
ተራና ተራራ ስናያቸው ተቃራኒ ቃላቶች ይመስላሉ። ተራ ሰው ሲባል ተርታ ሰው ማለት ነው። አራዳዎች በገንዘብ ትልቅ አቅም ያለውን ሰው ተራራ ይሉታል። ርዕሴ ተራዎቹ ተራራዎች የሚል ነው። የተራራ ተራ የለውም ብል ሳይንሳዊ ማስረጃ አምጣ እንደማትሉኝ እገምታለሁ። ተራራ፣ ጋራ በተፈጥሮ ከፍ ያለ ስፍራ ነው። ግን ተራዎቹ ተራራዎች ያልኩት ግን ስለመርካቶ ግብይት ተራዎች ላወጋችሁ ሽቼ ነው።
የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በገጽ 1272 ላይ ቃላቶቹን ፤ ተራራ ረጅምና ከፍተኛ አምባ፣ ብርቱ ሥፍራ የምድር ራስ፣ በትግርኛ ተረረ ጠና፣ ጠነከረ፣ በረታ ማለት ነው። ተራ ወደሚለው ፍቺ ስንመጣ ደግሞ ተራ ረድፍ ፊና ወረፋ፤ ተርታ መናኛ፣ ትሁት፣ ተራ፣ መደዳ ሲለው እንዲሁም ተርታ ሰው፤ ሹመት ማዕረግ የሌለው ተራ ሰው ይለዋል።
እኛ ከገበያ ስፍራ አንፃር የጠቀስነውን ቃል ደግሞ ተራ የሸቀጥ መደብ ፣ መደብር ሥፍራ። እህል ተራ፣ በግ ተራ፣ ጌሾ ተራ፣ አጠና ተራ፣ ማዕዘን ተራ፣ ሰንጋ ተራ በማለት ይፈታዋል። የደበበ ኃይለጊዮርጊስ የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋሮች መጽሐፍ ደግሞ ተራ ሰው ሥልጣን የሌለው ሰው፣ ተራ ወታደር ማዕረግ የሌለው፣ ተርታ ሰው የማይረባ ሰው በሚል በፈሊጣዊ አነጋገር እንደሚፈታ ያሳያል።
ሰሞኑን የመርካቶ ሰዎች ግርግር ለማስነሳት ሞክረው ነበር። በገቢዎች ቢሮ ያለ ደረሰኝ ትነግዳላችሁ ነው ነገሩ። ርግጥ አብዛኛው የመርካቶ ነጋዴ ያለ ደረሰኝ ነው የሚነግደው። የንግድ ሥርዓቱ ራሱ ሥርዓተ አልበኝነት በሰፊው የሚታይበት ነው። ኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ በስፋት የተንሠራፋበት መርካቶ ጉዱ ተዘርዝሮ የሚያልቅም አይደለም። ለማታውቁት ገብታችሁ ብታዩት ጉድ! ጉድ! ጉድ! ነው የምትሉት።
ግብይቱን በደረሰኝ የማካሄዱንና ሥርዓት የማስያዝ ሙከራው ግን የሚናቅ አይደለም። ቀስ በቀስ ፈር እንደሚይዝ እሙን ነው። እዚህ ላይ ግን በተጨማሪ ዕሴት ታክስ የሚነግዱ ነጋዴዎች ማሰብ ተገቢ ነው። ተጨማሪ ዕሴት ታክስ (ተዕታ) የሚነግዱት በደረሰኝ እንዲሆን ሕጉ ያስገድዳቸዋል። ግን በአደባባይ ያለ ተዕታ የሚነግዱትን ማየትም ይገባል።
ዕቃ ስትገዙ ከፊሎቹ በተ.ዕ.ታ ይሁንልህ? ብለው ገበያተኞችን ይጠይቃሉ። ያው ተዕታ ከሌለ ይቀነስልሀል ነው ነገሩ። የተወሰኑት ደግሞ በተዕታ ሽጠው ደረሱኝ አይሰጡም። 15 በመቶውን ወደ ኪሳቸው ይከታሉ። ገበያተኛውም ተዕታ ደረሰኝ አይጠይቅም። የተዕታው ንግድ ራሱ ሥርዓተ አልበኝነት የሚታይበት ነው። ማን ሥርዓት ያስይዘው? ቅድሚያ ያለ ተዕታ ደረሰኝ የሚሸጡ ነጋዴዎችንና የሚገበያዩ ሰዎች ፈር እንዲይዙ ማድረግ ይገባል።
