
ከሰሞኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመንቀሳቀስ አጋጣሚው ነበረኝ። አስር ቀናትን በፈጀው ጉዞዬ ላይ የአርሶ አደሮችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የሥራ ፈጣሪዎችን እና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የማነጋገር አጋጣሚውን አግኝቻለሁ። የጋዜጠኝነት ሥራ ከሚሰጣቸው መልካም እድሎች ውስጥ አንዱ ከተለያየ አመለካከት፣ የኑሮ ሁኔታ እና ደረጃ ጋር ከሚገኙ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ የመወያየት አጋጣሚው አንዱ ነው።
ጋዜጠኛ መሆን የዜጎችን ድምፅ (ስኬት፣ ችግር፣ እና ቅሬታ) በቀጥታ ከመስማት ባሻገር ከሕዝቦች የሕይወት ልምድ በቀጥታ መማርን፣ ማዳመጥን ያስችላል። እኔም በእነዚህ አስር ቀናት ውሰጥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የማለፍ እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን የመሰብሰብ እድል አግኝቼ ነበር። በዚህም የጤና ማዕከላትን፣ የግብርና ቦታዎችን፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን፣ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎቸን አግኝቻለሁ። በተለይ ከአርሶ አደሮች፣ ሥራ ፈጣሪዎችና እና የጤና ባለሙያዎች ጋር የነበረኝ ቆይታ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ እንድረዳ እድሉን ፈጥሮልኛል።
በዛሬው የነፃ ሀሳብ ዓምድ ላይ የሚከተለውን ምልከታዬን ካገኘሁት ሃቅ ጋር አስታርቄ ለማቅረብ የፈለግኩትም በዚሁ ምክንያት ነው። ልዩ ትኩረትን ይሻሉ ብዬ የማስባቸውን (የጉዞዬ አካል የነበሩ) ጉዳዮችን እንደሚከተለው ለማንሳት እወዳለሁ። በአስሩ ተከታታይ የጉዞ ቀናት ውስጥ ከተመለከትኩት አካባቢ ውስጥ አንዱ የሲዳማ ክልል አንዱ ነበር። እንደሚታወቀው ከሰሞኑ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ጋር በተያያዘ የምንሰማው የወረርሸኝ ስጋት ተጋላጭ ከሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው።
ትኩረቴን ከሳቡት ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ጤና እንደመሆኑ መጠን በሲዳማ ክልል ውስጥ የሕዝብ ጤና መኮንኖች ከዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክሲ) መስፋፋትን ለመከላከል ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ይህ በሽታ በርካታ ሰዎችን ስላላጠቃ ብቻ እንደ ሩቅ ነገር ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን በብዙ የገጠር ማኅበረሰብ ውስጥ የመስፋፋት አደጋው እጅግ ሰፊ ነው። በመሆኑም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በሲዳማ በነበረኝ ቆይታም የተገነዘብኩት ይህንኑ ነው። የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የጤና ቡድን ወረርሽኙ ከመስፋፋት ለመከላከል ማዕከሎችን ገንብቷል፤ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቋቋም ሠራተኞቻቸውን አሰልጥነዋል። በዘመቻ ለሕዝብ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ከክልሉ ከፍተኛ የጤና ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ በነበረኝ ግንኙነት ማወቅ ችያለሁ።
ነገር ግን ከዚህም በላይ ጠንካራ ጥረት ያስፈልጋል የሚል የግል ምልከታን ይዣለሁ። በተለይ መልዕክቱ ሁሉም ሰው ላይደርስ ይችላል። በዋናነት በርቀት (በገጠራማ አካባቢዎች) የሚገኙ ሰዎች (ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ) የማያገኙ የማኅበረሰብ አካላት ልዩ የግንኙነት እና ግንዛቤ መፍጠሪያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ እራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስገንዘብ ይገባል። ብዙዎች የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ምንነት እና የስርጭት መንገድ ላይገነዘቡ ይችላሉ። ስለዚህ አዲስ ስልት መፍጠር ይገባል የሚል መልዕክት ለማንሳት እወዳለሁ።
በሲዳማ ክልል ቆይታዬ የተገነዘብኩት ሌላ ፈታኝ ሁኔታ የላቦራቶሪ ተደራሽነት ነው። አንድ ሰው ምልክቶችን ሲያሳይ ናሙናዎች በምርመራ ለማረጋገጥ አዲስ አበባ ድረስ መላክ አለበት፤ ይህ ሂደት ቀናት ይወስዳል። የታመሙ ሰዎች በሚጠብቁበት ጊዜ በሽታውን ሊሰራጭ ይችላል። የጤና ባለሙያዎች ይህ ችግር በቅርቡ ይፈታል ብለው ቢያምኑ ከችግሩ ስፋት አንፃር አፋጣኝ እልባት ያስፈልገዋል ብዬ አስባለሁ። በአንዳንድ አካባቢዎች በቀጥታ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ጋርም ባይሆን የመድኃኒት እና የመከላከያ አቅርቦቶችን እጥረት መኖሩን መገንዘብ ችያለሁ። ይህ ክፍተት ማኅበረሰቡ ላይ ስጋት እንዳይሆን ትኩረትን ይሻል።
በሲዳማ በነበረኝ ቆይታ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPOX) በተጨማሪ የወባ በሽታ በተለይ በሞቃት እና እርጥብ አካባቢዎች ወቅታዊ ስጋት መሆኑን አውቄያለሁ። ኮሌራም ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በፍጥነት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ፍርሃት አለ። በተለየ ንፅህና አጠባበቅ፣ የውሀ አጠቃቀም እና በጥቅሉ እራስን ከስጋት ለማድረግ የሚያግዙ የጥንቃቄ እርምጃዎች በባለሙያዎች ሊወሰዱ ይገባል።
ብዙውን ግዜ ስለ ሕንፃና ሆስፒታሎች እንዲሁም ክሊኒኮች ግንባታ እንነጋገራለን። በእርግጥ መሰረተ ልማቶቹ አስፈላጊ ናቸው፤ ነገር ግን ከበሽታ በቅድሚያ እራስን ለመከላከል ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ጥሩ የንፅህና አጠባበቅ፣ በአቅራቢያ የሚገኙ ላቦራቶሪዎች እና የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም የታመመ ልጅ ማጥናት አይችልም፣ የታመመ አርሶ አደር ሰብሉን ሊንከባከብ አይችልም፣ የታመመች እናት የቤተሰቧ ሁለንተናዊ ጤንነት ልትንከባከብ አትችልም በመሆኑም ጤና ለሁሉም ነገር መሠረት ነው በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ሌላው በአስሩ ቀናት ቆይታዬ ከደረስኩበት ከተማ ውስጥ አንዱ መተሀራ ነው። በዚያ ልዩ ትኩረት አድርጌበት የነበረው የትምህርት ዘርፍ ነው። ከትምህርት ደግሞ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የተለየ ትኩረቴን አግኝቶ ነበር። በመተሃራ ከተማ ውስጥ ከተማሪ ምገባ ጋር የተገናኘው ጉዳይ እውነተኛ እርምጃ መሆኑን ማየት ችያለሁ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተመለከትኩት የምገባ ፕሮግራም ነበር።
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በንጹህ ግቢ ውስጥ ምሳ እየበሉ ነበር። ሳምንቱን ሙሉ ተማሪዎች ለፈተና ዝግጅት ሲያደርጉ ገንቢ ምግቦችን ይመገባሉ። ይህ ትንሽ መስሎ ሊታይ ይችላል።, ግን ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ከፕሮግራሙ በፊት ብዙ ተማሪዎች ወደ ቤት ውስጥ በምግብ ምክንያት ይቀሩ ነበር፤ በክፍል ውስጥም በሚገባ ትምህርታቸውን አይከታተሉም ነበር።
አሁን ግን ትምህርት ቤት ይመጣሉ፤ በትኩረት ይከታተላሉ። መምህራንን፣ ተማሪዎችን እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን ባነጋገርኩበት ወቅትም ተመሳሳይ ምላሽ ነበር ያገኘሁት። የምገባ ፕሮግራም በተማሪዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በመተሀራ ቆይታዬ መመልከቴ በግሌ አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ይሁን እንጂ በቆይታዬ በከተማዋ ትምህርትን ከቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን አይቻለሁ። የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እጥረት እንዳለባቸው የትምህርት ቢሮ ፅህፈት ቤት ኃላፊዋ አጫውተውኛል። መንግሥትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ በያዝነው ሃያ አንደኛ ክፍለዘመን ተማሪዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር ማገናኘት የግድ ይለናል። ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለመፍጠር ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ።
ትምህርት ማሻሻል ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት በላይ ነው። ልጆችን በትምህርት ቤት ውስጥ በፍላጎትና በትኩረት እንዲማሩ ማቆየት ማለት ነው። ስለዚህ በመተሀራ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እና ጥራትን ለማስጠበቅ መሥራት ይገባናል።
በአስሩ ቀናት የጉዞ ቆይታዬ ከተመለከትኩት የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከንባታ ዞን ሃደሮ ወረዳ አንዱ ነበር። በዚህ ወረዳ ውስጥ የተለያዩ ቀበሌዎች ተዘዋውሬ ከአርሶ አደሮች ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር።
የሀድሮ ወረዳ ለምለም መሬት እና በጥሩ ዝናብ የተባረከ ሥፍራ መሆኑን አይቻለሁ። በተለይ በአካባቢው ዝንጅብል፣ አቡካዶ፣ ቡና እና ጃክ ፍሩት በስፋት ይገኛል። ሆኖም ዝንጅብል አካባቢውን የሚገልጽ ልዩ ሰብል ነው። ነዋሪዎች ‹‹የሃደሮ ወርቅ›› ይሉታል። አንዳንድ አርሶ አደሮች በየዓመቱ በሄክታር ከ300 ወይም ከ400 ኩንታል በላይ ያመርታሉ። ሥራቸው አስደናቂ ነው። መንግሥት ይህንን ፀጋ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይ አርሶ አደሮች ያለባቸውን ችግር ከጎናቸው በመሆን ፈትቶ ከወረዳው የተሻገረ ለሀገር የሚጠቅም ሀብት ማፍራት ይቻላል።
በሀደሮ ወረዳ በነበረኝ ቆይታ የአርሶ አደሩ ስጋት ዝንጅብል የሚገዙ ደላላዎች መሆናቸውን አውቄያለሁ። ደላሎቹ ከአርሶ አደሩ በዝቅተኛ ዋጋ ገዝተው በትላልቅ ከተሞችና ድንበሮች ላይ በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣሉ። ምክንያቱም ከአርሶ አደሩ በተገቢ ዋጋ በመግዛት ዝንጅብልን አቀነባብሮ የሚያቀርብ ፋብሪካ በወረዳው የለም። በዚህ ምክንያት ገበሬዎቹ ምንም አማራጭ የላቸውም። በወረዳው 5700 ሄክታር መሬት በዝንጅብል ተሸፍኖ ውጤታማ ምርት ቢሰጥም የገበያ ሰንሰለቱን ደላሎች መቆጣጠራቸው አርሶ አደሩ እንዳይለወጥ ምክንያት ነው።
አርሶ አደሩ የአካባቢውን ፀጋ ተጠቅሞ በቂ ምርት ማምረቱ የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት ባለሀብቱን ወደ ወረዳው በመሳብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲገነባ ማበረታታት ይኖርበታል። አርሶ አደሩ በጸጋው የመለወጥና የማደግ መብቱም ሊረጋገጥለት ይገባል። ለዚህ ደላሎችን መከላከል ያስፈልጋል።
የአስር ቀናቱ ቆይታዬ አንዱ አካል የነበረው የባቱ ከተማ ነበር። በዚህ ከተማ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ የተረዳሁት ከተማዋ እራሷን ወደ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ማዕከልነት እየቀየረች መሆኑን ነው። ከከተማዋ ከንቲባ ጋር በነበረኝ ውይይት አዲስ የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ የሃይቅ ዳርና የከተማ መሀል የኮሪደር ልማት ሥራዎች ባቱን እንዴት እንደሚለውጡ አብራርቶልኛል።
በቆይታዬ የብስክሌት መንገዶችን፣ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ መናፈሻዎች፤ የደንበል ሐይቅ በንጽህና እና በቆንጆ ሁኔታ በመያዝ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ተግባሩ የሚደነቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለጎብኚዎች በቂ ጥበቃ ከማድረግ ባሻገር በሐይቁ አቅራቢያ የላስቲክ ቆሻሻ መጣል አንደማይፈቀድ አይቻለሁ። ይህ የከተማዋን ተግባራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ ናቸው። የባቱ ከተማ ከቱሪዝም በቀን እስከ 70 ሺህ ብር ገቢ ታገኛለች።
የባቱ ከተማ ከቱሪዝም በላይ ባለሀብቶችን እየሳበ ነው። በሁለት ዓመት ብቻ 79 አዳዲስ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ገብተዋል። በዚህም ሆቴሎች፣ ንግዶች እና የአገልግሎት ማዕከሎች እየተዘጋጁ መሆኑን ታዝቤያለሁ። የባቱ ከተማ የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች እና ልዩ ልዩ አመለካከቶች የሚጋሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብረው እንደሚኖሩባት አይቻለሁ። የማኅበረሰብ ክፍሎቹ በጋራ የሚኖሩ ጎረቤቶች ብቻ አይደሉም፤ ይልቁኑ አንድ የመቃብር ሥፍራ ይጋራሉ።
ሌላው የጉዞዬ አካል የነበረችው የሻሸመኔ ከተማ ነበረች። እንደሚታወቀው ከጥቂት ዓመታት በፊት በከተማዋ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ጥቂት ቡድኖች ከፍተኛ ጥፋት ደርሶ ነበር። ክቡር የሰው ሕይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሮ ነበር። ዛሬ ግን ይህ አሳዛኝ ክስተት ታሪክ ሆኖ አልፏል። ከተማዋ ቀድሞ የነበራትን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻል እና የልማት እሴት መልሳ ይዛለች።
በሻሸመኔ ቆይታዬ የከተማዋ ከንቲባ ጋር ቆይታ ነበረኝ። በዚህ በኮሪደር ልማት፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማት እና በሰላምና ፀጥታ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ነግረውኛል። ዛሬ ሻሸመኔ በየቀኑ 70 ሺህ ሰዎች ገብተው ነግደው፣ ተዝናንተው ዘመድ አዝማድ ጠይቀው የሚወጡባት ከተማ ሆናለች። ከነበረው ጥፋት ተመልሳ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ሶስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን በር መሰብሰብ ችላለች። ሕገወጥ ንግድን፣ አደንዛዥ እጽን በመቆጣጠር ፍትህን የማስፈን ሥራውም እንደቀጠለ ነው።
ሻሸመኔ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ተብላ ትጠራለች። ምክንያቱም ከ 27 ብሄረሰቦች በላይ በውስጧ አቅፋ ይዛለች። በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀር የሚጎበኟት ነች። ከተማዋ በሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት መልሳ እንደማታገግም ባለሙያዎች ግምታቸውን ቢያስቀምጡም በፍጥነት ወደ ነበረችበት እድገትና ልማት ተመልሳለች። ልጆች፣ እናቶች፣ ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚኖሩባት ውብ ከተማ ሆናለች።
ለማጠቃለል
በዚህ ጉዞ የጋዜጠኝነት ኃይልን የበለጠ ተረድቻለሁ። ዘጋቢ እንደመሆኔ መጠን ሥራዬ እውነታዎችን ሪፖርት ማድረግ ብቻ አለመሆኑን አውቄያለሁ። የማኅበረሰቡን እውነት፣ ፍላጎት፣ ስሜት እና ታሪኮቹን ቦታ መስጠት እንደሚገባ አውቄያለሁ። ለመጻፍ ብቻ ወደ እነዚህ ቦታዎች አልሄድኩም፤ ለማዳመጥና ስሜታቸውን ለመጋራትም ጭምር ነበር የተገኘሁት።
በዚህም የተማሪዎች ሳቅ ውስጥ ያለውን ደስታ አይቻለሁ፤ የከተሞችን የማደግ ተስፋና ጉጉት አድንቄያለሁ፤ ትክክለኛ የጤና ስጋት ምን አንደሆነ ለይቻለሁ፤ እውነተኛ የአርሶ አደሮችን ጥንካሬና ቅሬታዎች አዳምጫለሁ። እነዚህ መሰማት የሚገባቸው ድምጾች ነበሩ። ቸር እንሰንብት!!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም