የሕዝባችን ኅብር የተዋበውና የሰመረው በብሔረሰ ቦቻችን ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወጎችና ልማዶች በተዛነቁና በማይደበዝዙ ደማቅ የአብሮነት የትውልዶች የታሪክ ሥዕል አሻራ ላይ ታትሞ ነው፡፡ የቀስተ ደመና ቀለማትን ውበት እንዲሁ በማየት እናደንቃለን እንጂ የቀለማቱን ዓይነትና ኅብር በተመለከተ ብዛቱና ውህደቱ ይህንን ያህል ነው ብሎ ለማስተንተን እንኳን በሌጣ ዓይን ቀርቶ የዘመናችን ሳይንሳዊ ምርምርም ገና አልደረሰበትም፡፡
የሕዝባችን ውበትና ስብጥርም በተፈጥ ሯዊ የቀስተ ደመና ውብ ቀለማት መመሰሉ ስለዚሁ ነው፡፡ ለሀገራችን ብሔረሰቦች ቦታና ወሰን ከልለንላቸው መገኛቸው እዚያና እዚህ ነው በማለት አፍ ሞልተን ልንናገር እንችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚያን ብሔረሰቦች ቀዳሚና ነባር አባላት በወሰን ከተከለሉበት አካባቢም ይሁን ውጭ በደም ውርርስ የተቀላቀሏቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ዘርዝሮና አመላክቶ ለመጨረስ ግን የሚሞከር አይሆንም፡፡
ሰሜናዊው ወገናችን ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል፣ የምዕራቡም ወደ ምሥራቁ፣ የደቡቡ ወደ ሰሜን፣ የምዕራቡም ወደ ደቡብ እየተንቀሳቀሱ ለሺህ ዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ አብረው በመኖራቸውም በደምና በዘር ተቀላቅለዋል። እርስ በእርስ መጋመዳቸውም በቀላሉ ተተርትሮ ይጎለጎላል ተብሎ አይታሰብም። ሲዳማው ከአማራ፣ ትግሬው ከኦሮሞ፣ ጋሞው ከወላይታ፣ ሱማሌው ከአደሬ፣ ጎፋው ከጉራጌ፣ ኮሞው ከአፋር፣ ሽናሻው ከስልጤ ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል፡፡ ይህ ሕብረ ሕዝብ የውጭ ወራሪዎችን ሊመክት፣ ወይንም አትርፎ ሊነግድ፣ አለያም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰላማዊ ምክንያቶች ሳቢያ አንዱ ወገናችን ወደ አንዱ ሲንቀሳቀስ፣ ሌላኛው ወደ ሌላው አካባቢ ሲዘምት ተጓዥ ብቻ አልነበረም። የማንነቱን አሻራ ሲያትም የኖረውም የባህሉን፣ የቋንቋውን፣ የወግና የልማዱን፣ የታሪኩንና የማንነቱን አሻራ በማተም ብቻ ሳይሆን የደምና የአጥንት ትስስር በመፍጠር ጭምር ነው። ይወልዳል ይዋለዳል። ይበዛል ይባዛል።
ይህ መሠረታዊ የዜጎቻችን ተፈጥሯዊ መዋሃድ፤ «የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ» እንዲሉ ኅብሩ የደመቀውና ስብጥሩ የሰፋው በጋራ ታሪክና በደም የተሳሰረበት ማንነቱ የገዘፈ፣ ውበቱም እጅግ የደመቀ ስለሆነ እንለይህ ቢሉት የማይሞከር፣ እንከፋፍልህ ቢሉት የማይደፈር ሆኖ ስለተሠራ ነው፡፡
ታላቁ የሀገራችን የቀለም ቀንድ ከበደ ሚካኤል የዛሬ ሰባ ሰባት ዓመት ስለ ሕዝብ ማንነት የሰጡትን ድንጋጌ ማስታወሱ ሃሳቤን ይበልጥ ያጎላዋል፤ «ሕዝብ በአንድ ሀገር፣ በአንድ መንግሥት፣ በአንድ ሰንደቅ ዓለማ፣ በአንድ ሕግ ጥላ ተሰብስበው የሚኖሩ ሰዎች ማለት ነው፡፡
«አንድ ሕዝብ በትውልድ፣ በቋንቋና በሃይማኖት መገናኘት ብቻ ሳይሆን፣ ባለፈው ኑሮው ደስታና መከራን፣ በአንድነት የተካፈለ፣ በአስተዳደሩም በልዩ ልዩ ሥራ የተሳሰረ፣ ለወደፊቱም እሠራዋለሁ በሚለውና ስለ ሀገሩና ስለ መንግሥቱ ያለው ተስፋ አንድ የሆነ ማለት ነው፡፡»
ደራሲው «አንድ ነው» ሲሉ የደማቅ ኅብሩን ውበትና የትስስሩን ጥብቅነት ለማመልከት እንጂ አንዳንዶች በተጻፉ ሁለት መስመሮች መካከል ያልተጻፈ ሦስተኛ መስመር እያነበቡ «አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ማንነት» ለመስበክ ተፈልጎ ነው እያሉ ለአሀዳዊ የመንግሥት አወቃቀር በአብነት እንደሚጠቅሱት አይደለም፡፡ በፍፁም፡፡
ይህ ያለንበት ወቅታዊ ዐውድ በእንዲህ መሰሉ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ውህደት የተጋመደውን ሕዝብ ለማለያየትና በዘመናት መካከል የተገነባውን የአብሮነት ጠንካራ እሴት ለመናድ የሚደረገው እንቅስቃሴ እራሱን ቀስቃሹን ይጎዳ ካልሆነ በስተቀር አንዳችም የረባ ውጤት አያስገኝም፡፡ ወቅቱ ምንም ፈታኝ ቢመስልም ሰሞንኛ ነፋስ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ነገር ወደ ብርሃን ሲገለጥና ሕዝቡ ለሰለባነት መታጨቱን ሲረዳ ሴረኞችን አይቀጡ ቅጣት መቅጣቱ አይቀርም፡፡
እጅግ የሚያሳዝነውና ለታሪካዊ ትዝ ብት የሚዳርገውን ይህንን የአፍራሽነት ተውኔት በመሪ ተዋናይነት እየተጫወቱ ያሉት «ምሁር» የሚል ቅጥያ ከስማቸውና ከሰለጠኑበት ሙያ ፊት የለጠፉ ጥቂት ግለሰቦች መሆናቸው ነው። መዛግብተ ቃላት «ምሁር» ለሚለው ቃል የሚሰጡት ፍቺ «በትምህርት፣ በዕውቀት፣ በችሎታ አእምሮው የበለፀገን» ሰው ነው፡፡ የዘመናችን አንዳንድ «ተማሩ» ተብዬዎች ግን እንኳንስ የትምህርት፣ የዕውቀትና የችሎታ ባለጠጋ ሊሆኑ ቀርቶ የሰለጠኑበትን የትምህርት ሥነ ምግባር እንኳ በቅጡ ጠንቅቀው ስለማወቃቸው የሚያጠራጥሩ ናቸው።
መሰልጠንመሰይጠን፣መማርም መደንቆርእስከሚያስመስልባቸው ድረስ በግልጥና በስውር የሚሰሩት ደባ በይፋ የተገለጠ ዕለት ወዬው ለእነሱ፡፡ ጥበባቸው ለውርደታቸው፣ ብልጠታቸው ለጥፋታቸው እንደሚሆን ሐቁን የተረዱት አይመስልም፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው አንጋፋ ደራሲ ለእንደነዚህ መሰል የጨለማ ምንዱባን የሚከተለውን ግጥም አስፍረው ነበር፡፡
የደንቆሮ መንፈስ ምንኛ ታደለ፣
ብልጥነት አላጣም ጅል እየመሰለ፡፡
እንኳን መጽሐፍ ማንበብ ፊደል ሳያጠና፣
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና፡፡
ከመቼውም ዘመናት ይልቅ እንደዘንድሮ «ሁሉን አወቅ ነኝ ባይ ምሁራን» በሀገሪቱ ላይ የሰለጠኑበት ጊዜ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተ ሞከረው «የሕግ ምሁር፣ የሰላምና የደህንነት ጥናት ምሁር፣ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር፣ አክቲቪስት ምሁር ወዘተ…» የሚል ቅጽል ስም ከስማቸው በፊት እያስቀደሙ የመገናኛ ብዙኃንን መድረኮች በማጣበብ ከማቀራረብ ይልቅ መራራቅን፣ ከማስታረቅ ይልቅ ጠብን እየዘሩ በሕዝብ መንፈስና አእምሮ ላይ መርዝ እያንጠባጠቡ ሤራ ሲጎነጉኑ መዋላቸው እንግዳ ክስተት አይደ ለም፡፡
ተከባብሮ በኖረው ሕዝብ መካከል የእንክርዳድ መልዕክት እየጠመቁ እርስ በእርስ ለማሳከር የሚሞክሩ «ተማርን ባይ» ግለሰቦች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ እያስቸገረ ያለበት ወቅት ነው፡፡ በትዕቢትና በድፍረት ተሞልተው ነባርና ቅቡል ታሪክን እየናዱና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተገን አድርገው በመጠለል የሚሰሩት ያልተገባ አፍራሽ ተግባር ገበናውን ጊዜ እስኪገልጠው ድረስ የሚፈጥረው ቀውስ ቀላል ነው ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡
የሕዝቦች ልዕልና፣ አንድነትና አብሮ የመኖር ምሥጢር «ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ» ይሉት ዓይነት የሕፃናት ጨዋታ አይደለም። «ኢትዮጵያ ትበተናለች፣ ሕዝብ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ያመራል»እያሉ በይፋ የሚነዙት የሟርት መልዕክት የስብዕናቸውን ዝቅጠት ከማሳየት ውጪ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡
ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት፣
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት፣
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ፣
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ፡፡
እንዳሉት አንጋፋው ደራሲ እንደነዚህ ዓይነቶቹን «ስመ ምሁራን» ግለሰቦች ሕዝቡ ሊገስጻቸውና እነርሱን ሳይሆን እኛን አድምጡን ብሎ በአደባባይ ሊገትራቸው ይገባል፡፡ በደምና በአጥንት ውህደት የተሠራ ታላቅ ሀገርና ሕዝብ አይደለም ግራ ተጋብተው ግራ ለማጋባት በሚሞክሩ ጥቂት ግለሰቦች ቀርቶ ለታጠቀና በሚገባ ለደራጀና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ሊደልለው ለሞከረ ወራሪ ኃይል እንኳ አሜን ብሎ ለውርደት እጁን እንዳልሰጠ ታሪካችን ምስክር ነው፡፡
የፈጠራ ትርክት እያቀናበሩ በሕዝቦች መካከል የመቃቃር ዘር የሚዘሩና የመለያየት አዋጅ የሚያውጁ ግለሰቦች ምኞት ቅዠት፣ ህልማቸውም ከንቱ እንደሚሆን ልብ ኖሯቸው ልብ ቢሉ ይበጃቸዋል፡፡ የፖለቲካ ማስክ አጥልቀው፣ የአውቃለሁ ባይ ትርክታቸውን እየዘመሩ ሕዝብንከሕዝብ፣ወገንንከወገኑ፣ ወንድምን ከወንድሙ፣ ቤተሰብን ከቤ ተሰብ ለማናከስና ለማቆራቆስ መሞከር ጊዜያዊ የሙቀት ወላፈን ይፈጥር ካልሆነ በስተቀር በረጂሙ የሚዘልቅ የመለያየት ውጤት እንማያስከትል የታሪኩን ዋቢነት ቢያጣቅሱ መልካም ይሆን ነበር፡፡
አንድ ወንዝ ለታላቅነት ክብር የሚበቃው ከመነሻው እስከ መድረሻው በተለያዩ ገባር ወንዞች እየፋፋ ኅብር በመፍጠር ይጎለብታል እንጂ እስከ ውቂያኖስ ማረፊያው ተጓጉዞ የሚደርሰው ከአንዲት አነስተኛ ምንጭ በሚመነጨው ውሃ ብቻ አይደለም፡፡ የሕዝብ ፍሰት፣ ውህደትና ስምረትም በታላቅ ወንዝ ይመሰላል የሚባለው በዚሁ ምክንያት ነው። ይህን መሰሉን ታላቅ የሕዝብ ጅረት ፍሰቱን ለመግታትና ለማስቆም ጥቂት ግለሰቦች ወንዙ መሃል ቆመው ጭቃ እያድቦለቦሉ ለመገደብ ቢሞክሩ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ሕዝብ ኃያል ነው፡፡ ሕዝብ ታጋሽና ብርቱም ነው፡፡ አማራው ያለ ኦሮሞ ወንድሙ አያምርበትም፡፡ ትግሬው ያለ ጉራጌ አይደምቅም፡፡ ሱማሌው ያለ ሲዳማ ወገኑ፣ ጎፋው ያለ ወላይታ ጎረቤቱ፣ ኑኤሩ ያለ ሸኮ፣ ጌዲኦው ያለ አፋር ልሙጥ ጥለት ካልሆነ በስተቀር የጥበብ ሞገስና ካባ ላይደርብ ይችላል፡፡
የማከብረው መምህሬ ደበበ ሰይፉ ከሦስት አሠርት ዓመታት በፊት ይህንን ኢትዮጵያዊ ኅብር የገለጠበት አንድ አስደናቂ ግጥሙ የማይደበዝዝ መልዕክት እንደያዘ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡ ግጥሙ ትንሽ ዘለግ ስለሚል እንጂ ቢቻል ኖሮ እንዳለ ሙሉው ሃሳብ ቢቀርብ ትልቅ ትምህርት ይሰጥ ነበር። የግጥሙን ይዘት ባይመጥንም በአጭሩ መልዕክቱን ላስተዋውቅ፡ ለመንደርደሪያነት እንዲረዳም የግጥሙን የመጀመሪያ ስንኞች እንዳለ ልጥቀስ፡፡
ትግራይ ላከ ወሎጋ አበድረኝ ብሎ
አንድ ቁና ጤፍ፣
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን
ባህሉን ለመዝለፍ ቆሌውን መንቀፍ፤
ላከ ወደ ሸዋ ምናልባት ቢሰጠው
ለሰው እሚተርፍ፡፡
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን
ወደ ሐረር ዞረ፣
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ፡፡
ባሌም ወደ አርሲ፣ አርሲ ሲዳሞን፣
ሲዳሞም ተክዞ ግን የለኝም ብልስ፣
ማን ያምነኛል ብሎ፣
ወደ ጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅልሎ፡፡
ግጥሙ አላቀበቃም፡፡ በዝሩ ሃሳብ እንቀጥል፡፡ጋሞም ጓዳውን ቢዳብስ ምንም ስላላገኘ አቁማዳውን በክብር አሲዞ ወደ ወንድሙ ወደ ከፋ ላከው፡፡ ከፋም ዘመን ከፍቶበት ኖሮ ወንድሙ ጋሞን መርዳት ባለመቻሉ እንባውን እያዘራ ወደ ጎረቤቱ ወደ ኢሉባቦር አቁማዳውን ሰደደ፡፡ ለጭምቱ ኢሉባቦርም ጊዜ ፊቱን አዙሮበት ስለነበር የሚያደርገው ቢጠፋው ለጎጃም ወንድሙ ችግሩን አስተዛዝኖ አንድ ቁና ጤፍ እንዲልክለት ባዶውን አቁማዳ በአደራ ቃል ጠፍሮ ላከለት። ጎጃምም ጊዜያዊ ችግር አቆርፍዶት ኖሮ ወንድሜ ሆይ እባክህ ድረስልኝ ብሎ ወደ ወገኑ ወደ ጎንደር የአደራ መልዕክት ላከለት። ጎንደርም በወንድሙ በጎጃም እጦት ልቡ እጅግ ተነክቶ ጎታው ባዶ ቢሆንበት ወደ ወንድሙ ወደ ትግራይ አስተዛዝኖ መልዕከት ላከበት፡፡ ይሄን ጊዜ ትግራይ የራሱ አቁማዳ ተመልሶ እራሱ ዘንድ መድረሱን ሲያስተውል እንዲህ ብሎ ተቀኘ ይለናል ባለ ምጡቅ አእምሮው ደበበ ሰይፉ፡
ትግራይ አስተውሎ አቁማዳው
የራሱ መሆኑን ለይቶ፣
ረሀብእጣቸው የሁሉ ወንድሞቹ፣
መሆኑን አካቶ፣
ሀዘኑ አነቀው፣ ትንፋሹ መረረው
ትካዝ ሆዱ ገብቶ፡፡
“እኔና ወንድሞቼ” አለ በለዘብታ፣
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፡፡
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን ሁላችን፣
ከባዶ አቁማዳ ነው የሚዛቅ ፍቅራችን፡
ይህ ነው አንድነታችን፣
ይህ ነው ባህላችን፣
ዘመን ማዛጋቱ በየአንደበታችን።
የሕዝባችን መገለጫ እውነት ይህ ነው። ለዘመናት አስተሳስሮ ያኖረን የማይናወጠው እውነት ይሄው ነው። በመከራ ዘመን መደጋገፍ፣ በክፉ ዘመን መረዳዳት፣ በተድላ ዘመን መተቃቀፍ የሕዝባችን ታሪክና ባህል የሚነግረን ይህንን እውነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ይህ የሕዝባችን የቃል ኪዳን ትስስር ውሉ እንዳይላላ መጠበቅ ይኖርብናል እያልን ክፉዎችን የምንገስፀው፡፡ የተሳሳቱት ወደ እውነት እንዲመለሱ የምንመክረው፡፡ ሰላም ይሁን፡፡
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