
በአሜሪካ ማዕከላዊ ቴክሳስ በደረሰው ጎርፍ አደጋ የሟቹች ቁጥር ከ100 በላይ ሲደርስ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ደግሞ እስካሁን አልተገኙም። ተጨማሪ ዝናብ እና ነጎድጓድ በአካባቢው ስጋት የሆነ ሲሆን የነፍስ አድን ሠራተኞች በጭቃ በተሞሉ የወንዝ ዳርቻዎች ሰዎችን እየፈለጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ አደጋው ከደረሰ ከአራት ቀናት በኋላ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ እየጨለመ ነው። ሚስቲክ የተባለው የክርስቲያኒያዊ ወጣቶች ካምፕ 27 ሴቶች እና የሥራ ባልደረቦች ከሞቱት ውስጥ እንደሚገኙበት አስታውቋል።
ታዳጊ ሴቶች እና የካምፑ አማካሪ እስካሁን አልተገኙም። አደጋውን ቀድሞ መተንበይ አለመቻሉ የብሔራዊ አየር ጠባይ አገልግሎት በጀት መቀነስ አስከትሎት ሊሆን ይችላል የሚለውን ሀሳብ ዋይት ሐውስ አጣጥሎታል። ጓዱላፔ ወንዝ በከፍተኛ ዝናብ በተጥለቀለቀበት በኪር አካባቢ ቢያንስ 84 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
የአካባቢው የፖሊስ ቢሮ 22 አዋቂ ሰዎች እና 10 ሕፃናት እስካሁን ማንነታቸው አልተለየም ብሏል። ሚስቲክ የተባለው ካምፕ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ “ሊታሰብ የማይችለው ሐዘን ከገጠማቸው ቤተሰቦች ጋር ልባችን ተሰብሯል” ብሏል።
የ70 ዓመቱ የካምፑ የጋራ ባለቤት እና ዳይሬክተር ሪቻርድ ኢስትላንድ ሕፃናቱን ለማትረፍ ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፏል። የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ቀስ ብሎ የሚንቀሳቀስ ነጎድጓዳ አየር የተነበየ ሲሆን፤ ይህም በአካባቢው ደራሽ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል ሲል ገልጿል።
ለአካባቢው አየር ትንበያ የሚያወጣው አገልግሎቱ ባለፈው ሐሙስ ምሽት በቴክሳስ ግዛት ነጎድጓድ ሲበረታ አምስት ሠራተኞቹ ስራ ላይ ነበሩ። የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት ለአደጋው ፕሬዚዳንቱን ለመውቀስ መሞኮሩን አጣጥለዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስፍራውን እንደሚጎበኙ የተጠቆመ ሲሆን ክስተቱን “አስደንጋጭ እና አሰቃቂ” ሲሉ ገልፀውታል።
የቴክሳስ ባለሥልጣናት የጠፉትን ሰዎች ቁጥር ማረጋገጥ ባይችሉም ፍለጋው እና የነፍስ አድን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የነፍስ አድን ሰራተኞች በአደጋው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ጥረት የ165 ሰዎችን ህይወት የታደገው የነፍስ አድን ባለሙያ እየተሞገሰ ይገኛል።
የአሜሪካ የባህር ሀይል የነፍስ አድን ቡድን አባል የሆነው ስኮት ሩስካን የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ እየተደረገ ባለው ርብርብ 165 ሰዎችን ህይወት መታደጉ ተነግሯል።
ይህን ተከትሎም የሀገር ውስጥ የህዝብ ደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ክሪስቲ ኖይም ፔቲ ኦፊሰር ስኮት ሩስካንን የአሜሪካ ጀግና ሲሉ አሞካሽተውታል።
የ26 ዓመቱ ጠላቂ ዋናተኛ የነፍስ አድን ስራውን የተቀላቀለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን ተከትሎ ነው። የነፍስ አድን ስራ ስልጠናን ተከታትሎ ያጠናቀቀው በቅርቡ መሆኑንና ይህ የነፍስ አድን ተልዕኮ የመጀመሪያው መሆኑን የሚናገረው ስኮት ሩስካን፥ ጀግና የሚል ሙገሳ ከቀረበለት በኋላ በሰጠው አስተያየት፥ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
ስራዬ ይኸው ነው፥ ማንም በእዚህ ቦታ ላይ ቢኖር የሚችለውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፥ እኔም ያደረግኩት የተሰጠኝን ኃላፊነት መወጣት ነው ሲል ለኤቢሲ ኒውስ ተናግሯል።
ባለፈው አርብ “የጓንዳሉፔ” ወንዝ ባስከተለው ከባድ ጎርፍ በሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የዘገበው ሮይተርስ ነው።
ሰኞ ዕለት በነበረው የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ አደጋውን “የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ብለዋል።”ጎርፉ የተከሰተው በአስተዳደሩ ጥፋት አይደለም። ነገር ግን አስቀድሞ ተከታታይነት ያለው ማስጠንቀቂያዎች ነበሩ። ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ስራውን ሰርቷል” ብለዋል።
በዚህ ሳምንት ቴክሳስን ይጎበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፌደራል መንግሥት የበጀት ቅነስ የአደጋ ምላሽ አሰጣጡን አደናቅፎ ከሆነ ሲጠየቁ ጣታቸውን በቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ ቀስረዋል። “ነገር ግን ባይደንን ለዚህ አልወቅሰውም” ካሉ በኋላ፤ “የ100 ዓመታት አደጋ እንደሆነ ነው እላለሁ” ብለዋል።
የቴክሳስ ሴናተር የሆኑት ቴድ ክሩዝ ሰኞ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ጣት ለመቀሳሰር ጊዜው አሁን አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመላው ዓለም የሐዘን መግለጫዎች ቀጥለዋል።
የብሪታኒያው ንጉስ ቻርለስ ሣልሳዊ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ በአስከፊው የጎርፍ አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም