የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ያደረገው አዋጅ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ በአካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው የፋይናንስ ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚያግዝ የብሄራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅደውን የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡ የብሄራዊ ባንክ አዋጁ በሙሉ ድምጽ፣ የባንክ ሥራ አዋጁ በሶስት ታቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቀዋል፡፡

ረቂቅ አዋጆቹ ከመጽደቃቸው በፊት ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን፣ ከምክር ቤቱ አባላትም ጥያቄዎች ቀርበው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በወቅቱም ምክር ቤቱ መርምሮ ያጸደቀውን የብሄራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የምክር ቤቱ የፕላን፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ደሳለኝ ወዳጄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ባንኩ ዋጋን ለማረጋጋት፤ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት ለማስፈንና ለኢኮኖሚው ዕድገት መፋጠን እና ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚረዳው አስረድተዋል፡፡

የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከርና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለመተግበር እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዳብራሩት፤ የሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆኖ ቆይቷል። የውጭ ባንኮች በመስኩ እንዲሰማሩ ባለመፈቀዱ በሀገር ውስጥ ባንኮች መካከል ፈጠራ የታከለበት እና በአዳዲስ አገልግሎቶች የታገዘ ውድድር አነስተኛ ሆኗል፤ ከውጭ ገበያውና ኢኮኖሚው ጋር ያለው ትስስር ዝቅተኛ በመሆኑ ባንኮች ብድርና የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው መጠን ማቅረብ አልቻሉም።

የባንክ ዘርፉ ዘመናዊ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን ያልተከተለ፣ ወቅቱን ያልዋጀ፣ ብቃትን፣ ጥራትንና ውጤታማነትን ያላማከለ የተደራሽነት ውስንነት፣ የግለሰቦችንና የተቋማትን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች እጥረት፣ የፋይናንስ ገበያ መሠረተ ልማት ውስንነት ያለበት፤ ከባንክ ሥራ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ ብዙ የሚቀረው መሆኑን አመልክተዋል።

አዋጁን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የኢትጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፤ አዋጁ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ሆኖ አንዲቀጥል ያስችላል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ አደረጃጀትና ዓላማ ግልጽ እንዲሆን ከሌሎች የአቻ ማዕከላዊ ባንኮች ልምድ በመውሰድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መመሪያዎችን መሰረተ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በማርቀቁ ሂደትም የእንግሊዝ የስዊዲን፣ የኬንያ የሩዋንዳና ሌሎች አገራት ባለሙያዎች መሳተፋቸውንና ከየሀገሮቹም ሰፊ ልምድ መወሰዱንም አስታውቀዋል፡፡

የባንኩ ገዥ እንዳብራሩት፤ አሁን የወጣው የባንኩ ዋና ቁልፍ ሥራ ምን እንደሆነ በግልፅ ያመላከተ ነው። የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ማስቻል፣ የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማ እንዲሁም ቀጣይነት ላለው እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ የባንኩ ሶስት ዋና ዋና ቁልፍ ዓላማዎች ናቸው።

አዋጁ የኢትዮጵያን የቆየ ማዕከላዊ ባንከ አሰራር ከሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች አሰራር ጋር እኩል እንዲጓዝ እንዲሁም የማዕከላዊ ባንኩን አሰራር ዘመናዊ የሚያደርግ እና በሕግ፣ በአዋጅ እና በሕገመንግስት ለሕዝቡ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት የሚያስችል አውድ ይፈጥራል።

የክሪፕቶ አሴትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የክሪፕቶ አሴትና ቢተኮይንን በሁለት መልኩ ማየት የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን አስመልክተው ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ በመጀመሪያ የክሪፕቶ ማይኒንግ አለ። ይህ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከኃይል አቅርቦት መስፋፋት ጋር በተገናኘ /ከታዳሽ ኃይል ጋር ተገናኝቶ/ በስፋት ኢንቨስትመንት እየተደረገበት ይገኛል። ይህም ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ እና ኢትዮጵያ የክሪፕቶ ማይኒንግ መዳረሻ መሆኗ ምንም ችግር የሌለበት ነው። የዳታ ማዕከል ኢንቨስትመንት ተደርጎ የሚታይና አሁን ሥራ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።

ከዚያ በዘለለ ግን የክሪፕቶ አሴትን እንደመገበያያ መጠቀምን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የተፈቀደ አለመሆኑን አስታውቀዋል። በአጠቃላይ የዓለም የገንዘብ ፖሊሲ አካሄድ አሁን ሰው ጥሬ ገንዘብ /ካሽ/ መጠቀሙ እየቀረ ወደዲጂታል ከረንሲ እንዲዞር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የክሪፕቶ ከረንሲን በተመለከተ የዓለም የገንዘብ ፖሊሲ በሂደት እየተቀየረ ስለሚሄድ ለውጦችንና ልማቶችን እያየ ብሔራዊ ባንከ እንደሌሎች ማዕከላዊ ባነኮች እንደአስፈላጊነቱ መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል አመላከተዋል።

ምክር ቤቱ በእለቱ መርምሮ ያጸደቀው ሌላው አዋጅ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁን አስመልከቶም የምክር ቤቱ የፕላን፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ደሳለኝ ወዳጄ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ሰብሳቢው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ የባንኮችን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት በማሻሻል ለኢኮኖሚው ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ባቀረቡት ጥያቄና አስተያየት በቂ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠቱ የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መረዳት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ጠቀሜታው እንዳለ ሆኖ በተለይ የግል ባንኮች ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት እና አቅምን ያማከለ ረቂቅ አዋጅ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮችን ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል፡፡ የውጭ ባንኮች ከዲጅታል አሰራር ጋር በተያያዘ የሀገርን ሉአላዊነትና ደህንነት በጠበቀ መልኩ የፋይናንስ ስርዓቱ እንዲመራ ብሔራዊ ባንክ በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ማሞ ምህረቱ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ኢንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ አለው። ከ17 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የባንክ ዘርፉን በተመለከተ ሰፋ ያለ መሰረታዊ ማሻሻያ የተደረገበት አዋጅ ነው። ባንኮች በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው። የባንኮችን ጤናማነት ማረጋገጥ፣ የባንክ ሥራ የተሳለጠ መሆን ቀጥታ ከኢኮኖሚ ማረጋጋት ጋር ግንኙነት አለው።

የባንኮች ዋና ሚና ቁጠባ በማሰባሰብ፣ ወደ ተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በማሰራጨት ለኢንቨስትመንት ቀጣይነት ላለው ልማት ቁልፍ ሚና መጫወት መሆኑን የባንኩ ገዥ ጠቁመው፣ በባንኮች እና በተቆጣጣሪው መስሪያቤቶች ያለው ግንኙነት ከሌሎች ቢዝነሶች የተለየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ዘርፉ ያለው ተቆጣጣሪ መስሪያቤት በመሆኑ በባንኮች እና በተቆጣጣሪ መስሪያቤት መካከል ያለው ግንኙነት ከሌሎች ተቆጣጣሪ መስሪያቤቶች ካለው ግንኙነት ይለያል። ምክንያቱም ባንኮች ሲመሰረቱ፣ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንዲሁም ችግር ተከስቶ ባንኮች የሚፈርሱ ከሆነም ከምስረታቸው አንስቶ እስኪፈርሱ ድረስ ቁጥጥር የሚያደርግባቸው መስሪያቤት ብሔራዊ ባንክ ነው።

በመሆኑም ዘርፉን በአግባቡ መምራት ስርዓት ባለው መልኩ ፍቃድ መስጠት፣ የሚኖራቸውን ባለሙያዎች ብቁነትት ማረጋገጥ እና እነሱ ላይ ማረጋገጫ መስጠት፣ የሚሰሩበትን ሕግና የቁጥጥር ስርዓት ማስቀመጥ፣ መምራት፣ መቆጣጠር እና መከታተል የብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ኃላፊነት ነው ሲሉም አብራርተዋል። አዋጁ በዋነኝነት በባንክ ዘርፍ የውጭ እና የሀገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ የፍቃድ አሰጣጥ ላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ የተሟላ ማድረግ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዓለም አቀፍ አሰራር እና ደረጃዎች እንዲሁም ከወቅቱ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ባንኩ ገዥ ማብራሪያ፤ ይህ ጥረት የተደረገበት ዋና ምክንያት በአጠቃላይ የባንክ ዘርፉን ደህንነት፣ ጤናማነት እና መረጋጋት ለማረጋገጥ ነው። በሁለተኛ ደረጃ አዋጁ የሚያደርገው ነገር የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንዲደረግ ፣ ከዚህ በፊት በመንግስት የተላለፈውን የፖሊሲ ውሳኔ ወደ ተግባር ለማሸጋገር እና የውጭ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች በዘርፉ ተሰማርተው ለኢኮኖሚው ዕድገት ቀጣይነት ያለው አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችሉ ለማድረግ ነው አዋጁ የወጣው።

ረቂቅ አዋጁ ብዙ የተመከረበት፣ የባለሙያዎች ኮሚቴ ከማቋቋም አንስቶ፣ የሌሎች አገራትን ልምድ በመውሰድ፣ በባንክ ዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ከመወያያት ጀምሮ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ ነው።

አዋጁ አንድ ባንክ የፋይናንስ ቀውስ ሲያጋጥመው ለተከሰተው ቀውስ በብሔራዊ ባንክ እልባት ሰጪነት ሚና ስልጣንና ኃላፊነት በግልፅ ያስቀመጠ የመፍትሔ ሀሳቦችንና አማራጮችን በግልፅ ደንግጓል። ብሔራዊ ባንክ እንደተቆጣጣሪ መስሪያቤት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችሉትን የሕግ ድንጋጌዎችን አካቷል።

አዋጁን በጥንቃቄ ለተመለከተው ከ50 በመቶ በላይ የሚዘረዝረው የብሔራዊ ባንክ የእልባት ሰጪነት ስልጣን ነው ያሉት አቶ ማሞ፣ አንድ የፋይናንስ ተቋም ችግር ቢያጋጥመው፣ ቀውስ ቢያጋጥመው ምን መደረግ አለበት? በሚል የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ፣ የሶስተኛ ደረጃ እርምጃ ምን እንደሆነ እና በአጠቃላይ የአስቀማጮች ሀብት፣ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማነት እና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረታዊ የሕግ ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ በአይነቱ የተለየ አዋጅ መሆኑን አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህም የብሔራዊ ባንክ ከተሰጡት ቁልፍ ኃላፊነቶች መካከል አንደኛውና ዓይነተኛው የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት መጠበቅ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ብቻ የማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ይሆናል፤ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት የሚኖረው ይህንን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል የሕግ ድጋፍ ሲኖር ነው። ይህንንም ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል የሕግ ድጋፍ፣ የአሰራር ማዕቀፍ ያስቀመጠ አዋጅ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትተሮች ክፍት መደረግ እንዳለበት የፀደቀ መሆኑን አስታውሰው፣ አዋጁ በዋናነት የወጣው ይሄንን ውሳኔ ወደ ሕግ ለመቀየር ነው ብለዋል። የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በመደረጉ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅሙን እንደማያጣ አስታውቀው፣ ዘርፉን በመክፈት የቁጥጥር አቅሙን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

እንደ ባንኩ ገዥ ገለጻ፤ የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት ተደረገ ሲባል የውጭ ባንኮች እዚህ መጥተው እንደፈለጉ ይሰራሉ ማለትም አይደለም። መክፈቱ አለ፤ አከፋፈቱ ደግሞ የራሱ መንገድ አለው። በመጀመሪያ የውጭ ባንኮች መጥተው እዚህ ተቀጥላ ኩባንያ ሊያቋቁሙ ይችላሉ። ሁለተኛ የውጭ ባንኮች መጥተው ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና ሊሰሩ ይችላሉ። ሶስተኛ የውጭ ባንኮች መጥተው ቅርንጫፍ እዚህ ሊመሰርቱ ወይም የእንደራሴ ቢሮ የሚከፍቱበት ሁኔታም ይኖራል። ይህ ግን የውጭ ባንኮች መጥተው የኢትዮጵያን ባንክ ሊያጥለቀልቁ የሚችሉበት ሁኔታ እንደማይኖር ተናግረዋል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የብድር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማስፋት እና አምራች የሚባሉት የልማት ዘርፎች በቂ ብድር አግኝተው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ ተጨማሪ ዘመናዊ አዳዲስ አሰራሮች እንዲኖረው የሚያስችል አውድ ለመፍጠር የወጣ አዋጅ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ የፖሊሲ ውሳኔ መሰረተ የኢትዮጵያ ባንኮች የበለጠ ይጠናክራሉ፤ የበለጠ ይጎለብታሉ፣ የበለጠ ለአምራች ዘርፉ ፋይናንስ ያቀርባሉ፣ የበለጠ ሀብታቸው ይጨምራል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ባንኮች ገቡም አልገቡም የኢትዮጵያ ባንኮች ቀጣይነት ባለው መንገድ አቅማቸውን እያሳደጉ፣ ካፒታላቸውም እየጨመረ መሄድ ይኖርበታል። አስፈላጊ ከሆነም ከሌሎች ባንኮች ጋር እየተቀናጁ አሴታቸውን ትርፋቸውን፣ ካፒታላቸውን የሚሰበስቡበትን ሀብት መጨመር መቻል አለባቸው። የውጭ ባንኮች ስለሚገቡ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው እያደገ ስለሚሄድ ተለዋዋጭ ከሆነው ዘመን ጋር መሄድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የባንክ ሥራ አዋጁ ከ17 ዓመታት በኋላ ታሪካዊ የተባለውን የባንኮች አሰራር አዋጅ ቁጥር 1360/2017 በሶስት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። የብሄራዊ ባንክ አዋጁ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ 1359/2017 በሚል በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You