በመርካቶ በአግባቡ ነግደው ወገኖቻቸውን የሚያገለግሉ አሉ። በተፃራሪ ሕገ ወጥ ንግድ እያካሄዱ የእጥፍ እጥፍ ትርፍ ለማጋበስ የሚስገበገቡትም በርካቶች ናቸው። በአንድ ጀምበር ኢንቨስተር የሚሆኑ። የሚጠበቅባቸውን ቀረጥና ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ፣ በተጭበረበሩ ደረሰኞች የሚነግዱ፣ ምርቶችን እየደበቁ፣ እጥረት እየፈጠሩ ሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚቆልሉና የሀብት ማማ ላይ ለመቆናጠጥ ሸማቹንና ገበያተኛውን በችግር የሚቆነጥጡ ገበያው ይቁጠራቸው።
በአፍሪካ ትልቁ ገበያ መርካቶ ሁሉን አካቶ የያዘ የምንኮራበት ቱሪስቶች የሚጎበኙት ሥፍራ ነው። የበለጠ እንድንኮራበት ግን በሕጋዊ መንገድ ግብይት የሚካሄድበት ይሁን። ግብይቱን ማዘመንና ሕጋዊ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት። የመርካቶን አቅም ያሉት የተለያዩ ባንኮችና በባንኮቹ የሚገባውና የሚወጣው ብር ብዛት ይመስክረው ማለት ነው የሚሻለው።
የባንኮቹ ብዛት በመርካቶን የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ ያሳያሉ። አንድ ባንክ ቅርንጫፉን ከፍቶ አስፋልት ተሸጋሮ ፊት ለፊቱ የዛው ባንክ ቅርንጫፍ ያየሁት በመርካቶ ነው። እንደ መርካቶ በትንሽ ቦታ ብዙ ባንኮችን አካቶ የያዘ ሥፍራ በሀገሪቱ የለም። የሀገሪቱ እስከ 60 በመቶ የሚደርሰው ምጣኔ ሀብት የሚንቀሳቀሰው በዚህ ሥፍራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
መርካቶ ተራና ነጋዴና ተራራ ነጋዴ ያሉበት ሥፍራ ነው። ከጥቃቅንና አነስተኛ ቸርቻሪዎች እስከ ትልልቆቹ አስመጪና ላኪ ጅምላ አከፋፋዮች። ተለጣፊና ተነጣፊ በተለምዶ የአርከበ ሱቅና ማዳበሪያ ነገር አንጥፈው የሚሸጡት፣ ሱቅ በደረቴዎች ጫኝና አውራጆች፣ ደላላዎች የተለያየ ሙያ ባለቤቶች ያሉበት ሥፍራ ነው።
መርካቶ ከግብይቱን አልፎ ብዙ ባለሙያዎችን አካቶ የያዘ ነው። የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የሚያስንቁ የልምድ ባለሙያዎችን አሉበት። የኤሌክትሪክ፣ የቧንቧ፣ የቡና ማሽን፣ የቴሌቪዥን፣ የፍሪጅ፣ የኪስ ስልክ፣ የእጅ ሰዓት፣ የበር ቁልፍ ሆነ የመሳቢያ ቁልፍ ጥገና ሰዎች፣ ጫማ ሰፊው፣ ልብስ ሰፊው፣ ቀለም ቀቢው፣ አናፂው፣ ግንበኛው ወዘተ… የሚገኙበት ነው።
መርካቶ እንዳቅምቲ ድሃውም ሀብታሙም የሚገበይባት፣ የሚሸጥባት ቦታ ነች። ሁሉንም የምታስተናግድ ስፍራ ነች። ቀድሞ በባንኮቹ ብር በቦርሳ ሞልተው ድሆችም እንደቅማቸው ብር ሲያወጡና ሲያስገቡም ይታይ ነበረ። አሁን ቴሌ ብርና የሞይባል ባንክ ሲመጣ ብዙ ብር ለሚያወጣ መላ መጣ።
ከላይ እንደተገለጸው የግብይት ሥፍራዎቹ ተራ በማለት ይጠራሉ። ከተራ አንፃር የተጠቀሱትን ሥፍራዎች ቁሳቁሶች፣ ሸቀጦች የሚገኙባቸው ቦታዎች እንደሆኑ አመላካች ናቸው። ለአብነት ከመርካቶ ራቅ ያሉ አጠና ተራ፣ ሰንጋ ተራ፣ ሶማሌ ተራ የሚባለው ቦታዎች አሉ።
ሰንጋ ተራ ወደ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ያለው አካባቢ የከተማው ሰንጋ በሬ መገበያያ ስፍራ ነበር። ዛሬ ሰንጋ በሬ ለዓይን ባይታይም ሰንጋ በሬ የሚያስንቁ ሰንጋ ባንኮችና ኢንሹራንሶች የተሰገሰጉበት፣ ዋና ዋና ጽሕፈት ቤታቸውን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ አሰርተው ለመዲናዋ ለዛና መዐዛ የራሳቸውን ቅመም የጨምሩበት ሥፍራ ሆነ።
በሰንጋ ተራ ሰንጋ በሬ የለም። ዛሬ ሰንጋ ብሬ የምንላቸው የፋይናንስ ተቋማት አውራጃ ሆነዋል። መዲናዋን መዲና እንድትሆን አድርገዋታል ማለት ይቻላል። እናም በሰንጋ ተራ የራሳቸውን የፋይናንስ ተራራ ፈጠሩ ማለት ነው።
በነገራችን ላይ መዝገበ ቃላቱ ላይ ተራ ሲባል ሸቀጦች የሚገበያዩባቸው ሥፍራዎች ናቸው ቢልም፤ አይደሉም ብዬ እሞግተዋለሁ። ከፒያሳ ወረድ ብሎ ያለው ሶማሌ ተራ፣ በመርካቶ የሚገኘው ሲዳሞ ተራ በዘመኑ የአካባቢው ሰዎች በብዛት የሚገኙበት ሥፍራ ስለነበረ የወጣላቸው ስያሜ ነው። በመርካቶ የማይሸጥ ነገር የለም፣ ቅመማ ቅመሙ፣ አዝዕርቱ፣ አትክልቱ፣ ዱቄታ ዱቄቱ፣ ብረታ ብረቱ፣ ወርቃ ወርቁ (ጌጣ ጌጡ)፣ ጨርቃ ጨርቁ ወዘተ…።
በመርካቶ ውስጥ “ተራ” በመባል ከሚታወቁ መካከል፤ ምናለሽ ተራ፣ ቆርቆሮ ተራ፣ ጋዝ ተራ፣ ቦንብ ተራ፣ አውቶቡስ ተራ፣ ቆጮ ተራ ፣ብረት ተራ፣ ቡና ተራ፣ ሳጥን፣ ወንበር፣ ሸክላ፣ ፎዴ፣ ሸራ፣ ወራባ ተራ ይጠቀሳሉ። ሰሞኑን ድንች ተራ አካባቢ እሳት ተነስቶ ነበር። በአካባቢው ጌሾ ተራ፣ ሽንኩርት ተራ፣ ዶሮ ተራ፣ ሸማ ተራ፣ ሳህን ተራ፣ ዕጣን ተራ አንድ ፌርማታ በማይሞላ ርቀት ተዋሳኝ ናቸው።
በጣና ገበያ አካባቢ ደግሞ ፍራሽ ተራ፣ ድር ተራ፣ ቦምብ ተራ፣ ፎርድ ተራ፣ ተሻግሮ ደግሞ ሚሊቴሪ ተራ፣ ዱባይ ተራ …ወዘተ አሉ። ተራዎቹን ራሱ ብንዘረዝራቸው ለገፃችን ተራ አይበቃቸውም። መርካቶ በተራ ብቻ የተከፋፋለች አይደለችም። ገበያ፣ በረንዳ የሚባሉ ቦታዎችም አሉ።
የመሳለሚያው እህል በረንዳ የመዲናዋ ዋነኛ ጅምላና ችርቻሮ የእህል መገበያያ ሥፍራ ነው። ሰባተኛ በሌላ ስያሜው ሸንኮራ በረንዳ ይባላል። ሸንኮራ እየመጣ የሚራገፍበትና የሚሸጥበት ነው። በክረምት መባቻ ደግሞ የበቆሎ እሸት ለቸርቻሪዎች መሸጫ፣ ከፊሉም የበቆሎ እሸት እየጠበሱ የሚሸጡበት ሥፍራ ነው። ጎጃም በረንዳና ጨው በረንዳ ደግሞ ተጎራባች ሥፍራዎች ናቸው።
አብዶ በረንዳ ደግሞ በሌላ ስሙ ጫት ተራ ይባላል። የመዲናዋ ዋነኛ የጫት ጅምላና ችርቻሮ ማከፋፋያ ነው። ንግዱን ከእሁድ እስከ እሁድ የሚዘልቅ በማለዳ ተከፍቶ ምሽት የማይቋረጥ ነው። ቦታው የጫት ገረባ ቆሻሻ የሚጣልበት ነው። ንግድ ቦታዎቹ ደግሞ በፋይዚት እንጨት የተከፋፋሉ ዛኒጋባ ሱቆች ናቸው።
ነጋዴዎች ዕምቅ አቅማቸውን ለመደበቅና ግብር እንዳይጫንባቸው ሱቃቸው አዘምኖ ላለመሥራት የለገሙበት ነው። በመዲናዋ ጫት ከሚቅመው ሰው ብዛት አንፃር ትልቅ ዕምቅ አቅም ያለበት ሥፍራ ነው። ሱቁን ያላዘመኑት ግብር ለመሰወር በሚያደርጉት ጥረት መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ስለቦታው አንድ ሚዲያ ሲዘግብ አይቼ ሰምቼ አላቅም። ግን በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ተደብቆ ከመደበኛ ኢኮኖሚ ግን ልቆ የሚገኝ ቦታ ነው። የግብይቱ ሱቆች የተዝረከረኩና የጎዳና ተዳዳሪ ማደሪያ የሚመስሉ ናቸው። ይህን ቦታ ሥርዓት ለማስያዝ ጥረት ማድረግ የሚደገፍ ነው።
ገበያ ከሚባሉበት መካከል ደግሞ አመዴ ገበያ፣ አዳራሽ ገበያ፣ ጣና ገበያ ዋነኞቹ ናቸው። ከአመዴ ገበያ ወረድ ስንል በጀርባው ሳጥን ተራ (የሬሳ ሳጥን የሚሸጥበት) በነገራችን ላይ ራጉኤል አካባቢ እስከ ፖሊስ ጣቢያው የሚገኙ ሱቆች ሳጥን ተራ ይባሉ ነበር። የልብስ ሳጥን እየተሠራ ይሸጥባቸው ነበር። እንደ ወንበር የሚያገለግለው ሳጥን ማለት ነው። ቀስ በቀስ ሳጥኑን አራግፈው ሳጥን ተራ የሚለው ስማቸውን ታቅፈው ልብስ መሸጫ ሆኑ።
ከአመዴ ገበያ በጣም የዘመነ የገበያ ሥፍራ ነው። በንጉሡ ዘመን የተሠራው ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ በዘመናችን የተገነቡት የመርካቶ ሕንፃዎች በቁመት ቢበልጡት እንጂ በአገልግሎትና በጥራት ጐኑ አይደርሱም ብቻ የጎኑ ርዝመት ብዙዎቹን የመርካቶ የግብይት ሕንፃዎች ይበልጣቸዋል። ብዙ ተሽከርካሪና የትራፊክ መጨናቅ ባልነበረበት ዘመን ከመሠረቱ ሥር ሠፊ ፓርኪንግ የተሠራበትና ተሽከርካሪዎች የሚቆሙበት ሥፍራ ነው።
ከፎቁ ላይ ያሉ የገበያ ሥፍራዎች ኮሪደር መወጣጫው ደረጃ ሆነ እንጂ መኪኖች ጎን ማሳለፍ የሚችል ሠፊ ሥፍራ አለው። ከአመዴ ወረድ ብሎ ወንበር ተራ የቤትና ዕቃዎች (ቁም ሳጥን፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር ሶፋ የመሳሰሉ ዕቃዎች እዛው ተሠርተው የሚሸጡበት) ፊት ለፊቱ ቧንቧ ተራ፣ ወረድ ብሎ በርሜል ተራ የብረት በርሜል፣ ጉርድ በርሜል ሳፋ፣ ትንሽና ትልቅ ምጣድ የሚሠራበት ጀሪካንና ፕላስቲክ በርሜል የሚሸጥበት ቦታ አለ።
ከበርሜል ተራ ፊት ለፊት ዝነኛው ሸራ ተራ አለ። ድሮ ሸራ ጫማ ይሸጥበት ስለነበረ በድሮው ስያሜ የዘለቀ ነው። ዘንድሮ ቆዳ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች ጃኬቶች እዚያው በሚገኙ በአነስተኛ ጎጆ ኢንዱስትሪዎች እየተሠሩ ከመርካቶ አልፎ ለክልል ነጋዴዎች የሚላኩበት ሥፍራ ነው። አካባቢው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በጠባብ ቤት የሚሠራ ነው። ብዙ ሰዎችን ሥራ በማስያዝ ቀዳሚ ነው። እናም ጫማ መሥሪያ ቦታዎች ሰዎች ከመርካቶ መሃል እስከ መሳለሚያ ያሉ አካባቢዎችን ጫማ ማምረቻ ስፍራ አድርገውታል።
ስለመርካቶ ሲነሳ ስለምናለሽ ተራ ማንሳት ግድ ነው። በምናለሽ ተራ የማይሸጥ የሸቀጥ ዓይነት የለም። ሰዎች የተባለሸ ዕቃ ለማስጠገን መጠጋገኛ ቁሳቁስ ቢያጡ ወደ ምናሽ ተራ ያመራሉ። ምናለሽ ተራ ቀድሞ ኮረቻ ተራ ይባል ነበር። በርግጥም ባሕላዊ ኮርቻ አሸብርቆ ደምቆ ይሸጥበት ነበር። አንዳንዶች ጭድ ተራ ይሉታል። በዘመኑ የጭቃ ቤቶች ስለነበሩ ቤት ለመሥራት ግብዓት የነበረው ጭድ ይሸጥበት ነበር። አሁን ብዙ አሮጌ ዕቃዎች መሸጫና መጠገኛ ነው።
መርካቶ ከአብነት በተለይም ከሞላ ማሩ ጀምሮ አሜሪካ ግቢ በጎን ደግሞ ትልቅ ስፋት የያዘ ከአፍሪካ ቀዳሚ ዝነኛ የገበያ ቦታ ነው። በዚህ ቦታ ውስጥ የማይዘነጉት በጉርብትና የሚኖሩት የአንዋር መስጊድ እና የራጉኤል ቤተክርስቲያን ይገኛሉ። የመርካቶ ግብይት በብዛት ኢመደበኛ ኢኮኖሚ አካል ቢሆንም በአግባቡ የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው ።
መገበር ሕግን ማክበርና ማስከበር ነው። ነጋዴ ተረጋግቶ የሚነግደው ሰላምና ፀጥታው ሲጠበቅ ነው። እናም የሀገርን ልማት ለማሳለጥ ሰላምና ፀጥታን ለመጠበቅ ወደ ዕድገት ማማ ለመውጣት መገበር የዜግነት ብሔራዊ ግዴታ መወጣት ነው። ሀገሮች ወደ ብልፅግና ያመሩት ግብር ያለ ማጭበርበር እየገበሩ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም