አሁን ባለንበት ዲጂታል ዘመን የሰው ልጅ ከዲጂታሉ ዓለም ጋር አብሮ ለመጓዝ የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ኖሮት፣ የቴክኖሎጂውን መሳሪያም ታጥቆ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዲሰራ ይጠበቃል:: ይህን ማድረግ ካልተቻለ ዓለም ያፈራቻቸውን ብዙ ውጤቶች መቋደስ አይቻልም::
ለእዚህም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ለማስፋት በእጅጉ መስራት ይኖርባቸዋል:: የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል፤ የሀገርን ችግር በራስ አቅም መፍታት የሚችል ንቁ ዜጎችን መፍጠርም ይጠበቃል::
መንግሥት ይህን በመረዳት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርጾ ትግባራ ውስጥ ከገባ ዓመታት እየተቆጠሩ ናቸው:: በስትራቴጂውም የዲጂታል ምህዳሩን ምቹ ለማድረግና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑም ይገኛሉ:: በቅርቡም በኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ፕሮግራም አምስት ሚሊዮን ዜጎችን በዲጂታል ዘርፉ ለማሰልጠን ያለመ ሥራ መጀመሩም ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: ከዚህ ባሻገርም የዲጂታል ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ ለጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች (ስታርትአፖች) ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑም ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች እንደ ክረምት ወቅት ባሉ ጊዜያት በአንድ ማእከል በማሰባሰብ የፈጠራ ሃሳባቸውን እንዲያዳብሩ እየተከናወነ ያለውም ሥራ በጠንካራነት ይወሰዳል::
አሁን ለጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፤ የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን እንዲያፈልቁና ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ የሚያደርግ ምቹ ሥነ ምህዳር እየተፈጠረላቸው ይገኛል:: ይህም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውና ባለልዩ ተሰጥኦዎችን የሚያሳትፍ ከመሆኑም በላይ ብዙ የፈጠራ ሃሳቦች እና የፈጠራ ሥራዎች እንዲወጡና እንዲፈልቁም ምክንያት እየሆነ ይገኛል:: ለዚህም በየጊዜው በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች የምንመለከታቸው የፈጠራ ሃሳቦችና ሥራዎች ህያው ምስክር ናቸው::
በተለይ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን ከማበረታታት አኳያ በተለያዩ ጊዜያት በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች ላይ የምንመለከታቸው የፈጠራ ሥራዎችና ባለቤቶቻቸው ዛሬ ላይ ሆነን ስለነገ ብሩህ ተስፋ እንድንናገር የሚያደርጉ ናቸው:: ተስፋ የሚያጭሩ ፈጠራዎች በሀገር ልጆች እየተሰሩ ናቸው:: የፈጠራ ሃሳቦቹ ከኢትዮጵያ ልጆች አእምሮ ፈልቀው ተብላልተውና በስለው ወደ መሬት ሊወርዱ የተቃረቡ /አንዳንዶቹም መሬት የነኩ/ ናቸው፤ በዘርፉ ጠንክሮ በመስራትና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የራስንና የአካባቢን፣ የሀገርን አልፎም ተርፎ የዓለምን ችግሮች መቅረፍ እንደሚቻልም ያመላክታሉ::
የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ መሬት ለማውረድ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁስ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፤ ይህም ግብአት ከውጭ ለማምጣት ሲባል የሚባክነውን ጊዜ በማስቀረት እንዲሁም በግብአቶቹ አለመገኘት ሳቢያ የፈጠራ ሥራው ኅብረተሰቡን ሳይጠቅም ሊቀር የሚችልበትን እድል ይዘጋል::
የፈጠራ ሥራዎቹም ቁሳቁሶቹም የራስ መሆናቸው ከመገረምና ከመደነቅ አልፈን እውን እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች በኛ ሀገር የተሰሩ ናቸው ወይ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ እያደረጉንም ናቸው:: ይህም የነገ ሀገር ተረካቢው ወጣት ትውልድ እውቀቱን፣ ክህሎቱን ማውጣት ከቻለ የሀገሪቱን ችግሮች በመፍታት እየተጓዘችበት ያለችውን የልማት ጉዞ ቀና በማድረግ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል::
ብዙዎቹ የፈጠራ ሃሳቦች አካባቢ ላይ ያሉ ችግሮች መነሻ አድርገው ይፈጠሩ እንጂ ከአንድ አካባቢ አልፈው የሀገር ብሎም የዓለምን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ፤ እየተሻሻሉ ፣ እየሰፉና እያደጉ የሚሄዱም ናቸው:: የተፈጠሩት እዚሁ በሀገር ውስጥ ባሉ ጀማሪ የፈጠራ ሃሳብ ባላቸው ወጣቶች ቢሆንም፤ ውጤታማ ሲሆኑ ድንበር የለሽ ሆነው የሀገርም የዓለምም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦችና የፈጠራ ሥራዎች መረዳት ይቻላል:: በተለይ በሀገር ውስጥ በታዳጊዎች የሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሳይቀር ተወዳዳሪ ከመሆን በዘለለ አሸናፊ እየሆኑ መምጣታቸው ሀገሪቱ ነገ ብሩህ መሆኑን ያመላክታሉ::
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠራ ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ሮቦቲክስ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላቸው ትልቅ ትርጉም አለው፤ ወጣቶቹ ከሀገር አልፈው ድንበር ተሻግረው ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሳይቀር መቅረብ ችለዋል:: ይህ ደግሞ በርካታ ወገኖች ጭምር እየተሳተፉበት እዚህ ደረጃ የደረሰ ነው:: ይህ ሁሉ የብዙ ጥረትና ድካም ውጤት መሆናቸውን ያመለክታል::
በተለያዩ አውደ ርዕዮች ላይ የምናያቸው የፈጠራ ሃሳቦችና ሥራዎች በየጊዜው እየተበራከቱ ቢመጡም፤ እስከ መጨረሻው ተደግፈው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ግን ክፍተቶች ስለመኖራቸው ይሰማል:: ሃሳቦቹንና ሥራዎቹን አወዳድሮና መርጦ ለእይታ በማብቃት ሂደት ብዙ ጥረቶች ተደርገው እንደሚመጡ ይታወቃል::
ይሁንና ለእይታ ከቀረቡ በኋላ ጥቅም ላይ ውለው ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ከማድረግ አኳያ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ አካል እንደሌለ ይገለጻል:: እነዚህን የፈጠራ ሃሳቦች መርጦ ለማምጣት ኃላፊነት ያለው አካል እንዳለ ሁሉ፤ ሁሉንም ሰብስቦ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም መከታተል ላይ ግን ይሄ ነው የሚባል አካል እንደሌለም ጭምር መታዘብ ይቻላል::
ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎቹም ይህንኑ እየመሰከሩ ናቸው፤ የፈጠራ ሥራዎቹም ሆኑ ሃሳቦቹ በሚፈለጉበት ቦታ ላይ ካቀረቡ በኋላ ዞር ብሎ የሚያያቸው አካል እንደሌለ ሲናገሩ ይደመጣል:: ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ድጋፎች አግኝተው ተመርተው ወደ ገበያ የገቡ እንዳሉ ባይካድም፤ አብዛኛዎቹ በሚባል ደረጃ ግን ሥራዎቻቸው ከአውደ ርዕይ እይታ በኋላ የሚያስታውሳቸው የለም:: እድሉ ቀንቷቸው በግል ጥረት ለውጤት የሚበቁ እንዳሉ ሁሉ በፋይናንስ እጥረትም ሆነ በሌላ ምክንያት ወደ ተግባር ያልገቡ ቤት ይቁጠራቸው የሚባሉ ስለመሆናቸው ይገለጻል::
ይህ ደግሞ ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች አሁን ይዘው ከቀረቡት የፈጠራ ሃሳብና ሥራ በላይ ከዛሬ ሥራቸው ብዙ ተምረው በውስጣቸው ያለውን ሃሳብ እንዳያወጡ የሚገድብ ይሆናል:: አሁን የያዙትን የፈጠራ ሥራ በብዙ መልኩ አሻሽለው እንዲሰሩ፣ አልያም አዲስ ሊፈጥሩ የሚችሉበት ጊዜ ሳይሰጣቸው ይቀርና ተስፋ ሊቆርጡም ይችላሉ:: ይህም የፈጠራ ባለሙያዎቹን ብቻ ሳይሆን ችግሩ የሚፈታለትን ሕዝብና ሀገርም በእጅጉ ይጎዳል:: የፈጠራ ሃሳብ ብክነት እንዲኖርም ያደርጋል::
የፈጠራ ሥራዎች ኅብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ ተደርገው ችግሩን እንዲፈቱ ለማስቻል የሚያስተዳድራቸው አካል ሊኖር ይገባል፤ አለ ከተባለም በትኩረት እንዲሠራ መደረግ ይኖርበታል:: እስከ አሁን ካለው ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ግን የፈጠራ ሃሳቡና ሥራው እንደ ጎርፍ እየወረደ ነው፤ ችግር መፍታቱ ላይ ግን ብዙም የሚታይ ነገር አለመኖሩ ነው::
ሀገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ብዙ ሃሳቦችን አንድ ላይ አምጥቶ ወደ ውጤት መቀየር ካልተቻለ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን እንደሚታዩ ጥናታዊ ጽሁፎች መሆናቸው አይቀሬ ነው:: ይሄ ደግሞ የፈጠራ ሃሳብ አመንጪዎቹን ልጆች ሞራል ይጎዳል፤ ሕዝብና ሀገር የሚቀይር ሃሳብ እያባከነ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል:: ይህንንም የሚመለከታቸው አካላት በደንብ አይተው ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል ባይ ነኝ::
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም