ዛሬ ሐምሌ 10 በታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ቀን ነው፡፡ የአዲስአበባ ከተማ አዲስ ም/ከንቲባ አምና በዚህች ቀን (ሐምሌ 10/2010 ዓ.ም) ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩበት ቀን ነበር፡፡ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ በንቲ (ኢንጂነር) በአዲስአበባ አስተዳደር ምክርቤት ተሾመው ቃለመሃላ ፈጽመው ሥልጣን ከተረከቡ እነሆ ዛሬ አንድ ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡
ሕጋዊ ሂደቱን ለመጠበቅ ሲባል አዲሱ ከንቲባ የተሾሙት «ምክትል ከንቲባ» ተብለው ነው፡፡ ለምን ቢባል በከተማዋ መተዳደሪያ ቻርተር መሠረት ከንቲባው መመረጥ ያለበት ከከተማው ምክርቤት አባላት መካከል በመሆኑ ነው፡፡ አቶ ታከለ ኡማ ይህንን ስለማያሟሉ፣ በምክትል ከንቲባነት ወንበር ሊቀመጡ ግድ ሆኗል። ያው በከንቲባ ማዕረግ ምክትል ከንቲባ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ ይህንንም የምክትል ከንቲባነቱን ሥልጣን ያገኙት ከሹመታቸው አንድ ወር በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የቀረበው የአስተዳደሩ ቻርተር ምክትል ከንቲባው ከምክርቤት አባላት መካከል ይመረጣል የሚለውን አዋጅ ማሻሻል በመቻሉ ነው፡፡ የተሻሻለው አዋጅ ምክትል ከንቲባው የምክርቤት አባል ባይሆንም መመረጥ እንዲችል ይፈቅዳል፡፡
ታከለ ኡማ፤ ከ2005 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኃላፊነት የቆዩትን እና በኋላም በአምባሳደርነት የተሾሙትን አቶ ድሪባ ኩማን ተክተዋል፡፡
አቶ ታከለ ኡማ ለአዲስአበባ 31ኛ ከንቲባ ሲሆኑ አዲስአበባ በ1902 በከንቲባ መመራት ስትጀምር የመጀመሪያው ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ቢትወደድ ወልደፃድቅ ጎሹ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ታከለ ኡማ ማንናቸው?
አቶ ታከለ ኡማ የተወለዱት 1976 ዓ.ም በምዕራብ ኦሮሚያ አምቦ አቅራቢያ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎሮ ሶሌ እና ቶኬ ተምረዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጉደር እና አምቦ ተከታትለዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ በኋላ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመረቁ። በ2000 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ምህንድስና (ኢንቫሮመንታል ኢንጂነሪንግ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
አቶ ታከለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው። በተማሪነት ዘመናቸው በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ደጋፊ እንደነበሩ ይናገራሉ፤ በኋላም በ1999 ዓ.ም ኦህዴድ/አዴፓን ተቀላቅለዋል።
አቶ ታከለ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የኦሮሚያ የከተማ መሬት ዘርፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሆፕ 2020 ሥራ አስኪያጅ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የከተማ አመራርነት፣ የሆለታ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የሰበታ ከተማ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆንም በአጠቃላይ ለ11 ዓመታት በአመራርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በኃላፊነት ሰርተዋል።
የከንቲባው የመጀመሪያ ትንሿ ፈተና
የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ወደሥልጣን እንደመጡ የተለያዩ ድጋፍና ተቃውሞዎችን አስተናግደዋል፡፡ ሹመታቸው ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው የበርካቶች መነጋገሪያ ሆነውም ቆይተዋል። ሹመታቸውን የሚቃወሙ ወገኖች ከሚከራከሩባቸው ምክንያቶች መካከል፤ የከተማዋ ተወላጅ ስላልሆኑ ከተማዋን ለማስተዳደር የውክልና ጉድለት አለባቸው፤ ብሔር ዘመም አቋማቸው የበርካታ ብሔረሰቦች መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባን ካለ አድልዎ ለመምራት ያላቸው አቋም አጠራጣሪ ያደርጉታል የሚሉት ይገኙበታል።
በሌላ በኩል ሹመታቸውን የሚደግፉ ሰዎች የሥራ አፈጻጸም ችሎታቸው እንጂ ብሔራቸው ከጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፣ ተሰናባቹን ከንቲባን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ለተከታታይ በርካታ ዓመታት ከተማዋን አስተዳድረዋል፤ የአቶ ታከለ ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይሆንም ሲሉ ይከራከራሉ።
በእነዚህ ሀሳቦች ላይ ያላቸውን ምላሽ በወቅቱ የተጠየቁት አቶ ታከለ ኡማ ለተሰነዘሩት የድጋፍ እና የነቀፌታ አስተያየቶች አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል።
«አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ፣ የሁላ ችንም ከተማ ናት ብዬ አምናለሁ። ከኢትዮጵያዊነት አል ፎም የአፍሪካዊነት መገለጫ ናት፤ ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫም ናትና። ይህ እምነቴ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ነው» ብለዋል።
ም/ከንቲባ ታከለ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቁ መወለዳቸውና ማደጋቸው በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል እና ሥነ-ልቦናን እንዲረዱት እንዳገዛቸው ተናግረዋል። ለወደፊቱ የከተማዋን ነዋሪዎች በእኩል ዓይን የማስተዳደር፤ በተለይ ደግሞ የድሃውን ማህበረሰብ ፍላጎት ከምንጊዜም በላይ ለማሟላት የተቻላቸውን እንደሚያደርጉም አክለዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በመላው ኦሮሚያ ተቀጣጥሎ ለነበረው ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለው የመንግሥት እቅድ ነበር። ዕቅዱ ለሕዝብ ውይይት ሳይቀርብ የመንግሥት ኃላፊዎች በዕቅዱ ላይ ተወያይተው ነበር።
አቶ ታከለም በኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን በተላለፈ ውይይት ላይ ስለ ዕቅዱ የሰጡት አስተያየት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር። አቶ ታከለ በሰጡት አስተያየት «የአንድ ከተማ ፍላጎት ሳይሆን ይህ የማንነት ጥያቄ ነው። አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞችን ሊያሳድግ የሚችል ዕቅድ ሲታሰብ የኦሮሞን ማንነት፣ ፖለቲካ፣ ባህል እና ታሪክ ሊጎዳ በማይችል መልኩ መሆን አለበት። አርሶ አደሮችን እየገፋ የሚያድግ ኦሮሚያም ሆነ አዲስ አበባ እኔ በግሌ አልፈልግም» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።
በኋላም አቶ ታከለ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ «ማስተር ፕላኑን አስመልክቶ የሰጠሁት አስተያየት የበርካቶች የተቃውሞ ምክንያት መሆን የለበትም ብለዋል። በወቅቱ የሰጠሁት አስተያየት በተለየ መልኩ መተርጎም የለበትም፣ የሥጋት ምንጭም መሆን የለበትም…አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን የትኛውም ከተማ ድሃውን ኅብረተሰብ መግፋት የለበትም» በማለት ጠንከር ያለ አቋማቸውን ደግመው አንጸባርቀዋል፡፡
አያይዘውም «አሁንም ቢሆን ጥቂት ግለሰቦች የአርሶ አደሩ መሬት ላይ ባለጸጋ ሆነው አርሶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ልጅ ጥበቃ እና የጉልበት ሠራተኛ ሆኖ ማየት አልፈልግም። ይህ ደግሞ ኦሮሞን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በከተማዋ እና በዙሪያዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሚመለከት ነው» ብለዋል።
የታከለ ኡማ 365 ቀናትን በጨረፍታ
ታከለ ኡማ (ኢንጅነር) ወደአዲስአበባ አስተዳደር የከንቲባነት ሥልጣን ከተሳቡ በኋላ በሥራ ዘመናቸው የከተማዋ ነዋሪ ዋነኛ ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ጨምሮ፣ የውሃ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ለሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለማዳረስ ሀሳብ መሰነቃቸውን ገልጸው ነበር፡፡
የምክትል ከንቲባው የቆይታ ጊዜ ገና አንድ ዓመት መሆኑ ለግምገማ በቂ ባይሆንም ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራትን ማሳካታቸው ግን ያስመሰግናቸዋል፡፡
ካከናወኑት ተግባራት አንዱና ዋናው የመሬት ወረራን ማስቆም ነው፡፡ በተለይ በአዲስአበባ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ ሰዎች በአንድ ጀምበር ሀብታም የሚሆኑበት፣ በተቃራኒው ሀብትና ንብረታቸውን በጠራራ ጸሐይ በመዘረፍ በአንድ ጀምበር ወደቤት አልባነት የሚቀየሩበት ሒደት ለማስተካከል ብዙ ለፍተዋል፡፡
ጤናማ ከተማ ውስጥ የመኖር የሁሉም ነዋሪ ሕጋዊ መብቱ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ የሕግ አግባብነት የሌላቸው የሕገ-ወጥ ቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ በከፍተኛ ሁኔታ መበራከቱን አቶ ታከለ አምና በዚህ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡
በተለይም በቦሌ፣ የካ፣ ኮልፌ፣ ነፋስ ስልክ እና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተሞች ባለፉት ጊዜያት በተደራጀ መልኩ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ነግሶ ነበር፡፡
ባለሀብቶች፣ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት፣ ደላሎች እና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ጭምር በሚሳተፉበት ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከማፍረስ በተጨማሪ እነዚሁ አካላት በሕግ እንዲጠይቁ ይደረጋል ባሉት መሠረት ፈጽመዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለዘመናት በሕገ-ወጥ መንገድ ያለ ልማት ተቀምጦ የነበረን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ውስን የሕዝብ ሀብት መሬት ወደ መንግሥት እንዲመለስ አድርገዋል፡፡
በተለይ ያለፈው ዓመት ክረምት በማስመልከት የጽዳት ዘመቻ በከተማዋ በተከታታይ እንዲካሄድ መሠረት የጣለ ተግባር አከናውነዋል፡፡
ከተማዋ ለዘመናት ከነበረባት ውስብስብ ችግር አንፃር ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኗ የፅዳት ዘመቻው ይሄንን ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል ነው ብለዋል።
ኅብረተሰቡም የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን በማፅዳት እና የውሃ መተላለፊያዎች ላይ ቆሻሻ ባለመጣል የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ታከለ ጥሪ አቅርበዋል።
ግዙፍና አጓጊ ፕሮጀክቶች
አቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ይፋ ባደረጋቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከባለሀብቶች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ከኅብረተሰቡ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ተወያይተዋል፡፡
ከግዙፍ ፕሮጀክቶቹ መካከል ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ የዓድዋ ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት፣ ከፑሽኪን አደባባይ – ጎተራ ማሳለጫ የሚገነባው መንገድ እና የቤተ-መንግሥስት ቅርስ ጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ፣ የአዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሠረት በለገሃር የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ይህ የለገሃር የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ለከተማው አዲስ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ሲሆን፤ የልማት ተነሺዎች ሳይፈናቀሉ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ለመዲናዋ ዓይን ገላጭ ፕሮጀክት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የውሃ አቅርቦት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀርፋል የተባለው የለገዳዲ ቁጥር 2 የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክትን ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር ግንባታውን ከሚያከናውኑ ሥራ ተቋራጮች ጋር የስምምነት ፊርማ የተከናወነው በአቶ ታከለ ኡማ አስተዳደር ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ የሚገኙ አካባቢዎችን በዋነኛነት በጉለሌ እና የካ ክ/ከተሞች የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት አካባቢ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞችን እና ወረዳዎችም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ በቀን 86ሺ ሜ.ኩብ የውሃ አቅርቦት እንደሚሰጥ የሚጠበቀው የለገዳዲ ቁጥር 2 የውሃ ፕሮጀክት 860 ሺ የሚሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
አቶ ታከለ ኡማ ኃላፊነት በተረከቡ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 50 በመቶ የነበረው የውሃ አቅርቦት ሽፋን በርካታ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮን በማካሄድ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ መቻሉም በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ሌላኛው ተጠቃሽ ሥራዎቻቸው መካከል የጎዳና ላይ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተመሠረተው የማህበራዊ ትረስት ፈንድ አንዱ ነው፡፡ ፈንዱ እስከ አሁን ከ3 ሺ 147 በላይ ነዋሪዎች ከጎዳና ላይ በማንሳትና ሕይወታቸውን መቀየር፣ ፍላጎቱ ያላቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
የሥራ አጥነት ማህበራዊ ችግርንም ከመሠረቱ ለመፍታት የከተማው አስተዳደር የ2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲመደብና ወደሥራ እንዲገባ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ወደ መንግሥት የመሬት ማኔጅመንት ገቢ የተደረጉት መሬቶች በጊዜያዊነት ለመኪና ፓር ኪንግ አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ 38 የመኪና ማቆሚያ ዎችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች በማስገንባት ለከተማዋ ወጣት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ሊጠቀስ ከሚችሉ ተግባራት መካከል ይገኙበታል፡፡
እንደጉድለት የሚነሱ
አቶ ታከለ ኡማ ወደ አዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባነት ሥልጣን ሲመጡ ከተማዋን ከተተበተበችበት ትላልቅ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት እጥረት በቀዳሚነት ተጠቃሸ ናቸው፡፡ በያዝነው ዓመት የካቲት ወር የ13ኛ ዙር የ20/80 መኖሪያ ቤት እና የ2ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት በጠቅላላው 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ሲካሄድ ቤቶቹ ጥቂት የማይባሉ የከተማዋን ነዋሪዎች ችግር ሊቀርፉ እንደሚችሉ ታምኖባቸውም ነበር፡፡ ዕጣው መውጣቱ ከተሰማ በኋላ እንደኮዬ ፈጬ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች እስከ12ኛ ዙር ዕጣ አወጣጥ ድረስ ባልታየ መልኩ የቤቶቹን መተላለፍ ጥቅማችንን ይጎዳል ሲሉ ተቃወሙ።
ይህንንም ተቃውሞ ተከትሎ ቤቶቹን የማስተላለፍ ሒደቱ ከሚገባው በላይ መጓተቱ ብቻ ሳይሆን ይህን ችግር በመፍታት ረገድ ምን እየተሰራ ስለመሆኑ በየጊዜው ግልጽ መረጃ ለሕዝብ አለመሰጠቱ አሁን ድረስ ነዋሪዎቹን ቅር ያሰኘ የአስተዳደሩ ድክመት ነው፡፡ ችግሩ በቀጣይም እንዴት እንደሚፈታ እስካሁንም በግልጽ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ከዛሬ ነገ የመኖሪያ ቤት አገኛለሁ በሚል ሳይተርፈው የሚቆጥበውን አብዛኛው ሕዝብ በመንግሥት ላይ የነበረውን አመኔታ ሸርሽሯል፡፡
ከጸጥታም አንጻር የከተማውን ነዋሪ ሠላም የሚያውክ ማንኛውም ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትን የከተማ አስተዳደሩ እንደማይታገስ እና እርምጃ እንደሚወስድም አቶ ታከለ ኡማ በአንድ ወቅት ቃል ቢገቡም አፈጻጸሙ ላይ ግን ጉድለቶች ታይተዋል፡፡ ዛሬ በአዲስአበባ በሁሉም ክፍለከተሞችና የአዲስአበባ ጉራንጉሮች ተራ ቅሚያ እና ዝርፊያን ጨምሮ የተደራጀ ውንብድና እየጨመረ መምጣት ዜጎችን ክፉኛ እያስመረረ ይገኛል፡፡ ይህ አዲስ ክስተት የነዋሪውን በሠላም የመንቀሳቀስና ወጥቶ የመግባት ዋስትና አሳሳቢ ደረጃ አድርሶታል፡፡ የታከለ ኡማ አስተዳደር ይህን ችግር የሚመጥን ምላሽ ባለመስጠቱ በየጊዜው በነዋሪዎቹ ስሞታ (ቅሬታ) እየቀረበበት ይገኛል።
የከተማዋ የትራንስፖርት ችግሮች ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሚታይ፣ በሚዳሰስ ወይንም ትርጉም ባለው መልክ ችግሩን በመቅረፍ ረገድ የአቶ ታከለ ኡማ አስተዳደር ባሳለፈው የአንድ ዓመት አጭር ጊዜ እምብዛም የተሳካለት አይመስልም፡፡ (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጹሑፍ ጥንቅር የአዲስአበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ይፋዊ ድረገጽ፣ የቢቢሲ አማርኛ፣የጀርመን ድምጽ፣ የኢዜአ፣ የፋና…ዜናና ዘገባዎች በግብአትነት ተጠቅሜያለሁ፡፡)
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
ፍሬው አበበ