የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሟቋቋምና በመምራት ብዙ ዓመታትን አሳልፈዋል። በበሳል ፖለቲካዊ ትንታኔያቸው የሚታወቁም ናቸውⵆ አሁን ላይ የሚመሩት ወይም አባል የሆኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ባይኖራቸውም በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግን የነቃ ተሳትፎን እያደረጉ ይገኛሉ። አቶ ልደቱ አያሌው።
እኛም በዕለተ ረቡዕ አዲስ ዘመን ጋዜጣችን በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሁሉም ህብረተሰብ የልብ ትርታ በሆነው ህገ መንግስት ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታን አድርገናል። ይከታተሉት ዘንድ ግብዣችን ነው፦
አዲስ ዘመን ፡- ሉአላዊነትን በተመለከተ የብሔር ብሔረሰቦች እንጂ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት የለም፤ ይህንን ህገ መንግስቱ የሰጠው የተሳሳተ ድንጋጌ ነው ይላሉና ቢያብራሩት፤
አቶ ልደቱ፡- ይህንን እኮ ህገ መንግስቱን አንብቦ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፤ ይህንን መገንዘብም ከባድ አይደለም። ሉአላዊነት ለክልሎች ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሉአላዊነት አላት አይልም ፤በዚህም የአገሪቱ ወታደራዊ አቋምና የአገሪቱ ዳር ድንበር የሚወሰነው በክልሎች ነው። ሉአላዊነት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነው ኢትዮጵያ የምትባል አገርም አይደለም የዜጎችም አይደለም ይህ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጠ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁኔታ አስከትሏል የሚሉትን ችግርስ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ልደቱ፡- ያስከተለው ብዙ ችግር አለ፤ ምክንያቱም በየትኛውም ዓለም የአገር ሉአላዊነት መገለጫ የሚሆኑ ዜጎች ናቸው፤ አሁን ግን ቡድኖች ሆነዋል። እነዚህ ቡድኖች ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያን ህዝብ ሊወክሉ አይችሉም። በአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማንነቴ ይገለጻል እወከላለሁ ብሎ የሚያምን ግለሰብ ካልሆነ በቀር አንድ ዜጋ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ ሉአላዊነት እንዲሁም የአገር ባለቤትነት መብት የለውም።
አሁን በየክልሉ ይህ የእናንተ ክልል አይደለም ውጡ እየተባለ ሰዎች ሲባረሩ የምናየው እንዲሁም በየአካባቢው በሁለት በሶስት ክልሎች በወሰን ጉዳይ ችግር የሚፈጠረው ህዝብ የሚፈናቀለው ሰዎች ከአንድ አካባቢ ወደሌላ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሰርተው መኖርና ኢኮኖሚውን ማሳደግ የማይችሉበት ሁኔታ የተፈጠረው ህገ መንግስቱ ሉአላዊነት ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለሚባሉ ቡድኖች በመሰጠቱ ነው።
መሬቱ ባለቤት አለው፤ ይህ ደግሞ የቡድን ባለቤትነት ነው፤ ከዚህ ውጪ ግን ወጥቶ ሌላው ሰው በነጻነትና በእኩልነት እንዲኖር አይፈቀድለትም። እንደውም ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እንዲኖር ነው እየተደረገ ያለው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ደግሞ ሁለተኛ ሶስተኛ ዜጋ የሚባል ሊኖር አይገባም፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት እኮ በሌላ ክልል ውስጥ ሄደው የሚኖሩ ሰዎች የመጀመሪያ ዜጋ አይደሉም ማለት ነው፡፡ እናም ይህ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተገፏል የሚሉት የአገርና የህዝብ ሉአላዊነት ይመለስ ዘንድስ የሚያቀርቡት አማራጭ ሃሳብ ምንድን ነው?
አቶ ልደቱ፡- መልሱ ህገ መንግስቱን ማሻሻል የሚለው ነው፡፡ የምናሻሽለውም ለብሔር ብሔረሰቦች ብሎ በቡድን የሰጠውን መብት ተጠብቆ ቢቀጥል ችግር የለውም ፤ በቋንቋቸው መማርና መዳኘታቸው እንዲሁም ማንኛውም ሰው አካባቢውን የማስተዳደርና በፌዴራል መንግስት የመወከል መብቱ ተጠብቆ መቀጠል ይችላል። ምንም ችግር የለውም፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባውንና በህዝቡ አብሮና ተሳስቦ መኖር ላይ ችግር የፈጠሩ አንቀጾች መሻሻል አለባቸው፡፡
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ባለቤት ሁሉም ዜጋ መሆኑ መታወቅ አለበት፤ የአገሪቱ ባለቤቶች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይሆኑ መላው ዜጋ መሆንም እንደዛው፡፡ ይህንን ካደረግን ነው ችግሩን ልንፈታው የምንችለው። አሁን ባለው መንግስት ባለቤቶች ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው እነርሱ ስለሆኑም ከአገሪቱ በፈለጉት ጊዜ የመውጣት የመገንጠል መብት አላቸው፡፡ ይህም ስህተት ነው። ፌዴራሊዝም ጥቅም ላይ የሚውለው አንድ አገር ሲገነባ በውስጡ ያለውን ችግር ለመፍታት እንጂ አገሩ ባስፈለገ ጊዜ እንዲበተን አይደለም፤ እርሱ አማራጭም ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡
ይህ ህገ መንግስት ግን ባለቤቶቹ ብሔር ብሔረሰቦች አድርጎ በማቅረቡ እነሱ ደግሞ ልክ አዲስ አገርን እንደመፍጠር አድርገው ስለተስማሙ ችግሮች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ እያሉ ነው ፤ በዚህ ምክንያት ህገ መንግስቱ መለወጥ አለበት ፤ ከዚህም በላይ ሰነዱ ያለፈውን የአገሪቱን ህልውና እውቅና የሚነሳ መሆን አልነበረበትም፡፡
እዚህ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን ብንመለከት ከመሬት ፖሊሲ ጋር፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀርና መብት ጋር የተያያዙት ሁሉ የአገር አንድነትን ሊያስጠብቁ በሚችሉ የህብረተሰቡን መስተጋብርና አብሮ መኖር ሊያጠናክር በሚችል መልኩ ህገ መንግስቱና የፌዴራል አወቃቀሩ መሻሻል አለበት የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ ፤ ይህ መፍትሔ ደግሞ ውስብስብና አስቸጋሪ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግስቱ ለአገር አንድነትና ለህዝቦች መቀራረብ ዋስትና ያልሰጠ ነው እያሉ ያሉት?
አቶ ልደቱ፡- እኔ አይደለሁም ያልኩት ህገ መንግስቱ ነው ያለው፤ ህገ መንግስቱ የሚለውን ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ፈጥሬ የማወራው ነገር የለም፡፡ ህገ መንግስቱ ለአገሪቱ አንድ መሆን ምንም እውቅና አልሰጠም፡፡ ማንም ብሔር ብሔረሰብ በፈለገ ጊዜ ከኢትዮዸጵያ መገንጠል ይችላል፡፡ አሁንም ስሜቶቹ እየታዩ ነው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ የአገር አንድነትን አላስጠበቀም የምለው እኔ ሳልሆን እራሱ ህገ መንግስት በተግባር የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህግ መንግስቱ በዚህ ደረጃ መሻሻል ካለበት የክልሎች ይሁንታ ያስፈልጋል የሚለውን እንዴት ያዩታል? ከእነርሱ አንዱ ይሁንታ ከሌለው ማሻሻል አይቻልምን? በምንስ ሁኔታ ነው ይህ ሊስተካከል የሚችለው?
አቶ ልደቱ፡- መጀመሪያ ህገ መንግስቱን የትኛው ክፍሉ ነው ሊሻሻል የሚገባው ብሎ በነጥብ በነጥብ መያዝ ያስፈልጋል? በምን ይተካ የሚለው ነገርም ከመወሰኑ በፊት ሊታይ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግስቱን ራሱን የሚሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፡- ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
አቶ ልደቱ ፡- ህገ መንግስቱ ሲቀረጽ እኮ እንዳይሻሻል ተደርጎ ነው የተቀረጸው፤ ምን ማለት ነው የሁሉም ክልሎች ይሁንታ ካልተገኘ አይሻሻልም ፤ ይህ ደግሞ በየትም አገር የሌለ የህገ መንግስት ድንጋጌ ነው፡፡ በጣም ግትር እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ሰነድነቱ ህዝቦች ሲፈልጉት የሚያሻሽሉት ተደርጎ አይደለም የተቀረጸው፡፡
መጀመሪያ መሻሻል ያለበት ህገ መንግስቱ በሌሎች አገሮች እንዳሉት ሁሉ የሚሻሻል ማድረግ ነው ከዛ በኋላ ህገ መንግስት በሚፈቅደው መሰረት በህጋዊ አግባብ ህዝቦች እየተነጋገሩ ተቋማት እየተመካከሩበት በሂደት ሙሉ በሙሉ ማሻሻል ይቻላል፡፡ አሁን በለውጡ ሂደት መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል የሚያደርግ አንቀጽ መጨመር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ይሻሻል ታዲያ?
አቶ ልደቱ፡- ይህንን ህገ መንግስት አርቅቆ ያጸደቀው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው። ስለዚህ መንግስት ህገ መንግስቱ በማይሻሻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ መጽደቁን፣ ህዝቦችን ወደ ቅራኔ እየወሰደና አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት እያስገባ መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም ከአረቃቀቁ ጀምሮ ስህተት እንደነበር አምኖ የበለጠ ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባና የሚያለያይ መሆኑን አውቆ እራሱ ያጸደቀውን ህገ መንግስት ራሱ እንዲሻሻል ማድረግ አለበት። ፍላጎት እስካሳየና አገራዊ ችግር መሆኑን እስከተቀበለ ድረስ ለማሻሻል እድል ያለው አሁንም ገዢው ፓርቲ ነው።ወደፊት ሌላ ምርጫ ተካሂዶ የሃይል አሰላለፉ ከተለወጠ በኋላና በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ፓርቲዎች ከተመረጡ በኋላ ይህንን ህገ መንግስት በህጋዊ መንገድ ይሻሻላል ማለት ዘበት ከመሆኑም በላይ እነዚህ ነገሮች ከሆኑ በኋላ ሊሻሻሉ የሚችሉት በጉልበት ብቻ ነው፤ ስለዚህ በጉልበት ከሚሻሻል እራሱ ያጸደቀው ህጋዊ መንገድ ቢያሻሽለው ቀላል ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከነዚህ ከተነሱ ሃሳቦች አንጻር ባለፉት 27 ዓመታት ማለትም ህገ መንግስቱ በስራ ላይ በቆየባቸው ጊዜያት አላገለገለንም ማለት እንችላለን?
አቶ ልደቱ፡- 27 ዓመታት በዚህ ህገ መንግስት ተመራን ግን ወደ አንድነት ወደ መቻቻል ወደ ፖለቲካዊ መረጋጋት አልሄድንም፡፡ ከዛ ይልቅ ወደ መከፋፈል መለያየት መገነጣጠል ነው እየሄድን ያለነው። ይህንን ደግሞ አሁን ያለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ህወሃት እገነጠላለሁ ይላል ደቡብ ላይ ወደ አስር የሚሆኑ ዞኖች የክልል ጥያቄ አቅርበዋል፤ አጠቃለይ ሁኔታው የሚያሳየው ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እየገባን እንዳለን ነው።ህገ መንግስቱ ከመረቀቁና ከመውጣቱ በፊት ከነበርንበት ችግር በበዙ እጥፍ የላቀ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምንም መፍትሔ አልሰጠንም፤ አልሰጠንም ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስቱና ፌዴራሊዝም አዳዲስ ችግሮችን እየፈጠረብን ነው የሚለውን አምኖ መቀበልና ማሻሻል የግድ
ነው፡፡
ይህ አገር ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሸጋገርና መቀጠል ካለበት ህገ መንግስትንና የፌዴራል ሥርዓቱን ማሻሻል የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በብሔር የተደራጀ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት አይችልም፤ በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣልና ይህንን ሃሳብ ቢያብራሩልኝ፤
አቶ ልደቱ፡- አንድ አገር እራሱን በብሔር ፖለቲካ ካደራጀ በኋላ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የሚታሰብ አይደለም። የብሔር ጥያቄ የያዘ የፖለቲካ ድርጅት ሄዶ ሄዶ እኩል ቢሆንም እንኳን ጥያቄውን አያቆምም ምክንያቱም መብለጥ ስለሚፈልግ፤ አሁን እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ይህ ነው። ህወሃት በልጦ የበላይ ሆኖ ባለበት ጊዜ ሁሉን ነገር ተቀብሎ ተቀምጦ ነበር፤ አሁን ግን የበታች ሲሆን ሁኔታውን መቀበል አልቻለም ይህንንም እያየን ነው፡፡ ስለዚህ በብሔር የተደራጀ አካል ሄዶ ሄዶ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ የሌለው ነው ነው የሚሆነው።
በዓለም ላይ ዩጎዝላቪያና ሶቭየት ህብረት ነበሩ በብሔር የተደራጁትና ህገ መንግስታቸው ላይ የመገንጠልን አቋም ያካተቱ፤ ሁለቱም በመፍረስ ነው የተጠናቀቁት፤ ስለዚህ የእኛ እጣ ፈንታም ከእነሱ የተለየ አይደለም የሚሆነው ፤ይኼን አሁን በሃሳብ ደረጃ የሚያነጋግር አይደለም በእነ ዩጎዝላቪያና ሶቭየት ህብረት ተፈትኖ የታየ ነው ፤ ከእነሱም ውጪ እኮ በእኛ አገር ላይ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡
የዛሬ አስር ዓመት አልያም አምስት ዓመት የነበርንበት የአንድነት ሁኔታና አሁን ያለንበት አንድ ነው? የበለጠ እየተለያየን ግጭት ውስጥ እየገባን ነው። በታሪካችን አይተን የማናውቀው ስደትና መፈናቀል ውስጥ ነን፡፡
ስለዚህ ዴሞክራሲያዊነትና የብሔር አደረጃጀት አብረው የሚሄዱ አይደሉም፡፡ የብሔር ወይም የቡድን መብት እንዲመለስ ጥያቄ ማቅረብ ችግር የለውም ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል፤ እራስንና አገርን በብሔር አደራጅቶ ፖለቲካ እየሰሩ ወደ አንድነትና ዴሞክራሲ መምጣት አይቻልም፡፡ ዴሞክራቲክ የሚባል የኤትኒክ ብሔርተኝነት የለም ኖሮም አያውቅም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን ህወሃትና አዴፓ በየግላቸው መግለጫዎችን በማውጣት ሲወነጃጀሉ ነበርና እርስዎ ይህ አካሄድ ምን ያመላክታል ብለው ያስባሉ?
አቶ ልደቱ፡- ከላይ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ትልቅ መረጃና ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ከተቋቋሙ ከ40 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ አብረውም መስራት ከጀመሩ እንደዛው፡፡ ሄደው ሄደው ግን ወደበለጠ አንድነትና መዋሃድ ሳይሆን ወደ መለያየትና መፈረካከስ አመሩ፡፡ በብሔር የተደራጀ ድርጅት ሄዶ ሄዶ እኩልነትን አንድነትና ዴሞክራሲን አያመጣም፤ መለያየትን ግጭትና መነጣጠልን እንጂ፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ አሁንም ቢሆን አገሪቱ ወደኋላ ልትመለስ የማትችልበት አዘቅት ውስጥ ነው የምትገባው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ምን መምሰል አለበት?
አቶ ልደቱ፡- ከዛሬ 2 ዓመት በፊት የነበረውና ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሆነው የህዝብ ትግል ምን ዓይነት ጥያቄዎች ናቸው ህዝቡስ ምን ይደረግልኝ ምን ይለወጥልኝ ነው ያለው የሚለውን በደንብ አድርጎ ለመመለስ መሞከር ነው መፍትሄው፡፡ አሁን የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው አካል እኮ ይህንን እረስቶታል፤ አንደኛ እኔ ብቻ ነኝ መፍትሔ የማመጣው ብሎ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮ እየሰራ ነው ያለው ይህ ስህተት ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ የሆነና አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ሃይል ማሰባሰብና አብሮ መስራት አለበት፡፡ የችግሩ ብቸኛ አካል የሆነው ኢህአዴግ ችግሩን ለመፍታትም ብቸኛ ሊሆን አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የ2012 ዓ.ም ምርጫ ላይ ያልዎት ሃሳብ ምን ይመስላል?
አቶ ልደቱ፡- አሁን የገዢው ፓርቲም አገሪቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ህዝቡም እንደ ህዝብ ለምርጫ ገና ዝግጁ አይደለንም፡፡ ከምርጫ በፊትም ሊሰሩ የሚገባቸው የቤት ስራዎችም አልተሰሩም። በዚህ ሁኔታ ወደ ምርጫ ብንገባ የአገሪቱን ችግር የሚፈታ ሳይሆን ወደባሰ ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡
ስለዚህ ከምርጫ በፊት ቅድም የተዘረዘሩት ነገሮች መሰራት መቻል አለባቸው፤ ድርድር መደረግ አለበት ፤ህዝቦችን ማወያየትና መሻሻል የሚገባቸው ህጎችና ተቋማትን መሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ስራ ሰርተን በቂ የሆነ ብሔራዊ መግባባት ፈጥረን ወደ ምርጫ ከገባን እንዲሁም በእርግጠኝነት ምርጫው ነጻና ፍትሀዊ እንደሚሆን ካወቅን በኋላ እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ምርጫ መሄድና በዚህ ሁኔታ ማካሄድ ለእኔ እብደት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በፖለቲካው እንዴት ይታያል?
አቶ ልደቱ፡- በህገ መንግስቱ መሰረት እነዚህ የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡ አካላት መብታቸው ነው። ነገር ግን የት ነው የሚያቆመው ነው የሚለው ነው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው፤ ስለዚህ ይህ እየተበረታታ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርብ ከሆነ እንደ አገር ሰባ እና ከዚያ በላይ ክልሎች ሊኖሩን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የክልል መሆንን መብት ካገኙም በኋላ ጥያቄያቸው ይቆማል ማለት አይደለም የመገንጠል መብት፡፡
ህገ መንግስት የሚረቀቀውና የሚጸድቀው አገርን ለማፍረስ ሳይሆን የአገርን አንድነት ለማጽናትና ለማረጋጋት እንዲሁም ህዝብን አንድ አድርጎ ለመቀጠል ነው፡፡ የእኛ አገር ህገ መንግስት የረቀቀውና የጸደቀው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ አልሰጥም ብለው ነበርና ምክንያቱ ምንድን ነበር?
አቶ ልደቱ፡- እንግዲህ እንደምታውቂው ላለፉት አንድ ዓመት ሁሉም ተናጋሪ ተንታኝ ነበር ፤ የጎራ መደበላለቅም ታይቷል፤ ሰከን ብሎ የአገሪቱን የሃይል አሰላለፍ በደንብ ተረድቶ መረጃ የሚሰጥ ሰው አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ተናጋሪ እንጂ አድማጭ ጠፍቶ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት መናገሩ ደግሞ ምንም ፋይዳ አልነበረውም፡፡
አሁን ላይ ግን ትንሽ ነገሮች አቅጣጫቸውን እየሳቱ መሄዳቸውን ህብረተሰቡ እየተረዳ የተለያየ አመለካከት ለማዳመጥ እየተዘጋጀ ነው ከዚህ አንጻር በዝምታ ሁልጊዜ ማሳለፉ ለአገርም ለህዝብም አይጠቅምም በማለት ነው መናገር የጀመርኩት፡፡
አዲስ ዘመን ፡- እንደ እርስዎ በፖለቲካው ረጅም ዓመት ያሳለፉና ልምድ ያላቸው ሰዎች ከዚህስ በኋላ ላለው የአገሪቱ ሁኔታ ሚናቸው ምንድን ነው መምሰል ያለበት?
አቶ ልደቱ፡- ገንቢ በሆነ መልኩ ተሳትፎን አጠናክሮ መቀጠል ነው፤ አገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ አንጻርም ፖለቲከኞችም የምናቀርበው ጥያቄ የስልጣን መሆን የለበትም፤ አንዳችን በሌላችን ላይ ነጥብ ለማስቆጠር የበላይ ለመሆን መሆን የለበትም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሸናፊና ተሸናፊ ሆነን የምንፈታው የኢትዮጵያ ችግር የለም። ስለዚህ ሁላችንም ተባብረን የጋራ አሸናፊነትን ልናመጣ ወደምንችልበት አቅጣጫ ካልገፋን አሁን ባለው የመሸናነፍ ስሜት የኢትዮጵያን ችግር መፍታት በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የበለጠ እናወሳስበዋለን፡፡
ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ሰዎች ቅራኔን በማባባስና ለራስና ለቡድን የፖለቲካ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ሳይሆን ለአገሪቱና ለህዝቡ ችግር ቅድሚያ በመስጠት ገንቢ የሆነ የፖለቲካ ሚና በመጫወት ይህ ሽግግር ውጤታማ እንዲሆን ጥረት ማድረግ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡
የፖለተካ ግብግቡ በኋላ በምርጫ ወቅት የምንደርስበት ሆኖ አሁን ግን አገርን የማዳን ስራው ላይ ስለሆንን ለዛ የሚመጥን ትግልና ስራን መስራት ደግሞ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከዚህ አንጻር እርስዎም ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ያለብዎን ቅራኔ ፈትተው አገርን በማዳን ስራው ላይ ለመሳተፍ ምን ያህል ዝግጁ ኖት?
አቶ ልደቱ፡- እኔ በፖለቲካ ከሰዎች ጋር ተጣልቼ አላውቅም፡፡ ሌሎች ናቸው የተጣሉኝ ስለዚህ ችግሩ ያለውም በሌሎቹ እጅ ነው።እኔ ከማንም ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪም ሆኜ በቆየሁበት ጊዜ እንኳን ከሌሎች መሰሎቼ ጋር ይቅርና ከሚያስሩኝና ከሚገርፉኝ የገዢው ፖርቲ አባላት ጋር አብሬ ለመስራት ዝግጁ መሆኔን ነው እገልጽ የነበረው። እኔ ከማንም ጋር አብሮ ለመስራት ምንም ቅድመ ሁኔታ የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ምላሽ አመሰግናለሁ።
አቶ ልደቱ ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
እፀገነት አክሊሉ