በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና መምህርት ናት። ቀደም ሲል በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋ የሴት ዲን በመሆን አገልግላለች። አሁን ደግሞ መጪው ትውልድ ራሱን ያወቀ፤ የበቃና ሥራ መፍጠር የሚችል ሆኖ ለሀገሩ ይጠቅም ዘንድ በሚበጀው ተግባር ላይ ናት። ከማስተማሩ ጎን ለጎን ‹‹ነገን›› በሚል ስያሜ በትምህርትና ሙያ ማበልጸግ ዙሪያ የማሰልጠንና የማማከር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አቋቁማ በመሥራት ላይ ትገኛለች – ወይዘሮ ምህረት አብርሃ፡፡
ምህረት አብርሃ ሰዎችን በሥነልቦና ማነጽ ዋነኛ ሥራዋ ነው። ከማስተማሩ ባሻገር በአማካሪነት ታገለግላለች። ሁሌም አዳዲስ ነገሮች ይመቿታል። ዕቅዱ እንደ ሀገር ሳይታሰብና በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሳይካተት በፊት የሙያ ማብቃት ወይም ማበልጸግ (Career development) ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዳለች። በዚህ ዘርፍ በመሰማራትም ከድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የተለያዩ ተቋማት ጋር መስራት የጀመረች ሴት ነች።
ሀጫ በረዶ
ትውልድና እድገቷ አዳማ ልዩ ስሙ “ገንደሀራ ነው” ላይ ነው። ስለእሷ ይህን እውነት ለመቀበል የሚቸገሩ ግን በርካቶች ናቸው። ለምን ቢባል የእርሷ ጥርስ እንደ አዳማ ልጆች አይደለም። የተለየ ቀለም አይለይም። ይልቁንም የጥርሶቿ ንጣት ‹‹ሀጫ በረዶ›› ይሉት አይነት ሆኖ ይገለጻል። ይህን ሀቅ መቀበል የተሳናቸው አንዳንዶች ታዲያ ‹‹ ውሃ ከአዲስ አበባ እየተጫነልሽ ነው እንዴ ያደግሽው›› ይሏታል። ግን እርሷ ለጥያቄያቸው አንድም ቀን ምላሽ ሰጥታቸው አታውቅም። የአዳማ ልጆች መለያ የሆነው ጥርስ በምን ምክንያት ቀለሙን እንደሚቀይር አይገባትም። እናም የሁልጊዜ ምላሽዋ ፈገግታ ብቻ ሆኖ ያልፋል።
ምህረት የቤት ልጅ ናት። አባትና እናቷ የተማሩና ሰራተኞች በመሆናቸው ትምህርቷ ላይ ብቻ ትኩረት እንድታደርግ ይሻሉ። ከትምህርት ቤት ወጥታ እንድትጫወት ፈቅደውላት አያውቁም። ይህ አይነቱ ጫና በተለይ የእናቷ ነበር። ውጪ ከዋለች ትበላሽብኛለች በሚል ሥጋት ከዓይናቸው አያርቋትም። አባቷም በአብዛኛው በመስክ ሥራ ያሳልፋሉና ውሎዋን አይቆጣጠሩም። እንዲያም ሆኖ የእናቷ ደጋፊ ናቸው። አንዳንዴ ምህረት ጨዋታ ባማራት ጊዜ ጓደኞቿን ቤት ጠርታ ትጫወታለች። እሱም ቢሆን ከድብብቆሽ አይዘልም።
ምህረት የልጅነት ትዝታ የሆነውን ‹‹አበባየሆሽን›› እንደ እኩዮቿ አልተጫወተችም። ደጁንና የሰፈር ልጆችን ለማየት እንኳን ሱቅ በአጋጣሚ መላክ ነበረባት። ዛሬ ላይ ሆና ስታስበው በልጅነቷ ብዙ ነገሮች እንዳለፏት ይሰማታል። አጋጣሚው በአዕምሮዋ ጫና እንዳይፈጥርባት ግን በቤት ውስጥ የተለያዩ ተግባራትን ትፈጽማለች። አንዱና ልዩ ስጦታዋ ስዕልን መስራት ነበር። ስዕል ስትስል ፀጥታን አብዝታ ትፈልጋለች። አጋጣሚው ከማንም አያገናኛትምና ደስ ይላታል።
ምህረት ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ ነች። ከታላቋ ጋር ሰፊ የእድሜ ልዩነት አላቸው። በወቅቱ የሚሰጣቸው የቤት ውስጥ ሥራ ከእሷ ይልቅ ጫናው በእህቷ ይበረታል። የእሷ ድርሻ በጣም ቀላልና ለዕድሜዋ የሚመጥን ነው። ቤት ማጽዳት፤ ማስተካከልና አልጋ ማንጠፍ። ይህንን ከአጠናቀቀች በኋላ እንደፈለጋት ብትሆን ከልካይ የላትም። እንደልቧ ያሰበቻቸውን ሁሉ ትፈጽማለች፡፡
ምህረትን ከሚስቧት ስዕሎች መካከል ቅድሚያውን ስፍራ የሚዘው ተፈጥሮ ነው። እናም ዘወትር ተፈጥሮን እያየች ዘና ባትልም በምትስላቸው ስዕሎቿ ራሷን ታዝናናለች።
ሰፋፊ ባለጥለታማ ቀሚሶችን በመሳልም ባህላዊ የአለባበስ ስሜቷን ትገልጻለች። ይህ ልምዷ ደግሞ አሁንም ድረስ የዘለቀ ነው። በዚህ ችሎታዋ ዛሬን ዲዛይነር ሆና ቢሆን በብዙ መስክ የተሻለች ባለሙያ ትሆን እንደነበርም ታወሳለች።
ለምህረት ስዕል የስሜት መግለጫና ራስን ዘና ማድረጊያ እንጂ ቀጣይ ህልሟ አይደለም። በልጅነቷ መሆን ትመኝ የነበረው የሕግ ባለሙያ መሆን ነበር። በእቅዷ መሰረት ልታሳካው አልቻለችም እንጂ። ልጅነቷ ላይ የተሰጣት ልዩ ስጦታ ሰዎችን በሥነልቦና ማከም ነበርና ወደዚያ እንድታመራ ሆናለች። ይህም በአብዛኛው የሚገለጠው ሱቅ ተልካ በምትሰራው ተግባሯ ነበር። የያዘችውን ገንዘብ ለተቸገረ ሰጥታ በየጊዜው ትመለሳለች። ‹‹እንዲህ አታድርጊ›› የቤተሰቦቿ ተግሳጽ ነበር። ይሁን እንጂ የእርሷ ምላሽ አንድ ነው። ‹‹ሲያለቅሱ፤ የሚበሉት ሲያጡ ምን ላድርጋቸው›› የሚል። በዚህም አሁን ላይ ጥሪዋን አግኝታ እንድትሰራ እድል አግኝታለች። ብዙዎችን ተስፋ የምትሰጥ እንስት ሆናለች።
ከአዳማ ወደ አዳማ
በትምህርቱ ዓለም ምህረት ሁለት አይነት የመማር ማስተማር ሁኔታዎችን አልፋለች። አንደኛው የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ ያወቀችበት ሲሆን፤ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነጻነትንና የምርጫ ጉዳይን ተምራበታለች። መምህራን በተቻላቸው መጠን የሚያስተምሯቸው ቢሆንም ይህንን ካላደረጋችሁ ብለው አያስገድዷቸውምና በራሳቸው ወሳኝ እንዲሆኑም ያወቀችበት ነው።
ሌላው ምህረትን ያስተማራት ነገር በግል ትምህርት ቤቶች የነበረው የመማር ማስተማር ሥርዓት ነው። በዚህ ትምህርት ቤት መምህራን ክትትላቸው ጠንካራ ነው። ተማሪዎችም ቢሆኑ ውድድራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። በቋንቋ ልዩ አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው ይቀረጹበታል። በዚህ መማር የሚሻ ሁሉ አኗኗሩን ብቻ ሳይሆን የሚቀይረው የጥናት ሰዓቱንም ነው። ይህ ደግሞ ለእነ ምህረት አይነት መካከለኛ ተማሪ የተሻለ እድልን ይፈጥራል። ጉብዝናን ያመጣል። በዚህም ለምህረት ሁለቱም ትምህርት ቤቶች መምህሮቿ ሆነውላት አልፈዋል።
በመምህራኑ ስብዕና እና የማስተማር ብቃት የተሻለች ከሕይወት ክህሎቶቻቸው የተጋራች ሆና እንድትቀጥል እድል አግኝታለች። የነገ ተስፋዋንም አለምልማለች። ዛሬ ድረስም መርህ ያደረገቻቸው በርካታ ተሞክሮዎችን ቀስማለች። አሰራሮችን ወስዳም እየኖረችባቸው ትገኛለች።
ምህረት ትምህርቷን አሀዱ ብላ የጀመረችው አቢዮት ፍሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተባለ በሚጠራው የመንግሥት ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ቆይታለች። ስምንተኛ ክፍልን ‹‹ናፊያድ›› የተሰኘውን የግል ትምህርት ቤት እንድትቀላቀል ሆነች። ቤተሰቡ ያላት የትምህርት ብቃት ብዙም እንዳልሆነ ሲረዱ ነው ወደዚህ ትምህርት ቤት እንድትዛወር ያደረጓት። በትምህርት ቤቱ ለሁለት ዓመታት ከቆየች በኋላ በጣም ጎበዝ ተማሪ ሆነች። ቤተሰቦቿንም አስደሰተች፡፡
የምህረት ቤተሰቦች ይህንን ጊዜ ዳግም ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት መለሷት። አዳማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንም ተቀላቀለች ። በዚያም ቢሆን የምህረት ጉብዝና እንደቀጠለ ነበር። እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቷን ስትከታተልም ማንም የሚጥላት አይነት አልነበረችም። ሆኖም በቤት ውስጥ ያለው ጫና በመጠንከሩ የተነሳ ለትምህርቷ ብዙም ትኩረት እንዳትሰጥ ሆነች። በዚህም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቷ እንደጠበቀችው ሳይሆን ቀረ።
እቅዷ ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትና የሕግ ትምህርትን ማጥናት ነበር። ይህ ግን እቅድ ብቻ ሆኖ ነበር። ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባት ውጤት ብታመጣም የፈለገችውን የሕግ ትምህርት ለመቀላቀል አላስቻላትም። በሁኔታው በእጅጉ ተበሳጨች። ቁጭቷን ለመወጣትም ያላትን ምርጫ ተጠቀመች።
አዲስ ነገር መሞከር የምትወደው ምህረት በጊዜው ምርጫዋ ያደረገችውም የሥነልቦና ‹‹ሳይኮሎጂ›› ትምህርትን ነበር። ትምህርቱ ምን እንደሆነ አታውቅም፤ አዲስ ስለሆነ ብቻ ልትሞክረው መረጠችው። የትምህርት መስኩን ምንነት በአግባቡ እንኳን የተረዳችው እናቷ ጋር ስትደርስና ስለሁኔታው ስታብራራ ነው። እናቷ የ ተማሩ በመሆናቸው ምርጫዋ ትክክል እንዳልሆነ ነገሯት።
‹‹ትክክል አይደለሽም›› ግን የእርሳቸው ሃሳብ እንጂ የእርሷ አልነበረም። ምክንያቱም በጊዜው ለእርሷ አዲስ ነገር ነውና መሞከር ትፈልጋለች። የሕይወቷን መስመር በትምህርቱ ማቃናት ትሻለች። እናም ሞልተዋለችና ማንም ምንም ቢላት ልትቀበለው አልወደደችም። ያመነችበትን ላለመተውም ታተረች። በጊዜውም ‹‹ይሁን እሞክረዋለሁ፤ የተሻለ ውጤትም በማመጣት የማስበውን አደርጋለሁ›› ስትል ለራሷም ለእናቷም ቃል ገባች።
ቃሏን በተግባር ለመዋልም በቀጥታ ወደ ደረሳት አዳማ ዩኒቨርሲቲ ሄደች። በወቅቱ አዳማ ስለደረሳት ደስ አላላትም ነበር። ሆኖም ቁርጠኛ ከሆነች ነገሮችን እንደምታስተካክላቸው ታምናለችና መከፋቷን ለማንም ሳታሳይ ጊዜዋን በአግባቡ ተጠቀመች። ምንም እንኳን ለቤተሰቦቿ ቅርብ ብትሆንም እንደሌሎቹ ተማሪዎች በየጊዜው እናቴ ዘንድ ልሂድ አትልም። ጉዳይዋም ፣ ትኩረቷም ትምህርትና ትምህርት ብቻ ሆነ። በዚህም በየሴሚስተሩ የምታመጣው ውጤት ብዙዎችን ያስደምም ያዘ።
በማዕረግ መመረቅና አንገቷ ላይ ሜዳሊያውን ማጥለቅ እቅዷ ነበርና አሳካችው። በዚህም ቤተሰቦቿን አስደስታለች። የቀጣይ እድሏን በብዙ መልኩ አመቻችታለች። ለምህረት መማር የሚቆም ነገር አይደለምና ሁለተኛ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁን እየሰራችበት ባለው የሥነልቦና ትምህርት ተመርቃለች። ከዚያም ባሻገር ሁሌ በማንኛውም መንገድ ይምጣ ስልጠና የሚባል ነገር አታልፍም።
ስልጠናዎች ለእርሷ የሕይወትም፤ የእውቀትም መርሆዎች ናቸውና ትጠቀምባቸዋለች። ወደ መልካም ጎዳና የምትራመድባቸው የቀን አንቂዎቿም እንደሆኑ ታምናለችና መንገዷን ታስተካክልባቸዋለች። ለዚህም በአብነት የምትጠቅሰው ከኢትዮ- ጆብስ ጋር የሥራ ግንኙነት በፈጠረችበት ወቅት ያገኘችው የስልጠና እድል ነው። ስልጠናውን የወሰደችው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ሲሆን፤ ሙያን ማብቃት ወይም ማበልጸግ (Career development) ይባላል። ዛሬ ላይ ለተጨማሪ ሥራና የገቢ ምንጯ እድሎችን ያመቻቸላትም ነው።
ይህ የትምህርት መስክ በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ በሀገር ደረጃ እንቅስቃሴዎች የተጀመረበት ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ባለሙያዎች የግድ ናቸውና እንደ እርሷ አይነቶች በባትሪ እየተፈለጉ የሚሳተፉበትን እድል እያገኙ ነው።
የመጀመሪያዋ ሴት ዲን
እንደ ሀገር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመርጠው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲያስተምሩ ሲፈቀድ ምህረት ከእነዚህ መካከል አንዷ ነበረች። በእነርሱ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ባመጡበት ቦታ መቅረት አይቻልም። ሁሉም እጣ ፋንታቸው የወሰነላቸውን ዩኒቨርሲቲ ነው እንዲቀላቀሉ የሚደረጉት፡፡
ለዚህ ደግሞ ምድባቸውን የሚያውቁበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያስፈልጋቸዋል። ምህረትም ጋዜጣውን የተተዋወቀችው በዚህ አጋጣሚ እንደነበር ታስታውሳለች። አጋጣሚውን ተጠቅማም የተለያዩ መጣጥፎችን ማንበብ ጀምራ እንደነበር ትናገራለች።
የምህረት ምደባ ሁሉንም ቤተሰብ ያስጨነቀ ነበር። እርሷ ግን የሚሆነውን ሁሉ ለመቀበል ራሷን አዘጋጅታለች። አፋርም ይሁን ሱማሌ ሌላኛው ጠረፍ ቢደርሳት ምንም ግድ አልነበራትም። ዋናው ሀገሯን ማገልገሏ ብቻ ነው።
ሌላ ቦታ ከደረሰሽ አትሂጂ የሚለው የቤተሰቡ ጉትጎታ ግን ምድቧ ይፋ እስኪሆን ድረስ ቀጥሎ ነበር። የእርሷም አቋም እንዲሁ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ አሁን ፍርዱን ሊሰጣቸው ከእጃቸው ገብቷል። ሁሉም ተሰብስበው ለማየት ጓጉተዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ሚዛኑ ወደ ምህረት አዘንብሎ ነገሩን እንዲፈርድ ሆነ። ቤተሰቦቿ ልጃቸው ገና ከተመሰረተ ጥቂት ጊዜ የሆነውንና እነርሱ እንኳን በቅጡ የማያውቁትን ዩኒቨርሲቲ ልትቀላቀል በመሆኑ ፍራቻ ውስጥ ገብተዋል። እርሷ ግን ፊቷ በፈገግታ ያበራል።
በተደጋጋሚ ቁጭ ብለው በመወያየት እንድትቀርና በቅርብ ርቀት ላይ እንድትቀጠር ሊያሳምኗት ታገሏት። እርሷ ግን በአቋሟ ‹‹ወይ ፍንክች›› ሆነችባቸው። ከእነርሱ በተቃራኒው ቆማ ያሰበችውን ለማድረግ ‹‹ማቄን ጨርቄን›› ሳትል ጠቅልላ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለመጓዝ ተነሳች። ቤተሰቦቿ ቁርጥ መሆኑን ሲረዱም ከስፍራው ታደርሳት ዘንድ ታላቅ እህቷን አስከተሉላት።
እህቷ ለሳምንት ያህል የሚያስፈልጋት ሁሉ እስኪሟላ አለማመደቻት። ከዚያ የለመደች ሲመስላት ተሰናብታት ተመለሰች። ምህረትም ከጎኗ ማንም እንደሌለ ስትረዳ ራሷን በራሷ ለመምራት ዳዴ ማለት ጀመረች። ቆፍጣናና ቆራጥ ብትሆንም፤ አዳዲስ ነገሮች ቢስቧትም ወላይታን ግን ቶሎ መላመድ አልሆነላትም። በጊዜው ብዙ ነገሮች ከብደዋት ነበር።
የሥራ ዓለሙን ስትቀላቀል ገና የ23 ዓመት ወጣት በመሆኗ በርካታ ፈተናዎች ገጥሟታል። ቅጥነቷና አጭርነቷ ደግሞ ይበልጡን ልጅነቷን የሚያሳብቅባት ነበርና ከተማሪዎቿ ሳይቀር ትንኮሳዎች ይደረጉባት ይዘዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ወጥታ መግባት እስከማትችል ድረስ ፈትኗታል። እንጀራ ገዝታ ስለምትመገብ ድንገት ረስታ ከገባች ጦሟን እስከማደር ትደርስ ነበር። አጋጣሚው ቋሚ የመግቢያ ጊዜ ጭምር እንድታስቀምጥ አስገድዷታል።
ለምህረት ጾታዊ ትንኮሳው ብቻ ሳይሆን አካባቢውን፣ የማህበረሰቡን አኗኗርና ባህል እንዲሁም የአየሩን ሁኔታ መላመድ እጅጉን ከባድ ነበር። እርሷ ያደገችው የአየር ጸባዩ ሞቃታማ በሆነበት እንደ ልብ ወጥቶ በሚገባበት አዳማ ውስጥ ነው። ወላይታ ሶዶ ግን ከዚህ የተለየች ነች። እጅግ ቀዝቃዛና በአቧራ የታመቀች ስፍራ። በዚህም በየጊዜው ትታመም ነበር። ግን የማይለመድ የለምና ነገሮችን እያስተካከለች ሁሉንም ለመደቻቸው።
ወላይታ ሶዶ ለእርሷ ልዩ ቦታ እንደሆነም እየተረዳች መጣች። በዚህ ደግሞ በራሷ ላይ የተለያዩ ለውጦችን እንድታይ ሆነ። አንዱ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ቢሆንም ልምድ ያላቸው መምህራንን ማግኘቷ ነው። እነዚህ መምህራን ከልምዳቸው ልምድን ማጋራት ብቻ ሳይሆን ስትሳሳት ይመልሷታል። አዳዲስ ነገሮችንም እንድትሞክር ያበረታቷታል። ወጣትና ልጅ በመሆኗም የአቅሟን እንድትሯሯጥ ይመክሯታል። ሌላኛው ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ገና ብዙ ማደግ የሚጠበቅበት በመሆኑ የተሻሉ ነገሮችን እንድታመጣና እንድትተገብር አስችሏታል።
ምህረት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለዘጠኝ ዓመት ያህል ስትሰራ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የማገልገል እድልን አግኝታለች። የስርዓተ ጾታ ክፍል አስተባባሪ ነበረች። የተቋማዊ ጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ እንዲሁም የክፍሉ ዳይሬክተር በመሆን አገልግላለች። ከሁሉም የሚልቀው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆነችበት ነው። በጊዜው ብዙዎች ተቃውመዋት ነበር። በተለይም በሁለት ጎራ ተከፍለው የሚጣሉት የትምህርት ክፍሎች እርሷን በፍጹም አልፈለጓትም። ቦታው ላይ እንዳትቀመጥ ተቃውሞ በሚመስል መልኩ ያናገሯት ነበር።
የሚያሸማቅቁ ንግግሮችንም የተናገሯት አልጠፉም። ምህረት ግን ከልጅነቷ ጀምሮ የይቻላል መንፈስን በውስጧ የገነባች ስለሆነች ለማንም ለምንም አልተበገረችም። በአቋሟ ጸንታ ያሰበችውን ቦታ ይዛለች። መጥፎም ይሁን ደህና ለሚያጋጥማት ነገር ራሷን በማጋለጥ ገብታበታለች።
ኃላፊነት ሲሰጥ ትልቁ ሥራ የሚሆነው ሰውን ማሳመን ነውና ለዚህ ቦታ እንደምትመጥን ለማሳየት ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም። ከቤቷ ሻይ ቡና ሳይቀር ተሸክማ በመምጣት ማህበራዊ ሕይወትን ወደ ማጠናከሩ፤ ቁጭ ብሎ የመነጋገር ልምድን ወደ መፍጠሩ ገብታለች። በዚህም ብዙ ነገሮችን ለውጣለች።
የተከፋፈሉትን ሰዎች ወደ አንድ ማምጣት የቻለችበት ሁኔታ አንዱ ነው። ሰዎች ተስማምተው የሚሰሩበትን ሁኔታም ፈጥራለች። ጥቅማጥቅም ላይ የነበሩ ሹክቻዎችንም ቁጭ ብሎ በመነጋገር እንዲፈታ አድርጋለች። በተለይ ደግሞ ዛሬ ድረስ የምትነሳበትን ጠንካራ ተክል ማጽደቅ ችላለች። ይህም አዳዲስ ትምህርት ክፍሎችን ከመክፈት አልፎ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቶች የሚሰጡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው።
ምህረት ያለ ሥራ የምታሳልፈው ጊዜ የላትምና ከማስተማር ባሻገር የተለያዩ ተግባራትን ታከናውናለች። ከተቋማት ጋር በስምምነት አጫጭር ኮርሶችን ትሰጣለች። የማማከር ተግባራትንም ታከናውናለች። ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር፣ ከኮሌጆች ጋር በተለይም ጤና ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ የግል ኮሌጆች ጋርና ከኤምባሲዎች ጋር የምትሰራቸው ተግባራት ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ገጠመኝ
ወላይታ ሶዶ ለመዝናናት፤ ለመመገብና ለመጠጣት ምቹ ናት። በዚህም የአዳማ ልጅ በመሆኗ መቃምና መጠጣት ግድ እንደሆነባት ታምኖ በብዙ ተፈትናለች። አንደንዶችም አብረዋት እንዲያመሹ በንግግራቸው ሊያሳምኗት የሚሞክሩ ነበሩ። ሆኖም አይደለም ያለመደችውን ማድረግ የምታውቀውን እንኳን መጥፎነቱ ገዝፎ ከታያት አሻፈረኝ የምትለው ምህረት በእንቢታዋ ጸንታ ከብዙ ጓደኞቿ ጋር ተቀያይማለች።
ሌላው ገጠመኟ በጣም ኮስታራ ከመሆኗ ጋር የተያያዘውና ጾታዊ ትንኮሳን መሰረት ያደረገው ነው። ተግባሩ በሁለት አካላት የሚፈጸም ሲሆን፤ ከተማሪዎቿ ይጀምራል። በክፍል ውስጥ የሚፈታተኗትና ቢሮ ካልመጣሁ የሚላት ተማሪ ጉዳይ ግን ከሁሉም የሚብስ ነበር። የምትኖርበትን ቤት ሳይቀር አጥንቶ በር ላይ እንዲጠብቃት ያደረገም ነው። በወቅቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ነበር ቤት በር ላይ የደረሰችው። በዚህም ቤቷ እስክትገባ ፈርታ ነበርና ዙሪያ ገባውን እያየች በፍጥነት ወደ በራቸው ተራመደች።
ወደ መግቢያ በሯ ስትቃረብ ግን ያየችውን ማመን አቃታት። ተማሪዋ እንደ ጅብራ ተገትሮ እየጠበቃት ነው። ግራ ተጋብታም ‹‹ ምን ልትሰራ መጣህ›› ስትል ጠየቀችው። ተማሪው ግን ምንም ምላሽ አልሰጣትም። ዓይን ዓይኗን እያየ አፈጠጠባት። በጊዜው ምንም ለማድረግ አልወደደችም። ምክንያቱም የሆነ እርምጃ ብትወስድ የሚከሰተው ነገር ብዙ መዘዝ ይዞ ይመጣል። የተከራየችው ቤት የሚጠበቅ በመሆኑ ደግሞ በሚፈጠር ግርግር የእርሷንም የልጁንም ሕይወት ሊያሳጣ ይችላል። እናም ነገሩን በብልሃት አሳለፈችውና ልጁን ሸኝታ ወደ ቤቷ ገባች።
ጉዳዩ እጅጉን ስላሳሰባትም በማግስቱ አስጠርታው ስለሁኔታው አነጋገረችው፤ ትክክል እንዳልሆነም አስረዳችው። ልጁ ግን ሊቀበላት አልወደደም። ብዙም ሳይቆይ ዊዝድሮ ሞልቶ በመውጣቱ የሁለቱ ነገር ተዘጋ እንጂ ነገሮች ከባድ ይሆኑ እንደነበርም ታስታውሳለች።
የ ‹‹ነገን›› ምስረታ
ወይዘሮ ምህረት አርቆ አሳቢ ናት። ወጣቶች በተለይም ሴቶች የተሻለ ነገ እንዲኖራቸው ትሻለች። በዚህም መጪው ትውልድ ራሱን ያወቀ፣ ራሱን ያበቃና ሥራ መፍጠር የሚችል እንዲሁም ለሀገሩ የሚጠቅም እንዲሆን ‹‹ነገን›› የተሰኘ ድርጅት ከሁለት አጋሮቿ ጋር በመሆን ከፍታለች። በትምህርትና በሙያ ማበልጸግ ዙሪያ የማሰልጠንና የማማከር አገልግሎት እንዲያገኙ እየለፋችም ነው።
አሁን ተቋሙ ከተከፈተ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በትምህርትና አጠቃላይ ሙያ ነክ ስልጠናዎችን የሚሰጥና የሚያማክር ተቋም ነውና ዋና አላማው ብዙዎች ያዩትን ችግር ቀጣይ ሀገር ተረካቢዎች እንዳያዩት ማድረግና የተሻለ ነገን ለትውልድ ማስረከብ ነው።
‹‹ወጣቱ ከስልኩ ጋር ተቆራኝቶ ጊዜውን ሲፈጅ ስናይ የቀበጠ ይመስለናል። ሆኖም ችግሩ እርሱ አይደለም። ሥራ ማጣቱ፣ ምን እንደሚሠራ አለማወቁ፣ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባቱ፣ ፍላጎቱን የሚረዳ ሰው አለማግኘቱ ቢያሳስበው ራሱን ለማረጋጋት የሚያደርገው ነገር ነው፡፡›› የምትለው መምህርት ምህረት፤ ነገን የመሰረተችበት ዋነኛ አላማ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንደሆነ ታስረዳለች።
‹‹ ወጣቱ እጅጉን ያሳዝነኝ ነበር። ከተመረቀ በኋላ ምን እንደሚሰራ አያውቅም። ትምህርቱንም ለምን እንደሚማረው አይረዳውም። በቃ በዚያ ተቀጥሬ እሰራለሁ የሚል ራዕይን ሰንቆ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው። ይህ ደግሞ ውድድር በበዛበት በዚህ ዘመን አይቻልም። እናም ከምንም ሳይሆን አቅም እያለው እንዲቀመጥ አድርጎታል። ስለዚህም በግሌ ለምን እዚህ ላይ አልሰራም በሚል ወደ ስራው ገብቻለሁ›› ስትልም የማማከር ስራውን እንዴት እንደጀመረችው አጫውታናለች።
ፍልስፍና
የፈለግነውን ያህል ጠቢባን ብንሆን፤ የእውቀት ጥግ ላይ ብንደርስ ፈርሃ እግዚአብሔር ከሌለን የምናሳካው ነገር አይኖርም የሚለው የመጀመሪያው የሕይወት ፍልስፍናዋ ነው። በዚህም ቤተሰቧን ስትመራ፤ ተማሪዎቿን ስታስተምር ነገሮችን በፈርሃ እግዚአብሄር እንዲያደርጉ በማሳመን ነው። የሥነልቦና መምህር መሆኗ ደግሞ ለዚህ ተግባር በብዙ መንገድ እንደሚያግዛትም ታስባለች። እግዚያብሔርን መፍራት መከባበርን፤ አመስጋኝነትን፤መነጋገርን፤ እምነትን ወደ ውስጣችን እንደሚያመጣም ታምናለች።
ሌላኛው የሕይወት ፍልስፍናዋ ሰው መሆን መቻል ነው። ማንኛውንም ሰው የእግዚአብሔር ፍጥረት እስከሆነ ድረስ በእኩል ማስተናገድ፣ በእኩል ማገልገልና ለእርሱ የቅርብ መሆንን መምረጥ አቋሟ ነው። ይህንንም በአኗኗር ዘይቤያችን፤ በምንናገራቸው ቃላቶች፤ በእለት ተእለት ድርጊታችን መግለጥ ይኖርብናልም የሚል ፍልስፍና አላት።
ቀጣይ እቅድ
እቅድ ለምህረት በእያንዳንዷ ተግባራቷ ውስጥ መሰረታዊ ነገር ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በዚህም እስከ 10 ዓመት ድረስ ተጉዛ ነገዋን እያየች ታቅዳለች። የቀን ተግባራቷም እንዲሁ ከእቅዶቿ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። በመሆኑም በሥራ ዘርፏ የቀጣይ እቅዷ ብቁ የሆነ የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል መክፈት ነው። ይህ ማዕከልም ሁለገብ ተግባራትን የሚያከናውን እንዲሆንላት ትፈልጋለች።
ጤና ላይ፣ አስተሳሰብ ላይ፣ ፈጠራ ላይ፣ አመጋገብ ላይ፣ ቤተሰባዊ ዘይቤ ላይ የሚሰራ እንዲሆንላትም ትመኛለች። ይህ እምነቷም እውን እንዲሆን ሥራዋን አሀዱ ብላ ትገኛለች። በእርሷ እምነት መምህርነት ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖር ነው። የተማሪዎችን ነገ አውቆ ዛሬ ላይ መስራት ነው። ሀገርን እየሰሩ ማሻገር ነውና ከልጆቿ እስከ ተማሪዎቿ ድረስ ብቁ ዜጋን በማፍራት መቀጠሉ ሌላኛው እቅዷ አድርጋ የምትንቀሳቀስበት እንደሆነም አጫውታናለች።
ቤተሰብ
ትዳር ለምህረት በብዙ መልኩ ይተረጎማል። ጭንቀትን ማቅለያ፣ ነገን ማሳመሪያ፣ ደስታን መፍጠሪያ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኛ፣ መመካከሪያ፣ አዲስ እይታን መመልከቻ ወዘተ… ነው። 13 ዓመታትን በትዳር ስታሳልፍ እነዚህን ሁሉ እንዳገኘችበት ትናገራለች። ከባለቤቷ ጋር ስትገናኝ በአጋጣሚ ነበር። በዓይን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቢተዋወቁም በቅጡ እንኳን ሰላምታ አይለዋወጡም። የእህል ውሃ ነገር ሆነና ነገሩ ዳግመኛ ለትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገናኙ መቀራረብ እንዳለባቸው ወሰኑ። ሻይ ቡናም ተባባሉ። ነገሮች በንግግር ዳበሩናም ወደ ፍቅሩ ገቡ።
ሁለቱ አንድ የሚሆኑበትንም እድል አገኙ። በትዳር ተጋመዱ። ሆኖም ግን ወዲያውኑ ልጅ ለመውለድ አላሰቡም። ለፍቅራቸው፣ ለመረዳዳታቸው ረጅም ጊዜ ሰጥተዋል። ይህም አራት ዓመታትን የፈጀ ነው። ሁለቱም ትምህርታቸውን አጠናቀው መደላደሎችን ከፈጠሩ በኋላ አሁን ልጅ ያስፈልገናል አሉ። የበኩር ልጃቸውን የቤቱ በረከት አደረጉ። አሁን ላይ ሁለት ልጆችን አፍርተው በደስታ እየኖሩ ይገኛሉ። ቀጣዩን ጊዜያቸውን ለፈጣሪ ሰጥተውም በደስታ እየተጓዙ ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም