ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ፈተና ነበረባችሁ አይደል? ልክ አዲሱ ዓመት ሲገባ ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ ቃል በገባችሁት መሰረት ከስር ከስር በማጥናትና ትምህርታችሁን በአግባቡ በመከታተል ላይ እንደሆናችሁ አምናለሁ። ይህም በመሆኑ በፈተና ጥሩ ውጤት እንደምታመጡ እርግጠኛ ነኝ።
በትምህርት ቤታችሁ የባህል ቀን /culture day/ አክብራችኋል? ምን ዓይነት አልባሳትን ነበር የለበሳችሁት? የተለያየ ማለታችሁ አይቀርም። ልክ ናችሁ ። ምክንያቱም በአገራችንም ህዳር 29 ቀን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በመሆን በየዓመቱ ይከበራል።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ወይም የባህል ቀን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተሰብስበው የየራሳቸውን ባህል የሚያስተዋውቁበትና እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት እለት ነው። እናንተም ትምህርት ቤት በዓሉን ስታከብሩ ያያችሁት አዲስ ባህል አልያም አለባበስ አለ? የማን እንደሆነስ ጠይቃችኋል?
አያችሁ ልጆች ኢትዮጵያ ማለት ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ ብዙ ዓይነት ባህል ያላቸው ሕዝቦች በአንድ የሚኖሩባት አገር ናት። ስለዚህ ስለማታውቁት አንድ ባህል አወቃችሁ ማለት በተዘዋዋሪ ስለራሳችሁ አወቃችሁ ማለት ነው። እናም ሁሌም አዲስና የማታውቁትን አለባበስ፣ ጭፈራ፣ አመጋገብ፣ ቋንቋ ስታዩ ሆነ ስትሰሙ ስለዛ ባህል በደንብ ለማወቅ መጣር አለባችሁ።
ልጠይቃችሁ፤ ለምሳሌ እናንተ ቤት አንድ እንግዳ ቢመጣና ቤታችሁን ዞር ዞር እያለ እየተመለከተ፤ «ቤቱ ውስጥ ማን ማን ይኖራል?» ብሎ ቢጠይቃችሁ አላውቅም ትላላችሁ እንዴ? አትሉም። ለምን ቢባል ቤታችሁን በደንብ ጠንቅቃችሁ ስለምታውቁ «እገሌ እገሌ ይኖራል» ብላችሁ መልስ ትሰጣላችሁ። እንግዳው የሚጠይቀውንም ሁሉ በትክክል መመለስ ትችላላችሁ። ለአገራችሁም እንደዛ መሆን አለባችሁ። ልክ እንደ ቤታችሁ አገራችሁም የእናንተ ናት። ስለዚህ አገራችሁን በደንብ ማወቅ ይጠበቅባችኋል።
ብዙ እውቀትን ስታገኙ የትም አገር ብትሄዱ ስለአገራችሁ በደንብ አድርጋችሁ የምትናገሩ ሰዎች ትሆናላችሁ። ሌሎችም ወደ አገራችሁ መጥተው ምንም ነገር ቢጠይቋችሁ «አላውቀውም» አትሉም፤ ትነግሯቸዋላችሁ። እናም አዲስ ባህል፣ አዲስ አለባበስ፣ አዲስ ጭፈራና ሌሎችንም ስትመለከቱ፤ የራሳችሁ ስለሆነ ማወቅ የምትፈልጉትን ሁሉ ጠይቁ፤ ከዛም አልፎ መጻሐፍትን አንብቡ።
ዛሬ ስለብሔር ብሔረሰቦች አይደለ የምናነሳው? የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ነው የተከበረው። ለመሆኑ ዘንድሮ የት እንደተከበረ አውቃችኋል? አዲስ አበባ ላይ ነው። በ1999ዓ.ም የመጀመሪያው የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም በአዲስ አበባ ነበር የተከበረው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ሦስተኛውን እና አምስተኛውን የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ተቀብላ አክብራለችም። አሁን አራተኛዋ ነው ማለት ነው። ከዛ ውጪ በዓሉ በሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር እንዲሁም አፋር ተከብሯል።
የበዓሉ አከባበር ታድያ በዋናነት የባህል ትርዒት የታየበት ነው። እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ የየራሱን ባህል በአደባባይና በመድረክ አሳይቷል። በዓሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላት ወደ አንድ ቦታ የተሰበሰቡት የባህል ቡድኖችና የየብሔረሰቡ ተወላጆችም እርስ በእርስ የተተዋወቁበት፤ አብረውም ጥሩ ጊዜ ያሳለፉበት ነበር። ከስድስተኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ጀምሮ ደግሞ አዘጋጅ ከተሞች የተለያዩ አስደናቂና አዳዲስ ሥራዎችን ለእንግዶቻቸው አቅርበው ነበር። ለምሳሌ በስድስተኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፤ 4.6 ሜትር ቁመት ያለውና 16 ቶን የሚመዝን ግዙፍ ጀበና ለእይታ ቀርቧል። ይህም ጀበና 11 መቅጃ ቧንቧዎች ነበሩት።
ልክ እንደዛው ሁሉ ባህርዳር ከተማም ተራዋ ሲደርስ ብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ስታሰናዳ፤ 5ሜትር ርዝመት ያለው ረጅምና ሰፊ መሶብ ለእይታ አቅርባለች። ባህርዳርን በመከተል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዓሉ የተከበረ ሲሆን፤ በዚህም 400 ሊትር ወተት መያዝ የሚችል «ጎረፍ» ወይም ለግመል ወተት ማቅረቢያነት የሚያገለግል ባህላዊ እቃ ተዘጋጅቶ በጊዜው ብዙዎችን አስደንቆ ነበር።
ጋምቤላም እንዲሁ በተመሳሳይ እንግዶቿን ተቀብላ ስታስተናግድ በርከት ያሉ ጎጆ ቤቶችን ለእንግዶች ማረፊያ በልዩነት ሠርታ አቅርባለች። ሐረር ከተማ ከጋምቤላ ተቀብላ ስታስተናግድ ደግሞ ግዙፍ አገልግል ሠርታ አሳይታለች። ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የተገኘችበት የአፋር ምድር ላይ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር ደግሞ ምን ተሰራ መሰላችሁ? በባህላዊ አልባሳት ያሸበረቀና ዙሪያውን በቆዳ የተለበጠ ትልቅ ጎጆ ነው ለእይታ የቀረበው።
ዘንድሮ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ አይታችሁ ወይም ሰምታችሁ ከሆነ፤ «ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ» በሚል ሃሳብ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት ባህላዊ የቡና ስነስርዓት በመስቀል አደባባይ ተደርጓል። ይህ ሁሉ በብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሚደረገው ለምን ይመስላችኋል? አንደኛ አገራችን በብዙ ባህልና ውበት የታደለች አገር መሆኗን ለማሳየት ነው። በተጨማሪ ደግሞ በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ሰዎች ትኩረታቸውን ወደ አገራችን እንዲያደርጉ ያስችላል።
ልጆች! ልብ ብላችሁ ካያችሁ ከላይ የተጠቀሱት አስደናቂና ትልልቅ የእጅ ሥራዎች ጥቅማቸው ተመሳሳይነት አለው። ጀበናው፣ መሶቡ፣ አገልግሉ፣ ጎጆዎቹ፣ መጠጫው፣ ቡናው፤ ሁሉም የሚያስተላልፉት መልዕክት አንድ ዓይነት ነው። ምን እንደሆነ አወቃችሁ? መሰባሰብና አንድነትን ያሳያሉ። ለምሳሌ ጀበና እና ቡናን ስናይ፤ ቤተሰቦቻችን፣ የሰፈራችን ትልልቅ ሰዎች ቡና ሊጠጡ ሲሆን ይሰባሰባሉ። መሶብና አገልግሉም ልክ እንደዛው ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የመብላት ባህላቸውን ያመላክታል። ጎጆዎቹም አብሮ መኖርን ያሳያሉ።
ሌላ ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳይ ወይም እንዲህ አንድነትን የሚገልጽ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ከጓደኞቻችሁ ጋር ተጠያየቁ። መርሳት የሌለባችሁ ግን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተብሎ የሚከበረው የአገራችሁ የኢትዮጵያ ቀን መሆኑን ነው። የምታይዋቸው ብሔር ብሔረሰቦች የእናንተና የእኛ፤ እናንተና እኛም የእነርሱ፤ ሁላችንም ደግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን የምንሠራ ሕዝቦች ነን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ሊድያ ተስፋዬ