ለዓለም ሻምፒዮና የሚያበቃ ሰዓት የማስመዝገብ ትግል

በቶኪዮ የሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር ዛሬ 64 ቀን ይቀረዋል። በዚህ ትልቅ የአትሌቲክስ መድረክ በመካከለኛና ረጅም ርቀት እንዲሁም በማራቶን ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ለዚህም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች በሻምፒዮናው ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ሰዓት/ ሚኒማ ለማሟላት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማራቶን የሚሳተፉ አትሌቶችን ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ባስመዘገቡት ሰዓት መሠረት መርጦ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ከማራቶን ውጪ ባሉት ርቀቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ግን እስከ ጁላይ 20 (ከአስራ ሦስት ቀን በኋላ) በሚያስመዘግቡት ሰዓት መሠረት የሚመረጡ ይሆናል። በዚህም መሠረት ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለይም በ10 እና 5 ሺ ሜትሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እነማን እንደሚሆኑ ከወዲሁ ፍንጮች ታይተዋል። በአብዛኞቹ የመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ሰዓት ማስመዝገባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። እዚህ ላይ የትኛው አትሌት ከየትኛው አትሌት የተሻለ ሰዓት አስመዝግቦ ይመረጣል የሚለው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሚኒማ ማምጣቱ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሳሳቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና በተደጋጋሚ ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ሰዓት ማስመዝገብ ሲከብዳቸው የሚስተዋሉ የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ዘንድሮስ ማሳካት ይችሉ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ይስባል።

በዚህ ረገድ በቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና በአንዳንድ ርቀቶች መልካም ዜና እየተሰማ ቢሆንም በወንዶች 1500 ሜትር አስፈላጊውን ሰዓት አስመዝግቦ ኢትዮጵያን የሚወክል አትሌት የማግኘቱ ነገር ስጋት ውስጥ ወድቋል። በቀጣዮቹ አስራ ሦስት ቀናትም ይህ ስጋት ቁርጡ የሚታወቅ ይሆናል።

ከትናንት በስቲያ ምሽት በፈረንሳይ ሶትቪል በተካሄደው የብር ደረጃ ያለው ኮንቲኔንታል ካፕ የተሰኘ የሴቶች 800 ሜትር ውድድር ንግሥት ጌታቸው 1:59.89 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ በወንዶች 1500 ሜትር ኤርሚያስ ግርማ 3፡36.73 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ከወራት በፊት በናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያሸነፈችው አትሌት ንግሥት ጌታቸው ባለፈው ዓርብ በፈረንሳይ ኖንሲ በተካሄደ ሌላ የኮንቲኔንታል ካፕ የ800 ሜትር ውድድር ላይም 1፡58.15 በሆነ የተሻለ ሰዓት አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ይህች ወጣት አትሌት ከዚያም በፊት መስከረም ላይ በክሮሺያ ዛግሬብ 1፡57.47 የሆነ የግል ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በ800 ሜትር ሴቶች ከርቀቱ የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ከፅጌ ዱጉማ በመቀጠል በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን እንደምትወክል ከወዲሁ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

በኖንሲው የኮንቲኔንታል ካፕ የወንዶች 800 ሜትር ፉክክር ላይ የግሉ ምርጥ በሆነ 1፡44.49 ሰዓት አሸናፊ ለመሆን የበቃው ዮሐንስ ተፈራ በርቀቱ ለዓለም ሻምፒዮና ዝቅተኛውን መስፈርት (ሚኒማ) ለማሟላት በቅቷል፡፡ የወንዶች 800 ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሚኒማ ለማሟላት በተደጋጋሚ ሲቸገሩበት እየታየ የሚገኝ ርቀት ሲሆን ይህ ወጣት አትሌት የዓለም አትሌቲክስ በርቀቱ በሚያስቀምጠው ደረጃ መሠረት በቶኪዮ ተሳታፊ ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከመሐመድ አማን በኋላ በወንዶች ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል። ባለፈው ጥር ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደ ውድድር 1:44.50 ለሆነው ሚኒማ እጅግ የቀረበ 1፡44፡60 ሰዓት የሮጠው አትሌት ጀነራል ብርሃኑም መስፈርቱን ሊያሟላ የሚችልባቸው የውድድር ዕድሎች በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት አግኝቶ ሀገሩን የሚወክልበት ዕድል ሊኖር ይችላል።

በወንዶች 800 ሜትር ለኢትዮጵያውያን አስደሳች ዜና የመሰማቱን ያህል በወንዶች 1500 ሜትር በዓለም ሻምፒዮናው ሚኒማ አሟልቶ ሀገሩን የሚወክል አትሌት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። የዓለም አትሌቲክስ ለቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና በተለያዩ ርቀቶች ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶችን ዝርዝር በሚያመላክትበት የመረጃ ቋት (Road to Tokyo 25) ላይ እንደሚታየው በወንዶች 1500 ሜትር 3:33.00 (በትራክ ወይም በጎዳና ማይል 3፡50.00) የሆነውን ሚኒማ ያሟላ አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት የለም፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም ሻምፒዮናና በሌሎች ውድድሮች በተደጋጋሚ የሚሳተፉበት የወንዶች 1500 ሜትር እስከ ትናንት ባሉት ውጤቶች ሁለት አትሌቶች (መለሰ ንብረት እና አብዱልከሪም ተኪ) በዓለም አቀፉ ደረጃ መሠረት ሊያሳትፋቸው በሚችል 44ኛ እና 51ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ አትሌቶች እስከ ኦገስት 24/2025 በቀጥታ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ሰዓት ካላስመዘገቡ በስተቀር በዓለም አትሌቲክስ አሁን የተቀመጡበት ደረጃ ለቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ ያደርጋቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You