ከወደ ሀገረ አውስትራሊያ የተሰማው ሰሞነኛ ዜና በሀገሬም በሆነ ብዬ ተመኘሁ። አዎ አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ አግዳለች የሚለውን ብስራት ስሰማ በቨርቹዋል ኦቲዝም የምትሰቃየውን የእህቴን ልጅ አስታወሰኝ። እናቷም ሆነች አባቷ ገና ሁለት ዓመት ሳይሞላት ጀምሮ ከማጫወት ይልቅ የእጅ ስልካቸውን ሰጥተውና ቴሌቪዥን ከፍተው ስለሚተዋት ለዚህ ዘመን አመጣሽ የአእምሮ እክል ቨርቹዋል ኦቲዝም ዳርገዋታል። ያለ ጥፋቷ በወላጆቿ ስህተት ጤነኛ ሆና የተወለደች የምታሳሳ ህጻን ዛሬ በዚህ በሽታ የተነሳ ከእኩዮቿ የተለየች ህጻን ሆናለች።
ይቺ የእህቴ ልጅ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ ቢሆናትም አፍ አልፈታችም። ከእኩዮቿና ከቤተሰብ ጋር ከመጫወት ይልቅ ስልክና ቴሌቪዥን ላይ ማፍጠጥን ትወዳለች። ስልክ ካልያዘች ወይም ቴሌቪዥን ካልተከፈተ ትቅበጠበጣለች። የምትይዘው የምትጨብጠው ይጠፋታል። ስልክ ስትቀማ ደግሞ ምርር ብላ ስለምታለቅስ እና በሌላ ነገር ልትደለል ስለማትችል ስልክ ተመልሶ ይሰጣታል። ስልክ ከያዘች ቴሌቪዥን ከተከፈተላት ስለአባት ስለ እናቷ ግድ የላትም። ምግብ እንኳ በቅጡ አትበላም። እያደር እየዋል ባህሪዋ ወጣ እያለና እንግዳ እየሆነ መጣ።
አፍ ባለመፍታቷና ባህሪዋ እንደ እኩዮቿ ባለመሆኗ ወላጆቿ ለሥነ ልቦና ጫና ተዳርገዋል። አዎ እንደ ሌሎች እኩዮቿ በኮልታፋ አንደበቷ አታወራቸውም። አባቢ እማሚ ብላ አትጠራቸውም። ሥራ ውሎ የሚገባ አባቷን በናፍቆት አትቀበለውም። ከእሱ ይልቅ ስልኩን ለመቀበል ትጓጓለች። ጎረቤትም ቤተ ዘመድም ምነው እስካሁን አፍ ሳትፈታ ብሎ በጠየቀ ቁጥር እናትም አባትም መሸማቀቃቸው አልቀረም። አፍ አውጥተው ባይናገሩም በጥፋተኝነት ስሜትና በጸጸት እየተሰቃዩ መሆኑን ለመገንዘብ ሞራ ገላጭ መሆን አያስፈልገም። ሁለተኛዋ ልጅ ስትወለድ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ወትውቼ ወትውቼ ስልክና ቴሌቪዥን በአጠገቧ እንዳይደርስ በመደረጉ ከፈጣሪ ጋር የታላቅ እህቷ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማት እየተደረገ ነው። ወደ ነገረ አውስትራሊያ ስመለስ፤
አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ የሚያግደውን ሕግ በፓርላማ አፅድቃለች፡፡ በውሳኔው መሠረትም በሀገሪቱ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የቲክቶክ፣ ስናፕ ቻት፣ ፌስቡክ፣ ሬዲት፣ ትዊተር (ኤክስ) እና ኢንስታግራም አካውንት መክፈት አይችሉም፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የማህበራዊ ትስስር ገፆች ታዳጊዎች አካውንት እንዲከፍቱ የሚፈቅዱ ከሆኑ 50 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው መንግሥት አስጠንቅቋል።
የአውስትራሊያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ሚሸል ሮውላንድ በሀገሪቱ ሰፊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ ያገኘው ይህ ውሳኔ የታዳጊዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን፤ በአውስትራሊያ እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ጎጂ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች በማህበራዊ ትስስር ገፆች ሲመለከቱ እንደነበር አስታውሰው፤ ክልከላው ታዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደርስባቸውን ጫና ይቀንሳል ብለዋል፡፡
ከአውስትራሊያ አስቀድማ ስፔን ባለፈው ሰኔ ወር ከ14 እስከ 16 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ መከልከሏ ይታወቃል። በአሜሪካም በተወሰኑ ግዛቶች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ለመሆኑ ኦቲዝም ምንድነው? ቨርቹዋል ኦቲዝምስ ? ቆየት ካለ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያገኘሁትን ብያኔ ላጋራችሁና ልመለስ።
ኦቲዝም የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን ፍቺውም “ብቸኛ” የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ኦቲዝም (በሙሉ ስሙ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር) ያለባቸው ልጆች ከሌሎች ልጆች ጋር የማይቀላቀሉ፣ የሚረዳቸው ሰው ካላገኙ በቀር ማንም ሊረዳቸው ስለማይችል ብቸኛ ይሆናሉ። ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ኦቲስቲክ ይባላሉ። እነዚህ ልጆች የራሳቸው ዓለም ያላቸው ስለሆኑ የሚረዳቸው ሰው ይፈልጋሉ። የማያቋርጥ ክትትል ይጠይቃሉ።
በሀገራችን አብዛኛው ሕዝብ ስለ ኦቲዝም ብዙም ዕውቀት ስለሌለው ብዙዎቹ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ከማኅበረሰቡ ይገለላሉ። አንዳንድ ወላጆች ስለሚያፍሩባቸው ከቤት ስለማያስወጧቸው፣ አንዳንዶቹ ባለመረዳት መንፈስ ወይም አጋንንት አለባቸው በሚል የተሳሳተ ምልከታ ምክንያት በማሰር ያሰቃዩአቸዋል። ኦቲዝም ልክ እንደ ጨጓራ ቁስለት ወይም ኩላሊት ህመም እንጂ ሌላ አይደለም። የአዕምሮ መዛባት ችግር (disorder) ነው። ማወቅ ያለብን ነገር ኦቲስቲክ የሆነ ልጅ ማንም ሰው አጭር ወይም ጠይም ሆኖ እንደተፈጠረው ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ማኅበረሰብ ያንን መረዳት አለበት።
ኦቲዝም በሽታ ቢሆንም ኦቲስቲክ ያለባቸውን ልጆች ፍቅር፣ ትዕግስትና ጊዜ ከሰጠናቸው ከሰው ጋር ወደ መግባባት ወደ መሻሻል ይመጣሉ። ማኅበረሰቡ ያንን አውቆ ከታገሰ በየቤታችን፣ በየሰፈራችን በዚህ በሽታ የተያዙ ልጆችን ልንረዳቸውና ልናሽላቸው እንችላለን። ፍቅር፣ ትዕግስትና ጊዜ ግን ይፈልጋሉ።
ሰዎች መረዳት ያለባቸው ነገር ኦቲዝም ክትትል ካገኘ መሻሻልን የሚያመጣ ሲሆን ዳውን ሲንድሮም ግን ከዘረመል መዛባት /genetic disorder/ (ወይም ደግሞ የክሮሞዞም ከተለመደው ውጪ መሆን /chromosome abo=normality/) ምክንያት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ነው። የሚወለዱ ልጆች ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጣቸው ዕድል ከእናቶች ዕድሜ ጋር ተያያዥነት አለው። በአሃዝ ለማስቀመጥ ያህል፥ ዕድሜዋ 25 ዓመት የሆነች እናት ልጇ ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጥ ዕድሉ ከ1,250 አንድ ብቻ ሲሆን፥ ዕድሜዋ 40 ዓመት የሆናት እናት ግን ልጇ ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጥ ዕድሉ ከ100 አንድ አካባቢ ነው (ምንጭ)።
የእንግሊዝና የጣሊያን ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ጥናት እንደገለጹት አስቀድሞ የኦቲዝም ተጠቂዎችን ለመለየት የሚያስችል የደምና የሽንት ምርመራ በሕፃናት ላይ በማድረግ ለኦቲዝም ሕክምና መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን በቅርብ ጊዜ ተዘግቦ ነበር (ምንጭ)። ሕፃናት የኦቲዝም ተጠቂ መሆናቸውን ለማወቅ በደም ውስጥ የሚገኝ የፕሮቲን መጠንን በመለካት ማወቅ እንደሚቻልም ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑትንና ያልሆኑትን ሕፃናት በማነጻጻር በተደረገው የሽንትና የደም ናሙና ምርመራ በኦቲዝም የተጠቁት ሕፃናት ከፍ ያለ የፕሮቲን ጉዳት እንደታየባቸውና በኦቲዝም ያልተጠቁት ደግሞ የተሻለ የፕሮቲን ስብጥር በደማቸው መገኘቱን ገልጸዋል። ሕፃናት በደማቸው አነስተኛ የፕሮቲን ስብጥር በሚኖርበት ጊዜ ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድላቸውን እንዲሰፋ ያደርገዋል።
ኦቲዝም ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነትን በማምጣት በሰው ሥነ ባህርይ ላይ ጉዳት በማድረስ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ከዓመታት በፊት በአምስት ሀገራት የተደረገ ትልቅ ጥናት እንደሚያመለክተው 80 በመቶ ለኦቲዝም የተጋለጡ ሕፃናት በዘር የተላለፈባቸው እንደሆኑ ያመላክታል። ሌላ የብዙ ጥናቶች ውሁድ ጥናት (meta-analysis) እንደሚያሳየው ደግሞ በዘር በመተላለፍ ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድል ከ60 እስከ 91 በመቶ ሲሆን፥ በሥነ ሕይወት እና አካባቢ ምክንያት (environmental factors) ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድልም አሌ የማይባል እንደሆነ ያስረዳል።
ኦቲዝም ትልቅ የጤና ጉዳይ ነው፤ ከቀላል ምልክት እስከ ጥልቅ እና በጣም ከባድ የሆነ የጤና እክል ነው። በሽታው በአእምሮ ዘገምተኛ ሕፃናት እና በደንብ ባደጉ የአካዳሚክ ክህሎት ባላቸው ሰዎች ላይ እንደሚገኝ ኦቲዝምን የሚከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። የመጀመሪያዎቹ የኦቲዝም ምልክቶች በጣም ቀደም ብለው ይታያሉ፤ ብዙውን ጊዜ ከአስራ ሁለት ወራት በላይ በሆኑ ሕፃናት ላይ ይታያሉ፤ እንዲሁም ከሶስት ዓመት በፊት በግልጽ ይታያሉ።
በልጅ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በወላጆች ይስተዋላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ቀድሞውኑ በጨቅላነታቸው ሕፃኑ በጣም ጨዋ፣ የሚያያቸው ሰዎች ላይ የማያተኩር፣ እና ሲያነሱት ጠንካራ ነው። በተጨማሪም ሕፃኑ በአንድ ነገር ላይ ለሰዓታት ያተኩራል፤ ለምሳሌ አይጮኽም ወይም ንግግር አያዳብርም። በተጨማሪም የልጁ እድገት መጀመሪያ ላይ መደበኛ እና ያልተለመዱ ባህሪያት በድንገት ሊከሰቱ ይችላሉ።
ኦቲዝም በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ሁከት ይፈጥራል። የኦቲዝም ልጆች ብዙውን ጊዜ አይታዩም፣ ለምሳሌ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የዓይን ለዓይን ግንኙነት (eye contact) አይፈጥሩም፤ አሊያም ቢፈጠሩም በጣም ለአጭር ጊዜ ነው። ኦቲስቲክ ልጅ እንደ ታመመ ብቻውን ጊዜ ማሳለፍ ይመርጣል። አንዳንድ ጊዜ አይታየኝም እና አይሰማኝም የሚል ስሜት ይሰማቸዋል።
ወደ ቨርቹዋል ኦቲዝም ስንመጣ ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በብዛት ስክሪን እንደ ቴሌቪዥን፣ ስልክ ፣ ታብሌት የመሳሰሉትን በብዛት በመጠቀም የሚፈጥረ የአእምሮ ችግር ነው። ወጣ ያሉ ባህሪዎችን፤ የመግባባት ውስንነቶችን፤ እረፍት የለሽ መሆን ፤ትኩረት ማድረግ አለመቻል፤ ጨዋታዎች ላይ ፍላጎት መቀነስ፤ ማህበራዊ መስተጋብር ወይም ተግባቦት አለመኖር፤ ተለዋዋጭ ስሜት፤ የመረዳት እክል፤ አፍ የመፍታት ወይም የንግግር እና ቋንቋ መዘግየት፤ የተገደበ የዓይን ግንኙነት፤ ወዘተረፈ ከቨርቹዋል ኦቲዝም ምልክቶች ጥቂቶች ናቸው። የሚያሳዝነው እነዚህ ሁሉ ባህሪዎች በእህቴ ልጅ ላይ ይታያሉ።
የቪርቹዋል ኦቲዝም ህመምን በባህርይ እና የስፒች ቴራፒ፤ ልጆች ስክሪን ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ በማቆም፤ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በመጨመር፤ ፊት ለፊት የሚናገሩበትን መንገድ በመፍጠርና በማስተዋወቅ፣ ወዘተረፈ ማስተካከል ይቻላል። ከዚህ ጎን ለጎን ህጻናትንና ታዳጊዎችን ከማህበራዊ ሚዲያ የሚጠብቅ ሕግ ሊወጣ ይገባል። ይሄን ለማለት መግፍኤ የሆኑኝን ነጥቦች መለስ ብዬ ላነሳሳ።
አሁን አሁን ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር ጭቃ አቡክቶ ቦርቆ ከመጫወት ይልቅ ቴሌቪዥንና እጅ ስልክ ላይ መጣድን ይመርጣሉ። ቀደም ባለ አንድ መጣጥፌ ለመግለጽ እንደሞከርሁት፤ እኔ በምኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤት ቅዳሜና እሁድ ሆነ በአዘቦት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ በእረፍታቸው ውጭ ወጥተው ሲጫወቱ አላይም ። ድንገት መብራት ሲጠፋ ግን ቴሌቪዥን ስለሚቋረጥ ፣ ብሮድ ባንዱም ስለማይሠራ ከየቤታቸው መውጣትና ሰፈሩን መቀወጥ ይጀምራሉ ። በዚህ መሃል መብራት ከመጣ ሰፈሩን በጩኸትና በፉጨት ያደበላልቁና ወደየቤታቸው ይመለሱና ሰፈሩ መልሶ ጭር ይላል ። ሩጦና ዘሎ ያላደገ ህጻን አካላዊም አእምሯዊ ብቃቱ ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለአፍታ አስቡት ።
የእጅ ስልክ ምርኮኛ እየሆኑ ነው ። ዘመድ ቤት ሲመጣም ሆነ እናንተ ዘመድ ጥያቄ ስትሔዱ ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህጻናት ሳይቀሩ ጠጋ ብለው የእጅ ስልክን ተቀብለው ከአንድ አንድ ጌም ፍለጋ ነው የሚገቡት። ሶስት ዓመት ያለፋት የእህቴ ልጅ ቤት ስትመጣ ስልኬን ለመቀበል ነው የምትሽቀዳደመው። መጣጥፎችን በእጅ ስልኬ ስለምጽፍና ብዙ ዶክመንት ስለሚይዝ ታጠፋብኛለች ብዬ ስለምፈራ ስለማልሰጣት ሁል ጊዜ በመጣች ቁጥር ጸብ ነው። ስታለቅስ ሌላ ስልክ ሰጥተው ያባብሏታል።
ልጅ ሲያለቅስ በከረሜላ በቼኮላት ሳይሆን የሚደለለው በስልክ ሆኗል ። ይህ የስልክ ፍቅር አብሮ ያድግና ከፍ ሲሉ ስልክ ካልተገዛልን ከወላጅ ጋር ጸብ ነው ። መቼም ወላጅ የሚኖረው ለልጆቹ ነውና እነሱን ለማስደሰት ቢያጣም ተበድሮና ተለቅቶ ገዝቶ መስጠቱ አይቀርም ። ስልኩን ገዝቶ ይስጥ እንጂ አጠቃቀሙ ላይ ቁጥጥር ስለማያደርግ ልጆቹ በጌምና እንደ ቲክቶክ ባሉ የማህበራዊ ሚዲያ ሱስ ይጠመዳሉ ። ለከፉ ሌሎች አደጋዎችም ሊጋለጡ ይችላሉ ። ሱሱ ያድግና ለተለያዩ የአእምሮ ሕመሞች ይዳርጋቸዋል ።
ለጭንቀት ፣ ለድብርት ፣ ራስን ለመጥላትና ራስን ለማጥፋት ይጋለጣሉ። ዛሬ ልጅን አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ ማብቃት ፈታኝ እየሆነ ነው። ልጆቻችን ከእጃችን እያመለጡን ነው ። ከእድሜያቸው ቀድመው ለተለያዩ እኩይ ተግባራት እየተጋለጡ ነው። ችግሩ ዓለምአቀፋዊ ነው። መጠኑ ይለያይ እንጂ ምዕራባውያን በዚህ እየተፈተኑ ነው ። ቢቸግራቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች የእድሜ ገደብና የይዘት ክልከላ እንዲያደርጉ ግፊት ቢያደርጉም የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ስላልሆነ ከእነ አካቴው ይታገዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይሄን ውትወታ ታዋቂ ሰዎች ሳይቀሩ እየተቀላቀሉት ይገኛል።
ፋሪድ ዘካሪያ በዋሽንግተን ፖስት መጣጥፉ፤ “ የሁለት ሴት ልጆች አባት ስለሆንሁ ግማሹ ልቤ ቲክቶክ ቢታገድ ይለኛል ። በሚያስፈራ ሁኔታ ሱስ አስያዥ ስለሆነ። በአሜሪካ 150 ሚሊዮን ሰዎች የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ፤ ከሶስቱ ተጠቃሚዎች ሁለቱ ነፍስ ያላወቁ ብላቴናዎች ወይም ልጆች ናቸው።
ልጆች ለቲክቶክ ሱስና ለአእምሮ በሽታዎች ማለትም ለጭንቀት ፣ ለድባቴ ፣ ራስን ለማጥፋት ለሚገፋፋ ስሜት እየተዳረጉ ነው። አሜሪካውያንን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የሥነ አእምሮ ሊቃውንትና ፖለቲከኞች ከቲክቶክ ጋር በተያያዘም ሆነ ስለተቀረው ማህበራዊ ሚዲያ ልጓም ለቆ ቼ ፈረሴ ይቁም ። ሳይቃጠል በቅጠልን እየለፈፉ ነው ። እኔም ሀገራችን ህጻናትንና ታዳጊዎችን ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ወይም የሚገድብ ሕግ እንድታወጣ እጠይቃለሁ።
በተለይ ልጆችን ለሱስና ለአዕምሮ ሕመም እየዳረገ ስላለው የማኅበራዊ ሚዲያና አንድምታው ላንሳ። በአሜሪካው ነጩ ቤተ መንግሥት የሕዝብ ጤና ተጠሪው ወይም ሰርጀን ጄነራል ዶ/ር ቪቬክ ሙርዚ የልጆችንና የወጣቶችን የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የወቅቱ የሕዝብ የጤና ቀውስ ይሉታል ።ዶ/ር ቪቬክ በአደባባይ ወጥተው፤ “እንደ ኢንስታግራምና ቲክቶክ ባሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተነሳ የልጆቻችን የአዕምሮ ጤና ጉዳይ በብርቱ ያሳስበኛል።” ሲሉ ለመንግሥታቸውም ሆነ ለአሜሪካውያን የማንቂያ ደወሉን አሰምተዋል።
ፋሪድ ዘካሪያ በ”ዋሽንግተን ፖስት”ጋዜጣ ፣ “Why banning TikTok won’t do any good” ወይም “ቲክቶክን ማገድ ለምን ፋይዳ ቢስ ይሆናል” በሚል ርዕስ ባስነበበን የግል አስተያየቱ፤ ስለ ቲክቶክ ባሰብሁ ቁጥር ይበልጥ ያስፈራኛል የሚለው ፋሪድ ዘካሪያ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለተከታታይ ሁለት እሁዶች በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣም ሆነ በCNN/GPS ጽፎ አያውቅም። ባልተለመደና ተከታዮቹን ባስገረመ ሁኔታ ስለ ቲክቶክ ግን ጻፈ።
ይህ የቻይናው መተግበሪያ አሜሪካንን እንዴት እንዳሳሰባትና እረፍት እንደነሳት ጥሩ ማሳያ ነው። ፋሪድ፣ ባለፈው ሳምንት የቲክቶክን መታገድ ተቃውሜ ሞግቼ ነበር ይለንና። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ባደረግሁት ውይይት የተገነዘብሁት ነገር ቢኖር፤ የአሜሪካውያን ዋና ስጋት ቲክቶክ የቻይናዊ ንብረት መሆኑ ሳይሆን ከየትኛውም ማኅበራዊ ሚዲያ በላይ አደገኛ ሱስ አስያዥ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንን እያሳሰበን ያለ ጉዳይ ስለሆነ ሳንዘገይ አንድ ነገር ማድረግ አለብን።
አሜሪካውያን በ2022 ዓ.ም ከሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች በአንደኛ ደረጃነት ቲክቶክን አውርደዋል። ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ የአሜሪካ ብላቴናዎች ወይም ታዳጊ ልጆች ቲክቶክን ይጠቀማሉ። ከስድስቱ አንዱ ደግሞ በቲክቶክ ሱስ ተለክፈዋል። በሀገራችንም በጥናት ባይረጋገጥም ህጻናትንና ታዳጊዎችን ሱሰኛ እያደረገ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ከሆነ ሰነበተ። አበው እመው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የሀገራችን ህጻናትም ከዚህ ዘመን አመጣሽ ወረርሽኝ መጠበቅ ስላለባቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ የማህበራዊ ሚዲያ ገደብና ክልከላ ሊደረግ ይገባል።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም