ደስ የሚል ቀን ነው። ሆኖም በዚህ ሰዓት ልታደረገው ያሰብከው ምንም ነገር የለም። ጓደኞችህ ግን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ፕሮግራም አላቸው። ሁሉም ወጣ ብለው እየተዝናኑ ነው። ዛሬም ግን አንተን አልጠሩህም። ይህ በራሱ የሚያስከፋ ነገር ነው። ከዚህ የባሰው ደግሞ ለምን እንዳልጠሩህ ስታስብ የሚፈጠርብህ ስሜት ነው። “ሰዎች አብሬያቸው እንዳልሆን የማይፈልጉት አንድ ችግር ቢኖርብኝ ነው” ብለህ ታስባለህ።
እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ ገጥሞህ ሊሆን ይችላል። አንተና እኩዮችህ እንዳትቀራረቡ የሚያደርግ ሰፊ ገደል በመካከላችሁ እንዳለ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ከእነርሱ ጋር ለማውራት በሞከርክ ቁጥር አፍህ ይንተባተብበሃል። አብረሃቸው ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችል አጋጣሚ ስታገኝ ዓይንአፋርነት በቀላሉ እንዳትቀላቀላቸው እንቅፋት ይሆንብሃል። ከሌሎች ጋር መጫወት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሚሆንብህ ለምንድን ነው? ከእኩዮችህ ጋር መቼም መቀላቀል እንደማትችል በማሰብ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ገደሉን ለመሻገር የሚያስችልህን ድልድይ ለምን አትሠራም? ይህን ማድረግስ እንዴት ነው የምትችለው?
የመጀመሪያው ገደል ስለራስህ ያለህ አሉታዊ አመለካከት ነው። አንዳንድ ሰዎች ሁልጊዜ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። ማንም ሰው እንደማይወዳቸውና ጨዋታ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። አንተም ስለራስህ እንደዚህ ይሰማሀል? ይህ የሚሰማህ ከሆነ እንዲህ ያለ አሉታዊ አመለካከት መያዝህ በአንተና በእኩዮችህ መካከል ያለውን ገደል ይበልጥ ከማስፋት ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ድልድዩ ደግሞ ጠንካራ ጎኖችህ ላይ ማተኮር ነው። ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ያሉህን አንዳንድ ተስጥኦዎች ወይም ግሩም ባህሪያት ለማሰብ ሞክር። ከዛም በወረቀት ላይ በዝርዝር አስፍራቸው።
አንዳንድ ጉድለቶች እንደሚኖሩህ ግልፅ ነው። ደግሞም ጉድለቶችህን ማወቅ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ጥሩ ነገሮችም ይኖሩሃል። ጠንካራ ጎኖችህን ማወቅ በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ስለሚረዳህ ስለራስህ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ለማስወገድ ያስችልሃል።
ሁለተኛው ገደል ዓይን አፋርነት ነው። ከሌሎች ጋር መጫወት ትፈልጋለህ። ሆኖም አጋጣሚው ሲፈጠር አፍህ ስለሚተሳሰርብህ ምን እንደምትል ግራ ይገባሀል። ብዙዎች ዓይን አፋርነት አብሯቸው የኖረ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ። ሰዎችን በጋራ በሚያሰባስቡ መድረኮች ላይ ቀርቦ ለመነጋገር ዳገት ይሆንባቸዋል። ይህን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ ሌሎች ሰዎች ተቀራርበው ሲያወሩ ከማድነቅ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም። አንተም ከሰው ጋር ተቀራርቦ ማውራትን አግዝፈህ እስካየህ ድረስ ሌሎች ተቀራርበው ሲያወሩ እነርሱን ከማድነቅ ውጭ ምንም የምታደርገው ነገር የለም።
ለዚህ ገደል ደግሞ ድልድዩ ከሌሎች ጋር ለመግባባት ልባዊ ጥረት ማድረግ ነው። ይህ ሲባል በጣም ተጫዋች ሰው መሆን አለብህ ማለት አይደለም። መጀመሪያ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ለመግባባት መሞከር አለብህ። ሰዎችን ይበልጥ ለማወቅና ለመግባባት ስለደህንነታቸው ወይም ስለሥራቸው መጠየቅ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ልብ ልትለው የሚገባው ነገር በአንተ እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ብቻ ለመቀራረብ መሞከር እንደሌለበህ ነው። አንዳንዴ ሰፊ የእድሜ ልዩነት ባላቸው ሰዎች መካከል ጓደኝነት ሊፈጠር እንደሚችልም መረዳት ይኖርብሃል። ስለዚህ የእድሜ ልዩነት ብዙ ሊያሳስብህ የሚችል ጉዳይ መሆን የለበትም።
በተጨማሪም ጭውውት ሲባል ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚያደርጉት የሃሳብ ልውውጥ እንጂ አንድ ሰው ብቻ የሚቆጣጠረው መድረክ አለመሆኑን አትዘንጋ። ሰዎች ከሚያዳምጣቸው ሰው ጋር መጨዋወት ያስደስታቸዋል:: በመሆኑም ዓይን አፋር ከሆንክ አንድ ነገር አስታውስ። ከሰዎች ጋር ስትጨዋወት ብዙ ማውራት አይጠበቅብህም። ይበልጥ ልታውቃቸው ከምትፈልጋቸው ትልልቅ ሰዎች መካከል የሁለቱን ስም በወረቀት ላይ አስፍር። ስማቸውን ከፃፍካቸው ሰዎች መካከል ወደ አንዱ ቀረብ ብለህ ጨዋታ ለመጀመር ሙከራ አድርግ። ተቀራርበህ ለመጫወት በሞከርክ ቁጥር ብቸኝነቱ እየለቀቀህ መምጣቱ አይቀርም።
ሶስተኛው ገደል የማይመች ባህሪ ነው። ሁሉን አውቃለሁ ባይ የሆነ ሰው ሌሎችን መንቀፍና መተቸት እንዲሁም በአሽሙር መናገር ይቀናዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መከራከር የሚወድና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ የሚል ሰው አለ። እንዲህ ያለው ሰው እጅግ ፃድቅ ስለሚሆን የእሱን አስተሳሰብን የማይቀበልን ሰው ለመንቀፍ ይቸኩላል። እንዲህ ዓይነት ባህሪ ካላቸው ሰዎች ጋር መሆን እንደማያስደስትህ የታወቀ ነው። ይሁንና ከሌሎች ጋር እንዳትቀራረብ የሚያደርግህ ገደል የተፈጠረው አንተ ራስህ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆንህ ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ራስህ መልስ መስጠት ይኖርብሃል።
ለዚህ ገደል ድልድዩ የሌላውን ስሜት በቅጡ መረዳት ነው። አንድ ሰው በሚናገረው ነገር ባትስማማም እንኳን በትእግስት አድምጠው። ትኩረትህን በሚያግባቧችሁ ነጥቦች ላይ በማድረግ ሃሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። በአንድ ጉዳይ ላይ እንደምትስማማ መግለፅ እንዳለብህ ከተሰማህ ሃሳብህን በዘዴና በረጋ መንፈስ ተናገር።
ሰዎችን የምትናገረው ሌሎች አንተን እንዲያናግሩህ በምትፈልግበት መንገድ ሊሆን ይገባል። ምንጊዜም ቢሆን አንድ ነገር ስታደርግ ሳታጉረመርምና ሳትከራከር መሆን አለበት። አላስፈላጊ ክርክር መጀመር ወይም በሌሎች ላይ ማሾፍ እንዲሁም ራስን በማመፃደቅ ሌሎችን መተቸት ወይም መንቀፍ ሰዎች እንዲርቁህ ያደርጋል። ንግግርህ ምንጊዜም ለዛ ያለው ከሆነ ግን ሰዎች ይበልጥ ይወዱሃል።
ከላይ ከቀረቡት ነጥቦች አንፃር ራስህን ከመረመርክ በኋላ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳትቀራረብ የሚያግድህን ገደል ለመሻገር የሚያስችል ድልድይ መሥራት የምትችልባቸው መንገዶች እንዳሉህ አስተውለህ ሊሆን ይችላል። ርግጥ ነው ምክንያታዊ መሆን ይኖርብሃል። ሁሉም ሰው እንዲወድህ መጠበቅ የለብህም። ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ ሰዎችን እንኳን የሚጠሉ ግለሰቦችም እንዳሉ መገንዘብ ይኖርብሃል።
ጓደኛ መያዝ የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንዳልሆነ አትርሳ። ስለዚህ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍለህ ጓደኞች ለማፍራት ጥረት ማድረግ እንደማያዋጣህ ተገንዘብ። እንዲያም ሆኖ ግን በቀላሉ የምትቀርብ ሰው ለመሆን ጥረት ማድረግህን አታቁም። የተወሰነ ጥረት ካደረክ ይህን ማሳካት ትችላለህ። በነገራችን ላይ በጣም የምትወደው ጓደኛህ በድንገት ቀንደኛ ጠላትህ ሊሆን ይችላል። በጣም በሚዋደዱ ጓደኞች መካከል እንኳን እንዲህ ያለ ነገር ሊከሰት ይችላል። ፈፅሞ የማይነጣጠሉ ይመስሉ የነበሩ ጓደኞች መነጋገር እንኳን ሊያቆሙ ይችላሉ። ታዲያ በአንድ ወቅት ደስ የሚል ጓደኝነት የነበራቸው ሰዎች በድንገት መጣጣም የሚያቅታቸው ለምንድን ነው?
ስለዚህ የብቸኝነት ገደሎችን ለመሻገር የሚያስችሉ ድልድዮችን ማወቅ እንዳለብህ ሁሉ በአንተና በጓደኞችህ መካከል መሻከር ሲፈጠር እንዴት ማደስ እንዳለብህ መረዳት ይኖርብሃል። መቼም ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም። ስለዚህ ጓደኛህ አንተን የሚጎዳ ነገር ቢያደርግ ወይም ቢናገር የሚያስገርም አይደለም። አንተም ሌሎችን የጎዳህበት ጊዜ ይኖራል። ሁሉም ሰው ፍፁም ስላልሆነ አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን ቅር ማሰኘታችን አይቀርም። ለዛም ነው ቀላል በሆነ አለመግባባት የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚያስፈልገው።
በሌላ በኩል በአንተና በጓደኛህ መካከል የነበረው ግንኙነት በአንድ ወቅት በተፈጠረ ችግር ምክንያት ሳይሆን ከዚህ ቀደም ታስቡት የነበረውን ያህል ተመሳሳይ ፍላጎት እንደሌላችሁ እየተገነዘባችሁ በመምጣታችሁ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እያደክ በመጣህ ቁጥር ለነገሮች ያለህ አመለካከት ሊለወጥ እንደሚችል ሁሉ የጓደኛህም ፍላጎት ሊለወጥ እንደሚችል አስታውስ።
በአንተና በጓደኛህ መካከል ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረ እንደሆነ ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ጓደኝነትህንስ እንዴት ነው ልታድስ የምትችለው? ለምሳሌ አንድ በጣም የምትወደው ልብስህ ተቀዶብህ ያውቃል? ምን አደረክ? ልብሱን ጣልከው ወይስ ጠገንከው? በርግጥ ይህ የተመሠረተው ልብሱ ምን ያህል ተቀዷል? ወይም ልብሱን ምን ያህል ትወደዋለህ? ለሚሉት ጥያቄዎች በምትሰጠው መልስ ላይ ነው። ልብሱን በጣም የምትወደው ከሆነ በሆነ መንገድ ልትጠግነው መሞከርህ አይቀርም። አብዛኛውን ጊዜ በጓደኞች መካከል ችግር ሲፈጠርም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይቻላል።
በአብዛኛው ይህ የተመሠረተው በተፈጠረው ችግር ክብደትና ለግንኙነታችሁ በምትሰጠው ቦታ ላይ ነው። ለምሳሌ ጓደኛህ ደግነት የጎደለው ነገር በመናገር ወይም በማድረግ ጎድቶህ ከሆነ ጓደኝነታችሁን አሽቀንጥረህ ከመጣልህ በፊት ነገሩን በጥሞና አስብበት። ጓደኛህ የጎዳህ ሆን ብሎ ነው? ርግጠኛ ካልሆንክ ሆን ብሎ እንዳልሆነ ማሰቡ የተሻለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለችግሩ መፈጠር አንተም አስተዋጽኦ አድርገህ እንደሆነ ራስህን መመርመር ትችላለህ። ለምሳሌ አንድ ጓደኛህ ሚስጥርህን ስላወጣብህ አዝነሃል እንበል። ይሁንና መጀመሪያውኑም ቢሆን ሚስጥርህን መንገርህ ጥበብ የጎደለው ርምጃ ይሆን? ምናልባትም የነገርከው ሚስጥር ሸክም ሆኖበት ሊሆን ይችላል።
ልታስብበት የሚገባ ሌላም ነጥብ አለ። ብዙ የምታወራ ወይም የሞኝ ንግግር የምትናገር ከሆነ ሌሎች እንዲቀልዱብህ መንገድ የምትከፍተው ራስህ ልትሆን ትችላለህ። በመሆኑም ጓደኛዬ ይበልጥ እንዲያከብረኝ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ይኖርብኝ ይሆን? ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንዲያም ሆኖ ግን የተጎዳህበትን ነገር እንዲሁ ችላ ብለህ ማለፍ እንደማትችል ቢሰማህስ? በዚህ ጊዜ ጓደኛህን ማነጋገር የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህን የምታደርገው ተቆጥተህ ባለህበት ሁኔታ መሆን የለበትም። ብዙ ጊዜ ግልፍተኛ ሰው ጠብ አነሳሽ ነው። በተቃራኒው ታጋሽ ሰው ጠብን ያበርዳል። ስለዚህ ሁኔታውን ለማስተካከል ከመሞከርህ በፊት ቁጣህ እስኪበርድልህ መቆየቱ የተሻለ ነው። ጓደኛህን በምታነጋግርበት ጊዜ አላማህ ችግሩን መፍታትና ጓደኝነታችሁ እንደቀድሞ እንዲሆን ማድረግ መሆን አለበት። አለበለዚያ ትርፉ መቃቃርና ጥቅም አልባ ይሆናል።
ዞሮ ዞሮ ውጥንቅጥና ጫጫታ በበዛበት በዚህ ዘመን በርካታ ተስፋ አስቆራጭና ሕይወት እንዲሰለች የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ምክንያቶች ብቸኝነትን ወደ መምረጥ የመግፋት እድላቸው ሰፊ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ብቸኝነትን የመሸነፊያ ቁልፉ በእጅህ ላይ ነው። እናም ወዳጄ! ቁልፉን ተጠቀምበት። ብቸኝነትን እስከ ወዲያኛው ታሰናብተዋለህ!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም