ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው:: ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብ ነው:: ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው:: ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መሽቶ በነጋ ቁጥር በሰላም አውለኝ፤ በሰላም አሳድረኝ ብሎ ፈጣሪውን ይማጸናል:: ሀገሩም በሰላም ውላ እንድታድር እንደየእምነቱ ይለምናል::

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ እና የሰላምን ዋጋ የተረዳ ነው:: ሆኖም የዘመን ጉድ የሆኑ ፖለቲከኞች ነን ባዮች የዚህን ኩሩ ሕዝብ የዘመናት ዕሴቶች ለመናድ ሲሯሯጡ ይታያሉ:: ልዩነቶችን ጌጡ አድርጎ የኖረውን ሕዝብ እርስ በእራሱ እንዳይተማመን እና እንዲጋጭ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመፍጠር በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ ያለመታከት በመሥራት ላይ ይገኛሉ:: እገሌ ነጻ አውጪ የሚል ታፔላ በመለጠፍ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለማባላት ሲታትሩም ይታያሉ::

በዚህም የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት አደጋ ላይ የጣሉና የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ሙከራዎችም ተከስተዋል:: በወለጋ፣ በሶማሌ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመተከልና በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በእነዚሁ የጥፋት ኃይሎች አማካኝነት በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ለአስከፊ ሕይወት ተጋልጠዋል::

ከሁለት ዓመታት በፊት በትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዶ በርካታ የሰው ሕይወት እና የሀገር ሀብት ጠፍቷል:: በጦርነት አሸናፊ መሆን አይቻልም እና ችግሩን በድርድር ለመፍታት ተችሏል::

ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል:: በተለይም መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል:: ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።

የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል::

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስጀመር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል። ይህ ሁሉ ጥረት ዛሬ ፍሬ ማፍራት ጀም ሯል::

በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላም የተመለሰው የትግራይ ክልል በጦርነት ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸውን ወጣቶች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እያደረገ ይገኛል:: በአሁኑ ወቅትም በክልሉ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን በአራት ወራት ውስጥ በተሃድሶ ሥልጠና ወደ ማኅበረሰቡ የመመለስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል::

በኦሮሚያ ክልልም ባለፉት ዓመታት በርካታ ግጭቶች ተካሂደዋል:: በዚህም የበርካታ ንጹሃን ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ሕዝብ ተፈናቅሏል፤ በአጠቃላይ አለመረጋጋት ተከስቶ ቆይቷል:: ሆኖም በተደረጉ ጥረቶች እራሱን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት ብሎ የሚጠራው አካል ለሰላም ቀናኢ ሆኖ ተገኝቶ ሰሞኑን ፊቱን ወደ ሰላም መልሷል:: በዚህም ክልሉ የተረጋጋ ሰላም አግኝቷል፤ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል:: ይህ ቡድኑ የወሰደው የሰላም አማራጭ ለሌሎች በጫካ ለሚገኙ ቡድኖች ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው::

በተመሳሳይም በአፋር ክልል ለረጅም ጊዜያት ያህል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ አካላትም የሰላም መንገድ መርጠው ተመልሰዋል:: በተመሳሳይም የቅማንት እና ጉሙዝ ታጣቂ ችግሮቻችን የሚፈቱት በሰላም እንጂ በጦርነት አይደለም በሚል መሣርያቸውን አስቀምጠው ማረሻ እና ሞፈር ጨብጠዋል::

የእነዚህ ቡድኖች ድርጊት የሚበረታታ እና የሚመሰገን ነው:: አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን በመሣርያ ኃይል ማስመለስ እንደማይቻል እና ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ድርጊት ስለሆነ በአርአያነቱ የሚታይ ነው:: ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ አካላት በመጀመርያ የያዙትን መሣርያ አስቀምጠው የሕዝብን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ማረጋገጥ አለባቸው:: ይህ ሲሆን ለሕዝብ መቆማቸውን ማሳየት ይችላሉ::

ከዚህ በተቃራኒ ሕዝብን እየዘረፉ እና እያዋረዱ አለፍ ሲልም እየገደሉና እያቆሰሉ ለሕዝብ ቆመናል የሚል መታበይ በመጨረሻ የሚያስከትለው ውርደትን ነው:: ስለዚህም በየጫካው መሳርያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ለሕዝብ ክብር ሊሰጡ ይገባል:: በሕዝብ ስም እየማሉ እና እየተገዘቱ ለሕዝብ ቆመናል ማለት ጊዜ ያለፈበት ፋሽን መሆኑን መረዳት ይገባል:: ሰሞኑንም በአማራ ክልል የታየው ሀቅ ይኸው ነው::

ሰሞኑን የአማራ ክልል ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ለሰላም ጥሪ አድርጓል:: በግጭት እና በጦርነት መማረሩን በገሃድ ወጥቶ ተናግሯል:: በየጫካው የሚገኙ ቡድኖችም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፏል:: ባለፉት ዓመታትም በግጭቱ ምክንያት ታሞ መታከም እንዳልቻለ፤ ልጆቹን ትምህርት ቤት መላክ እንዳቃተው፤ አርሶ እራሱን እና ልጆቹን መመገብ እንደተሳነው በምሬት ገልጿል:: ቆመንለታል የሚሉ አካላትም በጥቅሙ እና በእድገቱ ላይ እንደቆሙበት ተናግሯል::

ስለዚህም የሕዝብን ጥሪ እና የሰላም መልዕክት መቀበል የግድ ሊል ይገባል:: ከሕዝብ በላይ አዋቂ ከሕዝብ በላይ መስካሪ የለም:: ጦርነት በቃኝ ፤ ሰላም ናፈቀኝ ካለ መብቱ ሊከበርለት ይገባል:: ሕዝቡ ጥቅሜ የሚከበርልኝ በጦርነት ሳይሆን በምክክር ነው ካለ የሕዝቡ ፍላጎት ቅድሚያ ሊሰጠው የግድ ነው::

ሕዝብ ሁልጊዜም ቢሆን ትክክል ነው:: ሕዝብ ምንጊዜም ቢሆን ሰላም ፈላጊ ነው:: ስለዚህም ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የራስን ፍላጎት በግድ መጫን ዞሮ ዞሮ ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፤ መጨረሻውም አያምርም:: የአማራ ክልል ሕዝብም ያስተላለፈው መልዕክት ይኸው ነው:: በአደባባይ ሰላም እንደናፈቀው ተናግሯል:: ስለዚህም ዛሬ ነገ ሳይባል የሕዝቡ ድምጽ ሊደመጥ ይገባል::

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You