አንዳንዶች ያላቸው ክህሎት እና ተሰጥኦ በሌሎች ሰዎች እውቅናን አግኝቶ በዙሪያቸው በርካታ ደጋፊዎችን አግኝተው ስኬታማ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ያላቸው ክህሎት ላይ ጥረት አክለው ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ። ህልማቸው እና ጠንክሮ መሥራታቸው ነጋቸውን እንደሚያስውበው ያውቃሉ። ወጣትነታቸው በጥረት እና በፈተና ማለፍ የግድ እንደሚለውም በመረዳት ለማደግ እንጂ ለመውደቅ ቦታ የላቸውም።
ተገኑ ደርጉ ይባላል። ችሎታውን እና ያሉትን እድሎች በመጠቀም ሕይወቱን ለማሻሻል በመጣር ላይ የሚገኝ ወጣት ነው። ትውልድና እድገቱ ከአዲስ አበባ በቅርበት በምትገኘው ሙከጡሪ ከተማ ነው። ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን እረኝነት ልጅነቱን ያሳለፈበት ነው። በሚኖርበት ሙከጡሪ ከተማ በልጅነቱ የወላጆቹን ከብቶች በመጠበቅ እና በእረኝነት ጊዜውን አሳልፏል። ሶስት እህትና ወንድሞች ያሉት ተገኑ ሕይወቱ የሚያቀይር አጋጣሚ የተፈጠረው ገና የሕይወትን ውል ባልተረዳበት በዚህ የልጅነት ጊዜው ነበር።
በልጅነት እድሜው እንደሌሎች ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ያልታደለው ተገኑ በአንድ በአቅራቢያው በሚኖር ጎረቤት አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሁኔታው የማታለል እና የልጅነት ጉልበት መበዝበዝን መሆኑን የተረዳው አዲስ አበባ መጥቶ ሥራ ከጀመረ በኋላ ነው። ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ወደ ከተማ መምጣት ፍላጎቱ እንዳልነበር የሚያስታውሰው ተገኑ አንዱ የማታለያ መንገድ ገንዘብ ይከፈላችኋል የሚል እንደነበር ይገልጻል።
‹‹ቤተሰቦቼ ሳያውቁ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ከመጣን በኋላ የእረኝነት ሥራ ተቀጠርን። ›› አሁን ላይ ቦታው ለልማት ተብሎ የመኖሪያ መንደር እንደሆነ የሚገልጸው ተገኑ ከ13 ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በወላጆቹ ቤት ይሰራው የነበረውን የእረኝነት ሥራ በአሰሪዎቹ ቤት ውስጥ እየኖረ መሥራት ጀመረ። አንድ ዓመት ያክል ጊዜ ሥራውን ሲሰራ ቃል እንደተገባለት ግን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። ይልቁንስ ተገኑ ለሚሠራው ሥራ የሚከፈለው ገንዘብ ግን የሚገባው አታለው ያመጡት ጎረቤቶቹ ኪስ ነበር።
ተገኑ ይሠራበት ከነበረው ከዚህ ሥፍራ ወጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ለመሄድ ፍላጎት ነበረው። ነገር ግን ገና የ11 ዓመት ልጅ ነውና እንዴት አድርጎ መሄድ እንዳለበት ባለማወቁ የተሻለ ቀን ይመጣል የሚል ተስፋን ይዞ መሥራቱን ቀጠለ። ምንም እንኳን ልጅ ቢሆንም የተገኑ ወላጆች ተለያይተው የሚኖሩ በመሆናቸው ሥራውን ትቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመኖር ምቹ ሁኔታ እንዳልተፈጠረለት ያን ጊዜ ያስታውሰዋል።
ታዲያ የሕይወት መስመር የሚፈጥረው እድል አይታወቅም እና ተገኑ አብዝቶ ጠዋት ጠዋት ቁርሱን ከሚበላበት ቦታ አንዲት የቤቱ ሠራተኛ ጋር መተዋወቅ ቻለ። የተገኑን ልጅነት ገና ከፊቱ የተመለከተችው ይህች ሴት ለምን ትምህርትን አትማርም የሚል ጥያቄ አቀረበችለት። በዚህ የተጀመረው ጨዋታ ቀልቧን የሳባት ይህች ሴት በአንድ ህጻናትን የሚያስተምር እና የሚያሳድግ ሀገር በቀል ማሳደጊያ ማዕከል ውስጥ የተሻለ ሕይወትን ማግኘት እንደሚችል አስረዳችው።
ተገኑ በዚህ ሃሳብ ተስማምቶ ማሳደጊያ ድርጅቱን ከአንድ ዓመት የሥራ ቆይታ በኋላ ተቀላቀለ። ቢዘገይም የትምህርት ሕይወትን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ ተገኑ ሥራ ለመሥራት አይገደድም፤ ለመኖር የሚያስፈልጉት ሁሉ ተሟልተውለታል። ኑሮውንም ቢሆን በድርጅቱ ውስጥ ከሚኖሩ ከሌሎች እኩያ ጓደኞቹ ጋር ነበር።
ይህ ቦታ በዙሪያው የሚረዳው ለሌለው እና በልጅነት እድሜ ላይ ላለው ተገኑ ጥሩ ቦታ ሆኖ አግኝቶታል። ነገር ግን በድርጅቱ ውስጥ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ካልሆነ በቀር ከሚኖርበት ጊቢ መውጣት ፈጽሞ የተፈቀደ አልነበረም። ‹‹ በድርጅቱ ውስጥ ትምህርቴን እስከሚጨርስ ድረስ የመቆየት እድል ነበረኝ ግን እዛ መቆየት በጊዜው በጣም ረጅም መስሎ ነበር የታየኝ። ›› የሚለው ተገኑ ሶስት አመት በድርጅቱ ውስጥ ከቆየ በኋላ ወጥቶ የራሱን ሕይወት በራሱ ለመምራት ወሰነ። 18 ዓመት ያልሞላው ሰው ይህንን ሃሳብ ማምጣቱ ራስን በራስ መምራት ምን ማለት መሆኑን በቅጡ ባይረዳው ነው ያሉት የድርጅቱ አስተዳዳሪዎች ሃሳቡን ሊያስቀይሩት ሞክረዋል።
‹‹አሁን ያለሁበትን ሕይወት በራሴ እንደምፈጥረው አውቅ ስለነበር በዛ መቆየት አልፈለኩም። ›› የሚለው ተገኑ የራሱ ውሳኔ መሆኑን በፊርማው አረጋግጦ አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ወሰነ። አብዛኛዎቹ የማሳደጊያ ድርጅቶች የሚቀበሏቸውን ህጻናት እድሜቸው 18 ዓመት እስኪሆን ድረስ በማሳደጊያ ውስጥ የማቆየት ልምድ አላቸው። ከዚያ በኋላም ሕይወትን እንዲጋፈጡት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ኑሯቸውን እንዲመሩ ያደርጋሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ብሎ ከማሳደጊያው መውጣት የሚፈልግ እነዚህን ድጋፎች ከተቋሙ አያገኝም። ተገኑ በጊዜው ከድርጅቱ ሲወጣ አንድም ቤተሰቦቹ ጋር መሄድ እንደሚፈልግ መግለጹ ሊፈቀድለት የቻለበት አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።
ከድርጅቱ ከወጣ በኋላ የወሰነው ውሳኔ ላይ ጥቂት እንዲያስብበት አድርጎት እንደነበር ያስታውሳል። ‹‹መጀመሪያ እንደወጣው ወዴት እንደምሄድ ራሱ አላውቅም ነበር። ሁለት ቀን በቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ አድርያለሁ። ›› በማለት ጊዜውን የሚያስታውሰው ከሁለት ቀን በኋላ በመንገድ ላይ በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ሌላ የሕይወት እድልን ሊሰጡት ችለዋል።
ሲታይ ብዙም በችግር ውስጥ ያለፈ የማይመስለው ተገኑ ቀልባቸውን የሳባቸው እኚህ የጽዳት ሠራተኞች የተገኑን ታሪክ ከተጋሩ በኋላ አብሯቸው እንዲኖር ፈቅደው ወደቤታቸው አስገቡት። ትምህርቱን ካቋረጠበት እንዲቀጥል አገዙት። እሱም ትምህርቱን እየተማረ ከትምህርት ቤት መልስ እነሱን በሥራ በማገዝ ሕይወትን ቀጠለ። በተለያየ መንገድ ችግር ውስጥ የሚገኙ እና በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያላቸውን ልጆች በተለያየ መንገድ ድጋፍ እንደሚያደርግ መረጃው ያላቸው የተገኑ ቀን አሳላፊዎች ያለውን የትምህርት አቀባበል ተረድተው የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ስር እንዲሆን አደረጉት።
‹‹ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በየወሩ የኪስ ገንዘብ እና ሌሎች ግብዓቶችን ይረዳኛል። እኔም ያገኘሁትን ሥራ እሠራለሁ።›› ተገኑ ይህንን ድጋፍ ማግኘቱ በሕይወት ተስፋ አድርጎ ትምህርቱን እንዳያቋርጥ አድርጎታል። ነገር ግን ሌሎች አማራጮችን ፈልጎ ሕይወቱን ማሻሻል እና ራሱን መቻል ነበረበት።
በሚኖርበት አካባቢ ለሰዎች ውሃ በመቅዳት፣ የጉልበት ሥራ በመሥራት ሌሎችም ገቢ ያስገኙልኛል ያላቸውን ሥራዎች ይሠራል። ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሚማሩት ትምህርት ባሻገር ሌሎች ተሰጥኦቸውን እና ክህሎታቸውን ፈልገው የሚያገኙበት ነው። ተገኑም ለመማሪያነት ተብለው ከሚሰጡ የተግባር ሥራዎች ተገኑን ወደ ፈጠራ ሥራዎች እና የስዕል ሥራዎች እንዲሳብ አድርገውታል።
‹‹በክፍል ውስጥ የተለያዩ ስዕሎችን እንድስል አሳይመንት ሲሰጠን የብዙዎቹን ተማሪዎች ስዕል እኔ ነበር የምስለው። ›› በማለት የሚያስታውሰው ተገኑ የስዕል ችሎታ እንዳለው ከተረዳ በኋላ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ፣ ወረዳውን በመወከል የተለያዩ የስዕል ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አሸናፊ መሆን ቻለ።
የሥራ ሕይወትን በልጅነቱ የተቀላቀለው በመሆኑ እና ያለበት የሕይወት መስመር ሕይወትን በራሱ እንዲያሸንፍ እና እንዲጋፈጥ የግድ ነው። ይህ የተገኑ የሕይወት እውነታ መሆኑን አስቀድሞ ተረድቷል። በመሆኑም የስዕል ችሎታውን የተረዱ ሰዎች በሚያቀርቡለት ጥያቄ ስዕልን በመሳል ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ተረዳ።
በይበልጥም የስዕል ችሎታው ላይ በማተኮር ሰዎች በተለያዩ ጊዜ ለሰዎች ስጦታ መስጠት ሲፈልጉ የወዳጆቻቸውን ፎቶ በስዕል መልኩ ለማበርከት ተገኑን ምርጫቸው ያደርጋሉ። እሱም የመጡለትን ደንበኞች በማስደሰት እና በተሻለ መልኩ በመሥራት ጥሩ ገቢን ያገኛል። ‹‹ብዙ ሰዎች ለስዕል ቦታ የላቸውም። ነገር ግን እኔ ጋር ሲመጡ ጥሩ አድርጌ እሰራላቸዋለሁ እነሱም ይወዱታል። ›› በማለት ጥሩ ደንበኞች ማፍራቱን ይናገራል።
የእርሱን የስዕል ሥራ ያዩ ሰዎች ለሌሎች ሰዎች በመጠቆም ተገኑ በግል ከመሳል ባለፈ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ ወጣት ማዕከላት ላይ በግድግዳ ላይ የሚሳሉ ስዕሎችን ይስላል። ስዕል ለመሳል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግን በሀገራችን በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም ይላል። የሚገኙት ግብዓቶች የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛ ነው። ‹‹በካንቫስ፣ በአቦጀዲ ጨርቅ ላይ የተለያዩ ቦታዎች የግድግዳ ስዕሎችን እሰራለሁ። በአብዛኛው የምጠቀመው ቀለም ሲሆን አንድ ስዕል ሥራ ሰርቼ በማገኘው ክፍያ የምሥራባቸውን እቃዎች አሟላለሁ። ›› በትምህርትት ቆይታው የፈጠራ ሥራዎች ላይ በይበልጥ የሚሳተፍ ሲሆን ድጋፍ ለሚያደርግለት የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጤና ፎቶ በመሳል በስጦታ አበርክቶላቸዋል ።
ተገኑ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ብቻውን ተከራይቶ የሚኖር ሲሆን ትምህርቱንም በቦሌ አዲስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ብቻውን ቤት ተከራይቶ በመኖር እና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ሕይወቱን ይመራል። እንደሌሎች አኩዮቹ መዝናናት እና ጊዜውን በተለያዩ ቦታዎች ማሳለፍ ለእሱ ጊዜው አሁን እንዳልሆነ ይገልጻል። ሕይወቱን የሚያሻሽልባቸውን መንገዶች በመፈለግ እና ያገኘውን ሥራ ሳይንቅ በመሥራት ሕይወቱን ለማሻሻል ይጥራል።
ወጣት ተገኑ የስዕል ችሎታውን በመጠቀም በተለያዩ ሰዎች አማካኝነት ሲታዘዝ በሚሠራቸው የስዕል ሥራዎች ገንዘብ ሲያገኝ ፤ ሌሎች ሥራዎችንም ጭምር ይሰራል። ‹‹ሥራ አልመርጥም ያገኘሁትን እሰራለሁ። የቀን ሥራ እሰራለሁ፣ ስዕል ማሳል የሚፈልጉ ሰዎች ሲኖሩ ለልደት ለስጦታ እና ለተለያዩ ፕሮግራሞች ስዕል እሰራለሁ። በትምህርት ቤቶች እና በተለያዩ ቦታዎች ላይም የግድግዳ ላይ ስዕሎችን በትዕዛዝ እሰራለሁ። ›› ይላል። ወጣት ተገኑ ወደፊት ገና ብዙ የሚያሳካቸው የሕይወት ህልሞች እንዳሉትም ይናገራል። የተለያዩ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ማስተዋወቅ ከህልሞቹ ውስጥ አንዱ ነው። የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማሟላት ውድ መሆኑን የሚገልጸው ወጣቱ የስዕል ሥራዎቹን ለማጠናከር የሚያግዝ ግብዓት እና ቦታ ቢመቻችለት የተሻለ መሥራት እንደሚችልም ገልጿል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም