ከገጸ ሰብ ባህር

ምድራችን ከተሸከመቻቸው እጅግ ግዙፍና ጥልቅ ባህሮች የገዘፈው ባህር የት ነው ካልን የትም ሳንሄድ እኛው ውስጥ ነው። ከሰውነት ክፍሎቻችን መካከል ባህርን የመሰለ ባህሪ ያለው ከራስ ቅላችን ላይ የሰፈረው አዕምሯችን ነው። የገጸ ሰብ ባህረ ሃሳብ የሚለን አንድም እንዲህ ይመስለኛል።

ባህር የምናውቃቸውንና የማናውቃቸውን ፍጥረታትና ቁሳዊ አካላትን አጭቆ የያዘ ምስጢራዊ የምድራችን ክፍል ነው። አዕምሮም ሌላው ሰው ቀርቶ ራሱ ባለቤቱም በውል ባልገባው ውስብስብ ነገሮች የተደረተና ምስጢራዊው የሕይወት ቁልፍ የተሰወረበት ስፍራ ነው። ባህር ማለት ግዙፍ የውሃ ክምችት ብቻ አይደለም። በዓይናችን ልናጤናቸው ከማንችላቸው ነፍሳት እስከ ግዙፍ ፍጥረታት ድረስ አሉበት። እጅግ አስደናቂ የሆነውን ውበት የምንመከተው ከባህር ውስጥ ነው።

መድኃኒትና መርዝ ከአንድ ግዙፍ ውሃ ውስጥ ይኖራሉ። የሰው ልጆች ለመብልነት ከሚጠቀመው ዓሳ ጋር የሰውን ልጅ የሚበላው አዞ ይገኝበታል። ለፍቅር አቻ የለውም ከሚባለው ዶልፊን አጠገብ አደገኛው ሻርክ ብቅ ይልበታል። በድምሩ እዚህ ውስጥ ሞትና ሕይወት መሳ ለመሳ ሲዋኙ እንመለከታለን። ከተንኮል የነጹ የዋሆች፣ አደገኛ መርዝ አንጋቢዎች፣ ውብና ማራኪ፣ አስቀያሚና ዘግናኝ… ቁጥር ራሱ ቆጥሮ የማይችላቸው ፍጥረታት ከአንድ ባህር ውስጥ ይኖራሉ። የአንድ ደራሲ የምናብ ዓለምም ልክ እንዲሁ ነው።

የአዕምሮው የባህር ውሃ ማለት ሃሳቡ ነው። ሃሳብ ከሌለ ውስጡ ደረቅ በረሃ ነው። በረሃ ከሆነ ደግሞ ከእነዚያ ፍጥረታት መካከል አንዳቸውም አይኖሩም። ባህሩንና የባህሩን ዓሳዎች የፈጠረው ፈጣሪ ሁሉን ሠሪና አድራጊ እንደሆነበት ሁሉ፤ ከራሱ የሃሳብ ባህር ውስጥ የሰጠመ ደራሲም በባህሩ ውስጥ ያሻውን ፈጥሮ እንዳሻው ያደርጋቸዋል። እኚህ የደራሲው ፍጥረታትም ገጸ ሰብ(ገጸ ባህሪያት) ናቸው። በሃሳባዊው የታሪክ ውሃ ውስጥ ነዋሪ አድርጎ የየራሳቸውን መልክና ግብር ይሰጣቸዋል።

የፈጣሪው ፍጡር፣ ምስኪኑ ደራሲ እሱም ባምሳሉ ይፈጥራል። የሰው ልጅን የፈጠረ አምላክ ከአፈር አበጅቶ፣ እስትንፋሱን እፍ ብሎ ሲያበቃ “በአምሳሌ ፈጠርኩት” ይላል። ታዲያ ምናልባትም ከአምሳል ሁሉ አንደኛው አምሳል ይህ የደራሲው የመፍጠር ሃይል ይሆናል። ደራሲው የእግዜር፣ ገጸ ባህሪያቱም የደራሲው አምሳል ናቸው።

በመለኮታዊው አምላክና በደራሲነት ውስጥ ያለው ፈጣሪነት ሁለቱም ያለማንም ጣልቃገብነት የፈለጉትን እንዳሻቸው መፍጠራቸው ነው። ነገር ግን በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ገሀዳዊ መለኮትና ምናባዊ ተምሳሌት ነው። አንደኛው የመንፈስ፣ ሁለተኛው ደግሞ የአዕምሮ ጨዋታ ነው። አምላካዊውና እውን ሆኖ በሚታየው ፈጣሪነት ውስጥ ሙሉእነትና ዘላለማዊ የራስ የበላይነት ያለበት ነው።

ምስኪኑ ደራሲ ግን በውበትና ጥበብ ሁሉንም ፈጥሮ ሲያበቃ ለራሱና በራሱ ላይ ምንም ነገር ለማድረግ የማይችልበት ሰንኮፍ ውስጥ ሊሆን ይችላል። አንደኛውን ገጸ ባህሪ ሀብታም፣ ጀግና፣ ዘናጭና አማላይ አድርጎ ፈጥሮት እሱ ግን ምንም የሌለው መናጢ ድሃ ሊሆን ይችላል። ያሻውን ነገር ላሻው ገጸ ሰብ አስታቅፎ የሚያንበሸብሸው ምስኪኑ ደራሲ የዕለት ጉርሱንም ሊያጣ ይችላል። የርሱ ትልቁ ሕይወት ለጥበብ እስትንፋሱን ሊሰጥ ከስጋ ዓለም መንኖ ወደ ባህሩ መሄድና መጥለቅ ነው።

በአንድ ባህር ውስጥ፣ በአንዱ ምስኪን ደራሲ ምናብ ውስጥ መልከ መልካም መልአክና መልከ ጥፉ ሰይጣን፣ ምስኪን የዋህና አስፈሪ ጨካኝ፣ ሀብታምና ድሃ፣ ቆንጆና አስቀያሚ፣ ጥቁር ወፍራምና ቀይ ቀጭን፣ ምሁርና መሃይም…አድርጎ የፈጠራቸውን ገጸ ባህሪያት ጎንበስ ቀና እያደረገ ባሻው መልኩ እግዜራቸው ይሆናል።

ስለ ደራሲው ዓለም የምናብ ባህረ ሃሳብና የውስጡ ፍጥረት ስለሆኑት ስለነዚሁ ገጸ ሰቦች ከባህሩ የማንኪያ ያህል እንጭለፍ። ታዲያ የደራሲው ምናባዊ ፍጥረት የሆኑት እኚህ ገጸ ባህሪያት፤ ከባህሩ እየቀዘፉ ከወዴትስ ይሄዳሉ? አድራሻና መልክ ግብራቸውስ?

መገኛቸው ባህሩ ነው። ባህሩም ከደራሲው ምናብ ውስጥ ነው። ደራሲውም በዋናነት ምናልባትም ከሁለት በአንዱ ላይ ነው፤ ከፊልም አሊያም ከመጽሐፍ መርከብ ላይ። ከሃሳብ ውሃው ላይ ከሚሽከረከረው ባህር ሰርጓጁ መርከቡ ላይ ስምጥ እየገባ፣ እምጥ እየተሰወረ፣ የታሪክ አፈርን በውሃው ለውሶ የወደደውን ይፈጥራል። ብሽቅ፣ ጨካኝ፣ አጎብዳጅ፣ አሽሟጣች፣ ተወዳጅና ተናፋቂ፣ ውብ፣ ፉንጋ… ሁሉንም እንደ ጥበቡ። እኛ ግን እንደ እይታ ከሁለት ከፍለን ልንመለከታቸው ይገባል።

የመጀመሪያው ነገር በፊልሞች ውስጥ የምንመለከታቸው ገጸ ባህሪያትና በመጽሐፍት ውስጥ የምናገኛቸው፤ በሁለቱ መካከል አንድ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አለ። ደራሲው ስዕላዊ አድርጎ በአንድ የልቦለድ ታሪክ ውስጥ ያኖራቸው ገጸ ሰቦች፤ የሚታዩት በአንባቢው ዓይነ ህሊና ነው። በፊልም ውስጥ የሚገኙ ገጸ ባህሪያት ግን አካላዊ ገጽታን ተላብሰው፣ በተዋንያኑ ተምሳሌትነት ገሀድ ሆነው ይታያሉ።

ሁለቱም ገጸ ባህሪያት ውልደትን እንጂ ሞትን አያውቁም። ይህ ማለት በታሪኩ ሴራ ውስጥ አይሞቱም ሳይሆን፤ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ከመጀመሪያው የሚጨምር ዕድሜና ማንነት አይኖራቸውም። ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ዕድሜው 40 የነበረው ገጸ ባህሪ ዘንድሮም ያው አርባ ነው። አርጅቶ መሸበት፣ እድሜ ገፍቶ መሞት የሚባል ነገር አይደርስባቸውም። ደራሲው መጀመሪያ ላይ የወሰነላቸውን እጣ ፈንታ መኖር ነው ድርሻቸው። ደራሲው የረገማቸው እንደሆን ዘለዓለማቸውን እንደተረገሙ ይኖራሉ። የባረካቸው እንደሆነም እንደተባረኩ ይኖራሉ። ምንም የማያውቁ መሃይም ከነበሩ እድሜ ልካቸውን መሃይም እንደሆኑ ናቸው። በደራሲው የተጫነባቸውን የድህነት ቀንበር የሚያወርድላቸው አይኖርም።

አብዛኛውን ጊዜ በተለይ ደግሞ የታሪኩ ቁልፍ የሆኑ ገጸ ባህሪያት ከደራሲው እውነተኛ ማንነትና አስተሳሰብ ጋር የሚዛመዱ ናቸው። እንዲሆን የሚፈልገውንና የሚመኘውን የሚያኖረው እነርሱ ላይ ነው። ለዚህ እንደ ምሳሌ ፍቅር እስከ መቃብርን እንውሰድ። ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብርን ሲጽፉልን እንዲሁ ከምናብ ብቻ በመነሳት አልነበረም። ለምን ካልን ብዙሃኑን የሚያስማማው የዚህ መጽሐፍ ወግ ፍቅር ነው። በዛብህና ሰብለ ወንጌል ናቸው። ሀዲስ ያሳለፉትንና የነበሩበትን የፍቅር ሕይወት በቀጥታም ባይሆን ከእነርሱ ላይ አሳርፈውታል።

ሀዲስ በጣም አብዝተው የሚወዷትና ነብሳቸውን የሰጧት ሴት ነበረቻቸው። እሷም ክበበ ጸሐይ ናት። በጣፋጭ ፍቅራቸው መሃል ግን መራራ የሞት ጽዋ ተደፋበት። ጸሐይ ለዘለዓለሙ አሸለበች። ከዚያ በኋላ ሲወራ የምንሰማው እውነትም ከእርሷ ሞት በኋላ ሀዲስ ከማንኛይቱም ሴት ጋር አለመድረሳቸውን ነው። ውሃ አጣጭ ፍለጋ ቀርቶ የሌላ ሴት ጠረን ከትንፋሻቸው ጋር ተዋህዶ አያውቅም። የደራሲው ይኼ ሁኔታም በበዛብህና በሰብለ ወንጌል ፍቅር ላይ ተጽኗዊ ዐሻራውን አሳርፏል።

በአንድም ሆነ በሌላ ደግሞ የገጸ ባህሪያት ማንነትና ምንነት በደራሲው ቀሪ ሕይወት ላይ ዳፋቸውን ያኖራሉ። ለዚህ ማሳያው “ኦሮማይ” ነው። በዓሉ ግርማ እምጥ ይግባ ስምጥ እንዳይታወቅ የሆነው በጻፈው ታሪክ ብቻ ሳይሆን በገጸ ባህሪያቱ አሳሳልም ጭምር ነው። አንዳንዱ ገጸ ባህሪያት መልክና ቁመና እንዲሁም ድርጊቶቻቸው የገሀዱ ውክልና አለባቸው የሚል ነው። ታዲያ ከታሪክና መቼት ባሻገር ገጸ ባህሪያት በራሳቸው አንድ የተለየ ጭብጥ ይኖራቸዋል። በዓሉ ግርማ ጸጋዬን ጋዜጠኛ አድርጎ ሲፈጥረው ከራሱ መስታየት ፊት ቆሞ ነው። ምክንያቱም ራሱ በዓሉ ጋዜጠኛ ነበር። ጋዜጠኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊውን ማንነቱን ያሰፈረው በፈጠረው ጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማርያም ላይ ነው። የነብሱን አዱኛ ዘርቶበታል። በመጽሐፉ ውስጥ በውክልና የተቀመጠው ብቻውን አይደለም። ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ፣ የሺጥላ ማስረሻ፣ ተድላ ረጋሳ፣ ስዕላይ ባራኺ የተሰኙት ገጸ ባህሪያትን መጥቀስ ይቻላል። ምንም እንኳን የነበረው የፍቅር ግንኙነት ፈጠራ ቢሆንም ፊያሜታ ጊላይም ከእውን የተወሰደች ናት። ግዳችን ስለ እነርሱ ስላልሆነ እነማን ናቸው የሚለውን ባንጠቅሰውም እኚህ ሁሉ ግን ተደማምረው በዓሉን አስምጠውታል።

ገጸ ባህሪያት የሚወለዱት ከደራሲው የምናብ ባህር ብቻ ነውን? እርግጥ ነው ከደራሲው ምናባዊ ዓለም ውስጥ ይወለዳሉ። ግን ከደራሲው፣ በደራሲው ብቻ የሚፈጠሩ አዲስ ፍጥረት አይደሉም። ከእኛ ማንነትና ሕይወት የራቁ፣ ከዚህ ቀደም ዓይተንና ሰምተን የማናውቃቸው እንግዳ ፍጡራን አይደሉም። በአንድም ሆነ በሌላ እኚህን ገጸ ባህሪያት ከዚህ ቀደም እናውቃቸዋለን አሊያም ደግሞ ከሆነ ጊዜ በኋላ እንገናኛቸዋለን።

በአንድ ፊልም ላይ አሊያም መጽሐፍ ላይ የምናገኘው ገጸ ባህሪ ከቤተሰቦቻችን መካከል አንደኛው ሊሆን ይችላል። ከጓደኛ ወዳጅ ዘመድ፣ ከሰፈርና ሥራ ቦታዎቻችን ከአንደኛው አይጠፋም። የደራሲው ምናባዊ ፈጠራ ናቸው ስንል ፈጽሞ በዚህች ምድር ላይ የሌሉ፣ ያልነበሩና ወደፊትም ሊኖሩ የማይችሉ ናቸው ማለት አይደለም። ደራሲው ከዚህች ዓለም ተገልሎ ለብቻው የኖረ አይደለምና ምናባዊ ማማው የተገነባው ከልጅነቱ ጀምሮ ከኖረው፣ ከተመለከተውና ከሰማው፣ እንዲሁም አሁን ከሚኖረው ሕይወት ላይ ነው። ነገር ግን ፈጠራ እንዲባል ያደረገው ነገር የገጸ ባህሪያቱም ሆነ የታሪኩ መቼት ማለትም ደግሞ በጊዜና ቦታ የተወሰነ ማስረጃና መረጃ ሊገኝለት ስለማይችል ነው።

የገጸ ባህሪያት ውልደት ከማህበረሰባዊ የኑሮና ህይወት ማኅፀን ውስጥ ነው ስንል ደግሞ በአንደኛው ገጸ ሰብ ውስጥ የተመለከትነውን ባህሪና ማንነት ሁል ጊዜም ሳይጎድልና ሳይሸራረፍ እንደወረደ ከአንድ ሰው ላይ ልናገኘው እንችላለን ማለት አይደለም። ደራሲው አንዱን ክፉ ገጸ ባህሪ ለመግልጽ ጨካኝ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ ሴሰኛ፣ ኪስ አውላቂ…አድርጎ ቢስለውና ይህን ሰውዬ ከገሀዱ ዓለም ብንፈልገው እኚህን ሁሉንም ያሟላ አናገኝ ይሆናል። ነገር ግን አምስቱንም ባህሪያት ከተለያዩ አምስት ሰዎች ላይ ለማግኘት ሩቅ መሄድ አይጠበቅብንም።

የደራሲው ትልቁ የፈጠራ ችሎታም አምስቱን ማንነቶች ማስቀመጡ ላይ ሳይሆን፤ አምስቱንም ወደ አንድ ማንነት አምጥቶ ከታሪኩ ጋር የሚገጣጥምበት መንገድ ነው። ይህም የገጸ ባህሪያት የአሳሳል ጥበብ ልንለው እንችላለን። እንድንወዳቸውም ሆነ እንድንጠላቸው የሚያደርገን ቁልፍ ያለው እዚህ ጋር ነው።

ለምሳሌ ለየትኛውም ሰው ሌብነት በድፍኑ ወንጀል ወይ ደግሞ ሀጢያት ነው። ስለዚህ በሁሉም ሰው ጭንቅላት ውስጥ የተሳለው የሌብነት ምስል መጥፎና አስቀያሚ ነው የሚል ነው። አንድ ደራሲ ግን የአዕምሮ ህጋችንን ሽሮ ሌባውን ገጸ ሰብ እንድንወደው ሊያደርገን ይችላል። ነብሰ ገዳይ መሆኑን እያወቅን እንድናዝንለት አልፎም እንድናለቅስለት ለማድረግም ይቻለዋል። ይህ የሆነውም ደራሲው ገጸ ባህሪውን ከታሪኩ ጋር የሳለበት ልዩ ፈጠራዊ ችሎታው ነው።

በአፈንጋጭና ወጣ ባሉ ድርጊቶች ውስጥ ሳንወድ በግድ እንድንቀበለው ያደርገናል። ሌላኛው የገጸ ባህሪያት አሳሳል ደግሞ እውነት፣ ባህል፣ ቋንቋና መሰል ማህበረሰባውያንን መሠረት በማድረግ የሚቀመጥ ነው። በመጽሐፍትና በሌላውም ውስጥ ያለ ቢሆንም በጉልህ የምንመለከተው ግን በአብዛኛው ፊልሞች ውስጥ ነው። ለአብነት ፊልሙ የተሠራው በአንድ ማህበረሰብ ቀዬ ውስጥ፣ በዚያው ማህብረሰብ የሚያጠነጥን ቢሆን፤ ገጸ ባህሪያቱ ከአለባበስና አነጋገር አንስቶ እነርሱኑ መስለው ይሳላሉ።

ከዚህ በመነሳት አንዳንድ ጊዜ ድርጊትና አነጋገር ማንነትን የሚወክል ሆኖ ይሳላል። በፊልሞቻችን ውስጥ ይህ የተለመደ ነው። አንደኛው ገጸ ባህሪ የመጣበትን ማህበረሰብ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ነገር ሳይታይበት፣ መሀል አዲስ አበባ ውስጥ ከፎቆች ጫካ ስር ቁጭ ብሎ በአነጋገር ዘዬው ብቻ ከወዴት እንደመጣ ልንለየው እንችላለን። ታዲያ ንግግሩ ሁላችንም በምንሰማው አማርኛ እንጂ ባደገበት ቋንቋ አይደለም።

እንደገና ከሌላ ፊልም ውስጥ ሌላኛው ገጸ ባህሪ ከአንድ ሱቅ ላይ ሆኖ ብቅ ሲል ገና የሰውየውን ማንነትና ንግግሩ እንዴት ሊሆን እንደሚችል አስቀድመን እንገምታለን። ከወንዝ ወርዳ እንሥራዋን በውሃ እየሞላች ያለችውን ሴት ስንመለከት ማን እንደሆነች ግልጽ ሆኖ ይታየናል። የእብድ ገጸ ባህሪን ለማሳየት ሙሉ ለሙሉ ለማለት ጥቂት በሚቀረው መልኩ አንድ ዓይነት ገጽታ፣ አንድ ዓይነት አነጋገርና አኳኋን እንመለከታለን። ሰካራምና ፈላስፋውንም ሆነ ምሁር ፕሮፌሰሩን ለመግለጽ በአንድ ዳይሬክተርና ሜካፕ አርቲስት የተዘጋጁ ያህል ተመሳስለው ይታያሉ። ሌላው ቀርቶ ገበሬውን ገጸ ባህሪ ለማሳየት ማንን እንደምንጠቀም ሳይጻፍ በአዕምሯችን ቀርጸን የያዝነው ሕግ ያለ ይመስላል።

ይህን መሰሉ የገጸ ባህሪያት አሳሳል መጥፎ ነው ባንለውም የሚያጎድለው ነገር ግን ብዙ ነው። የመጀመሪያው ነገር በድግግሞሽ የተሞላና ተመልካችን የሚያሰለች መሆኑ ነው። ሁለተኛው ስንክሳር ደግሞ አንድን ባህል ወይንም ማህበረሰብ የወከልንበት ጽንሰ ሃሳብ የተሳሳተና ያንን ማህበረሰብ ብቻ የማይወክል ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ጊዜ ልንጠቀመው እንችላለን ግን በሁሉም ቦታና ጊዜ እሱኑ ብቻ መደጋገም አስፈላጊ አይደለም። እነዚህ ምክንያቶች ደግሞ ሦስተኛውን እንድንል ያስገድዱናል፤ የደራሲውንም ሆነ የዳይሬክተሩን የፈጠራ ችሎታ ያወርደዋል። ከላይ ለአብነት ያሰፈርናቸው አሳሳሎች ቀላልና ማንኛውም ተመልካች ሊያውቃቸው የሚችሉ ናቸው። ደራሲው ሲጽፍ ሌላ ምንም ዓይነት የጥናትና ምርምር ምልከታ ሳያደርግ በቀላሉ ከምናቡ ላይ የሰፈረውን ያወርደዋል። ዳይሬክተሩም በተለምዶ የሚያውቀውን ምስል ቁጭ ያደርገዋል። በአዲስ እይታ፣ አዲስ ፈጠራ ውስጥ እንዳይዋኙ፤ ባሉበት ብቻ መንቦራጨቅ ይሆናል።

የገጸ ባህሪያትን አሳሳል ጠቅለል ስናደርገው በሁለት ዋና ክፍሎች ልንመድበው እንችላለን። የመጀመሪያው ውጫዊ (አፋዊ) አሳሳል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጣዊ (አዕምሯዊ) የአሳሳል መንገድ ነው። በአንደኛው መንገድ ላይ የምንመለከተው ነገር ሁሉ ግልጽና ለሁሉም ተመልካች አንድ ዓይነት ምስልን የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ አለባበስ፣ የሰውነት ገጽታ፣ መልክና ቁመት የመሳሰሉት የሚታዩበት ነው። በውስጣዊ ወይንም አዕምሯዊ የገጻ ባህሪያት ምስል ውስጥ ብዙ ጉዳዮች በቀጥታ በዓይን ብቻ ሊስተዋሉ የማይችሉ ናቸው። ከዓይን ይልቅ ለዓይነ ህሊና የቀረቡ ናቸው። በብዛት ከአንደኛው ገጸ ባህሪ በሌላኛው የሚገለጹ ናቸው። ክፋትና ደግነት፣ ኀዘንና ደስታ፣ ርህራሄና ጭካኔ ዓይነት ስሜቶች የሚዘዋወሩበት ነው። ባልናቸው ነገሮች ሁሉ ገጸ ባህሪያትን ተነፈስናቸው እንጂ ገና ምናቸውንም አልተመለከትነውም። ከምናብ ባህር የሚወጡ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም ሌላ ባህር ናቸውና ከግዙፍ መጽሐፍ ላይ ሁለት መስመር እንደማንበብ ይቆጠር።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You