የቡናው ልማት በአዲስ ምዕራፍ!

ሀገራችን ወደ ውጪ የምትልከው የቡና መጠንና ከዚህም የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ትርጉም ባለው መልኩ እየጨመረ ነው። ባለፈው በጀት ዓመት 300 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባለች፤ ከዚህም ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች። ዘንድሮ ደግሞ ከ450 ሺ ቶን በላይ ቡና በመላክ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ለማግኘት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች፡፡

መንግሥት ቡና ለኢኮኖሚው ትልቅ አቅም መሆኑን በመገንዘብ በልማቱም በግብይቱም ላይ በትኩረት መሥራቱን ተያይዞታል። በተለይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዘርፉ ሪፎርም በማካሄድ በግብይቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ማነቆዎችን በመለየት መፍታት ተችሏል፤ በልማቱም እንዲሁ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ ቡና እያለማ የሚገኘው አርሶ አደሩ ብቻ አይደለም ባለሀብቱም ነው፡፡

ይህን ትከትሎም ለውጭ ገበያ በሚቀርበው የቡና መጠንም ሆነ በሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ የታየበት ዓመትም እንዳለ ይታወቃል።

የቀጥታ የግብይት አማራጭ በመዘርጋት የግብይቱን ደንቃራዎች ማስወገድ ተችሏል፤ በቡና ግብይቱ ላይ ደላሎች ያደርሱት የነበረውን ችግር ቆርጦ መጣል ተችሏል። ለላኪዎች ብቻ ተወስኖ የኖረውን ቡናን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ አርሶ አደሩም አቅራቢውም ጭምር እንዲሰማሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ዓለም አቀፍ የቡና ኢግዚቢሽኖችን በማካሄድ፣ ከኮሜርሻል ቡና ይልቅ ስፔሻሊቲ ወይም ልዩ ጣእም ቡና ላይ በስፋት በመሥራት፣ ቡና የሚላክባቸውን ሀገሮች ቁጥር በመጨመር፣ ወዘተ የተከናወኑ ሥራዎች በዘርፉ የተያዙ እቅዶች ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ካስቻሉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በልማቱም በኩል ለውጦች እየታዩ ናቸው። በተለይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን የቡና ችግኞች እየተተከሉ ናቸው፤ ያረጀ ቡና በመጎንደል ምርታማ እንዲሆን ለማድረግም እየተሠራ ነው።

መንግሥት ከቡናው ዘርፍ አሁንም ብዙ ይጠብቃል። ዘንድሮ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ለማግኘት ታቅዷል፤ ሀገሪቱ ይህን ለማሳካት አቅሙ እንዳላት ተለይቷል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የታየው አፈጻጸምም ያንን እንደሚያመላክት ታምኖበታል። ከሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ወዲህ ያለው አፈጻጸም ይህንኑ እንደሚያመላከት እየተገለጸ ይገኛል።

ሁሉም ሥራዎች ቡና በከፍታው ላይ ከፍታ እንዲጨምር አድርገዋል። ቡና በቀጣይም ብዙ ተስፋ እንዳለው በቅርቡ የወጣው ዜና ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተገኝተው የጎበኙት በአንድ ባለሀብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመስኖ እየለማ ከሚገኘው የቡና እርሻ ይህንኑ መረዳት ይቻላል። በዚህ የቡና ልማት በሄክታር 60 ኩንታል ማግኘት ይቻላል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በሄክታር 10 ኩንታል ነው እየተገኘ ያለው።

አዲሱ ልማት ይዞት የመጣው ይህ አዲስ መንገድ ባለፉት ዓመታት ትልቅ እምርታ እያስመዘገበ የመጣው ቡና ወደፊት በእምርታ ላይ እምርታ እንዲያስመዘገብ ያስችላል። ይሄ ትልቅ የምስራች ፣ ትልቅ ዜናም ነው።

የቡና ልማቷንና ግብይቷን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ለምትሠራዋ ኢትዮጵያ ይህ በርግጥም ትልቅ ዜና፣ አዲስ ምዕራፍ ነው። ይህን ተሞክሮ ጠጋ ብሎ ተመልክቶና ቀምሮ ለማስፋት መንቀሳቀስ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ምርታማነት ቀዳሚ የሆኑትን ብራዚልንና ቬይትናም ለመፎካከር በተለይ ቬይትናምን በልጣ ለመገኘት በቡና ዛፍ ጉንደላና በችግኝ ተከላ ላይ አተኩራ እንደምትሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በአንድ ወቅት መግለጻቸው ይታወቃል። ይህ ቡናን በአዲስ ቴክኖሎጂና በመስኖ የማልማት ሥራ በሀገሪቱ እውን መሆኑ ደግሞ ሀገሪቱ ይህን እቅድ ፈጥና እንድታሳካ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይችላል።

በሀገሪቱ ቡናን በመስኖና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እያለሙ ማሳየት ደረጃ መድረስ በርግጥም ለዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ነው። ይህ ልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ተሞክሮው ሊቀመር ልማቱ ሊሰፋ ይገባል። የባለሀብቱ የቡና እርሻ ጥሩ ትምህርት ቤት ይሆናል።

ተሞክሮውን በማስፋት ወደ ውጤት ለመሸጋገር ጊዜ ሊወስድ ቢችልም፣ የዘርፉ የምርምር ተቋማት ይህን ተሞክሮና ልምድ በሚገባ በመቀመር ወደ ሌሎች የቡና አልሚዎች ለማስፋት ፈጥነው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። የምርምር ተቋማቱ ወይም ተመራማሪዎች ቡና በእዚህ መንገድ ሊለማ እንደሚችል በምርምር ደረጃ አልሄዱበትም ተብሎ አይታሰብም። ዋናው ነገር የምርምር ውጤቱ መሬት ላይ ወርዶ ሕዝብንና ሀገርን መጥቀም ወደሚያስችል ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉ ላይ ነው።

አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ልማቱን ለማዘመን ቡና በሚለማባቸው አካባቢዎች ያሉ የምርምር ተቋማት በዚህ ላይ ሊሠሩ ይገባል። በቡናው ዘርፍ የተሠማሩ አልሚዎችም ይህን ቴክኖሎጂና የመስኖ ልማት በሚገባ ተመልክተው ልማቱን ከተለመደው አሠራር ለማውጣት ጥረት ማድረግ መጀመር አለባቸው!

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You