ዜና ትንታኔ
ሥፍራው የተለየ ስሜት የሚፈጥር ነው። የገጠሩንም የከተማውንም ድባብ ቁልጭ አድርጎ ያስቃኛል። ይህ ሲባል በርቀቱ እንዳይመስልዎት። በሚፈጥረው መልካም ገጽታ ነው። መግቢያው ፒስታ ቢሆንም ግቡብኝ፤ ተራመዱብኝ የሚል ነው። ግራና ቀኙን የቃኘ ሰው በአንድ መንደር ውስጥ የገጠርንም የከተማንም ገጽታ እያየ የሚያዝናናው ነው።
የምድሪቱ ልምላሜ ከነፋሻማው አየር ጋር ተዳምሮ ውስጥን እያረሰረሰ ወደ መንደሩ እንድንገባ ያስገድደናል። በሌላ በኩል ሰብላቸው የደረሰ አርሶአደሮችን እያሳየ ጊዜው ሰብል የሚሰበሰብበት ወቅት እንደሆነ ይነግረናል። አለፍ ብለን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ደግሞ ሳናስበው በመደዳ የተደረደሩ ሱቆችን በስፋት እንድናይ ፤ ትርምሱን እንድንቃኝ ያደርገናል።
ከገጠርኛው ስሜታችን ወጥተን ሌላኛውን ዓለም እንድንቀላቀለው ይፈቅድልናል። ይህም የከተማው ድባብ ሲሆን፤ በርከት ባሉ ታፔላዎች አጅቦ ከተማ ላይ ነው ያሉት ይለናል። በውብ ቀለሞች ተሞሽረው በሚታዩ ሼዶች ብዛት መንደሩ ውስጥ ሲንጎማለሉ ደግሞ በመንደሩ ውስጥ ምን ምን አገልግሎቶች እንደሚሰጡ እንዲረዱ ያግዞታል ።
ሥፍራው ገላን ጉራ የጋራ መኖሪያ መንደር ይባላል። መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቷቸው ከገነባቸው መንደሮች አንዱ ነው። እኛ በሥፍራው ስንደርስ ዝግ ቢሆኑም በርከት ያሉ የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት ተሠርተውለታል። የዳቦ፤ የእንጀራ መጋገሪያ ሸዶች፤ የምገባ ማዕከላት ለመንደሩ ነዋሪዎች የተበረከቱ ልዩ ስጦታዎች መሆናቸውን የምንመሰክረው ሀቅ ነው። ወጣቱም ሆነ ልጆች አካባቢው ላይ የአዲስነት ስሜት እንዳይሰማቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎችና መዝናኛዎች መመቻቸታቸውም እንዲሁ ይበል ያሰኛል።
ይህ ልዩ መንደር ካዛንችሶችን እንዳሉ ያሰፈረ፤ እንደ ፒያሳ፣ ሽሮሜዳና መገናኛ የመሳሰሉ ቦታዎች የተነሱ ነዋሪዎችን ቀላቅሎ መልካም ጎርብትናን የፈጠረ ነው። ጊዜው ገና ሁለት ወራትን ያስቆጠሩበት ቢሆንም ያላቸው አኗኗርና አሰፋፈር ትናንትን እያሰቡ ዛሬን የሚኖሩበትም ነው። ቡና ጠጡዋቸው ሰፍቶ፤ ማህበራዊ መስተጋብራቸው ተጠንክሮ አንቺ ትብስ አንተ ትብስ ተባብለው እየኖሩም እንደሆነ ምስክርነታቸውን የሰጡን ነዋሪዎች አሉ።
ወይዘሮ በቀለች ኮርያ ይህንን እውነት የሚያረጋግጡልን አዛውንት ናቸው። መጀመሪያ ተወልደው ከአደጉበት ሥፍራ ሲነሱ ስቅስቅ ብለው አልቅሰዋል። መንግሥት ምን ሊያደርገን ነው ብለዋል። ፍራታቸው ወደር አልነበረውምም። በተለይም ቤታቸው የፈረሰ ቀን ያለቀሱትን መቼውንም አይረሱትም። ጎረቤቶቻቸው መለየቱ ደግሞ ሌላው ራስ ምታታቸው ነበር። ግን ወደ ገላን ጉራ መንደር ሲገቡ ነገሩ የተለየ ሆኖ አግኝተውታል። ጎረቤቶቻቸው ከእርሳቸው አልራቁም፤ ቤታቸው ደግሞ የጠበቁት ሳይሆን ያልጠበቁት ነው።
ጭቃና ሊወድቅ የተቃረበ ቤት ፈርሶባቸው ያገኙት ግን ቅንጡ ኮንደሚኒም ነው። በዚህም በወቅቱ አዲሱን ቤት ለመረከብ አቅማምተው እንደነበር አይረሱትም። ‹‹‹መልሺ የምባል መስሎኝ ነበር›› ሲሉ ጊዜውንም ወደኋላ መለስ ብለው በፈገግታ ይናገራሉም፡ ፡ይህ ልማት ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ እንደሆነ ይገልጻሉ። የቀደመውን መናፈቅ የፈለገ ካልሆነ በስተቀር ልማቱን አለመቀበል የዋህነትም፤ ሞኝነትም እንደሆነ ይናገራሉ።
ይቀጥሉናም ሰው ከተለያየ ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ በዚህ መንደር ውስጥ ሊሰፍር የሚሰማው ስሜት ይኖራል። አንዳንዱ ደስ ሲለው አንዳንዱ ይከፋዋል። ነገር ግን ይህ ልማት ነውና ሁሉንም በእኩል አስተናግደኝ ማለት አይቻልም። ሥፍራው በአንድ ጊዜ ሙሉ ይሁንልንም ሊባል አይገባም። ምክንያቱም ሥራዎች የሚከናወኑት ደረጃ በደረጃ ነው። ስለሆነም ብዙ ችግሮች መጀመሪያ አካባቢ ሊገጥሙት ግድ ነውና ለጊዜው እንታገስ ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ጤና ጣቢያ በዚህ አቅራቢያ እንጂ በመንደሩ ውስጥ የለም፤ ባንክ ቤትም እንዲሁ ገና አልተከፈተም። ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎችም የመንደሩ ነዋሪዎች ይኖሯቸዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጠን አምናለሁ የሚሉት ወይዘሮ በቀለች፤ ነዋሪዎች በማማረር የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ አምነው ዛሬ የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ ማመስገን ይገባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ። አቅም በፈቀደ እኛ የምንሠራው ከሆነ በመደጋገፍ መንደራችንን ወደ ተሻለ መንደርነት መቀየር ይኖርብናልም ይላሉ። ከዚያ ያለፈውን ደግሞ ለመንግሽት እያሳሰቡ መቀጠል ነው የሚያዋጣውም በማለትም አስተያየታቸውን ይለግሳሉ።
መምህር ቢኒያም ደምሴ በገላን ጉራ የነዋሪዎች መንደር ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው ያገኘነው። እንደ ወይዘሮ በቀለች ሁሉ ስለ መንደሩ የራሱ አስተያየት አለው። እርሱ እንደሚለው፤ ይህ መንደር ቃል ወደ ተግባር የተቀየረበት ነው። ኢትዮጵያውያን በጥሩ አመራሮች ከተያዙ የተሻለ መንደር ብቻ ሳይሆን የተሻለችውን ሀገር መገንባት እንደሚችሉ የታየበት ነው። ምክንያቱም ትምህርት ቤቱን ብንወስድ እቅዱ የዘጠና ቀን ቢሆንም በስልሳ ቀን እቅድ ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል። ሥራዎቹም የሚያስደምም ጥራት ያላቸው ናቸው።
የልጆች መተኛ ይሉት የልጆች መጫወቻ ፤ መጸዳጃ ቤቶችና መመገቢያ ክፍሎች እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብተው አገልግሎት መስጠታቸው ደግሞ የነዋሪዎችን ምቾት ከመጠበቅ አኳያ የማይተካ ሚና አለው። እንደ ሀገር ሳይቀር ብዙዎች ጋር የታየ አይደለም። ትንሽ ሜዳ እንዳለ ሁሉ ሰፊ ስቴዲየም ተገንብቶ ጥቅም ላይ የዋለበት መንደር ይህ ይመስለኛልም ይላል። ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር መመስገን ያለባቸው አካላት መኖራቸውን ይጠቁማል።
መምህር ቢኒያም ከምስጋናው ባሻገር ቢስተካከሉ፣ ቢታሰብባቸው ያላቸው መሠረታዊ ነገሮችም አሉ። አንደኛው የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ ነው። በተለያየ መልኩ በነበሩበት አካባቢ ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች አሁን ላይ ዝም ብለው ተቀምጠዋል። ስለሆነም እንደ መንግሥት ተደራጅተው የሚሠሩበት ሁኔታ ቢመቻች ይላል። ሌላኛው ደግሞ የመንገድ መብራቶች ሲሆኑ፤ ከመንደሩ ወጥተው የሚሠሩ ሰዎች ሲመለሱም ሆነ ወደ ሥራ ቦታቸው ሲሄዱ እየፈሩ እንደሆነ ይጠቁማል። ጤና ተቋማት አለመኖራቸው ብዙ ችግሮች እንደዲፈጥሩም እያደረገ እንደሆነ አሳስቦታል።
ሌላው ቢታሰብበት ይገባል ያሉት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ነው፤ አካል ጉዳተኞች ምድር ላይ የሆነ ቤት ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን ኮንደሚኒሙ ሲገነባ አንድ ደረጃ እንዲወጡ ይገደዳሉ። በመሆኑም ለመውጣትና ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ነገር ቢመቻችላቸው መልካም እንደሆነ አስረድቷል። ባንክ ጉዳይም መሠረታዊ መሆኑን በአስተያታቸው አመላክተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም