‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው ይሄን ነው!››

‹‹ገበያን ፍላጎት ይመራዋል›› ይላሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች። አቅርቦት ደግሞ ፍላጎትን ይከተላል። ይህን ለማወቅ የኢኮኖሚስት ባለሙያ ድረስ አያስኬድም። ለማንም ተራ ግለሰብ ሁሉ ግልጽ ነው።

አንድ ነጋዴ ዕቃ የሚያመጣው የሚሸጥለትን ነው። ደንበኞቹ በተደጋጋሚ ‹‹… አለህ?›› የሚሉትን ዕቃ ያመጣል። በተመሳሳይ አቅራቢም እንደዚያው፤ የሚፈለገውን ነገር ነው የሚያቀርበው።

ይህን ነገር ያነሳሁት ስለ ኢኮኖሚ ለማውራት አይደለም። ይልቁንም ‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው ይሄን ነው›› እየተባለ በዋናዎቹም፣ በማህበራዊ ሚዲያዎችም የሚደረገውን ቅጥ ያጣ ድርጊት ለመታዘብ ነው። ‹‹ለምን እንዲህ ዓይነት ነውር ነገር ታደርጋላችሁ?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው ይሄንን ነው›› ይላሉ። የማህበራዊ ሚዲያ አሰራጮች ደግሞ ‹‹ብዙ ሰው የሚያየው እንዲህ ሲደረግ ነው›› ይላሉ። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ከባሕልና እሴት ያፈነገጡ ሁሉ ናቸው።

ለምሳሌ፤ ታዋቂ ሰው በሞተ ቁጥር አንድ የሚደጋገም አሰልቺ ነገር ቢኖር የ‹‹ዩትዩቦች›› የማጭበርበሪያ አሉባልታ ነው። ታዋቂ ሰው በሞተ ቁጥር ዋና ጉዳይ የሚሆነው እነርሱ የሚፈጥሩት የሀሰት አጀንዳ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ለለቅሶ የሚሄደውን ሀዘንተኛ የግል ገመና ሁሉ ሳይቀር ለገበያ ማቅረብ ነው። ማን ሳቀ ማን አለቀሰ የሚል ግምገማ ሁሉ ሳይቀር ይካሄዳል። በዚህ ምክንያት የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ሲደረግ ጭራሹንም እንዳይገቡ መከልከሉን አስታውሳለሁ።

ዋናው ጥያቄና ትዝብት ግን ይህ ለምን ሆነ? የሚለው ነው!

ዩትዩበሮችን እንደ ነጋዴ እንውሰዳቸው። እኛ ደግሞ ሸማች (ደንበኛ ነን)። እያቀረቡልን ያሉት የምንፈልገውን ነገር መሆኑ ነው። በርግጥ አንድ ነጋዴ ጥራት የሌለው ዕቃ ወይም ጎጂ የሆነ መርዛማ ነገር ሲሸጥ ይጠየቃል። በዚህ መሠረት ሀገርና ሕዝብ የሚጎዳ ነገር የሚያቀርቡት የዩትዩብ ሸቃዮች መጠየቅ ነበረባቸው። እስከዚያ ድረስ ግን የእኛን የሸማቾችን ችግር ልብ እንበል!

ከእውነተኛ ነገር ይልቅ ለአሉባልታ ቅድሚያ እንሰጣለን። አንድ የሕክምና ዶክተር ስለአንድ ገዳይ በሽታ የሚያብራራ ቪዲዮ ቢለቀቅ እና አንድ ምንም ሙያ የሌለው ተራ ግለሰብ ‹‹የእገሌ አሟሟት ምሥጢሮች›› የሚል ቪዲዮ ቢለቀቅ የትኛው ነው ብዙ ተመልካች የሚያገኘው?

ሕይወታችንን የሚያድን ሙያዊ ማብራሪያ ከሚሰጠው ሐኪም ይልቅ፤ የሌላ ሟች የአሟሟት ሁኔታ ምን ይሆን የሚለው ያሳስበናል። ይሄ መጥፎ ልማዳችን ነው።

ግደለም! ምሥጢራዊ ነገሮችን ለማወቅ መጓጓት የሰው ልጅ ባህሪ ነው እንበል! ቢያንስ ግን የዩትዩብ ተደጋጋሚ ውሸት ግልጽ ማጭበርበሪያ መሆኑ እየታወቀ እንዴት ሰው ደጋግሞ ይሸወዳል? እንደዚያ የሚያደርጉት እኮ ውሸት መሆኑን እያወቅንም ቢሆን ስለምናይላቸው ነው።

ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ወይም ፋና ወይም ዋልታ ወይም ሌላ ‹‹ሜይንስትሪም›› ሚዲያ እንደዚያ ዓይነት ርዕስ ቢሠጥ ምናልባት የምርመራ ዘገባ ሰርተው ነው በሚል ያጓጓል፤ ሀሰት ቢሆን እንኳን ግልጽ የሆነ ተጠያቂነት ያለባቸው እና ለመውቀስም ተቋማዊ ባለቤት ያላቸው ስለሆኑ አያደርጉትም ብለን እናምናለን። በአጠቃላይ መረጃውን ለማየት እንገደዳለን።

ሰው እንዴት በአንድ ግለሰብ የሚመራ፣ የኤዲቶሪያል ሕግ የሌለው፣ ለሀገር ግንባታ ሳይሆን ለግለሰብ ሳንቲም መልቀሚያ ተብሎ የተከፈተ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ይሸውደዋል? የዚያ ገጽ (ቻናል) ባለቤት እኮ ግለሰብ ነው። በአንድ ግለሰብ ስሜት ብቻ የሚመራ ነው። ስለዚህ ብዙ ተመልካች ያስገኝልኛል ያለውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።

እዚህ ላይ ግን በኃላፊነት የሚሠሩ የሉም ማለቴ አይደለም። ፈቃድ አውጥተው፣ ብቁ ባለሙያዎችን ቀጥረው፣ በትልልቅ መገናኛ ብዙሃን የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች የሚሰሩባቸው የዩትዩብ ቻናሎች መኖራቸውን አምናለሁ። እነርሱ እንዲህ ዓይነት የበሬ ወለደ ዜና አይሠሩም፤ እያወራሁ ያለሁት ተመልካች ለማግኘት ብቻ ብለው ስለሚያጭበረብሩት ነው።

ሲጀመር በተገቢው የጋዜጠኝነት ሙያ የሚሠራ ዜና የሚጮህ ርዕስ የለውም። አንድ የዜና ርዕስ ጯሂ ከሆነ የውሸት ወይም የተጋነነ የመሆኑ ምልክት ነው። አርዕስተ ዜና ይዘቱን ጠቅልሎ የሚነግር ጥቅል ርዕስ ነው። በዜናው ውስጥ የማይገኝን ነገር መግለጽ የለበትም። በዩትዩብ ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነት የነጭ ውሸት ርዕሶች የተለመዱ ሆነው ሳለ በተደጋጋሚ የሚሸወዱ ሰዎች ናቸው የሚያሳዝኑት።

በበኩሌ በዩትዩብ ርዕስ ተሸውጄ አላውቅም። ገና ርዕሱን አይቼ ነው የሚገባኝ። ‹‹አዳምና ሔዋን ከገነት ሲባረሩ ለማየት ሊንኩን ይጫኑ›› ዓይነት የማይመስሉ ነገሮችን ለማየት ደቂቃ አላባክንም። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንዳልኩት እውነተኛ ነገር ጯሂ ርዕስ አይጠቀምም።

ሚዲያን የመከታተልና የማወቅ ልማዳችን ለማጭበርበር ምቹ ነው። የውሸት ርዕስ የሚጠቀሙ ሰዎች ሌላ የተለየ ዓላማ ኖሯቸው ሳይሆን ሳንቲም ለማግኘት ነው። የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው በሚፈጠረው ውዥንብር የሚጠቀሙት ነገር ስላለ ነው። እነዚህኞቹ ግን በተመልካች ብዛት ክፍያ እንደሚገኝ ስለሚያውቁ ለክፍያው ነው። ለፖለቲካ አጭበርባሪዎችም ሆነ ለሳንቲም አጭበርባሪዎች ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ግን ተመልካቹና ተከታዩ ነው።

ለዚህ መፍትሔው፤ ‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው ይሄን ነው›› የሚለውን ትርክት ማጥፋት ነው። ይህ አባባል እኮ ንቀት ነው። ሕዝቡ ሃሳባዊ፣ ሳይንሳዊና ሙያዊ የሆነ ነገር አይገባውም፣ አይመጥነውም እያሉ ነው፤ ይሄ ንቀት መሆኑ ሊገባን ይገባል።

አንድ ብዙ ተከታይ ያለው ‹‹ቲክቶከር›› የብልግና ነገሮችን ይናገራል። በዚህ ሰው ገጽ ላይ ታዋቂ አርቲስቶችና ባለትዳር ሰዎች ሳይቀር ቀጥታ እየገቡ የእሱን ነውር ቃላት እያዳመጡ ይስቃሉ። እሱ ጋ የሚሄዱበት ምክንያት ብዙ ተከታይ ስላለው ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ነው።

ይህ ሰው ግን በሌላ ማህበራዊ ሚዲያ እንግዳ ሆኖ ሲናገር፤ ‹‹እኔ በጨዋነት ያደግኩ ነኝ፤ ባለጌ ሆኜ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሕዝቡ የሚወደው እንዲህ ዓይነት ነገር ስለሆነ ተከታይ ለማብዛት እና ገንዘብ ለማግኘት ብዬ ነው›› ብሎ ግልጹን ተናግሯል። ይህ ሰው ንቆናል ማለት ነው። ለእናንተ የሚመጥናችሁ እንዲህ ዓይነት ነገር ነው እያለ ነው ማለት ነው። ስለዚህ አብዛኞቻችን የምንከታተለው አስተማሪና ቁም ነገር ያላቸውን ነገሮች ቢሆን ኖሮ የማህበራዊ ገጾች ዝንባሌ ወደ እንዲህ ዓይነት ነገር አይሆንም ነበር ማለት ነው።

በነገራችን ላይ የማህበራዊ ገጾችን ነገር መናቅ ልክ አይደለም፤ የሚፈጥሩት የትርክት ጫና ቀላል አይሆንም። በማህበራዊ ገጾች ላይ ብቻ ተገድቦ አይቀርም፤ በማህበራዊ ሕይወታችን እና በአጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ይኖረዋል።

ስለዚህ ‹‹ሕዝቡ የሚወደው ይሄን ነው›› እያሉ ከሚንቁን፤ እኛ እንናቃቸው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You