አይበለው እንጂ! አንድ ሰው በተለያየ ምክንያት አደጋ ደርሶበት ወይም ታሞ … ወዘተ መንገድ ላይ ወድቆ ቢገኝ ማንነቱ የሚለየው በመታወቂያው ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ለማህበራዊ ደህንነቱ ቅድሚያ መታወቂያ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ሰው በሰውነቱ መታወቅ ስላለበት።
በዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሥርዓት ደግሞ፤ መስፈርቱን አሟልቶ መታወቂያ ያገኘ ሰው ከማህበራዊ ደህንነቱ ባሻገር መሠረታዊ አገልግሎት ለማግኘት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲሁም ተጠቃሚ ለመሆን ይችላል።
ዓለም ባንክ እ.ኤ.አ በ2022 ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ላይ ከ850 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት 450 ሚሊዮን ሰዎች ምንም ዓይነት መታወቂያ እንደሌላቸው አመላክቷል።
በኢትዮጵያም ከጠቅላላ ሕዝቦቿ 40 በመቶ የሚሆነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ስለሌላቸው ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከፋይናንስ እንዲሁም ማንነትንና መታወቂያን ከሚጠይቁ አገልግሎቶች ሁሉ ይገለላሉ።
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተለያዩ ግልጋሎቶች እንዳይገለሉና ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል በዓለም ላይ ከ90 ሀገራት በላይ የተተገበረውን የብሔራዊ (ዲጂታል) መታወቂያ ሥርዓት በኢትዮጵያም መስጠት ተጀምሯል። ይህ መታወቂያ በርካታ ጥቅሞች አሉት፤ ለአብነት ያህል ተደራሽና አካታች ስለሆነ ማንኛውም ሰው መብቱን ያስከብርበታል። የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ሌሎቹ መታወቂያዎች ለተቋማት የውስጥ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ሲሆን፤ ብሔራዊ መታወቂያ ግን ሁሉንም የመታወቂያ አገልግሎቶች በአንድ በማስተሳሰር የመታወቂያውን ባለቤት ማንነት የሚያረጋግጥ ነው።
ሌላኛው ጠቀሜታ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊነት የሚኖር ሰው ብሔራዊ መታወቂያ የማግኘት መብት አለው። መታወቂያውንም ያለ ምንም ቢሮክራሲ ማንነትን የሚገልጽ ማንኛውንም መረጃ በመያዝ ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት መቻሉ ነው።
መታወቂያውንም በዜጎች በተለይ በባንኮችና በኢትዮ-ቴሌኮም በኩል በቀላሉ በአቅራቢያቸው የሚያገኙበት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ተዘርግቶ፤ ብዙዎች መታወቂያቸውን ወስደዋል። ይሁን እንጂ የአገልግሎት አሰጣጡ አሁናዊ ሁኔታ ሲፈተሽ በተለይ በባንኮች በኩል ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ተቀዛቅዞ ይታያል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቀደም ሲል አንድ ሰው ባንክ ቤት እንደሄደ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማሳየት ወዲያው አገልግሎት ያገኝ ነበር። አሁን ላይ ይህ አሠራር ቀርቶ፣ አንድ ሰው ወደ ባንክ ቤት በሄደበት ቀን አገልግሎት ማግኘት አይችልም። ስልክ ቁጥር ሰጥቶ እንዲመለስ ይደረጋል። ከዚያም በሌላ ቀን ስልክ ተደውሎለት አገልግሎቱን እንዲያገኝ ይጠራል። ይህ ዓይነት አገልግሎት አሰጣጥ ከተደራሽነት አኳያ በጣም ውስንነት የሚታይበት አሠራር ነው።
ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የሚስተዋለውን ውስንነት በመቅረፍ መታወቂያውን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በንቅናቄ መልክ ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህም አንድ ሚሊዮን ዜጎች ለመመዝገብ በ119 ወረዳዎች እንዲሁም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤቶች ተ ቋቁመው ሥራ ተጀምሯል።
ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተቋቁሞ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። በዚህ መልኩ ጽሕፈት ቤቶቹ ወደታች ወርደው ለህብረተሰቡ አገልግሎቱን መስጠታቸው ተደራሽነቱ ላይ ጉልህ ሚና ስላለው ይበል የሚያስብል ተግባር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ መልክ በቅዳሜና እሁድ ገበያ ቦታዎች እንዲሁም በተመረጡና ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ አገልግሎቱ እየተሰጠ በመሆኑ፤ ሕብረተሰቡ በተለያየ ምክንያት ወደነዚህ ቦታዎች ሲያመራ እግረ መንገዱን መታወቂያ የሚያገኝበት አግባብ ተፈጥሮለታል።
ይህም ከተደራሽነት አኳያ እየተሠራ ያለው ሥራ በጣም የሚያስመሰግን ነው። ከተደራሽነት አኳያ በመዲናዋ እየተሠራ ያለው ሥራ ወደ ሌሎች ክልሎች ቢስፋፋ፤ አጠቃላይ ከብሔራዊ መታወቂያ ተደራሽነት አኳያ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ በአጭር ጊዜ ለማሳካት በእጅጉ አጋዥ ይሆናል።
በብሔራዊ መታወቂያ አሰጣጥ ዙሪያ ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ምንም ዓይነት መታወቂያ ለሌላቸው ሰዎች፤ ሌሎች በአካባቢው ነዋሪ የሆኑና ብሔራዊ መታወቂያ ያወጡ ሰዎች ምስክር ሆነዋቸው ብሔራዊ መታወቂያ ማግኘት መቻላቸው ነው።
ይሁን እንጂ በዚህ አግባብ ብሔራዊ መታወቂያ ማግኘት እንደሚቻል የሚያውቀው ጥቂት ሰው ይመስለኛል። ስለሆነም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በስፋት ተጠናክሮ ቢተገበር፤ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን ግብ በአጭር ጊዜ ማሳካት ይቻላል።
ብሔራዊ መታወቂያ መሠረታዊ መታወቂያ ነው። ምክንያቱም መታወቂያው ከአንድ አገልግሎት ጋር የተሳሰረ አይደለም፤ በመሠረታዊነት ሌሎች ለአገልግሎት አሰጣጥ የሚሰጡ መታወቂያዎችን ከጀርባ በመሆን የሚያስተሳስር ነው።
በመሆኑም ለሀገር ኢኮኖሚና ደህንነት የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም። ተቋማትና ዜጎች በመረጃ ማጭበርበር ወንጀል እንዳይፈጸምባቸው ያግዛል። ብሔራዊ መታወቂያ አንድ ሰው ይዞ የሚቀርብ ከሆነ፤ ለማንኛውም አገልግሎት አሰጣጥ ማንነትን በተመለከተ የሚያስተማምን ይሆናል።
ማጭበርበርም አይቻልም። ምክንያቱም ብሔራዊ መታወቂያ ሲሰጥ “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርህ ሊያስተገብር በሚችል መሠረታዊ በሆኑ ሁኔታዎች ነው የተደራጀው።
መታወቂያው “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርህ ከማስተግበሩ በተጨማሪ የፋይዳውን ቁጥር የማረጋገጥ ተግባርም በቀላሉ መሥራት በሚያስችል ሁኔታ ተዘጋጅቷል። በመታወቂያው መሠረት የአንድን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ ፋይዳ ጽሕፈት ቤት ድረስ መሄድ አያስፈልግም።
አገልግሎቱን የሚሰጠው ተቋም በሲስተም ግንኙነት ውስጥ ሆኖ መታወቂያውን ያቀረበውን ሰው ማንነት በማየት ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ ማጭበርበርን ለመከላከል እንዲሁም ለማስቀረት ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው። መንግሥት ያቀረበውን ይህን አሠራር በመደገፍ ሁሉም ዜጋ ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣት ይገባዋል።
ወደፊት ተቋማት ለሚሰጡት አገልግሎት ብሔራዊ መታወቂያን መጠየቃቸው አይቀሬ ነው። እንደውም አስገዳጅ ሊያደርጉት ይችላሉ። ስለሆነም እስከ አሁን መታወቂያውን ያላወጣ ሰው አሁን ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣት እንዲህ ቀላልና ተደራሽ በሆነበት ሁኔታ ቢያወጣ በብዙ መንገድ አትራፊ ነው።
ምክንያቱም ወደፊት አገልግሎት ፈልገው ወደ ተቋማት ሲሄዱ አገልግሎቱን ለማግኘት መታወቂያዎን ማቅረብ ወይም የፋይዳ ቁጥርዎን መናገር አስገዳጅ በሚሆነበት ጊዜ ከመሯሯጥ ያድናል። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ከየትኛውም ቦታ የሚመጣ መሸኛን የሚቀበለው ብሔራዊ መታወቂያን መሠረት በማድረግ ነው።
በዚህም ኤጀንሲው ብሔራዊ መታወቂያን ከየትኛውም ክልል መሸኛ ይዞ የሚመጣ ግለሰብ ከየት እንደመጣና ማንነቱን ለማረጋገጥ እየተጠቀመበት ይገኛል። በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጉዳይ ያለው ግለሰብም አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልግ ከሚጠየቁ መረጃዎች ውስጥም የብሔራዊ መታወቂያ አንዱ ነው። በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንክ ቤቶች ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት አዲስ የባንክ ደብተር የሚከፍቱ ተገልጋዮች የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢ መሆን እንደሚገባቸው አሳስቧል።
ይሁንና ይህን መሰል ሁኔታዎች ሲታዩ በቀጣይ አብዛኛውን አገልግሎት ለማግኘት የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢ መሆን ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣት ግዴታ ባይሆንም፣ በቀጣይ አገልግሎት ለማግኘት ሲባል የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢ መሆን አይቀሬ ይሆናል።
ይህም በመሆኑ አንድ ሰው ቀደም ብሎ ለብሔራዊ መታወቂያ ሳይመዘገብ ቀርቶ የሆነ አገልግሎት ለማግኘት አገልግሎቱን ወደሚሰጠው ተቋም ሲሄድ የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢ መሆኑን የሚያመላክት መረጃ አቅርብ ሲባል፤ በወቅቱ አገልግሎቱን ከማግኘት ይልቅ የብሔራዊ መታወቂያ ለመመዝገብ ላይ ታች ማለት ይመጣል። ቀደም ብሎ ለብሔራዊ መታወቂያ የተመዘገበ አገልግሎት ፈላጊ ግን መረጃውን አቅርቦ በወቅቱ ተስተናግዶ ወደ ጉዳዩ ይሄዳል።
አሁን በንቅናቄ መልክ በብዙ ቦታ ተደራሽ በሆነበት ሁኔታ መጠቀም ካልተቻለ በቀጣይ ንቅናቄው ጊዜው ተጠናቆ ብሔራዊ መታወቂያ መመዝገብ እንደልብ ተደራሽ ላይሆን ይችላል። በወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ በክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ በተመረጡ ባንክ ቤቶች፣ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ በየመንገዱ፣ በሰንበት ገበያ ቦታዎች፣ ወዘተ. ብሔራዊ መታወቂያ እየተሰጠ ባለበት በዚህ ወቅት ችላ ሳይባል አገልግሎቱን ማግኘት ይገባል እላለሁ።
ማንኛውም ተመዝጋቢ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ካካሄደ በኋላ የምዝገባ ቁጥሩ በስልኩ ላይ ሳይደርስ ቢዘገይ ወይም የፋይዳ ቁጥሩ ቢጠፋ ወይም መዘንጋት ቢያጋጥም በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት መንገድም ወደ *9779# አድርጎ በመደወል ‹‹የነዋሪነት አገልግሎት›› የሚለውን በመምረጥ ማግኘት ይቻላል ።
ሌላው ደግሞ “id.gov.et” በሚለው ዌብ ሳይት ውስጥ በመግባት የሚያስፈልጉትን መረጃዎች በማስገባት የተዘነጋን ወይም የጠፋን የፋይዳ ቁጥርን ማግኘት ይቻላል። መታወቂያውን በሕትመት ለማግኘት ደግሞ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል ማግኘት ይቻላል። ይህንና ይሄን የመሰሉ አሠራሮችና መረጃዎች ህብረተሰቡ ጋር የሚደርስበት እንዲሁም ግንዛቤውን የሚያዳብረበት ሁኔታዎች በስፋት ቢኖር ጥሩ ነው።
አሁን እየተተገበረ ባለው የንቅናቄ አሠራር በመጠቀም ሁላችንም ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት እንመዝገብ። የፋይዳ ቁጥራችንንም እንያዝ። ሌሎችም እንዲኖራቸው መረጃውን እናጋራቸው።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም