፡፡ ለዚህም በቅድሚያ ጥናት አድርገዋል፡፡ ‹‹ ይህን ለመሥራት የሚያስችለኝ በቂ ልምድና ቦታ ስላለኝ በትንሹ ተጀምሮ ወደ ትልቅ የሚያድግ የጎጆ ኢንዱስትሪ ለመሥራት ተነሳሳሁ፤ ጥናት ሳደርግ ሰምቼው ለማላውቀው ለምድጃና ለምጣድ ግብዓት የሚሆን ‹‹ሬዚስታንስ›› ማምረት ወሳኝ ሥራ ሆኖ አገኘሁት›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ ሥራ የጀመሩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሬዚስታንስ›› ሀገር ውስጥ ለሚመረቱ የኤሌክትሪክ ምድጃዎችና የኤሌክትሪክ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ግብዓትነት የሚውል ነው፡፡ የምርቱ የጥራት ደረጃ የሚወሰነው በሬዚስታንስ ምርቱ ነው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ሬዚስታንስ ለማምረት ባለሙያዎች በማማከር ብቻ ቴክኒካል እውቀቱ ሳይኖራቸው በይቻላል መንፈስ በድፍረት ወደ ሥራው መግባታቸውን አቶ ዮሐንስ ያመላክታሉ፡፡ ባደረጉት ጥናት የምርቱ የጥራት ችግር ሀገሪቱ ላይ ያለ ትልቅ ችግር መሆኑን ተረድተዋል። ይህን ችግር መፍታት እችላለሁ ብለው ቆርጠው ተነሱ፤ ችግሩን ለመፍታትም አቅማቸውን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተዋል፤ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ የሚያደርስ ቢዝነስ ለመሥራት በማሰብ የዛሬ መዳረሻውን ጉዞ መጀመራቸውን አጫውተውናል፡፡

አቶ ዮሐንስ፤ ከጓደኞቻቸው ጋር የሰሯቸው አራት ቢዝነሶች ካፒታል፣ እውቀትና የሚመጣውንም አደጋ ለመጋራት የሚያስችል ልምድ ለማግኘት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ በዚህም በትክክልም የፈለጉትን ልምድ ማግኘት ችለዋል፤ አላማቸውን ለማሳካት ረድቷቸዋል፡፡ ልምድና እውቀቱ በቂ ሆኖም የአሁኑን ሥራቸውን ብቻቸውን እንዲጀምሩትም አስችሏቸዋል።

በሁለት ሺ ብር ካፒታል የጀመሩትን ይህን ሥራ ለመጀመር ሲነሱ ሰው የሰጣቸውን የተበላሸ ማሽን ለማሠራት ዘጠኝ መቶ ብር አውጥተዋል፤ ጥገናውም ሦስት ወራት ወስዷል፡፡ ይህ ማሽን አዲሱ በ600 ብር ሊገዛ ይችል ነበር፤ እሳቸው ግን ይህን ያወቁት ቆይተው ነው፡፡ ለአሮጌው ማሽን ጥገና የወጣውንና ለማስጠገን የወሰደውን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡት ሁሌም ይገርማቸዋል፡፡

ምርቱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ አምርተው ወደ ገበያ ለማቅረብ ጥሬ እቃዎች ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች፣ አቅራቢዎችና የተረካቢዎች ለማግኘት የሚያስችል ጥናትም አካሂደዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ጨርሰው ወደ ሥራው ሲገቡ ሌላ ፈተና ገጠማቸው፡፡ ይህም ሰዎች በቢዝነስ ላይ ብዙ ጊዜ የሚያዩት የሥራውን ጥራት ሳይሆን የሚሠራውን ሰው አቅም ወይም ካፒታል መሆኑን ይረዳሉ፤ ለዚህም መፍትሔ ለማምጣት ወዲያውኑ ጥናት ወደ ማድረግ ገቡ፤ በዚህም መላ ፈጥሩ፡፡

በዚህም ደረጃውን የጠበቀ ቢዝነስ ካርድ በማሳተም እና ማስታወቂያ አሠሩ፤ ለድርጅቶች በመስጠትም ራሳቸውን የሽያጭ ባለሙያ በማድረግም እያስተዋወቁ መሸጥ ውስጥ ገቡ፡፡ ይህን ያደረጉት በምርቱ ጥራት ስለሚተማመኑና ራሳቸው እያስተዋወቁ ቢሸጡ የበለጠ ጥሩ ነው ብለው በማሰባቸው ነው፡፡

ለምርቱ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ከመግዛት ጀምሮ አምርቶ ለተጠቃሚዎች እስከ ማቅረብ ድረስ ያለውን ሥራ ብቻቸው ይሠሩ እንደነበር አስታወሰው፤ ምርታቸው እየታወቀ ሲመጣ ከስድስት ወራት በኋላ ሌላ አንድ ሰው መቅጠራቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሥራው መሸከምን ጭምር የግድ ይል ነበር፤ ከ30 እስከ 40 ኪሎ ግራም የሚደርስን ምርት በሌላ ሰው ለማድረስ ለማምጣት የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፤ ተሸካሚ ላይገኝም ይችላል። ስለዚህ የግድ ራሴ ተሸክሜ አደርሳለሁ›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ሪዚስታንሱን ማምረት የጀመረው ከ11 ዓመት በፊት በ2006 ዓ.ም ነው፡፡ ሥራው ሲጀምርም ዮሐንስ አየለ የቤት ውስጥ መገልገያ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ማምረቻ በሚል ድርጅት ስም ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም የአማሔ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል ስያሜ ከሬዚስታንስ ምርት በተጨማሪ ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ እንጀራ ምጣዶችንና የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን ወደ ማምረት አድጓል፡፡ ድርጅታቸው ሥራውን በምርምር እና በዲዛይን በማጎልበት ለሀገርና ለተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚጠቅም የሬዚስታንስ ምርት የጥራት ደረጃ ስታንዳርድ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል፡፡

ድርጅታቸው በዚህ ሥራውም ከተለያዩ ተቋማት እውቅናና የምስክር ወረቀት ማግኘቱን አቶ ዮሐንስ ጠቅሰዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በኤሌክትሪክ ምድጃዎች እና እንጀራ ምጣድ ምርት በሀገራችን ቀዳሚነት ያለው ኃይል ቆጣቢ፣ ጥራት ያለው እና የተሻለ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬትና ዋንጫ አግኝቷል፡፡ የግርግዳ ተለጣፊ ምጣድን ተጣጣፊ፣ ተንቀሳቃሽ ለአጠቃቀም ምቹና ሳቢ አድርጎ በመሥራቱም ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ የባለቤትነት መብት ተሰጥቶታል፡፡

ድርጅቱ ኃይል ቆጣቢ ምርቶችን በተለያዩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በሚያዘጋጇቸው ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በቀዳሚነት ተመራጭ እየሆነ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት የድርጅቱን የቢዝነስ እቅዶች በመመልከት በጎሮ አካባቢ የማምረቻ ቦታ ሰጥቶታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 250 የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ምጣዶችንና ምድጃዎችን ያመርታል፡፡ ምርቶቹንም በሁለት ማከፋፈያ ሱቆችና በሀገሪቱ ባሉ በሁሉም ሱፐር ማርኬቶች ተደራሽ አድርጓል፡፡ ከ35 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡

‹‹ምርቶቻችን በምርምር ላይ በተደግፈ መልኩ ስለሚሠሩ በጥራት፣ በኃይል ቆጣቢነትና በምንሰጣቸው አገልግሎቶች ተመራጭ ናቸው›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ ለአብነት ምጣዶች ብንመለከት አብዛኛው በሀገር ውስጥ የሚሠራው ምጣድ ገበያ ከሚገኝ አልሙኒየም የሚሠራ ነው ይላሉ፡፡ ድርጅቱ ግን ለምግብ ተስማሚ ከሆኑ አልሙኒየሞች እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ ተሟሽተው ሁሉ ነገር አልቆላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ምጣዶች ለገበያ እንደሚያቀርብም ተናግረዋል፡፡ የተጠቃሚን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ 12 ዓይነት ምጣዶች እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ይህ መሆኑም ተጠቃሚዎች ከቦታ፣ ከዲዛይንና ከዋጋ አንጻር አማራጭ እንዲኖራቸው ማድረግ ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ የእአምሯዊ ንብረት የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ያገኘ የመጀመሪያው የግርግዳ ተለጣፊ ምጣድ አምራች ነው። ምጣዱ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች የፈለጉበት ቦታ ላይ ወስደው እንዲሠሩበት ታስቦ ተሠርቷል፡ ግድግዳ ላይ አሊያም ሌላ ቦታ ላይ አድርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ዲዛይኑም ያማረ፣ ማንኛውም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል፤ ቦታ ቆጣቢ የሆኑ ምጣድ በማምረት የባለቤት መብት አግኝቷል።

‹‹ምርምር ላይ መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ስለምንሠራ ሁሉም ምርቶቻችን የጥራት ማረጋገጫና የባለቤትነት መብት ያገኘንባቸው ናቸው፡፡ ምርቶቻችን በሙሉ ተለጣፊ ምልክቶች ያሏቸው በመሆናቸው በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ቁጥጥር ያደረግባቸዋል፤ ሁሉም ምርቶቻችን በከፍተኛ ደረጃ ጥራት የሚያሟሉ፣ አማራጭን ያሰፉ እና የሰዎች ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ ችግር ፈቺ ናቸው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ አሁን ትኩረት የተሰጠው ለኃይል ቆጣቢ ምርቶች ነው፤ እሳቸውም ይህንን ይደግፋሉ፤ ወቅቱ የካርበን ልቀት ዓለማችንን በከፍተኛ ደረጃ እያሰጋ ያለበት ነው፡፡ እነዚህን ምርቶች በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የደን ጭፍጨፋው ይቀጥላል፡፡ በቀጣይም ምርቶቹ ከውጭ ከሚመጡት የተሻሉ እንዲሆኑ አድርጎ መሥራትን ያስፈልጋል፡፡

መረጃዎች ዋቢ አድርገው ሲያብራሩም የቤት ውስጥ መገልገያዎች ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚወስዱ አስታውቀዋል። እነዚህ ምርቶች ከግማሽ በላይ ኃይልን መቆጠብ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምድጃዎች ብዙ ሰዎች እንደሚጠቀሙባቸው ጠቅሰው፤ እነዚህ ምርቶች በሀገር ውስጥ የሚሠሩ ባለመሆናቸው ሲበላሹ ለመጠገን እንዲሁም መለዋወጫ ለማግኘት እንደሚቸግር ጠቁመዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶችም እንዲሁ ከፍተኛ ኃይል እንደሚበሉ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች የሚፈታ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ ማምረት ከተቻለ ብዙ ተጠቃሚ ማግኘት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

ምርቶቹ ካላቸው ከፍተኛ ጥራትና ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ በዋጋም ተመጣጣኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥራታቸው የተጠበቀ ሰፊ አማራጮችን የያዙ ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ ያላቸውና ዋጋም የተቀመጠላቸው መሆናቸውን አብራርተው፣ ተጠቃሚዎች በፍላጎታቸው መሠረት ገዝተው መጠቀም እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

ድርጅቱ በሁለት ሺ ብር ካፒታል ሥራውን የጀመረው ድርጅታቸው፣ አሁን ከፍተኛ መጠን ያለው ካፒታል ያለውና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ የደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የምጣዶቹ አጠቃላይ ስም የታቤጋ የሚባል መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ማዕድ፣ አገልግል፣ መሶብ፣ ማኛ፣ ሌማት እና የመሳሰሉት የተለያየ ሀገራዊ ስሞች የተሰጣቸው እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡

የማህበራዊ ኃላፊነቱ ከመውጣት አንጻርም ድርጅቱ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በበዓላት ወቅት እጅ ያጠራቸውን ማዕድ በማጋራት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በበርካታ ሥራዎች ላይ በመሳተፉ የእውቅና ሰርተፍኬቶች ተሰጥተውታል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት አማካኝነትም አነስተኛ ገቢ ላላቸውና በሴፍትኔት ለሚተዳደሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የጠበቁ ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ እያቀረበ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በቀጣይ ድርጅቱ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎቹን በማምረት ተደራሽነቱን ለማስፋት፣ በዚህም ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን ለማስቀረት ይሠራል፡፡ ለውጭ ገበያ ለማቅረብም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ ገበያ ለመግባት የመጀመሪያ ናሙና ተልዕኮ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ድርጅቱ ተግዳሮት የሆነበት ማስፋፊያ ቦታ እጦት፣ የውጭ ምንዛሪ እና የብድር አማራጮች ችግሮች ከተፈቱለት በኢንዱስትሪ ደረጃ በስፋት ምርቶችን ማምረት ይፈልጋል፡፡ ሦስትና አራት እጥፍ ማምረት የሚያስችለው አቅም ይፈጥራል፡፡ በዚህ ለ100 ያህል ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል፡፡ ህብረተሰቡ ኃይል ቆጣቢ ምርቶችን አውቆ ለይቶ ቢጠቀም ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታውን ከግማሽ በላይ መቆጠብ እንደሚችልም ጠቁመው፣ ተኪ ምርቶችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማስቀረት እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You